
ሰመራ፦ ለሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ እድገት ከቱሪዝም ፖሊሲ ጎን ለጎን ወቅታዊና ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ ጠንካራ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፎ መንቀሳቀስ እንደሚገባ የውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩት አስገነዘበ።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ደሳለኝ አምባው ትናንት በሰመራ ከተማ በተካሄደው የፖሊሲ የውይይት መድረክ እንደተናገሩት፤ ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት የሀገር ውስጥ ጎብኚውን ቁጥር ማሳደግ ትኩረት ቢያሻውም በተለይም ሀገሪቷ በየጊዜው የሚፈትናትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ቁጥር ከማሳደግ አንጻር በርካታ ሥራዎች መሠራት አለባቸው።
በተለምዶ “ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ” በመባል የሚጠራው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለብዙ ሀገራት አማራጭ የኢኮኖሚ መሠረት ሆኖ ያገለግላል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያ ካላት እምቅ የቱሪዝም ሀብት አንጻር ሲመዘን በተለያዩ ምክንያቶች ከዘርፉ መጠቀም ባለባት ልክ መጠቀም አልቻለችም ሲሉ ገልጸዋል።
እንደሀገር ያሉንን ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ሀብቶቻችንን በአግባቡ ከተጠቀምን እንደብዙዎቹ ሀገራት ሁሉ በሥራ ፈጠራ፣ የውጭ ምንዛሪን በማስገኘትና የሀገራዊ ምርት እድገትን በማረጋገጥ የኢኮኖሚ መሠረት መሆን ይችላል” ብለዋል።
አክለውም፣ ይህ ህልማችንና የዘወትር ቁጭታችን እውን እንዲሆን ሌሎች መሠራት ያለባቸው ሥራዎች እንዳሉ ሆነው በዋናነት የጠራ የዘርፉ ፖሊሲና ተያያዥ የማስፈጸሚያ ስልቶች ወይም ስትራቴጂዎች የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዙም አብራርተዋል።
የሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ እንዲያብብና ለኢኮኖሚ እድገት ተገቢውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የሁሉም ባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሠራር እንደሚጠይቅ ጠቅሰው፤ አግባብነት ያለው ፖሊሲና ስትራቴጂ መንደፍና ማስፈጸም፣ ሰላምና ጸጥታን ማስፈን፣ የመሰረተ ልማት እንዲሁም አገልግሎት ዘርፉን ማዘመንና ለጎብኚዎች ምቹ ማድረግ በዋናነት ከመንግሥት የሚጠበቅ ቢሆንም በዚህ ረገድ የግሉ ዘርፍም ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል።
በተጨማሪም፣ ተመራማሪዎች በቱሪዝም ዲፕሎማሲና የቱሪዝም ዘርፉን ማሳደግ በሚቻልባቸው ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ጥናት ከማድረግም ባለፈ የምርምር ውጤቶቻቸው ለፖሊሲ እና ትግበራ እንዲያግዙ ተደራሽ ማድረግ አለባቸው።
የፕሮሞሽን ባለሙያዎች፣ የጥበብ ሰዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የባሕል አምባሳደሮች ድርሻም ቀላል የሚባል አይደለም ሲሉ አስረድተዋል።
በውጭ ግንኙነት ኢንስቲትዩት በተዘጋጀው በዚህ የውይይት መድረክ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ለቱሪዝም ዘርፍ እድገት ያለውን ሚና እንዲሁም የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዲፕሎማሲ ስትራቴጂያዊ አቅጣጫዎች፣ ትግበራ እና ተግዳሮቶች ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች በዘርፉ ምሁራን ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በውይይት መድረኩ የፌዴራልና የክልል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተመራማሪዎች፣ የቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያዎችና ሌሎችም ተጋባዥ እንግዶች መታደማቸውን ለማወቅ ተችሏል።
አብዱረዛቅ መሐመድ
አዲስ ዘመን ሰኔ 24 ቀን 2014 ዓ.ም