ራሴ የጠፋብኝ ሰው ነኝ..ራሴን ካጣሁት ሰንብቻለው:: ማነህ ላለኝ ማቲያስ ነኝ እላለው እንጂ ማቲያስ ማን እንደሆነ አላውቀውም:: ሰው እንዴት ራሱ ይጠፋዋል? ስል እኔው በኔ እደነቃለው:: ሰው ራሱን አጥቶ ምንም ቢያገኝ እንደማይረካ አንድ ማለዳ ነው የተገለጠልኝ:: ‹እኔ ማነኝ? ለምንድነው ሰው የሆንኩት? ወደዚህ አለም ለምን መጣሁ? ብዬ ራሴን ጠይቄ መልስ ያጣሁ ጊዜ:: ከዚህ ጥያቄ በኋላ ነበር ራሴን ፈልጌ ማግኘት እንዳለብኝ የተሰማኝ::
አንድ ጊዜ አንድ ካፌ ቁጭ ብዬ መጽሀፍ አነባለው:: አጠገቤ ጸጉሩን ያንጨፈረረ ጆሮው ላይ ሎቲ የሰካ አንድ ደንደሳም ጎረምሳ ተቀምጧል:: የሰውነቱ ማማር ከሩቅ ይስባል:: ቅልብ ኮርማ ነበር የሚመስለው:: እንደ እኔ ያሉ አስር ኮሳሳዎችን የሰለቀጠ መሰለኝ:: ሰው አያይም..አይኖቹን ስልኩ ላይ አፍጦ የሆነ ነገር ይጎረጉራል:: ፊቱ ላይ እየሄደ የሚመጣ ሳቅና ግርምት፣ ኩስተራና አርምሞ ተስሏል::
ከእሱ አጠገብ ደግሞ ከዘራቸውን ወንበር ላይ ያስደገፉ ባለ ነጭ ጸጉር አዛውንት ተቀምጠዋል:: ራሴን ፍለጋ ላይ ስለሆንኩ ሊያስተምረኝ ከሚችል ከማንኛውም ነገር ለመማር ዝግጁ ነበርኩ:: መጽሀፌን እየከደንኩ ሲያሰኘኝ እየከፈትኩ ዙሪያዬን መቃኘት ያዝኩ:: በዛ ሰፊ መናፈሻ ውስጥ እኔ፣ ደንደሳሙ ጎረምሳና አዛውንቱ በቅርብ ርቀት ላይ ተሰይመናል:: ወዲያው በአንዲት ፈገግተኛ አስተናጋጅ ተይዞ የሽማግሌው ምሳ መጣ:: ምሳው ጠረጴዛ ላይ ከማረፉ ከሽማግሌው አፍ አንድ ቃል ወጣ…‹እንብላ ልጆቼ› የሚል ቃል::
በዚያ ቅጽበት እያነበብኩ ነበርና ከማነበው መጽሀፍ ላይ ቀና ብዬ አየኋቸው:: እርጅና የተጫናቸውን፣ በነጫጭ የሽፋል ጸጉር የተከበቡ አይኖቻቸው ወርውረው አንዴ እኔን አንዴ ወጠምሻውን እያዩ አገኘኋቸው:: ምላሽ እየጠበቁ እንደሆነ ስለገባኝ…
‹አመሰግናለው አባቴ› ስል የድርሻዬን ተወጣሁ:: ራሱን ያጣ ሰው ነበርኩ..ለአንድ ሽማግሌ የሚሆን መልካም ቃል ከጠፋው ማንነቴ ውስጥ በማግኘቴ ደስታ ተሰማኝ:: ራሴን እያገኘሁት መሰለኝ..ላልገኝ እየጠፋሁም:: አይኖቼን የማነበው መጽሀፍ ላይ መልሼ የጠፋውን ራሴን ፍለጋ ስጀምር ከወጣቱ ጉሮሮ የወጣ የሚመስል ጎርናና ድምጽ ተሰማኝ:: ለሁለተኛ ጊዜ ቀና አልኩ:: ወጣቱ ወጠምሻ አይኖቹን ከሞባይሉ ላይ ሳይነቅል ‹ይሄ ነገር ዛሬም አልቀረም እንዴ ፋዘር? ሲል ሰማሁት::
‹ምኑ? ያልገባቸው ሽማግሌ መልሰው ጠየቁ::
‹እንብላ የሚለው ነገር ነዋ? አሁን እኮ 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ነን›:: አለ:: አሁንም አላያቸውም.. አይኑ፣ ልቡ፣ ቀልቡ፣ መንፈሱ ሁሉ ሞባይሉ ላይ ነበር::
የትዝብት ሳቅ ሳቅ ብለው ‹የአሁኑ ትውልድ ጥሩ ነገር አታውቁም:: ለልጆቻችሁ ምን እንደምታወርሷቸው እግዜር ይወቀው:: እንብላ እኮ የኢትዮጵያዊነት ቀለም ነው:: ኢትዮጵያዊነትን ከነሙሉ ክብሩና ማዕረጉ የምታገኘው እዛ ውስጥ ነው:: ከትላንት ዛሬ የደረስነው አብረን እየበላን፣ አብረን እየጠጣን ነው:: ጣሊያንን ያሸነፍነው፣ በኡጋዴንና በአንባላጌ በካራማራም ድል ያገኘነው አብረን ስለበላን ነው:: የአባቶችህን ወግ ብታደምጥ ኖሮ ብዙ ቁም ነገር ትሰማ ነበር› ሲሉ በምሬት ተናገሩ::
ሽማግሌው ብቻ ሳይሆኑ እኔም ተገረምኩ:: እኔን እላለው እንጂ ለካ ከኔ በላይ ራሱን ያጣ ሰው አለ:: ለሀገሬ አዘንኩላት..ለካ ራሱን ያጣ መካን ትውልድ ነበር ታቅፋ የምትኖረው:: ሰው ራሱ ሲጠፋው እንደ እኔና ልክ እንደዚህ ወጣት ምንም ነው ስል አሰብኩ:: ከእሱ ግን እንደምሻል እርግጠኛ ነበርኩ:: እኔ ራሴ ብቻ ነው የጠፋኝ ይህ ወጣት ግን ታሪኩንም ነው ያጣው:: ከዛም አላረፍኩም ‹ዘመናዊነት ምንድነው? ስልጣኔስ? ስል ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ:: ብዙ ጥያቄዎች በአእምሮዬ ውስጥ ተፈጠሩ:: መጽሀፌን ከድኜ ማሰላሰል ጀመርኩ::
አዛውንቱ አንዴም ወደ ምግቡ እጃቸውን አልዘረጉም:: እሳቸው የሚያውቁት ሀቅ አብሮ መብላት ነው:: እኔና ይሄ ወጣት ደግሞ በእሳቸው እውነት ላይ ቆመን የእሳቸውን እውነት የከዳን ወጥቶናል:: በየመሀሉ ቀና እያልኩ አያቸዋለው..ትውልድን የሚወቅስ ፊት ያስታቅፉኛል:: በመሀል ድምጻቸውን ሰማሁት..
‹ልጄ አትሳት..ዘመናዊነት አብሮነት ነው:: እኛ እጅ ካልሰጠን በቀር ባህል የሚሽር፣ ልማድ የሚበርዝ ዘመን የለም:: የዘመን ገዢ የሰው ልጅ ነው:: አንተ እንደምትለው 21ኛው ክፍለ ዘመን የግለኝነት ዘመን ሆኖ ሳይሆን ለዘመኑ እኛ ምቹ ሆነን ስለተገኘን ነው የብቻ ዘመን ያደረግነው:: አብሮ መብላት አብሮ መሆን ነው:: አብሮ መብላት ወንድማማችነት ነው:: ዛሬ ላይ በብዙ ነገራችን ተለያይተን የቆምነው የድሮ መልካም ባህሎቻችንን ስለተውን ነው::
በዘመን ውስጥ መብቀል እንዲህ አይደለም፣ ስልጣኔ የአባቶችን ስርዐት መተው አይደለም..ስልጣኔ ራስን ለዘመን ማዘጋጀት ሳይሆን ዘመንን ለራስ ማዘጋጀት ነው:: አንተ እኔን አባትህን ጎንህ አስቀምጠህ ከሞባይልህ ጋር የምትጫወተው ጊዜን ስለበለጥከው ሳይሆን በጊዜ ስለተበለጥክ ነው:: ሰው በዘመን ሲበለጥ እንዳንተ ነው የሚሆነው:: ከመጣሁ ጀምሮ አንዴም አላየህኝም:: ይሄን ሁሉ ወሬ ሳወራህ እንኳን ቀና ብለህ ቀይ ልሁን ጥቁር አላስተዋልከኝም:: እንብላን ብታውቅ ታየኝ ነበር› ሲሉ ተናግረው ዝም አሉ::
ወጣቱ አሁን አያቸው….የተቀየመ ያዘነ ሽማግሌ ፊት ተጋረጠበት::
‹በአዛውንቶች ልብ ውስጥ ያለችውን ጥንታዊቷን ኢትዮጵያ ፈልጋት:: እርሷን ስታውቅ አሁንህን ትጠላዋለህ..ድሮነት ምን ያክል ዋጋ እንዳለው ትረዳለህ:: እርሷ ለእኔም ለአንተም ለሁላችንም የጋራ እውነት ናት:: ሲሉ ተናግረው እጃቸውን ወደ ምግቡ ዘረጉ::
መጽሀፌን ዘግቼ ከራሴ ጋራ ግብ ግብ ገጠምኩ:: የሽማግሌው እውነት ውሰጤ ዘልቆ ተሰማኝ:: ከተናገሩት ውስጥ አንድም ውሸት የለም:: እውነት በዛ ቀን ላይ እዛ ቦታ ከእሳቸው ጎን በመቀመጤ ደስ አለኝ:: ኢትዮጵያን እንካ ብለው የሰጡኝ ነበር የመሰለኝ…ደግሞም ሰጥተውኝ:: እንደሳቸው እውነት የነገረኝ ሰው የለም:: በዙሪያዬ ያሉ ብዙ ሰዎች የውሸት ተረት እየፈጠሩ ኢትዮጵያዊነትን የሚያረክሱና የሚያቆሽሹ እንደሆኑ አውቃለው እርሳቸው ግን ልዩ ነበሩ::
በተቀመጥኩበት ራሴን እንዲህ አልኩት…አንተ እኮ ራስክን ብታውቅ፣ ኢትዮጵያዊነት ምን እንደሆነ ብትረዳ የአለም አይኖች ማረፊያ ነበርክ:: በታላቅ ሀይል ተሞልቼ ከወንበሬ ተነሳሁ…ስነሳ ከእንግዲህ በአዛውንቶች ልብ ውስጥ ያለችውን እውነተኛይቱን ኢትዮጵያ ፈልጌ ላገኝ ለራሴ ቃል በመግባት ነበር::
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵያ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2022