የጥፍር ፋሽን በዓለም አቀፍ ደረጃ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት ገበያ ሆኗል። የተለያዩ ጥናቶች እንደሚጠቁሙትም የጥፍር ውበት አጠባበቅ እድገቱ ፈጣን መሆኑን ማስተዋል ይቻላል። በኢትዮጵያም የጥፍር ውበት አጠባበቅ በሴቶች ዘንድ በተለይም በከተሞች አካባቢ እጅግ እየተስፋፋ ስለመምጣቱ ብዙ ማሳያዎች አሉ።
የውበት እና የፋሽን ኢንዱስትሪው የተለያዩ አማራጮችን በማቅረብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዘመነ እና እያደገ መጥቷል። የእጅ ውበት አጠባበቅን በተመለከተ ሰው ሰራሽ ጥፍሮችን ማስተከል በምዕራቡ ዓለም የሚዘወተር አንድ የመዋቢያ መንገድ ነው። ይህም የውበት ኢንዱስትሪውን መቆጣጠር ከቻሉ ተዘውታሪ የፋሽን ዘይቤዎች አንዱ እንዲሆን አድርጎታል።
ሰው ሰራሽ ጥፍሮች በተለያዩ ቀለሞች እና ዲዛይን የተሰሩ ሲሆኑ ከዚህ ቀደም ለየት ላሉ ዝግጅቶች በስተቀር በኢትዮጵያ ሴቶች ዘንድ እምብዛም ያልተለመደና ያልነበረ ቢሆንም አሁን አሁን ግን ብዙ ሴቶች የዕለት ተዕለት የመዋቢያ ምርጫ ነው።
በመላው ዓለም የሰው ሰራሽ ጥፍሮች የመጠቀም ፍላጎት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መጥቷል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት የፋሽን እና የውበት ዘርፍ ከጊዜ ወደጊዜ እየዘመነና እያደገ ከመሄዱ በተጨማሪ የተፈላጊነት መጠኑም እየጨመረ ይሄዳል። ለዚህም ይህ ነው የሚባል ምክንያት ማስቀመጥ ከባድ ቢሆንም የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች መስፋፋት ሴቶች ስለመልካቸው፣ ስለአለባበሳቸው እና ስለአቀራረባቸው ልዩ ትኩረት እየሰጡ እንዲሄዱ ማድረጉ በሰው ሰራሽ ጥፍር ላይ ፍላጎት እንዲጨምር በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይታመናል።
በዋነኝነት ሁለት ዓይነት ሰው ሰራሽ የጥፍር አሰራሮች እንዳሉ በዘርፉ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። አክሪሊክክ እና ጄል ይባላሉ። የጄል ሙሌት በመባል የሚታወቀው የጥፍር ውበት ሙሌት የሚከናወነው በሶስት የሂደት ደረጃ ሲሆን ይህም በመጀመሪያ የሚተከለውን ሰው ሰራሽ ጥፍር ለመያዝ እንዲያመቸው ተፈጥሯዊውን የሴቷን ጥፍር ሙሉ ለሙሉ የመሞረድ፣ የመቦረሽ፣ እና በጥቂቱ ቆዳዋን የማንሳት ስራ ይሰራል። በመቀጠል ሰው ሰራሽ ጥፍሩን በተፈጥሯዊ ጥፍሯ ላይ ለማጣበቅ የሚያስችለውን ጄል በመጠቀም ሙሌቱ ይከናወናል፣ የተለጠፈው ጥፍር UV በሚባል መብራት ውስጥ ከ30 ሰከንድ እስከ ሁለት ደቂቃዎች እንዲደርቅ ይደረጋል። በመጨረሻም እንደተጠቃሚዋ ፍላጎት ጥፍር ቀለም በመቀባት ስራው ይጠናቀቃል።
አክሪሊክ የጥፍር አይነት ደግሞ ሰው ሰራሽ ጥፍሩን ለመለጠፍ በተዘጋጁ ፈሳሽ እና ዱቄት ኬሚካሎች በመታገዝ በጥፍር ላይ የሚለጠፍ ሲሆን የአሰራር ሁኔታው ጥንቃቄ የተሞላበት፣ ረዘም ያለ ደቂቃዎችን የሚወስድ እና ከጄል አንጻር ከሰው ጥፍር ጋር ተመሳሳይነቱ የጎላ ነው።
እነዚህን አገልግሎቶች ለመጠቀም የሚጠየቀው ዋጋ ተጠቃሚዋ እንደምትመርጠው ቦታ የሚለያይ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በአብዛኛው ከሁለት መቶ ብር እስከ አንድ ሺ ብር በላይ ክፍያ ሊጠየቅበት ይቻላል።
ሰው ሰራሽ የጥፍር ማስዋብ ስራ በወጣት የፋሽን ተከታዮች ዘንድ ተወዳጅ እየሆነ መምጣቱ ለብዙ የውበት ባለሙያዎች ራሱን የቻለ የስራ እድል ለመፍጠር ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም። ለዚህም ማሳያ የሚሆኑት አሁን አሁን በከተሞች ላይ በብዛት የሚስተዋሉት የጥፍር ውበት ሳሎኖች ናቸው።
የጥፍር ውበትን ለመጠበቅ ሰው ሰራሽ ጥፍሮችን ማስተከል አዲስ ነገር ባይሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለይ ወጣት ሴቶች ተጠቃሚነታቸው ከፍተኛ ሆኗል።
ከውበት አኳያም ከተፈጥሮው ጥፍር ይልቅ ቀለማቸውን ሳይለቁ በመቆየት እና ከጥንካሬ አኳያ ተመራጭ መሆናቸውን ባለሙያዎች ይናገራሉ። የሰው ሰራሽ ጥፍር ለሴቶች ተጨማሪ በራስ የመተማመን እንደሚጨምርም ይነገራል።
የሰው ሰራሽ ጥፍር ከውበት አኳያ ብዙ ጥቅም እንዳለው በርካቶች የሚስማሙ ቢሆንም ከጤና አኳያ “ሲያጌጡ ይመላለጡ” እንዳይሆን ነገሩ የጎንዮሽ ጉዳት ይኖረው እንደሆን ጥያቄ የሚያነሱ አይጠፉም። ብዙ የሕክምና ባለሙያዎችም የሰው ሰራሽ ጥፍር አለመጠቀምን ይመክራሉ። በአብዛኛው ጥፍር ማሳደግ የሚያስቸግራቸው ሴቶች አርቴፊሻል ጥፍርን መጠቀማቸው ወይም ጥፍራቸው ጥሩ የሆኑ ሴቶችም ለውበት ሲሉ መጠቀማቸው እንደማይመከር እና ጥፍርን ለመለጠፍ የሚጠቀሙት ኬሚካል እንዲሁም የማድረቂያው ጨረር በተደጋገመ ቁጥር ከጥፍርም በተጨማሪ ጥፍርን የሚደግፈውን ቆዳም የማስረጀት ባህሪ እንዳለው የሕክምና ባለሙያዎችና ጥናቶች ያስቀምጣሉ። ከዚህ በተጨማሪ ለተለያዩ የፈንገስና የባክቴሪያ በሽታዎች ሊዳርግ እንደሚችልም መረጃዎች ይጠቁማሉ። ተፈጥሯዊ ጥፍር ጤናው የሚረጋገጠው በየጊዜው በሚያሳየው እድገት እና መተካካት ነው፣ ነገር ግን የሰው ሰራሽ ጥፍር ይሄን እድገት በመጫን ተፅዕኖ ያሳድራል ተብሎ ይታመናል።
የጥፍር ውበት እና ፋሽን አመጣጥን ከአንድ ባህል እና አገር ጋር ብቻ ማዛመድ አይቻልም። ከዚህ ጋር በተያያዘ ጥናት ያካሄዱ ተመራማሪዎች በ5000 ዓ.ዓ ገደማ ግብፃውያን የሞቱ ከብቶችን ግብዓት በመጠቀም ሰው ሰራሽ ጥፍር በመስራት እና ሂና በመቀባት ለመዋቢያነት ይጠቀሙት እንደነበር ያስቀምጣሉ። ጊዜው በውል ባይታወቅም የመጀመሪያውን ዘመናዊ የሰው ሰራሽ ጥፍር ሰርታ ያቀረበችው አገር ቻይና እንደሆነች የሚነገር ሲሆን ይህም የእንቁላል አስኳል፣ ሰም፣ አበባ፣ ቀለማማ ድንጋዮችን እና ዝልግልግ ቅባቶችን በመጠቀም ይሰሩት እንደነበር ተፅፏል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2014