በሳንምታዊው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን በ1950 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የነበሩ ጋዜጦችን ተመልክተናል። ገሚሶቹ ርዕሰ ዜናዎች የተጻፉበት መንገድና ዜናዎቹ የተጻፉበት መንገድ ባይጣረስም፤ ርዕሰ ዜናዎቹ በተጻፈበት መንገድ ዜናዎቹ የተሟሉ ሆነው ያልቀረቡ ነበሩ። ዜናዎቹ ከተነበቡ በኋላም ከዛስ ምን ሆነ የሚያሰኝ ጥያቄ ያስከትላሉ። ከሦስት ዓመት እርግዝና በኋላ 2ኪሎ ከ150 ግራም በሕክምና ቀዶ ጥገና በወጣላቸው ሴትዮ ስንገረም ስለተወለደው ህፃን ግን የሚለን የለም። ቁመቱ ሁለት ሜትር ከሩብ የሆነው የሐረር ሰው በርዕሰ ዜናው ከሆስፒታል ወጣ ቢለንም ስለቁመቱ ችግር እንጂ ስለጤናው ችግርና ሕክምና የሚለን የለም። የቀ.ኃ.ሥላሴ ቤተመጻሕፍት ስጦታ ማግኘቱ፣ በወሎ 50 ሺህ የዛፍ ጉድጓድ እንደሚቆፈር የሚነግረንን ዜናም አካተናል።
የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የመፃሕፍት ስጦታ አገኘ
ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ቅጥር ግቢ የሚገኘው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቤተመጻሕፍት ፸፯ ልዩ መጻሕፍት ከቸኰስላቫኪያ መንግሥት አግኝቷል።
መጻሕፍቶቹንም፤ በኢትዮጵያ የቸኰስላቫኪያ ኤምባሲ ካልቸራል አታሼ ሚስተር ሀርቻካ ዝንዲኰ ፤ግንቦት ፲፪ ቀን ፤ወደ ዩኒቨርሲቲ ቤተመጻሕፍት ሔደው፤ ለኮሌጁ ሳይንስ ዲን ፤ለፕሮፌሰር ጃቦትንስኪ አስረክበዋል። የካልቸራሉ አታሼ መጻሕፍቱን ባስረከቡበት ወቅት፤ እነዚህ መጻሕፍት ለዩኒቨርሲቲው ጠቃሚ ሆነው ከተገኙ፤ የቸኰስላቫኪያ መንግሥት
ተጨማሪ መጻሕፍት ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን አስገንዝበዋል። ፕሮፌሰር ጃስቲን ኪም በሰጡት መልስ፤ መጻሕፍቱ ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ከፍ ያለ ጥቅም የሚሰጡ መሆናቸውን ገልጸው፤ እኔ የሳይንስ ፋክልቲ ዲን እንደመሆኔ መጠን፤ ለወደፊት ከቸኰስላቫኪያ መንግሥት የሚሰጡት መጻህፍት ሳይንስ ነክ ቢሆኑ በጣም ደስ ይለኛል በማለት፤ ከዚያ የነበሩትን አሳቁዋቸው። (አዲስ ዘመን ግንቦት 13 ቀን 1957ዓም)
በጎፍ ተራራ ላይ ፶ ሺ የዛፍ ጉድጓድ ይቆፈራል
(ከኢትዮጵያ ወሬ ምንጭ)
ደሴ፤ በወሎ ጠቅላይ ግዛት ጽህፈት ቤትና ጠቅላይ ግዛቱ የእርሻ ሚኒስቴር ተባባሪነት ፤ የጎፍ በተባለው ተራራ ላይ ዛፍ ለመትከል ስለታሰበ፤ የተራራውን አቀማመጥ የጠቅላይ ግዛቱ እንደራሴ ክቡር ፊታውራሪ ማሞ ስዩም ተመለከቱ። በዚሁ ጊዜ የጠቅላይ ግዛቱ የእርሻ ሥራ ዳይሬክተር አቶ ክንድዬ ኃይሉ የኮምቦልሻ ማዘጋጃ ቤት ሹም አቶ ሽፈራው ወልደ ልዑልና ሌሎችም ሰዎች ከተራራ ጫፍ ድረስ ወጥተው አካባቢውን ተመልክተዋል።
የጠቅላይ ግዛቱ የደን ክፍል ኃላፊ አቶ ኃይሉ ዳኜ፤እስከ አሁን ድረስ ፲፭ ሺህ ጉድጓድ እንደተቆፈረና በጠቅላላው እስከ ፶ ሺህ ጉድጓድ ለማስቆፈር የታሰበ መሆኑን ለክቡር እንደራሴ ገለጹ።
ከዚህም ሌላ የዚሁ አጋር ም/ወረዳ ገዥ ሻምበል አሰፋ ወዳጄ በቦታው ተገኝተው ስለነበር፤ አነሳስተው ጉድጓድ በማስቆፈር ይህን የተቀደሰ ተግባር በመፈጸማቸው ፤ ክቡር እንደራሴው አመስግነዋል። ( ግንቦት 28 ቀን 1957)
፫ ዓመት አርግዛ በኦፕራሲዮን ተገላለች
እመት አሰገደች መኩሪያ የተባሉ የ27 ዓመት ሴት፤ ሦስት ዓመታት ሙሉ በእርግዝና ከቆዩ በኋላ ግንቦት ፳፯ ቀን ፲፱፻ ፶፯ ዓ.ም የጳውሎስ ሆስፒታል ሀኪሞች በኦፕራሲዮን የተረገዘውን ከሆዳቸው አውጥተውላቸዋል። እመት አሰገደች ነዋነሪነታቸው በአሩሲ ጠቅላይ ግዛት፤ በሶሬ ወረዳ፤ በጥሪባ ገብርኤል አጠገብ ነው። እርሳቸውም የአንድ ወንድና የአንድ ሴት ልጅ ወላጆች ሲሆኑ ፤አቶ ተከስተ በቀለ የሚባሉ የትዳር ጓደኛ አሉዋቸው። ትናንትና ከእመት አሰገደች መኩሪያ ሆድ የወጣው ሁለት ኪሎ ከ150 ግራም እንደሚመዝን ከሆስፒታሉ የተገኘው ወሬ ያስረዳል።
ስለዚሁ ጉዳይ ኦፕራሲዮን ያደረጉት የቅዱስ ጳውሎስ ሐኪሞች ዶክተር አርብራያዶቪችና ዶክተር ጎሮቪስቢያ ሲያስረዱ ያለቦታው ለተረገዘ ልጅ ሳይሆን ቀርቷል። ይህ እንደ ህፃን ያለ ነገር ያረፈበት ቦታ ከመጥበቡ የተነሳ በሴትዮዋ ላይ ጉዳት ለማስከተል ይችል ነበር ብለዋል።
እመት አሰገደች በበኩላቸው ሲናሩ ለሕክምና ናዝሬት ሆስፒታል ሄጄ ሐኪሙ ደምሽ አልቆ ነው ብሎኝ ተመልሻለሁ። እርግዝና መሆኑን ግን በደንብ አውቀው ነበር። ቢብስብኝ ጊዜ ይህ ሆስፒታል ይፈውሳል ፤ በነፃም ያክማል ማለትን በወሬ ስለሰማሁ፤ እዚሁ ልሙት ብዬ መጣሁ። አሁን ግን ከዚህ ስቃይ ሳልፈወስ አልቀርም በማለት ገልጸዋል።( ግንቦት 28 ቀን 1957)
ለመጀመሪያ ጊዜ በአገራችን ቁንዶ በርበሬ ተተከለ
በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የቁንዶ በርበሬ ተክል መተከል መጀመሩን ጅማ የሚገኘው የእርሻ ሚኒስቴር መ/ቤት ገልጿል። የቁንዶ በርበሬው ተክል የተከሉት አቶ አካለወርቅ ልብነወልድ የእርሻ ሚኒስቴርና አቶ መንገሻ መኮንን የጅማ ጠቅላይ ግዛት ረዳት እንደራሴ ናቸው።
የቁንዶ በርበሬው ተከላ በጅማ ከተማ በስተምሥራቅ ሲል ከከተማው ስምንት ኪሎ ሜትር ካለው መልኰ ከተባለው ሥፍራ ላይ ሰኔ ፲ ቀን ተከናውኗል።
በዕለቱ በተደረገው የዛፍ ተከላ በዓል ፫ሺህ ፮፻ የቁንዶ በርበሬ ችግኞች ተተክለዋል። የቁንዶ በርበሬዎቹ ዛፎች የተተከሉበት ሥፍራ ፭ ሺህ ካሬ ሜትር ይሆናል። በዕለቱም ለዛ ተከላው በዓል የተገኘው ሕዝብ ብዛት አንድ ሺህ ያህል እንደሚደርስ ተገምቷል።
የጂማውን የእርሻ ሚኒስቴር መ/ቤት ጠይቀን እንደተረዳነው፤ ከሦስት እስከ አራት ሚሊዮን የሚሆኑ የዛፍ ችግኞች ተሰናድተው ለሕዝብ ሊታደሉ፤ በመጠበቅ ላይ መሆናቸው ተነግሮናል። የዛፍ ችግኞቹም ያገርና የውጭ አገር ሲሆኑ የዓይነት ብዛታቸውም አሥራ ሰባት መሆኑን ተረድተናል።
ይህን ዘንድሮ የተተከለው ቁንዶ በርበሬ ዛፍ፤ ፍሬ መስጠት የሚጀምረው ከአምስትና ስድስት ዓመታት በኋላ ነው። ማንም እንደሚያውቀው እስከዛሬ ወደ አገራችን ይገባ የነበረው ቁንዶ በርበሬ እየተቆላ በመሆኑ ለዘር የማይሆን ነበር። (ሰኔ 13 1957 ዓ.ም)
ቁመቱ ፪ ሜትር ከ፳፭ ሳንቲም ሜትር የሆነው ሰው ከሆስፒታል ወጥቷል
ስለጀማል ሔሬድ ከዚህ በፊት በጋዜጣችን ገልጠናል፤ ጀማል ቁመቱ ሁለት ሜትር ከሩብ፤ ደረቱ አንድ ሜትር ከ፲፭ ሳንቲም ሜትር የሆነ ነው፤ ሦስት ሰዎች በቀን የሚበሉትን ጀማል ብቻውን ያቀላጥፈዋል ተብሏል።
ሲተኛ ደንበኛው የሰው አልጋ አይበቃውም፤ ከቅልጥሙ በታች ያለው እግሩ ከአልጋው ይተርፋል፤ ጀማል ደንበኛ የሰው ቁመት ካለው ሰው ጋር አብሮ ሲቆም ለሌሎች ረጅም የሚመስሉ ከጀማል ትከሻ በታች ይቀራሉ።(ግንቦት 25 ቀን 1957)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2014