የአፍሪካ የነፃነት ቀን በዓል ፫ኛ ዓመት ዛሬ ተከብሮ ይውላል።
የአፍሪካ የነፃነት ቀን ግንቦት ፲፯ ቀን ዛሬ በመላው ዓለም ተከብሮ ይውላል። በዓሉ ፫ኛ ዓመት በተለይም በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት መናገሻ ከተማ በአዲስ አበባ በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ በአፍሪካ አዳራሽና በዓድዋ አደባባይ የአፍሪካ ነፃ መንግሥታት ሰንደቅ ዓላማዎች ተሰቅለው በመውለብለብና የሦስቱ ክፍል የሙዚቃ ጓዶች የሙዚቃ ስልት በማሰማት በዓሉን አድምቀው ይውላሉ።
ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴይህንን የአፍሪካ ነፃነት ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ ዛሬ በስምንት ሰዓት ንግግር ያደርጋሉ።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ለመመሥረት የአፍሪካ መሪዎች በተሰባሰቡበት ወቅት ግንቦት ፲፯ ቀን የአፍሪካ ነፃነት ቀን እንዲሆን በወሰኑት መሠረት ይህ እለት በመላው ዓለም በተለይም በአፍሪካ ከፍ ባለ ሥነስርዓት ተከብሮ ይውላል።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት በሆነው በአፍሪካ አንድነት ቤት ውስጥ ጸሐፊው ክቡር ሚስተር ዲያሎ ቴሊ ዛሬ ማታ የሪሴፕሽን ግብዣ እንደሚያደርጉ ታውቋል። በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የአፍሪካ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች የአፍሪካ የነፃነት በዓል በደንበኛው አክብሮ ለመዋል በአስፈላጊው ዝግጅት ተካፋይ ሆነዋል።
(ግንቦት 17 ቀን 1958 ከታተመው አዲስ ዘመን)
የኡጋንዳ ነዋሪዎች የጦር መሣሪያ እንዲያስረክቡ ተጠየቁ
ከናይሮቢ፤ትናንት ማለዳ የካምፓላ ሬዲዮ ‹‹ማንኛውም ባለ ጦር መሣሪያዎች ዛሬ እንዲያስረክቡ አለበለዚያ ግን በሕግ የሚቀጡ›› መሆናቸው አወጀ።
ከዚሁ ሬዲዮ ጣቢያ የተገኘው ወሬ፤ የተመዘገቡም ሆነ ያልተመዘገቡ መሣሪያዎች በሙሉ ለመንግሥት እንዲመለሱና በአገሪቱ የተሠሩም መሣሪያዎችም ቢሆኑ በሕግ የማይጠየቁበት ምክንያት የሌለ መሆኑን አረጋገጠ።
በዑጋንዳ ካባካ በሰር ኤድዋርድ ፍሬዴሪክ ሙቴሳ ላይ የወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዲወሰድ ማዕከላዊ መንግሥት እርምጃ ከወሰደበት ጊዜ አንስቶ የሚደረገው የሬዲዮ አዋጅ ፤የፖሊስ ጣቢያዎች የጦር ማሣሪያዎችን የሚረከቡ መሆናቸውን ይገልጣል። የጠፉት የዑጋንዳው ካባካው መንግሥት ሰላምና ፀጥታ እንደሰጠው አመልክቷል። የዑጋንዳው መንግሥት ካባካው የት እንደሄዱ የማያውቅ ነው ብሏል የሬዲዮ መግለጫው።
(ግንቦት 23 ቀን 1958 ከታተመው አዲስ ዘመን)
በሲዳሞ ወህኒ ቤት ፳፪ ሺህ እግር ቡና ተተክሏል
አዋሳ፤(ኢ-ዜ-አ-) የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ወህኒ ቤት በ፫፻ ሺህ ሜትር ካሬ ቦታ ላይ ፳፪ ሺህ እግር ቡና አልምቷል።
የጠቅላይ ግዛቱ ወህኒ ቤቶች አስተዳዳሪ ሌተናል ኰሎኔል ተስፋዬ ለማ ስለ ወህኒ ቤቱ ጠቅላላ የሥራ እርምጃ ሲያስረዱ በወህኒ ቤቱ እሥረኞች ጉልበት የተገኘው ገቢ የገንዘብ ሚኒስቴርና ያገር ግዛት ሚኒስቴር እንዲያውቀው ከተደረገ በኋላ ተመልሶ ለወህኒ ቤቱ እሥረኞችና አስፈላጊ ለሆኑ የሥራ ተግባሮች ወጪ እንዲሆን ይደረጋል።
ወህኒ ቤቱ በአሁኑ ሰዓት ባደረገው መሻሻል አጥፊዎቹ የሞራልና ግብረ ገብነት ፤ የቀለምና የሙያ ትምህርት እያገኙ የሚሰለጥኑበት አቅማቸውና ችሎታቸው የሚፈቅድላቸውን የሚመክሩበትና ላደረጉትም ስህተት እንዲፀፀቱ የሚደረግበት ጥሩ የማኅበራዊ አኗኗር ትምህርት ይሰጣቸዋል።
ሌተናል ኰሎኔል ተስፋዬ ለማ ስለ ወህኒ ቤቱ ልማት ሁኔታ እንዳስረዱት በ፲ ወሮች ውስጥ ከቡና ተክልና ከልዩ ልዩ የእጅ ሥራዎች ሽያጭ ፲፬ ሺህ ፭፻፶፮ ብር ገቢ ሲገኝ ፹፫ ሺህ የቡና ችግኞች ጸድቀዋል። በትምህርት በኩልም በወህኒ ቤቱ የሚገኙት እሥረኞች እስከ ፮ኛ ክፍል ደርሰዋል።
ከዚህም በቀር ልዩ ልዩ የእጅ ሥራዎች በእሥረኞቹ እየተሠሩ በገበያ ላይ ውለዋል። የእሥረኞቹ ጉልበት ዛሬ በሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት እየተወደደ በመሄዱ ከዚህ በፊት አንድ እሥረኛ በቀን ዜሮ ፴ ሳንቲም ይሠራ የነበረው አሁን ወደ ዜሮ፷ ሳንቲም ከፍ ብሎ በመታየቱ እራሳቸውን ለማስተዳደር ይረዳቸዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን በማለት ሌተናል ኰሎኔል ተስፋዬ ያላቸውን ተስፋ ገለጡ።
(ግንቦት 29 ቀን 1960 አዲስ ዘመን)
62 ኪሎ የሚመዝን ዓሣ
አቶ ወርቁ ካሣ የተባሉ የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኛ እሁድ የካቲት ፲፫ቀን ፲፱፻፶፰ ዓ.ም ከመንጠቆአቸው ሲታገሉ ከዋሉ በኋላ ክብደቱ ፷፪ ኪሎ ግራም የሚመዝን ርዝመቱ ፪ ሜትር ተኩል የሆነ ዓሣ ለመያዝ ችለዋል።
አቶ ወርቁ ከዓሣው ጋር ሲጓተቱ ከቆዩ በኋላ ሰዎች ደርሰው አግዘዋቸው ከውሃው ውስጥ ሊያወጡት ቻሉ። መንጠቆአቸውን ቢመለከቱት ግን ቀንቶ አገኙት። አቶ ወርቁ ‹‹ትልቅ ዓሣ መያዝ ዱሮም ልምድ አለኝ። ነገር ግን የዛሬን ያህል ግዙፍ ዓሣ ጥምጄ አላውቅም። ሰው ባይደርስልኝ ኖሮ ዓሣው ጎትቶ ከሐይቁ ውስጥ ሳይጨምረኝ ባልቀረም ነበረ። የረዱኝን የማሣ ክፍል ሠራተኞች ሳላመሰግናቸው አላልፍም ።››አሉ
ዓሣው ታርዶ ሆዱ ቢከፈት ሌላ ፶ ሣንቲ ሜትር ርዝመት ያለው ትንሽ ዓሣ ተገኘ። ይህ ሁሉ የሆነው በሸዋና በስድስተኛ ሠፈር መካከል ከሚገኘው ሐይቅ ነው፤ ሲል የወንጂና የሸዋ ዜና ማሠራጫ ገለጠ።
(ግንቦት 25 ቀን 1958 ከታተመው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2014