ሸማ በየፈርጁ . . . እንዲሉ ባለ ውለታነትም እንደዛው ነው፤ በየዘርፉ፣ በየፈርጁ … ውለታ አለ። በመሆኑም ይህ ዓምድ በእስከ ዛሬ ጉዞው ባለውለታዎችን ከየፈርጁ ሲያመጣ ሲዘክራቸው፤ ለትውልድም ሲያስተላልፋቸው የቆየው። ከጦር ሜዳ እስከ ሕክምናው፤ ከሳይንቲስቱ እስከ ነጋዴው፤ ከሠዓሊው እስከ ሥነጽሑፍ ባለሙያው ወዘተርፈ ድረስ ዘልቆ ባለውለታዎቹን ወደ አሁኑ ዘመን ብቅ አድርጓል። ይህ ደግሞ፣ ጀግናን ማወደስ፣ ባለውለታን ማስታወስ ግድና ኃላፊነትም ስለሆነ፣ ወደ ፊትም የሚቀጥል ይሆናል።
የዛሬውም ልክ እንደ እስከ ዛሬዎቹ ሁሉ ተመሳሳይ ሲሆን፤ ተመሳሳይነቱም ባለውለታን ማስታወስና ሕይወትና ሥራዎቹን መቃኘት ነው።
በዚሁ መሠረትም ወደ ሥነጽሑፉ ዓለም ጎራ በማለት በዚሁ ዘርፍ ለአገር፤ በተለይም ለዘርፉ ያበረከቱትን አስተዋፅዖ፤ በገደምዳሜውም ቢሆን ”ሕይወታቸውን”ና ተሞክሯቸውን እንቃኛለን።
ዛሬ በእዚህ ዓምዳችን የምንዘክራቸው ባለውለታ የመጀመሪያው የፎክሎር ተመራቂና መምህር፣ ተመራማሪ፣ ሃያሲና ባለቅኔ፣ ሰባት ቋንቋዎችን ይናገሩ የነበሩ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው ናቸው። ባለ ውለታነታቸው ድንበር የለውም፤ በተለይ በሙያ ዘርፋቸው፤ በጥናትና ምርምር መስካቸው ያለ ምንም ወደ ኋላ ማፈግፈግ ያላቸውን ሲቸሩ የኖሩ ስለመሆናቸው የሚያውቋቸው ሁሉ ይናገራሉ። ይህ ጸሐፊም በተወሰነ መልኩ፣ በሚያውቃቸው ልክ ይህንን አስተያየት ይጋራል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህርነት ለረጅም ዓመታት ያገለገሉት ገጣሚ፤ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው፤ ተወዳጅ መምህር፤ በሥነ- ግጥም አጻጻፋቸው ለየት ያሉ መሆናቸው የተመሰከረላቸው ናቸው።
ይህንን የሰይፉን ልዩ ችሎታና ለየት ያለ የአገጣጠም ብልሀት (ብርሀኑ ”አፈንጋጭነት” ይለዋል) በተግባር ለማረጋገጥ ከተፈለገ ብርሃኑ ገበየሁ በአዘጋጀውና በአገራችን በአይነትና አቀራረቡ ”አዲስ” መሆኑ በተነገረለት ”የአማርኛ ሥነ ግጥም” መጽሐፍ (በተለይም ከገፅ 41 እስከ 48 ድረስ ባለው) ውስጥ አጥኝው የተነተነውን የገጣሚውን ሥራ፤ እንዲሁም፣ በድሉ ዋቅጅራ ”በሥነ-ጽሑፍ ቋንቋን ማስተማር” (1996 ዓ.ም) ገጽ 72 ላይ ከሰይፉ ሥራዎች አንዱና ምናልባትም ከአሁኑ ዘመን ሞጋች ሥራዎች መካከል አንዱ የሆነውን ”የተጓጎጠ ልብ”ን የፊት ሽፋን በመውሰድ እንዴት በመጽሐፉ ይዞት ለተነሳው ዓላማና ይዘት ማጎልበቻነት እንዴት እንደ ተጠቀመበት መመልከት ይቻላል።
የሰይፉ መታፈሪያ ፍሬውን በ 88 ዓመታቸው፣ ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ተከትሎ በጀርመን ሃንቡርግ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ እና የኢትዮጵያ ጥናቶች የትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጌቲ ገላዬ እና ሌሎች የቀድሞ ተማሪዎቻቸው በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እንደተናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬውን ”መምህር” ወይም ”ሰር” ወይም ”ጋሼ” አልነበረም የሚሏቸው። የሚሏቸው ”አብዬ ሰይፉ” ነበር።
በ1983 ዓ.ም ስልጣን ላይ የወጣው ኢሕአዴግ ካባረራቸው 42 አንጋፋ ምሑራን መካከል አንዱ በነበሩትና ለስደትም ከተዳረጉት ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው ከተማሩት አንዱ የዶቼ ቬለው ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድም በዶቼ ቬሌ ጣቢያ እንደተናገሩት የሰይፉ መታፈሪያን የአስተማሪነት ለዛና ብቃት አውርቶ መጨረስ አይቻልም፤ የሚጠገብም አይደለም። ነጋሽ “ሰይፉ” ይላል በፈገግታ፤ “አብዬ ሰይፉ ነበር የምንላቸው። ብቻ ‘አብዬ’ ያልዋቸው ከኛ ቀደም ብሎ የነበሩ ተማሪዎች ናቸው።” ይላል። ሲቀጥልም “ሰይፉ መታፈሪያ እንደ አስተማሪ፣ እንደ ጓደኛ፣ እንደ አባት ነበሩ” ሲልም ነው የሚያስታውሳቸው።
በሐረር ልዑል ራስ መኮንን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአዲስ አበባ ተፈሪ መኮንን ከዚያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው፤ በአቴና ዩኒቨርሲቲ (ነገረ መለኮት)፣ በፓሪስ – ሶርቦን (እስልምና-ነክ) ትምህርት መከታተላቸው ለሥራዎቻቸው ስኬታማነት እጅጉን እንደጠቀማቸው ይነገርላቸዋል።
በዘርፉ ”ቁንጮ” ሊባሉ የሚገባቸው፣ ስድስት የታተሙ፤ እና ሦስት ያልታተሙ የግጥም መድበሎች አሏቸው፤ ረጃጅም መጣጥፎችንና በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን ያበረከቱት ሰይፉ የተዋጣላቸው ሃያሲም ናቸው። ይህንን የሃያሲነት ሙያቸውን በአንድ ወቅት ስለ ገብረክርስቶስ “ገብረክርስቶስ ገጣሚው” በሚል ርዕስ ባስነበቡት ጽሑፍ መመልከት የሚቻል ሲሆን፤ እንዲህ ብለውለት ነበር፤
“ገብረክርስቶስን የማውቀው ከሐረር ትምህርት ቤቱ ጀምሬ ነው”። እዚያ ባዶ እግራችንን፣ በቴኒስ ኩዋስ ተጫውተናል። ገብረክርስቶስ፣ የእግር ጣቶቹ እኩል ስለሆኑ፣ ኳሱን የሚመታው በእግር ኩርኩም ነበር – ኹሌ የከረረች ምት።
ከእለታት ባንዱ ቀን ግን፣ ዕረፍት ወጥተን፣ ግማሹ በሚሯሯጥበት፣ ግማሹም ኳስ በሚጫወትበት ሁኔታ ውስጥ፣ ገብረክርስቶስ ጥጋት ተቀምጦ፣ ቁም”ጣ ሱሪውን አጋልጦ ባዶ ጭኑ ላይ ሥዕል ሲሠራ እንዳየሁት አስታውሳለሁ። እና አሁን መለስ ብዬ ሳስብ ሥዕል ምንኛ ከልጅነቱ ከጭንቅላቱ ገብቶ ኖሯል እላለሁ። ለዚህም የአባቱ የአለቃ ደስታ ነገዎ የድጉሥ፣ የቁም ጽሕፈትና የብራና መጻሕፍት ላይ ሥዕል ምን ያኽል ተፅዕኖ አድርጎበት ነበር ይሆን? በምንስ መንገድ? እላለሁ።
ያ እንዳለ ሆኖ ግን፣ ገብረክርስቶስን እዚህ እማንቀራብጥ በሠዓሊነቱ ሳይሆን በገጣሚነቱ ነው።
የገብረ ክርስቶስን ግጥሞች አንዴ ወጥቻቸው የግጥም መድበል መጽሐፉን (“መንገድ ስጡኝ ሰፊ” 1998 ዓ.ም) እንዳጠፍኩ፣ ገብረክርስቶስ ባሳብ አካቶው ምንኛ አይጠገቤ ነው። በእይታ ስንዘራውም ምንኛ አራዝሜ ነው፤ በሌላ ምንኛ … ምንኛ … ምንኛ አልኩ።” በ”አሰነኛኘት” ንዑስ ርዕስ ስርም ”ገብረክርስቶስ ደስታ፣ ዘጠና በመቶውን ወል ግጥም ገጣሚ ነው።” በማለት የገብሬን ሥራዎች በይነዋል። (የአብዬ ሰይፉን የሂስ አቅምና የሃያሲነት ብቃት በሚገባ ለመገንዘብ ሙሉ ጽሑፉን (ድረ-ገፅ ላይ አለ) ማንበቡ ጠቃሚ ነው።
ስለ ከበደ ሚካኤልም ”በስንኝ-አጠፍ ስንኝ” ንዑስ ርዕስ ስር ”ስንኝ – አጠፍ፣ አንዱን ሙሉ ውል ስንኝ ከሁለት ግጥማዊ ወይም ስንኛዊ እኩሌታ፣ ወይም ወል ገጽታውን ከማያሳጣ ቦታ ማጠፍ ነው። የስንኝ-አጠፍ ስንኝ – ምናልባት – የመጀመሪያው ተጠቃሚ ከበደ ሚካኤል ናቸው።”
ሰይፉና ኢትዮጵያ ምን እና ምን ናቸው?
ሁለቱ የሚለያዩ አይደሉም። አንድ ናቸው ማለት ይቻላል። ለዚህ አስተያየታችን መነሻችን ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈራረቀ ሕዝብና አገር የሚያተራምሰውን፣ በቆሸሸ አስተዳደር የተሞላውን፣ በፀረ-ዲሞክራሲነት የታበየውን … የኢትዮጵያ ሥርዓትና መንግሥታቱን በሚሸነቁጡበት ”የተጓጎጠ ልብ” መድበል ከ”ብእሮጋዊ መግቢያ” ባለው ገጽ በ”አበርክቶት” ርዕስ ያሰፈሩት ግጥም ሲሆን፤ እሱም᎓-
ለናት ኢትዮጵያ
ላገሬ
ሕዝባዊት ማኅደሬ
. .
ለሱዋ አንድነት
ነፃነት
የዘራይነቱዋ ኩራት።
. .
ለዘላለም ተገኝቶቱዋ
ብሔር ጥናቱዋ
እናት ጥራቱዋ።
. .
ለድል ብርታቱዋ
በየተሰለፈችበት
ያፍሪካ ጌጥ ነቱዋ።
. .
ለሱዋ ይሁን
ይሄ አበርክቶ
ከኔ
ለኔ – ’ናት
ለኔ – ’መቤት
በርከክ ብዬ እነሆሽ እምላት።
ሰይፉ መታፈሪያ በጠንካራ ሠራተኛነቱና ባበረከታቸው ሥራዎቹ ብቻ የሚለካ ምሑር ሳይሆን ለተለያዩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች፣ ማስተማሪያ ቴክስቶች ወዘተ በግብዓትነት ማገልገሉ በራሱ አንድ ትልቅ ውለታ ነውና በዚህም ሊነሳ፣ ሊታወስና በባለውለተኛነት ሊወደስ ይገባዋል። በተለይ ለሙያ ዘርፉ ካበረከተው አስተዋፅኦ አኳያ ከላይ የጠቀስነውን የብርሃኑን መጽሐፍ ወስዶ በምሳሌነት መመልከት ይቻላል።
ብርሀኑ ገበየሁ ከአስር ዓመት በላይ በፈጀ መጽሐፉ ዝግጅት ወቅት ይሁነኝ ብሎ ከወሰዳቸው፤ ለጥናትና ምርምር ሥራው ማሳያ ይሆኑት ዘንድ አብዝቶ ከጠቀሳቸው፤ ለትንታኔው ይበጁት ዘንድም በስፋት ካብራራቸው ሥነጽሑፋዊ ሥራዎች መካከል የሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው ሥራዎች በርካቶች ናቸው። በተለይ ከሰይፉ ሥራዎች ጎልቶ ከሚታወቅለት ”ውስጠት” መድበሉ ውስጥ ”ልዩ-’ቃ”ን ወስዶ በምንና በእንዴት አይነት ሁኔታ ለንባብ እንዳበቃው፤ ከቅርፃዊ መዋቅር አኳያ ሰይፉ ምን ያህል ከሌሎች የተለየ ገጣሚ እንደሆነ ለተመለከተ እውነትም ሰይፉ ለዘርፉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገ፤ በዘርፉም ልዩ የሆነ ሥነጽሑፋዊ ማንነት (በተለይም ከወጥነት (ኦሪጂናሊቲ) አኳያ) እንዳለው ወዘተ አፍታም ሳይቆይ ይገነዘባል።
በክፍል 2 ”ሥነግጥምን ማንበብና ማድነቅን መማር” ከሚለው የምዕራፉ ዐቢይ ርዕስ ስር በማጠናከሪያነት የሰይፉን ”በማንኛውም ባህል ማለት ይቻላል–የደህና ግጥም ንባብ፣ ሙዝ ላጥ-ዋጥ ሊሆን አይችልም-የሆነ ፅነት ወይም አስቸጋሪነት ይኖረዋል።” የሚለውን ለሚጠቅሰው ለብርሃኑ ገበየሁ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው ለብዙዎቻችን ያልተለመደና እንግዳ የሆነ የአገጣጠምና የቋንቋ አጠቃቀም ብልሀትን ይዞ የመጣ፣ አፈንጋጭ … (ገፅ 44 እና ሌሎችም)፣ ”ብርቱ ገጣሚ” (ገፅ 130) ሲሆን፤ በአማርኛ ሥርዓተ ጽሑፍ ውስጥ ያልተለመደ ደማቅ ነጥብ (ስንኞች በ’..’ መታጠራቸውን) ይዞ የመጣ (ከላይ የጠቀስንለትን የገጣሚውን ”አበርክቶት” ያስታውሷል)፤ ይህም በእስከ ዛሬው የአማርኛ ሥነግጥም ጉዞ በራሱ ያልተለመደና አስገራሚ ነገር (ገፅ 42) የሆነ ሲሆን ይህንን ያስተዋወቀው ደግሞ ሰይፉ እንጂ ሌላ አይደለምና ለዘርፉ ባለ ትልቅ ውለታ ነው።
የሰይፉን ሥራዎች ስንመለከት የየራሳቸው ቀለምና አሻራ ያላቸው ሆነው የምናገኛቸው ሲሆን ከእነዚህም መካከል የቃላት ስደራው፣ ፈጠራውና አጠቃቀሙ ይገኙበታል።
ሰይፉ ቃልን ከቃል በማገናኘት አንድ እራሱን የቻለ ጽንሰ ሀሳብ መፍጠር የተካነበት ሲሆን፤ ይህም ከ”አፈር ያነሳ ሥጋ” እና ከ”ውስጠት” በተለየ መልኩ በ”የተጓጎጠ ልብ” ውስጥ ጎልቶ ይታያል። ”ስንክን” (art) አንዱ ሲሆን ”ሰንካኞች” (artists) ለሚለው ይውል ዘንድ አስቦበት ተግባራዊ ያደረገ ገጣሚ ነው። (”ሥንኪን” ከ”ሥን” እና ”ኪን” ውህደት የመጣ ወይም የተፈጠረ ጽንሰ ሀሳብ ነው። ”ሥነጥበብ” እና ”ኪነጥበብ”ን ያስቧል፤ ከሁለቱም የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ እንደተወሰዱና ውህደት እንደፈጠሩም ልብ ይሏል።) ይህንን ከራሱ፣ ከሥነግጥም መድበልነቱ ባለፈ በሁሉን አቀፍነቱ (ፍልስፍና፣ ታሪክ፣ ፖለቲካ፣ ባህል …) ከሚታወቀው፣ ከ”የተጓጎጠ ልብ” አንድ አንቀፅ ወስደን እንመልከተው፤
ዛሬ ለኢትዮጵያዊነት የቆመ ሁሉ፣ ብሔራዊ እርስበቱ (ideal) ”አፈር ያነሳ ሥጋ” ሆኖበት እሚያደርገውን ያጣ ይመስላል። እንግዲህ፣ ይህ ሁኔታ ባስከተለባቸው ተጓጉጦት ነው ኃይሌና ዮፍታሔ እና እነሱን የመሰሉ ሰንካኞች (artists) ያኔ በኢጣሊያን ወረራ፣ ታዬና ሰይፉ እና እነሱን የመሰሉ ደሞ፣ ዛሬ በወያኔ/ኢሕአዴግ ተመሳሳይ ሥንክን-ዕዝል ስሜት ገልጸው የነበሩና የሚገልጹ። ይህም፣ የሁለቱ ዘመናት በሃገር መፍረስ መመሳሰል የቀሰቀሰው የሠንካኞች የሥዕል ቡርሽና የቅኔ ብዕር መሆኑ ነው። ቅብብሎሹ አምሮ ዳብሮ መቀጠል አለበት። (ገፅ 26 – የጀርባ ሽፋኑ ላይም ወጥቷል።)
ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው ይታወቃል ከተባለ እንኳን የሚታወቀው በገጣሚነቱ እንጂ በፎክሎር ምሑርነቱና ተመራማሪነቱ አይደለም። ይህን ስንል ሰይፉ በዚህ ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን የሠራና ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገ በመሆኑ ሲሆን፤ ለዚህም ለዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀው (እኔ ያገኘሁት ”የፎክሎር (1) መዝገበ – ቃላት ጥንቀራ ቅድመ ዝግጅት” በሚል ርዕስ የቀረበውንና በ”የፎክሎር ሙያነክ ቃላት” ላይ የሚያተኩረውን ሰፊና ጥልቅ ጥናት ነው።)
ሰይፉ በሃያሲነቱም በራሱ መንገድ እንጂ በተቀደደለት የመሄድ ፍላጎት እንደሌለው በበርካታ ሥራዎቹ ውስጥ ይታያል። ለምሳሌ ቀደም ሲል የእነ ገብረክርስቶስን ሥራዎች ባሄሰበት ጽሑፉ (አንድምታ ልሳን፣ ቁጥር 7) ውስጥ እንደምንመለከተው የሰነዘረው ሂስ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ሲሆን አንዱም አሰነኛኘትን የተመለከተው ነው። ሰይፉ ይህንን ክፍል በተለያዩ ንዑሳን ክፍሎች ከፋፍሎ ሥራዎቹን የመረመረ ሲሆን፤ ከእነሱም ”ሰያፍ ስንኝ”፣ ”ስንኝ-አጠፍ ስንኝ”፣ ”ቁልቁሎሽ ስንኝ” እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።
ነገሩ፣ ዶክተር ዮናስ አድማሱ ”ከሚቀር ይጥቆር” እንደሚለው ነው። ይህች ሚጢጢዬ የጋዜጣ ገጽ ላይ ጽሑፍ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬውን ትገልፃለች ብሎ ማንም ለክርክር አደባባይ አይወጣም። የዚህ ጽሑፍ ዐቢይ አላማ ባለውለታዎቻችንን ማስታወስና ለአዲሱ ትውልድ ማቀበል፤ ከተሳካልንም የጥናትና ምርምር ሰዎች፣ ደራሲያን … ገፋ አድርገው እንዲሄዱበት ማድረግ … እንጂ የባለ ውለታዎቻችንን ሙሉ በኩለሄ እንሸፍናለን ማለት አይደለም። የዛሬው ባለውለታችንም ጉዳይ እንደዛው ነው። ወደ ”አንቱ”ታችን በመመለስ እናጠቃለው።
እጅግ የረቀቁ፣ ውለታቸው ከፍ ያለ፣ በዘርፉ ሁሉን አወቅ፤ ነገር ግን የሥራቸውን ያህል ምንም ያልተነገረላቸው፤ በአካባቢውና በጥናት መስኩ አካባቢ ባሉ ሰዎች ካልሆነ በስተቀር ብዙም ያልተወሳላቸው፤ በዚህ የሰው ዘፈን ወስዶ አደባባይ በሚወጣበት ዘመን ስለ እሳቸው ምንም ያልተፃፈላቸው ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው ባለትዳር እና የአራት ልጆች አባት እንዲሁም የአራት ልጆች አያት የነበሩ ሲሆን፤ የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸው በስደት በኖሩበት በዩናይትድ ስቴትስ አትላንታ ጆርጅያ ተፈፅሟል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2014