
አዲስ አበባ፡- በ15 ሺህ 600 ብር ካፒታል በ41 አባላት የተመሰረተው አዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ መሰረታዊ የህብረት ሥራ ማህበር ጠቅላላ ሃብቱ ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ የአባላቱ ቁጥርም ከ75 ሺ በላይ መድረሱን አስታወቀ።
የህብረት ሥራ ማህበሩ በ2014 ዓ.ም ብቻ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለአባላቱ መስጠቱ ተገልጿል።
የፋይናንስ ተቋሙ የተመሰረተበትን 15ኛ ዓመት ክብረበዓል ማጠናቀቂያ መድረክ ትናንት ባካሄደበት ወቅት የተቋሙ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘሪሁን ሸለመ፤ ማህበሩ በየዓመቱ አቅሙን እያሳደገ ጠቅላላ ሃብቱን ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ማድረሱን አስታውቀዋል።
መሰረታዊ የህብረት ሥራ ማህበሩ ሲመሰረት የነበሩትን 41 አባላት ቁጥር በማሳደግም በአሁኑ ወቅት ከ75 ሺ በላይ አባላት መያዙን አቶ ዘሪሁን ጠቁመዋል።
የህብረት ሥራ ማህበሩ ባለፉት 15 ዓመታትም ከሶስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለተለያዩ ዜጎች መስጠቱን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ማህበሩ በ2014 ዓ.ም ብቻ የሰጠው ብድር ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በእስካሁኑ የብድር አመላለስ ሂደት ከ99 በመቶ በላይ የሆነ ጤናማ የብድር አመላለስ ውጤት እንዳለው ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል።
ማህበሩ በየጊዜው የቁጠባና የብድር አገልግሎቱን እያሰፋ ይገኛል። ተቋሙ በአዲስ አበባ አስተዳደር፣ በኦሮሚያ እንዲሁም በሲዳማ ክልሎች ቅርንጫፍ ከፍቶ የአባላቱን ቁጥር ለማሳደግ እየሰራ ነው ብለዋል አቶ ዘሪሁን።

በቀጣይም በአማራ ክልልና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቅርንጫፍ ለመክፈት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ በተለያዩ አካባቢዎች የብድርና ቁጠባ አገልግሎት የሚሰጡ ቢሮዎች ለማቋቋም ዕቅድ እንዳለው አቶ ዘሪሁን ጠቁመዋል።
የህብረት ሥራ ማህበሩ በ2019 ዓ.ም የአባላቱን ቁጥር 700 ሺ በማድረስ አጠቃላይ ካፒታሉን ወደ 20 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ለማድረስ ዕቅድ መያዙን አስታውቀዋል።
የህብረት ሥራ ማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ መስፍን ገብረስላሴ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የፋይናንስ ተቋሙ መቆጠብ መሰልጠን ነው በሚል መርህ በርካቶች እራሳቸውን በፋይናንስ እንዲያጠናክሩ ሲሰራ ቆይቷል።
አብዛኛው ማህበረሰብ በባንክ አገልግሎት ውስጥ በቀላሉ የማያገኘውን የብድር አገልግሎት አዋጭ በተለያዩ አማራጮች እያቀረበ ይገኛል። በዚህም በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችላል ሲሉ ተናግረዋል።
የህብረት ሥራ ማህበሩ የፋይናንስ አቅምንና ተደራሽነቱን በማሳደግ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን ለመቀላቀል እንቅስቃሴ ላይ ነው፣ በአሁኑ ወቅት አዋጭ የኢንሹራንስ አክሲዮን ማህበር ለማቋቋም የአክሲዮን ሽያጭ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የህብረት ሥራ ማህበሩ በቀጣይም የፋይናንስ አገልግሎት የስልጠና ማዕከል ለማቋቋም ውጥን እንዳለው አቶ መስፍን አስታውቀዋል።
ከ220 በላይ ቋሚ ሰራተኞች ያሉት አዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ መሰረታዊ የህብረት ሥራ ማህበር፤ የአፍሪካ የቁጠባ ብድር ህብረት ሥራ ኮንፌዴሬሽን አባል መሆኑ ታውቋል።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ሰኔ 13 /2014