ሌላኛው የዚህ ሳምንት ክስተት ደግሞ ከዚሁ ከግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም ክስተት የቀጠለው የደርግ ጣጣ ነው። ኮሎኔል መንግሥቱ ከግንቦት ስምንቱ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ቢያመልጡም፤ ከሁለት ዓመታት በኋላ ከመጣባቸው አውሎ ነፋስ ግን ማምለጥ አልቻሉም። ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ወጡ።
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) ፕሬዚደንትና የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ (ኢሰፓ) ሊቀመንበር የነበሩት ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም አገር ጥለው የሸሹት ከ31 ዓመታት በፊት ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም ነበር።
የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎችና የፖሊስ ሰራዊት አባላትን ይወክላሉ የተባሉና ከተራ ወታደር እስከ ሻለቃ ድረስ ማዕረግ ያላቸው 120 የጦሩ አባላት ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም በአራተኛ ክፍለ ጦር ግቢ ውስጥ ተሰብስበው ያቋቋሙት ‹‹የጦር ኃይሎች፣ የክብር ዘበኛ፣ የፖሊስ ሰራዊትና የብሔራዊ ጦር አስተባባሪ ኮሚቴ›› መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ከዙፋናቸው አውረደው። ስያሜውንም ‹‹ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ›› ብሎ በመለወጥ ስልጣን ይዞ ኅብረተሰባዊነት (Socialism)ን የፖለቲካ-ኢኮኖሚ መርሁ አድርጎ አገር መግዛት ጀመረ።
የመሰረተ ልማት አውታሮችን በተለይ ደግሞ ትምህርትን ለማስፋፋት ከተደረገው ጥረት ባሻገር የእርስ በእርስ ጦርነት፣ እስራትና ስርዓት አልበኝነት የአገዛዙ መለያዎች ሆኑ። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተለይ ደግሞ ኤርትራ ውስጥ ያለው ጦር ሲሸነፍ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም የሚወስዱት እርምጃ፣ የሊቀመንበሩ የአቋም ግትርነት (ጀግንነት እንጂ ዲፕሎማሲ አይችሉም እየተባሉ ይታማሉ) እንዲሁም ሌሎች ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ተደምረው የጦሩ መሪዎች በሊቀመንበሩ ላይ ጥርሳቸውን ነከሱ።
መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግም ሞክረውም ሳይሳካ ቀረ። የአገሪቱ ችግርም ከድጡ ወደ ማጡ ሆነ።
ከዚህ ሁሉ ችግር ለማምለጥ ከአገር መውጣትን ምርጫቸው ያደረጉት የአገሪቱ ፕሬዚደንት ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በኬንያ በኩል አድርገው አሁንም ድረስ መኖሪያቸው ወደ ሆነችው ዚምባብዌ ገቡ። ኮሎኔል መንግሥቱ ከሚመሩት መንግሥት ጋር ሲዋጉ ከነበሩት አማፂያን መካከል ‹‹ሻዕቢያ›› ኤርትራን ገነጠለ፤ ሕወሓትና አጋሮቹ ደግሞ ግንባር ፈጥረው ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም አዲስ አበባ ገቡ።
ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ከመንግስት ምክር ቤት የሚሰጥ መግለጫ እንዳለ እየደጋገመ ሲገልጽ ከቆየ በኋላ በመጨረሻ «ጦርነቱ ያስከተለው ሁኔታ እንዲለወጥ በልዩ ልዩ ወገኖች በልዩ ልዩ መልክ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ሆኖም ችግሩ አልተቃለለም። ይልቁንም ወደ ባሰ ደረጃ እየተሸጋገረ ይገኛል። ስለዚህ ደም መፋሰስ እንዲቀርና ሰላምም እንዲሰፍን በልዩ ልዩ ወገኖች የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከስልጣን መውረዳቸው እንደሚበጅ የታመነበት ስለሆነ ይህንኑ በማመዛዘን ፕሬዚደንት መንግስቱ ኃይለማርያም በዛሬው ዕለት ከስልጣን ወርደው ከኢትዮጵያ ውጪ ሄደዋል። ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን በመውረድ አገር ለቀው በመሄዳቸው የሪፐብሊኩ ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተናል ጀኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን ተክተው ይሰራሉ» የሚል አጭር መግለጫ ተላለፈ። በዚያው ኢህአዴግ አገሪቱን ተቆጣጠረ። የዚህን ዝርዝር በግንቦት 20 ታሪኮች እናየዋለን።
ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ግንቦት 13 ቀን ከአገር ከመውጣታቸው ቀደም ብሎ ባሉት ቀናት የነበሩትን ሁነቶች ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ ‹‹አብዮቱና ትዝታዬ›› በሚለው መጽሐፋቸው ያስታውሱናል።
ግንቦት 10 ቀን 1983 ዓ.ም ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም በመኖሪያ ቤታቸው ለከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸው የእራት ግብዣ አደረጉ። ግብዣው ሲጠናቀቅ ፕሬዚዳንቱ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ሁሉንም ተጋባዥ እንግዶች እበራፋቸው ላይ በመሆን አንድ በአንድ እየጨበጡ ሸኟቸው።
ግንቦት 12 ቀን 1983 ዓ.ም፤ ፕሬዚዳንት መንግስቱ መሉውን ቀን የተለያዩ ወረቀቶችን ቢሯቸው ውስጥ ሲቀዳድዱ ዋሉ፤ አመሻሽ ላይ ግን ወደ ዘመቻ መምሪያ በማቅናት ለከፍተኛ የጦር አዛዦቻቸው ንግግር አደረጉ።
ማክሰኛ ግንቦት 13 የፕሬዚዳንቱ ልዩ ረዳት ሻምበል መንግስቱ፤ ብላቴ ማሰልጠኛ ጣቢያ ደርሶ ከዚያም ወደ አስመራ ደርሶ መልስ የሚበቃ ነዳጅ የሞላ አንድ ዳሽ 5 አውሮፕላን እንዲዘጋጅ ትእዛዝ አስተላለፈ።
በዚያው ዕለት ከጠዋቱ ወደ 2 ሰዓት ገደማ ፕሬዚዳንቱ ከተመረጡ አጃቢዎቻቸው እንዲሁም ከሶስተኛ ክፍለጦር የመጣና የቅርብ አጃቢያቸው ከነበረው ከሻንበል ደመቀ ባንጃው ጋር በመሆን በኮሎኔል ተስፋዬ መሪነት ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በመድረስ ተዘጋጅታ ትጠብቅ ከነበረችው አውሮፓላን ተሳፈሩ።
ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም ፕሬዚዳንት መንግስቱ የ 17 ዓመት ስልጣናቸውን ለቀው ከኢትዮጵያ ወጡ፤ እነሆ እስከ አሁን ድረስም በዚምባቡዌ ሐረሬ ይኖራሉ።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 15 ቀን 2014 ዓ.ም