በዓባይ ወንዝ ላይ ከተገነቡት ድልድዮች አንዱ በውቧ ባህር ዳር ከተማ የሚገኘው ነው። በ1954 ዓ.ም እንደተገነባ የሚነገርለት የዓባይ ድልድይ ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት የአማራ ክልል አካባቢዎችን እንዲሁም ኢትዮጵያን ከሱዳን ጋር ሲያገናኝ ቆይቷል። ድልድዩ ለትራንስፖርት አገልግሎት ካለው ፋይዳ ባሻገር ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ለባህርዳር ከተማ ልዩ መለያ በመስጠት ውበትን አላብሶ ቆይቷል። ሆኖም ከእድሜ መርዘም እና በመንገዱ እየጨመረ ከመጣው የትራፊክ ፍሰት አንጻር ተደጋጋሚ ጉዳቶችንም ሲያስተናግድ ቆይቷል።
በተለይም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የሀገሪቱ ወጪና ገቢ ንግድ ምክንያት በዚህ ድልድይ የሚመላለሱ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ፍሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ ድልድዩ ላይ ጫና ፈጥረውበታል። ድልድዩ በቀን እስከ 24 ሺህ የሚደርሱ ቀላልና ከባድ የጭነትና የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን ሲያስተናግድ መቆየቱን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መረጃ ያመላክታል።
ድልድዩ 169 ሜትር ርዝመትና 10 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ሲሆን ፤ የጎን ስፋቱ ጠባብ በመሆኑ ለትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት ከመሆኑ ባሻገር ለእግረኛና ለብስክሌት ተጠቃሚዎች አመቺ እንዳልነበረ የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ።ከአቅሙ በላይ አገልግሎት በመስጠት ላይ በሚገኘው በነባሩ የዓባይ ወንዝ ድልድይ ላይ ይደርስ የነበረውን ጫና እና የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስ በአይነቱ በሀገራችን ግዙፍ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተተገበረበት አዲስ ድልድይ በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ይገኛል ።
ለግንባታው ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ይህ ድልድይ ግንባታ ፕሮጀክት የውል ስምምነት የተፈጸመው መጋቢት 18 ቀን 2011 ዓ.ም ነው። ድልድዩ 380 ሜትር ርዝመት እና 43 ሜትር የጎን ስፋት አለው። የድልድዩ የጎን ስፋት ከነባሩ የአባይ ድልድይ ጋር ሲነጻጸር በአራት እጥፍ ይሰፋል። ድልድዩ በግራና በቀኝ በአንድ ጊዜ ስድስት ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችል ባለሁለት አካፋይ አለው። በተጨማሪም በድልድዩ በሁለቱም አቅጣጫ የብስክሌት ተጠቃሚዎች መስመር ያለው ሲሆን አምስት ሜትር የእግረኛ መሄጃም ተካትቶበታል። በተጨማሪም የትራፊክ ምልክቶች ፣ የድልድይ ላይ መብራቶች ፣ የተሽከርካሪ መውጫና ሌሎች የኮንክሪት መዋቅሮችን አካቶ የያዘ ነው።
የድልድዩ ግንባታ ሙሉ ወጪ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ሲሆን፤ የፕሮጀክቱ ተቋራጭ የቻይና ኮንስትራክሽን ኮሙዩኒኬሽን ካምፓኒ (ሲሲሲሲ) ሲሆን፤ የማማከር ስራውን ደግሞ የቱርኩ ቦቴክ ቦስፈረስ የተሰኘ ድርጅት ካስታዲያ ኢንጂነሪንግ ስራዎች ድርጅት ከተባለ ሀገር በቀል ተቋም ጋር በመሆን እያከናወኑት ይገኛሉ።
የፕሮጀክቱ ምክትል ተጠሪ መሐንዲስ ኢንጂነር ፍቅረስላሴ ወርቁ እንደሚሉት፤ ድልድዩን በ2014 መጨረሻ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የድልድዩ ግንባታ 61 ነጥብ 5 በመቶ ላይ ይገኛል። የድልድዩን ግንባታ ለማጠናቀቅ ከተሰጠው ጊዜ 83 በመቶ ብቻ ተጠናቋል። ግንባታው በተያዘው እቅድ መሰረት እንዳይከናወን ያደረጉ የተለያዩ እንቅፋቶች ያጋጠመ ሲሆን፤ ኮቪድ 19 ፣ የወሰን ማስከበር ችግሮች፣ የግብዓት እጥረት እና የጸጥታ ችግሮች ግንባታው በተያዘለት ጊዜ መሰረት እንዳይካሄድ ምክንያት ሆነዋል ። በመሆኑም በየጊዜው ማሻሻያዎችን ማድረግ ያስፈለገ ሲሆን፤ በዚሁ መሰረት መስከረም 2015 እንዲጠናቀቅ የጊዜ ማሻሻያ ተደርጓል። በቀጣይ ስድስት ወራት ውስጥ ፕሮጀክቱን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ ርብርብ እንደሚደረግ ነው ያብራሩት።
ድልድዩ ሲጠናቀቅ ለአካባቢውና ለሀገሪቱ ከፍተኛ ፋይዳዎችን የሚያስገኝ ነው። አንዱን አካባቢ ከሌላው አካባቢ ጋር በማስተሳሰር የምርትና ሸቀጥ ልውውጥ ያለ እንግልት እንዲከናወን በማስቻል ለአካባቢው እና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
በአሁኑ ወቅት ከአቅሙ በላይ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘውን ነባሩ የአባይ ወንዝ ድልድይ ላይ ይደርስ የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅና ጫና በእጅጉ እንደሚቀንስ ምክትል ተጠሪ መሃንዲሱ አብራርተዋል። ከዚያ በሻገርም ከባህርዳር እድገትና ውበት ጋር ያልተመጣጠነ የነበረውን ነባሩን ድልድይ በመተካት ከተማዋ ከዘመኑ ጋር አብሮ የሚሄድ ደረጃውን የጠበቀ የመሰረተ ልማት ተጠቃሚ እንድትሆን እንደሚያደርጋት ጠቁመዋል።
አዲሱ ድልድይ ሰሜን ምዕራቡን ኢትዮጵያ ከቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ ከማሳለጡም ባሻገር ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገር ሱዳን ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ የሁለቱ ሀገራትን የንግድና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያስተሳስር ተጠቁሟል። ድልድዩ ለሀገሪቱ የወጪ ገቢ ንግድ እንቅስቃሴ መሳለጥም የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል።
ነባሩ ድልድይ ጠባብ በመሆኑ ምክንያት እግረኞች ድልድዩን በሚያቋርጡበት ወቅት ለተለያዩ አደጋዎች የመጋለጥ ስጋት ነበር። አዲሱ ድልድይ ሰፊ ከመሆኑም ባሻገር ለእግረኞች 5 ሜትር ስፋት ያለው መሄጃ ተዘጋጅቶለታል። በመሆኑም እግረኞቹን ከትራፊክ አደጋ ስጋት ነጻ ያደርጋቸዋል። ብስክሌት የሚጠቀሙ የከተማዋ ነዋሪዎችና ቱሪስቶችን ታሳቢ ያደረገ የመንገድ ክፍል በመሆኑ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
ድልድዩ በግዝፈቱ በሀገሪቱ ትልቁ ሲሆን ፣ እጅግ ዘመናዊ የሚባል ነው። በድልድዩ ላይ የሚተገበረው ቴክኖሎጂ ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ ያልተለመደ መሆኑን የፕሮጀክቱ ምክትል ተጠሪ መሐንዲሱ ያብራራሉ። በመሆኑም የበርካታ የቱሪስት መስህቦች መገኛ ለሆነችው ባህር ዳር አዲሱ ድልድይ ራሱን የቻለ ተጨማሪ መስህብ የመሆን እድል አለው።
ከዚህ ቀደም ያለው ድልድይ ጠባብ በመሆኑ ተሽከርካሪዎች ወረፋ ጠብቀው ድልድዩን ለመሻገር ይገደዱ ነበር። ይህም ለባህር ዳር ከተማ የትራፊክ መጨናነቅ የራሱን አስተዋጽኦ ሲያደርግ መቆየቱን የከተማዋ ነዋሪዎች ያነሳሉ። አሁን በመገንባት ላይ ያለው ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ለተሽከርካሪዎች ሁለተኛ እና ምቹ አማራጭ ስለሚሆን የከተማዋን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቅረፍ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ኢንጂነር ፍቅረስላሴ አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱ ገና ከአሁኑ የስራ ዕድል በመፍጠር ለበርካታ ዜጎች ጥቅም እያስገኘ ሲሆን በርካቶች ተቀጥረው የራሳቸውን እና የቤተሰባቸውን ህይወት እየለወጡበት ይገኛሉ። ይህም ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት የራሱን ሚና ያበረክታል። ለፕሮጀክቱ መዘግየት አንዱ ምክንያት እየሆነ ያለው የግብዓት ችግሮች ከተቀረፉ እስከ መስከረም 2015 ድረስ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።
የማማከር ስራውን እያከናወነ ያለው የቦቴክ ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ ባልደረባ እና የፕሮጀክቱ ዲዛይነር ኢንጂነር አሚር እንደተናገሩት፤ የድልድዩ አይነት በኢትዮጵያ ያልተለመደና አዲስ ነው። የተንጠልጣይና የሳጥን ቅርጽ ያላቸውን ረጃጅም ድልድዮችን ዲዛይን በማዋሃድ በአዲስ የዲዛይን ጥበብ የሚገነባውን ኤክስትራዶስድ የተሰኘ እጅግ ዘመናዊ ድልድይ ነው። ይህም ሀገሪቱ እጅግ ዘመናዊ የሚባል ድልድይ ባለቤት የሚያደርጋት ሲሆን የሀገሪቱ መታወቂያ ሊሆን የሚችል ድልድይ ነው ብለዋል።
ድልድዩ ዘመናዊ፣ በአይነቱ የተለየ እና እጅግ ግዙፍ ነው የሚሉት ኢንጂነር አሚር ፤ ለግንባታው የሚወጣው ወጪም ከፍ ያለ መሆኑን አንስተዋል። ለቀጣይ 100 ዓመታት ገደማ ያለ እንከን የማገልገል አቅም እንዲኖረው ሆኖ እየተገነባ ነው። ይህም በየወቅቱ ለእድሳት በሚል የሚወጣውን ወጪ ከመቀነሱም ባሻገር በተለያዩ እንከኖች ምክንያት የሚፈጠሩ ስጋቶችን የሚያስቀር ነው።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በትራንስፖርት ዘርፍ ከሚኖረው የላቀ ፋይዳ ባሻገር በግንባታ ዘርፍ ለቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ይሄንኑ ዘመናዊ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አመራሮችና ባለሙያዎች ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ በርካታ የፕሮጀክቶች ማናጀሮች ፣ በሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ የተመደቡ ሰራተኞችና አመራሮች የተሳተፉበት ሲሆን ልምድ ፣ እውቀትና ተሞክሮ የቀሰሙበት መሆኑን ተናግረዋል።
የአስተዳደሩ የመንገድ ሀብት ሲስተም ማኔጅመንት ዳይሬክተር ኢንጂነር አብርሃም አብደላ እንደጠቆሙት፤ በአባይ ወንዝ ድልድይ በዓለም ላይ በድልድይ ግንባታ ዘርፍ በአሁኑ ወቅት እየተተገበሩ ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ስራ ላይ እየዋለ ያለበት ነው። ድልድዩ በውጭ ባለሙያዎች እየተገነባ ቢሆንም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችም እየተሳተፉበት ነው። ኢትዮጵያውያን በስፋት እየተሳተፉበት መሆኑ ደግሞ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎችን ያስገኛል። በቀጣይ በራስ አቅም ድልድዮች መገንባትን ለማጎልበት ይረዳል።
በተጨማሪም የአስተዳደሩ ሠራተኞች የድልድዩ ግንባታ ዙሪያ ትምህርታዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ላቅ ያለ ፋይዳ አለው። በርካታ እውቀትና ልምድም እንዲቀስሙ ይረዳል ። በቀጣይ ጊዜያትም በሀገሪቱ የተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች የተግባር ላይ ልምምድ እንዲያደርጉ እድል ይፈጥራል። ይህም በኢትዮጵያ የድልድይ ግንባታና አስተዳደር ዘርፍ የእውቀት ሽግግር በማምጣት በቀጣይ በግንባታ ዘርፍ በተለይም በድልድዮች ግንባታ ሌሎች ሀገራት ከደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ለምታደርገው ጥረት አጋዥ ነው።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 6/2014