አዲስ አበባ፡- በሕገወጥ መንገድ የተገኙ ዲጂታል መታወቂያዎች በመንግሥት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ስለማያስገኙ መታወቂያ እንሠራላችኋለን ከሚሉ አካላት ሕብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባዋል ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ አሳሰበ።
ከሰሞኑ ዲጂታል መታወቂያዎች በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ አካላት ተመሳስለው እየታተሙና እየተሠራጩ መሆኑ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እየተሠራጨ ይገኛል። መታወቂያዎቹ እስከ 7 ሺህ ብር ድረስ ሲቸበቸቡ እንደነበር ጥናት አደርጌ አገኘሁ የሚሉ መገናኛ ብዙኃን ይፋ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ደውሎ ጉዳዩን ለማጣራት ባደረገው ሙከራ ከኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ምላሽ አግኝቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታከለ ነጫ፤ ዲጂታል መታወቂያዎቹ በሕገ ወጥ መንገድ መታተማቸውን አምነው እንዲያውም ከተጠቀሰው ዋጋ በላይ መሸጣቸው እንደተደረሰበት ገልፀዋል። ሆኖም የሚሸጡት መታወቂያዎች መለያ ኮድ ወደ መንግሥትም ሆነ ወደ ኤጀንሲው ቋት ያልገቡ በመሆናቸው መንግሥታዊ አገልግሎት ለማግኘት የማያስችሉ ተራ ወረቀቶች ናቸው ብለዋል።
ምንም እንኳን በማጭበርበር የተገኙት መታወቂያዎች ከመደበኛው ጋር ቢመሳሰሉም መለያ ቁጥራቸው ወደ ተቋሙ ቋት ስለማይገቡ ከመንግሥት ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችሉ አይደሉም።ኅብረተሰቡ ከዚህን መሰል ድርጊት ራሱን እንዲቆጥብ መክረዋል።
ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው ሁሉ ችግሩን ለመከላከል ከፀጥታ አካላት እና ከሌሎች መዋቅሮች ጋር በትብብር እየሠራ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። በዚህም ዲጂታል መታወቂያ እንሠራላችኋለን በማለት ሲያጭበረብሩ እጅ ከፈንጅ የተያዙ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና አስተዳደር ሠራተኞችን ጨምሮ ሌሎች በጉዳዩ የተሳተፉ አካላት በቁጥጥር ሥር ውለዋል ብለዋል። እስካሁን በተደረጉ ክትትሎች ከ11 በላይ ሰዎች ተይዘዋል።
የተቋሙ ሠራተኞች እንደ ሠሩት ሥራ ክብደትና ቅለት የደመወዝ ቅጣት፣ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያና የመሳሰሉ እርምጃዎች መወሰዳቸውንና ከመሥሪያ ቤቱ ውጪ ይህን ሥራ ሲሠሩ እጅ ከፈንጅ በፖሊስ ተይዘው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታዬ የሚገኙ እንዳሉ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
በተጨማሪም የኤጀንሲው ሠራተኞች ሆነው አስፈላጊውን መረጃ ላላሟሉ አገልግሎት ፈላጊ ዜጎች የልደት እና መሰል ሰርተፍኬት የሚሰጡ ሠራተኞች ከደመወዝ ቅጣት እስከ መጨረሻ ማስጠንቀቂያ በሚደርስ ቅጣት ተቀጥተዋል ተብሏል።
በተጭበረበረ መንገድ መታወቂያ ያወጡ ሰዎች ወደ መንግሥት ተቋማት ሄደው አገልግሎት ለማግኘት በሚሞክሩበት ጊዜ መለያ ቁጥራቸው አይሠራም ያሉት ዶክተር ታከለ፤ ይህን ዓይነት ነገር በሚገጥም ጊዜ ግለሰቦቹ በፖሊስ እንዲያዙ በማድረግ መታወቂያውን ያገኙበት መንገድ እንዲጣራ ተደርጎ ሁለቱም አካላት እንዲቀጡ ይደረጋል ተብሏል።
ማንኛውም አካል በተጭበረበረ በተገኘ መታወቂያ ከመንግሥት ሊያገኝ የሚገባውን አገልግሎት ስለማያገኝ ገንዘቡን አውጥቶ ለአጭበርባሪዎች አይጋለጥ ያሉት ዶክተር ታከለ እንደዚህ መሰል ነገሮች ሲያጋጥሙም 7533 ነፃ የጥቆማ የስልክ መሥመር ላይ ጥቆማ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
ውብሸት ሰንደቁ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2014