ባለፉት ጥቂት አስርተ ዓመታት በሀገራችን በመንገድ፣ በቴሌ፣ በባቡር እንዲሁም በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ዘርፎች ሰፋፊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ተከናውኗል። በተሠሩ ሥራዎችም የሀገሪቱ የመሠረተ ልማቶቹ ሽፋን ከፍ ብሏል። እነዚህ መሠረተ ልማቶች የሀገሪቱ ስም በመልካም እንዲነሳ ያደረጉ ናቸው። ይሁን እንጂ በሀገራችን የመሠረተ ልማት ዝርጋታን የሚያካሄዱ ተቋማት መካከል በቅንጅት የመሥራት ከፍተኛ ችግር ያለባቸው በመሆናቸው በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ችግሮች ተስተውለዋል።
በተለይም በከተሞች አካባቢ የመንገዶች፣ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌ እና የውሃ መሠረተ ልማቶች በሚዘረጉበት ወቅት ችግሩ በግልጽ ይታያል። አንዱ የራሱን መሠረተ ልማት ከዘረጋ በኋላ ሌላኛው ተቋም ደግሞ የተዘረጋውን መሠረተ ልማት በማፍረስ የራሱን መሠረተ ልማት ሲዘረጋ ማየት የተለመደ ነው። ጉዳዩን እጅግ አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ ሀገሪቱ ያላትን አንጡራ ሀብት በማፍሰስ የምትገነባቸው መሠረተ ልማቶች ወራት እንኳ ሳይቆዩ ለሌላ መሠረተ ልማት ዝርጋታ መፍረሳቸው ነው።
በዚህ ሁኔታ ከአንዴም ሁለቴ ወይም ሶስት አራቴ ፈርሰው የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች አሉ። የዚህ ችግር ዋነኛ ሰለባ እየሆነ ያለው የመንገድ መሠረተ ልማት ነው። አንድ የመንገድ ፕሮጀክት ተገንብቶ በተመረቀ በወራት ውስጥ ለኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ወይም ለውሃ መስመር ዝርጋታ ወዘተ ሲፈርስና ሲጠገን ማየት የተለመደ ነው። መንገዶቹ ፈርሰው ዳግም ሲጠገኑ እንደ መጀመሪያው ሊሆን ስለማይችል በአጭር ጊዜ ለብልሽት የመዳረግ እድሉ ላቅ ያለ ነው።
ለተለያዩ መሠረተ ልማቶች ዝርጋታ ተብሎ በተለያዩ አካባቢዎች የሚቆፈረው መንገድ ተመልሶ በአግባቡ ስለማይጠገን እና ጉድጓዶች በአግባቡ አለመደፈን እና ድንጋዮች በአግባቡ ቦታቸውን እንዲይዙ ስለማይደረግ ለትራፊክ አደጋዎች መንስኤ ሲሆንም ይታያል።
የቅንጅታዊ አሠራር አለመኖር መሠረተ ልማቶቹ ለማኅበረሰቡ ኑሮ መሻሻልና ለሀገሪቱ ልማት መፋጠን የሚጠበቀውን ያህል እንዳያበረክት እንቅፋት መሆኑም አልቀረም። ከዚያ አለፍ ሲልም ለጊዜና ለገንዘብ ብክነት መንስኤ ከመሆን አልፎ ለሌሎች ችግሮች መንስኤ ሲሆንም ታይቷል።
በቅንጅታዊ አሠራር እጦት ሳቢያ የፕሮጀክቶች ግንባታ መጓተት ሀገሪቱ በብድር፣ በእርዳታና በውስጥ ገቢ የምታገኘውን ውስን ሀብት ለታለመለት ዓላማ እንዳታውል ስለሚያደርግ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የራሱን አሉታዊ ጫና ያሳድራል።
ችግሩ የሰነበተ ሲሆን፤ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች ዛሬ በስፋት የሚታይ ክስተት ነው። አንዳንድ ጊዜ በተቋማቱ መካከል አለመናበብ በመኖሩ ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮች ሲታይ ተቋማቱ በአንድ መንግሥት ይመራሉ? እና ለአንድ ሀገርስ ነው የሚሠሩት የሚል ጥያቄ እንዲነሳ የሚጋብዝ ነው።
በቅርቡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸውን የ10 ወራት አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ እንደተናገሩት፤ ችግሩ ዛሬም ቀጥሏል። በዚህም ምክንያት የጊዜ እና የገንዘብ ብክነት እየተከሰተ ነው።
ይህም ከፍተኛ የጊዜ ብክነት እና ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ከማስከተሉም ባሻገር የመልካም አስተዳደር ችግር እያስከተለም ይገኛል። የሕዝቡ ምሬት ምንጭ ሲሆን ይታያል።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት የችግሩ ዋነኛ መንስኤዎች ሀገራዊ የቅንጅት ማስተር ፕላን ያለመኖር፣ ሀገራዊ የቅንጅት ስታንደርዶች ያለመኖር፣ መሠረተ ልማት ፈጻሚ ተቋማት የተሟላና የተደራጀ መረጃ ያለመኖርና መረጃዎች ቢኖሩም እንኳ ያለመናበብ ችግር ከዋና ዋና መንስኤዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
በዚህም ምክንያት የመሠረተ ልማቶች ዝርጋታ በማስተር ፕላን የማይመሩ መሆናቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች በማስተር ፕላን የሚመራ ቢሆን አንዱ ተቋም የራሱን መሠረተ ልማት በሚዘረጋበት ወቅት ለሌላኛው መሠረተ ልማት ዝርጋታ የሚሆን ቦታ ሊያስቀር ይችላል።
መሠረተ ልማቶችን መገንባት፣ ማደስ እና መጠገን ብቻ ሳይሆን መሠረተ ልማትን በሚዘረጉ ተቋማት መካከል ቅንጅታዊ አሠራርን መዘርጋት ላይ ማተኮር ለነገ የማይባል አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። በተለይም ከመንገድ ሥራ ፣ ከኤሌክትሪክ ግንባታና ከቴሌኮሙዩኒኬሽን መሠረተ ልማት ግንባታ ጋር ተያይዞ የሚሠሩ ሥራዎች አቀናጅቶ መምራት መቻል በመሠረተ ልማት ዘርፍ ከዋጋ፣ ከጥራትና ከጊዜ አኳያ የተሻለ ጥቅም እንደሚያስገኝ እሙን ነው።
በርካታ መሠረተ ልማቶች በቅንጅት በጋራ በሚዘረጋበት ወቅት ለተለያዩ መሠረተ ልማቶች ዝርጋታ ለየብቻ የሚወጣውን ወጪ በማስቀረት በአንድ ላይ ወጪ እንዲደረግ ስለሚያስችል ከፍ ያለ ፋይዳ አለው።
በቅንጅታዊ አሠራር እጦት ምክንያት እየደረሰ ያለውን የወጪና የጊዜ ብክነት ለመከላከል የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን በቅርቡ በፓርላማ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸውን የ2014 በጀት ዓመት የ10 ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ እንደተናገሩት፤ ችግሩን ለመቅረፍ ጥናት እየተካሄደ ሲሆን፤ በቅንጅታዊ አሠራር እጦት ምክንያት እየተከሰተ ያለውን የጊዜና የወጪ ብክነት የሚያሳይ ጥናት እየተካሄደ ሲሆን ጥናቱ በአሁኑ ወቅት 85 በመቶ ተጠናቋል።
ይህ ጥናት የችግሩን መሠረታዊ መንስኤዎችን ከመለየት ባሻገር የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ያመላክታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ነው። በቅንጅት አሠራር እጦት ምክንያት የሚከሰተውን የጊዜና የገንዘብ ብክነት በማስቀረት የመሠረተ ልማት ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያግዝ ይሆናል።
ጥናቱ በአስቸኳይ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ርብርብ ሊደረግ ይገባል። ጥናቱ ብቻውን በራሱ ችግሩን ለመቅረፍ ስለማያስችል ጥናቱን ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል። ጥናቱ ሲጠናቀቅም የጥናቱን ግኝቶችን ሳይሸራረፍ በመተግበር ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚመለከታቸው አካላት ዝግጁ መሆን አለባቸው።
ሚኒስትሯ አክለውም ባለፉት 10 ወራት 71 ፕሮጀክቶች በቅንጅትታዊ አሠራር፣ በካሳ ክፍያ፣ በዲዛይንና በወሰን ማስከበር ዙሪያ የነበሩባቸውን ችግሮች የሚያቃልል ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ተችሏል። ይህም እንደ ትልቅ ስኬት የሚታይ ነው። ችግሩን ለመቅረፍ የሚደረጉ ጥረቶችም ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።
በቅንጅታዊ አሠራር እጦት የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት እስኪቻል ድረስ ጊዜያዊ የመፍትሔ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል። ከተቻለ ከቅንጅታዊ አሠራርን ያልተከተሉ መሠረተ ልማቶች ዝርጋታ ሙሉ በሙሉ ማስቆም እና ቅንጅታዊ አሠራር ውስጥ እንዲገቡ ሊደረግ ይገባል። የመሠረተ ልማቱ ግንባታ ማስቆም ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን ከሆነና ግንባታው የግድ መካሄድ አለበት ተብሎ ከታመነበት ደግም ጥንቃቄ በተሞላበት አኳኋን መቀጠል አለበት።
በተለይም ለተለያዩ መሠረተ ልማቶች ዝርጋታ የሚቆፈረው መንገድ ለትራፊክ አደጋና ለሌች ችግሮች መንስኤ እንዳይሆን በአግባቡ መጠገን አለበት። ያፈረሰውን መሠረተ ልማት በአግባቡ የማይጠግን አካል በሕግ ተጠያቂ የሚደረግበት አሠራር ሊዘረጋ ይገባል ለሚፈጠሩ ችግሮች ካሳ የመክፈል ግዴታ ሊጣልበት ይገባል።
የመሠረተ ልማቶች ዝርጋታ በማስተር ፕላን ሊመራ ይገባል። የነባር ከተሞችን አሮጌ አካባቢዎችን መልሶ የማልማት ሥራ በሚሠራበት ወቅት ይህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። አጋጣሚውን በመጠቀም ከተሞቹ ሲመሠረቱ የተፈጠሩ ስህተቶችን በመጠኑም ቢሆን መቅረፍ ይቻላል። በነባር ከተሞች መሠረተ ልማቶች በማስተር ፕላን ብቻ መዘርጋት አዳጋች ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።
አዲስ በሚለሙ ከተሞች መሠረተ ልማቶችን በማስተር ፕላን የመዘርጋት ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። አዳዲስ ከተሞች ከነባር ከተሞች ትምህርት በመቅሰም የነባሮችን ስህተት ላለመድገም መጠንቀቅ አለባቸው።
ለመሠረተ ልማት ሥራዎች ውጤታማነት የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር እንዲቻል ሀገራዊ የቅንጅት ማስተር ፕላን የማዘጋጀት ጉዳይ ለነገ የማይባል ነው። በዚህ ረገድ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በጋራ ሊረባረቡ ይገባል። መሠረተ ልማት የሚዘረጉ ተቋማት በጋራ እቅድ በማውጣት፣ ሥራቸውንም በጋራ የሚሠሩበት እንዲሁም አፈጻጸማቸውንም በጋራ የሚገመግሙበት አሠራር ሊዘረጋ ይገባል።
ያለስታንዳርድ የሚሠሩ ሥራዎች የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ የማያስችሉ እንደመሆናቸው የሀገሪቱ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ የቅንጅት ስታንዳርድ ከሌለ በአስቸኳይ ማዘጋጀት፤ ካለ ደግሞ ተግባር ላይ ማዋል እንደሚገባ አንስተዋል። በተጨማሪም የመሠረተ ልማት ፈጻሚ ተቋማት መረጃ ሀብት መሆኑን በመገንዘብ የተሟላና የተደራጀ መረጃዎችን መያዝ አለባቸው። የተሟላና የተደራጀ መረጃ ሲኖር የዝርጋታ ሥራው የተቀናጀ እንዲሆን ለማድረግ ከፍ ያለ እገዛ ይኖረዋል።
መረጃ በራሱ ችግሮችን ስለማይፈታ ተቋማት መረጃ ከመያዝ ባሻገር መረጃዎቻቸውን ማናበብ አለባቸው። አንዱ ጋር ያለውን መረጃ ሌላው ማወቅ አለበት ይህ ሲሆን በመረጃ ተመርኩዞ የሚወሰኑ ውሳኔዎች ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችላሉ።
ግንዛቤ ማሳደግ ወሳኝ በመሆኑ፤ በክልሎች አካባቢ ስለመሠረተ ልማቶች ቅንጅት አስፈላጊነት የሚስተዋለው የአቅም ግንባታና የግንዛቤ እጥረት ለመቅረፍ በትኩረት ሊሠራ ይገባል።
ሁሉም አካላት የሚሠሩትን ሥራ በቅንጅት ለመሥራት ተገቢውን ትኩረት መስጠት አለባቸው። ችግሮች በሚፈጠሩበት ወቅት ደግሞ ጣት ከመቀሳሰር ይልቅ ችግሩን በጋራ ለመፍታት መረባረብ ያስልጋል።
የአንድ ሀገር እድገት ደረጃ ጠቋሚ ከሆኑት መካከል አንዱ መሠረተ ልማት መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት ለመሠረተ ልማት ዘርፍ እንቅፋት የሆነውን የቅንጅት እጦት ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ የችግሩን መንስኤ ለማወቅ ከሚደረጉ ጥናቶች ባሻገር የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የመንገዶች አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የኢትዮ ቴሌኮም፣ የውሃና ፍሳሽ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በቅርበት ሊሠሩ ይገባል። በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ መረጃ መለዋወጥ መቻልም ይኖርባቸዋል።
እያንዳንዱ መሠረተ ልማት ከመዘርጋቱ አስቀድሞ የሌሎች መሠረተ ልማቶች ዲዛይን መካተቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ለዚህም ተቋማት በየግላቸው መሠረተ ልማቶችን ከመዘርጋት ይልቅ ከሌሎች መሠረተ ልማቶች የሚዘረጉ ተቋማት ጋር አብሮ መሥራት ያስፈልጋል። ይህን በማድረግም የአገር ሀብት የሚፈስባቸውን የተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በጊዜ፣ በገንዘብና በሀብት መታደግ ይቻላል።
መላኩ ኤሮሴ