ባለፉት ጥቂት ዓመታት የአዲስ አበባ ከተማን የመንገድ ሽፋን የሚያሳድጉና የተቀላጠፈ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር የሚያስችሉ የመንገድ ግንባታዎች በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ተከናውነዋል። ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ 24 የሚደርሱ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸው ይታወሳል። በተያዘው በጀት ዓመትም የከተማዋ መንገዶች ባለስልጣን በርካታ መንገዶችን አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል።
ተጨማሪ የመንገድ ግንባታዎችን አጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ ነው። በድምሩ ከ100 በላይ መንገዶች በአሁኑ ወቅት ግንባታቸው እየተከናወነ መሆኑን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን መረጃዎች ያሳያሉ። የመንገድ ፕሮጀክቶቹ በተለያየ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው።
ፕሮጀክቶቹ የደረሱበት ደረጃ እንደፕሮጀክቶቹ የተለያየ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ የተሻለ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኙ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ አፈጻጸማቸው መካከለኛ ደረጃ ላይ መሆናቸውንና መጓተት የታየባቸውም እንዳሉ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢያሱ ሰለሞን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያብራራሉ።
ለመንገዶች ግንባታ መጓተት መንስኤ የሚሆኑ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉም ጠቅሰው፣ ዋንኛው ምክንያት ግን የወሰን ማስከበር ችግሮች መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። አንዳንድ ፕሮጀክቶች በተመሳሳይ ወቅት ተጀምረው፣ ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ ባሉ ጉዳዮች ምክንያት የፕሮጀክቶች አፈጻጸም እጅግ የተራራቀ ሆኖ ይታያል ይላሉ። የወሰን ማስከበር ችግር ያላጋጠማቸው ፕሮጀክቶች ግንባታ በከፍተኛ ፍጥነት ሲከናወን የወሰን ማስከበር ችግር ያጋጠማቸው ፕሮጀክቶች ግን ከፍተኛ መጓተት እየተስተዋለባቸው መሆኑን ያብራራሉ። ይህንንም በተመሳሳይ ወቅት ተጀምረው አፈጻጸማቸው በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሁለት ፕሮጀክቶችን ለአብነት በማንሳት ምክትል ሥራ አስኪያጁ ያስረዳሉ። እንደ እሳቸው ገለጻ፤ እነዚህ ፕሮጀክቶች ከአሌክሳንደር ፑሽክን ተነስቶ በቄራ ወደ ጎተራ ማሳለጫ የሚሄደው የመንገድ ፕሮጀክት እና አውቶብስ ተራ – መሳለሚያ – 18 ማዞሪያ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ናቸው። ሁለቱም ፕሮጀክቶች በ2012 ዓ.ም የተጀመሩ ናቸው። ሁለቱም ፕሮጀክቶች የረጅም ጊዜ የመንገድ ግንባታ ልምድ ባላቸው ተቋራጮች ነው ግንባታቸው እየተከናወነ ያለው።
እንደ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ በ2012 ግንባታው የተጀመረው ከአሌክሳንደር ፑሽክን አደባባይ / ሳር ቤት / ተነስቶ በቄራ ወደ ጎተራ ማሳለጫ የሚሄደው የመንገድ ፕሮጀክት የዋሻ ውስጥ መተላለፊያን ጨምሮ ተሸጋጋሪ ድልድይና የፈጣን አውቶብስ መመላለሻ ኮሪደርን አካቶ እየተገነባ የሚገኝ ነው። ይህ የመንገድ ፕሮጀክት 3 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመትና ከ30 እስከ 45 ሜትር የሚሆን የጎን ስፋት አለው። በአሁኑ ወቅት ከ90 በመቶ በላይ የግንባታ ሥራው ተጠናቋል። በከተማዋ በፍጥነት ከተከናወኑ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው። በቀጣይ ጊዜያት ቀሪ ሥራዎቹ ተጠናቀው ሙሉ በሙሉ ለትራፊክ ክፍት እንዲሆን ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
የአውቶብስ ተራ – መሳለሚያ – አስራ ስምንት ማዞሪያ ፕሮጀክት ግን በተመሳሳይ በ2012 ዓ.ም በሁለት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ የጊዜ ቀጠሮ ተይዞለት ግንባታው የተጀመረ ቢሆንም፣ ሁለት ዓመት ከአምስት ወር ገደማ አስቆጥሮም ግንባታው ገና 12 በመቶ ላይ ይገኛል። ፕሮጀክቱ ከፍተኛ መጓተት ከታየባቸው የመዲናዋ የመንገድ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው።
ለዚህ ፕሮጀክት መጓተት ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የወሰን ማስከበር ችግር ነው የሚሉት አቶ ኢያሱ ፤ እስካሁን ድረስ ከአውቶብስ ተራ ወደ መሳለሚያ ባለው ወደ 800 ሜትር የሚደርስ የመንገድ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ አስፋልት ለማልበስ ጥረት የተደረገ ቢሆንም ፤ ከዚያ በኋላ ባለው የመንገዱ ክፍል ላይ ሰፊ የወሰን ማስከበር ችግሮች አጋጥመዋል ይላሉ። የወሰን ማስከበር ችግሩ ከግለሰብ የመኖሪያ ቤቶች ጀምሮ የመንግሥት የልማት ተቋማት መሰረተ ልማቶችን በጊዜው ባለማንሳታቸው የመንገድ ግንባታውን በተያዘው የጊዜ ቀጠሮ መሰረት ሊከናወን አለመቻሉን አቶ እያሱ ያነሳሉ።
እንደ አቶ እያሱ ማብራሪያ ፤ መነሳት ያለባቸው የመንግሥት ልማት ተቋማት በጊዜው አለመነሳት በተለይም እንደ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያሉ ተቋማት መሰረተ ልማቶች አለመነሳት የመንገድ ግንባታ ሥራው እንዳይካሄድ እንቅፋት ሆኗል። እንዲሁም የመኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ድርጅቶች ያላቸው አካላት በጊዜው አለመነሳት ሌላኛው እንቅፋት ነበር። የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት የወሰን ማስከበር ችግሮች በመንገድ ግንባታ ሥራዎች ላይ እያሳደረ ያለው ተፅዕኖ ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱ ከሚችሉ ፕሮጀክት አንዱ ነው።
የመኖሪያ ቤት እጥረት የመዲናዋ ትልቁ ችግር በሆነበት በዚህ ወቅት ቤት ለማግኘት ቆጥበው እየተጠባበቁ ካሉት የከተማዋ ነዋሪዎች ጎን ለጎን ለልማት ተነሺዎች ቤት ማቅረብ ለመንግሥት ፈተና ሆኖ ቆይቷል የሚሉት አቶ ኢያሱ፣ ለመንገድ ልማት ተነሺዎች ቤት ማቅረብ አለመቻል የልማት ተነሺዎችን ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች በጊዜው ለማንሳት ፈተና ሆኗል ይላሉ። ለመንገድ ግንባታ ተነሺዎች ምትክ ቤትና ምትክ ቦታ ማቅረብ አለመቻል ተነሺዎችን ማንሳት እንዳይቻል አድርጎ መቆየቱን ጠቅሰው፣ የመንገድ ግንባታው እንዲፋጠን ምትክ ቦታና ቤት ማቅረብ አስፈላጊ መሆኑን ያስገነዝባሉ።
ምክትል ሥራ አስኪያጁ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በሚመለከታቸው አካላት መካከል ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ መሆኑን አስታውቀው፣ የወሰን ማስከበር ችግርን ለመፍታት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የመንገድ ግንባታው የሀገር ልማት አካል መሆኑን በመገንዘብ ያለ ማንም ጫና መሰረተ ልማቶችን ሊያስነሱ ይገባል ሲሉ ያመለክታሉ።
በሌላም በኩል የሚገነባው መንገድ የመላው የከተማው ነዋሪ ሀብት መሆኑን በመገንዘብ የልማት ተነሺዎች ትብብር ሊያደርጉ እንደሚገባም ነው የሚያስገነዝቡት። ለእነዚህ አካላት ምትክ ቦታና ቤት የሚያቀርብ አካልም ለጉዳዩ ትኩረት በማድረግ ምትክ በመስጠት ተነሺዎቹ እንዲነሱ እና የመንገድ ግንባታው እንዲፋጠን ሊያደርግ ይገባል ብለዋል አቶ ኢያሱ።
እንደ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ ከአውቶብስ ተራ- መሳለሚያ- 18 ማዞሪያ መንገድ በተጨማሪ በታቀደላቸው ጊዜ የግንባታ ሥራቸው ያልተከናወነ ሌሎች የተጓተቱ ፕሮጀክቶችም አሉ። ለአብነት የቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አንዱ ነው፤ ፕሮጀክቱ በ2009 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በ2012 ዓ.ም ተጠናቆ ወደ አገልግሎት እንዲገባ ታቅዶ ለግንባታውም ሁለት ቢሊዮን ብር ተበጅቶለታል። በቻይና ኤግዚም ባንክ የበጀት ድጋፍ ከሚከናወኑ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው በቂሊንጦ ፣ በቡልቡላ በኩል አድርጎ ቃሊቲ ማሰልጠኛ አካባቢ የሚገኝ የመንገድ ፕሮጀክትም የዚሁ አካል ነው።
የቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ወደ 11 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል። ከዚህ ውስጥ ሶስት ቦታዎች ላይ ከ240 ሜትር እስከ 50 ሜትር ርዝመት ያላቸው ሶስት የማሳለጫ ድልድዮችን ጨምሮ በቀኝ በኩል ያለው የመንገዱ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ አስፋልት ለብሶ አገልግሎት እየሰጠ ነው። ነገር ግን በመንገዱ ግራ ክፍል በኩል በተለይም በማሰልጠኛ በኩል ትልቅ የውሃ መስመር በመኖሩ ምክንያት የወሰን ማስከበር ተግዳሮት አጋጥሞ ነበር። የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ከረጅም ጊዜ መጓተት በኋላ በዚህ ዓመት የውሃ መስመሩን ቀይሯል።
ለረጅም ጊዜ ለመንገድ ግንባታው እንቅፋት ሆኖ የቆው ይህ የውሃ መስመር በመነሳቱ አሁን የመንገድ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ይላሉ። በዚሁ ሂደት ውስጥ በቻይና ኤግዚም ባንክ ለኮንትራክተሩ መከፈል ያለበት ባለመከፈሉ ከፋይናንስ ጋር ተያይዞ የገጠሙ ችግሮች እንዳሉም ይገልጻሉ። ይህንን ችግር ለመፍታትም የከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቅርቡ አንድ መፍትሄ ተቀምጦለት ወደ ግንባታ ይገባል ብለዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት የቆየው የኮተቤ- ካራ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አንዱ መሆኑን ምክትል ሥራ አስኪያጁ ይጠቁማሉ። ኮተቤ ካራ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በ 2009 ዓመተ ምህረት መጨረሻዎቹ ወራት የተጀመረ መሆኑን አስታውሰው፣ ሙሉ ግንባታው በ3 ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ታስቦ እንደነበረና ግንባታው አስከ አሁንም እንዳልተጠናቀቀ ያብራራሉ።
እንደ አቶ ኢያሱ ማብራሪያ ፤ ለዚህ ፕሮጀክት ችግር መፍትሄ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነው። መንገዱ ስድስት ኪሎ ሜትር አካባቢ የሚሸፍን ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ወደ 5 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የመንገዱ ክፍል ሙሉ በሙሉ አስፋልት ለብሶ አገልግሎት እየሰጠ ነው። በቀሪው አንድ ኪሎ ሜትር ውስጥ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የመጀመሪያ 400 ሜትር መንገዱን የመጀመሪያ አስፋልት የማልበስ ሥራ እየተሰራ ነው።
600 ሜትር በሚሆን የመንገድ ክፍል ላይ በተለይ ከኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ወደ ካራ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ያነሱትን ጥያቄ መመለስ ባለመቻሉ ግንባታው ሊጓተት ችሏል ይላሉ። ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምክንያታዊ ስለሆኑ ጥያቄዎቹን ሰምቶ መፍትሄ መስጠት አስፈላጊ ስለሆነ መፍትሄ የመስጠት ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው። መፍትሄ ከተሰጠ በኋላ ቀሪ ሥራዎችን ለመስራት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
የወሰን ማስከበር ችግሮች በአፋጣኝ እልባት እንዳያገኙ የሚያደርገው አንዱ ምክንያት የፍርድ ቤት እግድ መሆኑን የባለስልጣኑ መረጃዎች ያሳያሉ። ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ የሚነሱ አለመግባባቶች ወደ ፍርድ ቤት ሲወሰዱ ለረጅም ጊዜ ጉዳዩ እልባት ሳያገኝ የሚቀርባቸው ሁኔታዎች አሉ። በሌላ በኩል የካሳ ክፍያ ከተፈጸመ በኋላ ቶሎ ለመነሳት ፈቃደኛ ያለመሆን አዝማሚያዎችም የመንገድ ፕሮጀክቶች እንዲጓተቱ ምክንያት ሲሆን ይስተዋላል።
በአጠቃላይ በመዲናዋ በመንገድ ግንባታ ዘርፍ የሚተስዋለውን የወሰን ማስከበር ችግር ለመቅረፍ ሁሉም አካላት በትብብር ሊሰሩ ይገባል። ፍርድ ቤቶችም ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ውዝግቦች በአጭር ጊዜ ውሳኔዎች የሚሰጥበትን አሰራር ቢከተል መልካም ነው።
የከተማዋ ነዋሪዎችም የመንገድ ግንባታዎች የመላው ከተሜ እና የመላ ሀገሪቱ ልማት መሆኑን በመገንዘብ ለልማቱ ያላቸውን ቀናዒነት ማሳየት አለባቸው። ለመንገድ ግንባታ ለሚነሱ የከተማዋ ነዋሪዎች ምትክ መሬትና ቤት የሚያቀርበው አካልም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2014