ባለፈው ሳምንት ግንቦት ሰባትን አስታውሰናል። የግንቦት ወር የኢህአዴግና የደርግ ታሪክ ነው ማለት ይቻላል። ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም ብዙ ወጣቶች የተጨፈጨፉበት የዘመነ ኢህአዴግ ምርጫ የተደረገበት፣ ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም በደርግ ላይ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተደረገበትና ብዙ የጦር መኮንኖች የተረሸኑበት፣ ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከአገር ለቀው የወጡበት፣ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ኢህአዴግ የአገሪቱን ርዕሰ መዲና አዲስ አበባን የተቆጣጠረበት።
ሌላው የሚያስገርመው ደግሞ የሁለቱም መንግሥት መሪዎች የተወለዱት በግንቦት ወር መሆኑ ነው። ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የተወለዱት ግንቦት 19 ቀን 1933 ዓ.ም ሲሆን አቶ መለስ ዜናዊ ደግሞ የተወለዱት ግንቦት 1 ቀን 1947 ዓ.ም ነው።
ከእነዚህ የግንቦት ወር የደርግና የኢህአዴግ መንግሥታት ክስተቶች ለዛሬው የግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እና የግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምን ከአገር መውጣት እናስታውሳለን። የሻምበል ኢዮብ አባተ ‹‹ጀኔራሎቹ›› መጽሐፍ እና ሌሎች ሰነዶች የመረጃ ምንጮቻችን ናቸው።
ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም ሌተናንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ለጉብኝት ወደ ምስራቅ ጀርመን ሄዱ። በዕለቱም መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ የመጨረሻው የአድማ ስብሳባ ቦታ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ግቢ ነበር።
ሜጀር ጀኔራል መርዕድ ንጉሤ (የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም)፣ ሜጀር ጀኔራል ኃይሉ ገብረሚካኤል (የምድር ጦር ዋና አዛዥ)፣ ሜጀር ጀኔራል አምሃ ደስታ (የአየር ኃይል ዋና አዛዥ)፣ ሪር አድሚራል ተስፋዬ ብርሃኑ (የባሕር ኃይል ዋና አዛዥ)፣ ሜጀር ጀኔራል ወርቁ ዘውዴ (የፖሊስ ሰራዊት ጠቅላይ አዛዥ)፣ ሜጀር ጀኔራል አብዱላሂ ዑመር (የአገር መከላከያ ሚኒስቴር አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ)፣ ሜጀር ጀኔራል ፋንታ በላይ (የኢንዱስትሪ ሚኒስትር)፣ ሜጀር ጀኔራል አበራ አበበ (የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ዘመቻ መምሪያ ኃላፊ)፣ ብርጋዴር ጀኔራል ተስፋዬ ትርፌ (በአገር መከላከያ ሚኒስቴር ዘመቻ መኮንን)፣ ብርጋዴር ጀኔራል ደሳለኝ አበበ (የጦር ኃይሎች አካዳሚ ዋና አዛዥ)፣ ኮሞዶር ኃይሌ ወልደማርያም (በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የእቅድና ፕሮግራም መምሪያ ኃላፊ) እና ሌሎች የጦሩ አባላት ከመከላከያ ሚኒስትሩ ቢሮ አጠገብ ባለው አነስተኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ተሰበሰቡ።
በስብሰባው ላይ የተገኙት ከላይ ስማቸው የተጠቀሱት የጦሩ ባለስልጣናት ይሁኑ እንጂ ከየጦር ክፍሎቹ የተመለመሉት አዛዦችም የሚሰጣቸውን ጥዕዛዝ ለመፈፀም በተለያዩ አካባቢዎች ተዘጋጅተው ነበር። ለአብነት ያህልም፤ የ603ኛ ኮር መምሪያ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ዘውዴ ገብረየስ (ጎንደር)፣ የአየር ኃይል ምክትል ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ሰለሞን በጋሻው (ደብረ ዘይት)፣ የሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ደምሴ ቡልቶ (አስመራ) እና ሌሎች የጦሩ አባላት ተጠቃሽ ናቸው።
እዚህ ላይ አንድ መታወስ ያለበት አስቂኝ ድርጊት አለ። የመፈንቅለ መንግሥቱ ጠንሳሽና የአድመኞቹ ሰብሳቢ ሜጀር ጀኔራል ፋንታ በላይ ወደስብሰባው የመጡት ዘግይተው ነበር። ወደ አዳራሹ ሲገቡ የሰብሳቢነቱን ቦታ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ሜጀር ጀኔራል መርዕድ ንጉሤ ይዘውታል። ሜጀር ጀኔራል መርዕድ ቦታውን መልቀቅ ሲገባቸው ዝም አሉ። ይባስ ብለውም ሜጀር ጀኔራል መርዕድ ቦታውን የመልቀቅ አዝማሚያ ሳያሳዩ ስብሰባውን መምራት ቀጠሉ። መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ የተሰበሰቡት የጦር አዛዦች እዚያው በዚያው ሌላ መፈንቅለ መንግሥት አደረጉ። ሜጀር ጀኔራል ፋንታ በሁኔታው ተበሳጭተው ስብሰባውን ጥለው ወጥተው እጃቸውን ኪሳቸው ውስጥ አድርገው መንጎራደድ ጀመሩ።
ሌላው ደግሞ በመፈንቅለ መንግሥቱ ሴራ ውስጥ ከተሳተፉ የጦሩ አባላት መካከል አንዳንዶቹ መፈንቅለ መንግሥቱ እንደሚሳካ ቀድመው እርግጠኛ በመሆን ‹‹እዚህ አድማ ውስጥ እኔንም አካፍሉኝ እንጂ ጎበዝ! በ1953ቱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወቅት ሳይነግሩኝ ቀሩ። ዛሬም ልትተውኝ ነው እንዴ? …›› ብለው የተናገሩ የጦር መሪዎች እንዳሉ ስለመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው የተፃፉ ታሪኮች ያሳያሉ።
የመፈንቅለ መንግሥቱ ሴራ ጠንሳሾች ‹‹ታማኝ ናቸው›› ያሏቸውን የጦሩን አባላት ሰብስበው ሲነጋገሩ ንግግራቸው ጭቅጭቅ የበዛበት ነበር። የመንግሥቱ ኃይለማርያም አስተዳደር ተወግዶ በምትኩ በጀኔራል መኮንኖች የሚመራ አዲስ መንግሥት የማቋቋም እቅዳቸውን ተናገሩ። በብዙ ጉዳዮች ላይ መግባባትና መተማመን እያጡ በሄዱ ቁጥር ጊዜ እየመሸባቸው መሆኑን መገንዘብ አቃታቸው።
የደህንነት ሚኒስትሩ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደሥላሴ በሊቀ መንበሩ ሽኝት ላይ ሳይገኙ የቀሩ የጦር አዛዦች ሁኔታ ስላላማራቸው አዛዦቹን የሚከታተል ቡድን አደራጅተው ስለነበር እያንዳንዱን ድርጊት ይከታተሉ ነበር። ጉዳዩ የመፈንቅለ መንግሥት አድማ መሆኑን ሲያረጋግጡም ነገሩን የሊቀ መንበሩ ቀኝ እጅ ለነበሩት ለሻለቃ መንግሥቱ ገመቹና ለሌተናል ጀኔራል ተስፋዬ ገብረ ኪዳን አሳወቋቸው።
ኮሎኔል አዲስ ተድላ እና ኮሎኔል ደበላ ዲንሳ በሽምግልና ወደ መከላከያ ሚኒስቴር ቢላኩም የመፈንቅለ መንግሥቱ ሴራ ጠንሳሾች ግን ‹‹ያለቀለት ነገር ስለሆነ ሽምግልናና ድርድር አያስፈልግም›› ብለው መነታረካቸውን ቀጠሉ። ለመንግሥት ታማኝ በነበረው ጦርም ተከበቡ። በሁኔታው ተስፋ የቆረጡት አንዳንድ የጦር አዛዦችም ራሳቸውን አጠፉ።
የመፈንቅለ መንግሥቱ ጠንሳሾችና መሪዎች በፈፀሙት የእቅድና የአፈፃፀም ስህተት ለአራት ዓመታት ያህል ታቅዶበት ሲውጠነጠን የነበረው መፈንቅለ መንግሥትም ሳይሳካ ቀረ።
ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው በኋላ በተወሰደው እርምጃ ኢትዮጵያም በርካታና ‹‹በአፍሪካ ደረጃ ምርጥ ነበሩ›› የተባሉ የጦር መሪዎቿን አጣች። ደርግም የደመ ነፍስ ጉዞውን ቀጠለ። ሊቀ መንበር ሌተናንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከግንቦት 1981 መፈንቅለ መንግስት ቢተርፉም ከግንቦት 1983ቱ ግን ሳይተርፉ ቀሩ።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 15 ቀን 2014 ዓ.ም