ሌላኛው የዚህ ሳምንት ክስተት የፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ሕልፈተ ሕይወት ነው። የእርሳቸው ታሪክም ከኢሕአዴግ ጋር ይገናኛል። በነገራችን ላይ የግንቦት ወር የኢሕአዴግ ታሪክ ነው ማለት ይቻላል። ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም አዲስ አበባን የተቆጣጠረበት፣ ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም በታሪክ የተወቀሰበት ምርጫ የተካሄደበት እና ግንቦት 6 ቀን በግፍ ሲያሰቃያቸው ከነበሩ ሰዎች አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ያረፉበት ነው።
ፕሬፌሰር አሥራት ወልደየስ የሕክምና ባለሙያ ሲሆኑ በሕወሓት/ኢሕአዴግ በሕዝብ ላይ ይደርስ የነበረውን ግፍ ለመታገል የፖለቲካ ፓርቲ በማቋቋም መስዋዕት የከፈሉ ናቸው። የእኝህን ሰው ሕይወት እና የፖለቲካ ውጣ ውረድ እናስታውሳለን።
አሥራት ወልደየስ ከአባታቸው ከአቶ ወልደየስ አልታዬና ከእናታቸው ከወይዘሮ በሰልፍይዋሉ ጽጌ ሰኔ 12 ቀን 1920 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ። የአሥራት አባት አቶ ወልደየስ አልታዬ በጸሐፊ ትዕዛዝ ኃይሌ ወልደሥላሴ አስተዳደር ውስጥ በጸሐፊነትና በአስተዳደር ተግባር የተሠማሩ ነበሩ። እናታቸውም በአነስተኛ ንግድ የተሠማሩ ነበሩ። ፕሮፌሰር አሥራት የሶስት ዓመት ሕጻን እያሉ ወላጆቻቸው በፍች ምክንያት ስለተለያዩ ከእናታቸው ጋር ወደ ድሬዳዋ አቀኑ።
አሥራት ድሬዳዋ በነበሩበት ወቅት ጣሊያን ኢትዮጵያን ትወራለች። በዚህ ወቅት በእነ ሞገስ አስገዶምና አብርሃም ደቦጭ ግራዚያኒ ላይ የተደረገ የግድያ ሙከራን ለመበቀል ከግራዚያኒ በተላለፈ በቀል በሶስት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ33 ሺህ በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በዶማ፤ በአካፋና በገጀራ ጭምር ተጨፍጭፈዋል። የአሥራት አባት አቶ ወልደየስ አልታዬም እንደ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ሁሉ ተጨፍጭፈው በአርበኝነት ሞቱ። እናታቸው ወይዘሮ በሰልፍይዋሉ ጽጌም የባለቤታቸው ሞት ተጨምሮበት ብዙም ሳይቆዩ ታመው ሕይወታቸው አለፈ።
ወላጆቹን በሞት የተነጠቀው ታዳጊ በድሬዳዋ ከአያቱ ጋር አደገ። ቄስ ትምህርት ቤት ገብቶም ጎበዝና ፈጣን ተማሪ ነበር ይባላል። ከጣሊያን ወረራ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገባ። አንደኛ በመውጣትም ተሸላሚ ሆነ። በወቅቱ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በከፍተኛ ውጤት የሚያጠናቅቁ ወደ ውጭ ይላኩ ስለነበር አሥራት ወደ ግብጽ ተልከው ተከታትለዋል። ከዚያም በስኮላርሽፕ እንግሊዝ አገር ሄደዋል። እንግሊዝ አገር የሕክምና ትምህርት ተምረው ወደ አገራቸው በመመለስ በሕክምና አገልግለዋል።
ዶክተር አሥራት ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የሕክምና ማሰልጠኛ እንዲከፈት በመወትወታቸው ምክንያት የጥቁር አንበሳን ሆስፒታል እውን አደረጉ። የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲቋቋም የቴክኒክ ኮሚቴውን የመሩት እሳቸው ነበሩ። እ.ኤ.አ በ1965 ዓ.ም የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እውን ሲሆን ፕሮፌሰር አሥራት ተባባሪ ፕሮፌሰር በመሆን የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዲን ሆኑ። ከዚያ በፊት በውጭ ባለሙያዎች ነበር።
ፕሮፌሰር አሥራት በደርግ ዘመነ መንግሥት በተደጋጋሚ ዘመቻ የተላኩ ሲሆን፣ የሄዱበትን ዘመቻ በክብር ለመወጣት በቅተዋል። በዚህም መሠረት በ1968 ዓ.ም በቀዶ ሕክምና ሐኪምነት በቃኘው ሆስፒታል አስመራ፤ በ1969 ዓ.ም እንደገና በቃኘው ሆስፒታል አስመራ፤ በ1970 ዓ.ም በራዛ ዘመቻ በቀዳጅ ሐኪምነት እና ቡድን መሪነት በመቀሌ ሆስፒታል፤ እንዲሁም በሰኔ 1971 ዓ.ም በቀዳጅ ሐኪምነት ምጽዋ ዘምተው ግዳጃቸውን ተወጥተዋል። የተለያዩ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ሽልማቶችንም አግኝተዋል።
የደርግ ሥርዓት ተሸንፎ ኢሕአዴግ አገሪቱን በተቆጣጠረበት ወቅት፤ ሰኔ 24 ቀን 1983 ዓ.ም በተደረገው የሽግግር መንግሥት ቻርተር ውይይት ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ወክለው ተገኝተዋል፤ በእዚህም ወቅት ነው ፕሮፌሰር አሥራት የኤርትራን መገንጠል አስመልክቶ በተካሄደ ውይይት ላይ ‹‹ሃገር ላስገነጥል ተወክዬ አልመጣሁም›› በማለት ተቃውሞ ያሰማሉ። ‹‹ይህ ጉባኤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ምንም ጉዳይ ሊወስን፤ ሊያግድ ወይም ሊሰርዝ አይችልም›› በማለት ጉባኤው እያደረገው ያለው ውሳኔ ኢ-ዲሞክራሲያዊ መሆኑን አስረግጠው ሞገቱ። በዚህ ንግግራቸውም የተነሳ ከጉባኤው ሲወጡ ብዙ ማስፈራሪያና ዛቻ ተካሄደባቸው።
እንዲህ እንዲህ እያሉ ፕሮፌሰር አሥራት ወደ ፖለቲካው ዓለም ገቡ። የኢሕአዴን አገዛዝ ለመታገል የመላ አማራ ህሕዝብ ድርጅት /መአሕድ/ የተሰኘ ፓርቲ መሥርተው መንቀሳቀስ ጀመሩ። ከኢሕአዴግ ጋር አይጥና ድመት ሆኑ። ኢሕአዴግም እያሳደደ ያሥራቸውና ይፈታቸው ጀመር። ኢሕአዴግ እንቅስቃሴያቸውን ባየ ቁጥር እስርና እንግልቱን አጠናከረው። ለብቻቸው በማሰር ስቃይና መከራም ያደርስባቸው ጀመር።
የእስር አያያዛቸው የከፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በ1972 ዓ.ም የጀመራቸው የልብ ሕመም ተባብሶ እንዲሁም የስኳር መጠናቸው በመጨመሩ ከፍተኛ የጤና ችግር ላይ ወደቁ። ለብዙ በሽተኞች መድኃኒት የነበሩት አሥራት ሕክምና ተከልክለው የበሽታ መጫዎቻ ሆኑ። ከስኳራቸው ከፍ ማለት ጋር ተያያዞ አይናቸው ማየት ተሳነው። ሰውነታቸውም እንደፈለጉ አልታዘዝ አለ። የልብ ድካማቸው ጨመረ።
ሕክምና እንዲያገኙ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀር ደብዳቤ ጻፉ። መፍትሔ ግን አላገኙም። የኋላ ኋላ ሲዳከሙ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቢወሰዱም ሕመማቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑ መፍትሔ ሊያገኙ አልቻሉም። በመጨረሻም እ.ኤ.አ ታኅሳስ 27 ቀን 1998 ዓ.ም ወደ ውጭ ሃገር ሄደው እንዲታከሙ ተፈቀደ።
በከፍተኛ ሁኔታ በመድከማቸው አውሮፕላን ውስጥ በሐኪሞች እየታገዙ ወደ ለንደን ሆስፒታል በረሩ። ከ3 ቀናት ቆይታ በኋላ ወደ አሜሪካ ሆስተን አመሩ። በአሜሪካ ቅዱስ ሉቃስ ኤጲስቆጳል ሆስፒታል በነበሩበት ወቅት እንደተሻላቸውና ከልቡ ሲያስባቸው ለነበረው ሕዝብ መልዕክት አስተላልፈው ነበር። ትንሽ እንደተሻላቸው ዘመዶቻቸው ወደሚገኙበት ፊላደልፊያ ከወር በፊት ተዛውረው በነበረበት ወቅት ባልታወቀ ምክንያት ሕመማቸው ተባብሶ ተዳከሙ።
ሞትን ድል ሲያደርጉት የኖሩት ሐኪም ግንቦት 6 ቀን 1991 ዓ.ም ፊላደልፊያ በሚገኘው ፔኒሲለቫኒያ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በዕለተ ዓርብ በተወለዱ በ71 ዓመታቸው አረፉ። በወቅቱ የፕሮፌሰሩን ሞት ትልልቅ የዓለም መገናኛ አውታሮች ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ነበር።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2014 ዓ.ም