
መገናኛ ብዙኃን አብሮነትን፣ መከ ባበርንና መተዋወቅን መሠረት ያደረጉ ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃዎችን በማቅረብ የተዛቡ ትርክቶችና ጥላቻን ማስወገድ እንደሚገባቸው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ፡፡
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን አሚኮ ኅብር የተሰኘውን ሁለተኛ ቻናሉን ትናንት ባስጀመረበት ወቅት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ እንደተናገሩት ፤ ኢትዮጵያ ብዙ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ባሕልና ሥነ ምህዳር የሚገኝባት መልከ ብዙ ናት፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ ነብሩ ዥንጉርጉር በሚል የምንገለጽ ነን ፡፡መገናኛ ብዙኃን አብሮነትን፣ መከባበርንና መተዋወቅን መሠረት ያደረጉ ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃዎችን በማቅረብ የተዛባ ትርክትንና ጥላቻን ማስወገድ ይገባል፡፡
በሐሰት ትርክት ላይ ተጠምዶ፣ በጽንፈኝነት ጫፍ ተንጠላጥሎ ፣ ሕዝብን በጥላቻ መነጽር እያየ ፣ አንዱን ከአንዱ እያጋጨ መኖር እንደ ልምድና እንደ ጀግንነት መቆጠር እየተለመደ መጥቷል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ይህም እርስ በእርሳችን ለመተዋወቅ ባለመዘጋጀታችን ፣ ሚዛናዊና እውነተኛ መረጃ በየአካባቢው መድረስ ባለመቻሉ ልዩነቶችን እንደ ስጋት በመቁጠር በርካታ ግጭቶች ተፈጥረዋል ፡፡ በግጭቱ ተጠቂ የነበረው የአማራው ሕዝብ ነው ብለዋል ፡፡
የአማራ ሕዝብ በጎረቤት ሀገራት ጨምሮ በእውነተኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ ስም የለውም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤መገናኛ ብዙሃን የተዛባውን ትርክት በማስረዳት ለሚጠሉንና ለሚወነጅሉን ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ራስን የማስተዋወቅ ኃላፊነት አለባቸው ሲሉ አስገንዝበዋል ፡፡
እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን የምሥራቅ አፍሪካ ሕዝቦች ዕጣ ፋንታ በአንድነት የተጋመደ መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ፤ በዚህ ረገድ መገናኛ ብዙኃን አብሮነትን፣ መከባበርንና መተዋወቅን መሠረት ያደረጉ ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃዎችን በማቅረ የተዛባ ትርክትንና ጥላቻን ማስወገድ እንደሚገባም አስገንዝበዋል ፡፡
አሚኮ ኅብር የአማራ ክልል ብዝኃ ልሳንን ከማጠናከር አልፎ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንዲተዋወቁ እና ያለንን ኃብት በፍትሐዊነት ተጠቅመን እንድንኖር መንገድ ይከፍታል ብለዋል ፡፡
ሁላችንንም ልዩነታችንን እርስ በእርስ ተዋውቀን፣ ተከባብረን እና ተደማምጠን ከያዝናቸው የግጭት ምንጭ ሳይሆኑ የጌጥና የውበት ምንጭ ሆነው የሚያገለግሉ እንደሆነ ገልጸዋል ።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በበኩላቸው ፤ አሁን ላይ ሚዲያዎች ላልተፈለገ ጽንፈኝነት እና አክራሪነት ተጋል ጠዋል። ሚዲያዎቹ የኅብረተሰቡን ፍላጎት በትክከል መግለጽ ያልቻሉበት ጊዜ ላይ መድረሱን ገልጸዋል ፡፡
አብዛኞቹ ሚዲያዎች ኅብረተሰብን ከማቀራረብ ይልቅ የሚያራርቁ ኅብረተሰብን አንድ ከማድረግ ይልቅ የሚበትኑ አስተሳሰቦችን በማራገብ የአድኃሪያን አስተሳሰብ እንደተጠናወታቸውም አስረድተዋል ፡፡
በዚህ ሂደት አሚኮ የሕዝብ ልሳን በመኾን የሕዝብን ፍላጎት እና ትክክለኛ አመለካከት በማውጣት አኩሪ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው ፤ አሚኮ ለውጡ በአማራ ክልል እንዲቀጣጠል በማድረግ አኩሪ ታሪክ የፈጸመና ለውጡ ፈር እንዲይዝ እና ሕዝቡ ለውጡን ጠብቆ እንዲዘልቅ በማድረግ የሠራው ሥራ የሚያኮራ መሆኑን አውስተዋል ፡፡
በሌላ በኩል መንግሥት ሕግ በማስከበር በኩል ለሚሠራው ሥራ ትክክለኛ መረጃ በማቀበል እየሠራ በመሆኑ መንግሥት ከፍተኛ ምሥጋና አ ለው ብለዋል ፡ ፡
“አሚኮ አዲሲቷን ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የድርሻውን እየተወጣ ያለ ሚዲያ ነው ” ያሉት ደግሞ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ቦርድ ሰብሳቢው አቶ ግርማ የሺጥላ ፤ የተሳሳተ ትርክትን በማረም የክልሉን ሕዝብ እውነተኛ ማንነት ለዓለም እንደሚገልጥም አመልክተዋል፡፡
የቦርድ ሰብሳቢው ኮርፖሬሽኑ ዓለም የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ እንዲታጠቅ እና ብቁ ባለሙያዎችን እንዲያፈራ የክልሉ መንግሥት በትኩረት እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥት እና አጋር አካላት ከኮርፖሬሽኑ ጋር በጋራ እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዳንኤል ዘነበ