ለዛሬ ገጣሚ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣ ደራሲ፣ ሃያሲ፣ ተርጓሚ፣ መምህር፣ የሥነጽሑፍ ተመራማሪና የገዘፈ ሰብዕና ባለቤት የሆነው ደበበ ሰይፉ ለኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ፣ ተውኔትና ሌሎች የኪነጥበብ ዘርፎች ስላበረከታቸው አስተዋፅኦዎች በጥቂቱ እንመለከታለን።
ደበበ ሰይፉ ሐምሌ 5 ቀን 1942 ዓ.ም ከበጅሮንድ ሰይፉ አንተንይሥጠኝ እና ከወይዘሮ የማርያምወርቅ አስፋው ባለውለታው፣ የማንነቱ መገኛ፣ የዕውቀቱ መፍለቂያና መድመቂያ መሆኗን በግጥሙ ባሞካሸትና በደቡቡ የአገራችን ክፍል በምትገኘው ይርጋለም ከተማ ተወለደ። ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ልዩ የማንበብ ፍቅር ነበረው። ፊደል የቆጠረው በቄስ ትምህርት ቤት ነው። የትምህርት አቀባበሉ አስደናቂ ስለነበር መምህሩ የቤተ ክህነት አገልጋይ እንዲሆን ፈልገው ነበር። ይሁን እንጂ አባቱ ወደ መደበኛ ትምህርት ቤት እንዲገባ አደረጉት። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ይርጋለም ከተማ ውስጥ በሚገኘው ራስ ደስታ ትምህርት ቤት አጠናቀቀ።
በመቀጠልም ወደ አዲስ አበባ በመዛወር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በኮከበ ጽባሕ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤት ተማረ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተናውን በማለፍ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ)ን ተቀላቀለ። ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲገባ የቢዝነስ ትምህርት ክፍል ተማሪ ሆኖ ነበር። ይሁን እንጂ ደበበ የነፍሱ መሻት ሥነጽሑፍ እንጂ ቢዝነስ ስላልነበር የቢዝነስ ትምህርቱን ለአንድ ዓመት ያህል ከተማረ በኋላ ወደ ሥነጽሑፍ ትምህርት ተዛወረ። በ1965 ዓ.ም ከዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ ትምህርት ክፍል በከፍተኛ ማዕረግ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመረቀ። ቀጥሎም በ23 ዓመቱ በዚያው በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ሥነጽሑፍን ማስተማር ጀመረ። ከአምስት ዓመታት በኋላ ደግሞ በእንግሊዝኛ ሥነጽሑፍ (English Literature) የሁለተኛ ዲግሪውን እንደ ቀድሞው ሁሉ በከፍተኛ ማዕረግ ማጠናቀቅ ችሏል።
የትምህርት ክፍሉንና የጥናት መስኩን በተመለከተ የተሰሩ በርካታ ስራዎች እንደሚያሳዩት የጥናትና የምርምር ውጤቶች በስፋት መሠራት በመጀመራቸው እንደ ደበበ ሰይፉ ያሉ መምህራን በዚህ ትምህርት ክፍል ውስጥ መቀላቀል ሲጀምሩ የትምህርት ክፍሉም እየተነቃቃ፣ እያደገና እየተስፋፋ የመጣበት ዘመን ነበር። ደበበ የኢትዮጵያ የሥነጽሐፍ፤ በተለይም ዐቢይ የሥነጽሐፍ ዘርፍ የሆነው የሥነግጥም ታሪክንና በዚህ ታሪክ ውስጥ ደግሞ ኪነታዊ አስተዋፅኦአቸው ሰፊ የሆኑትን ታላላቅ ጸሐፊያንን ታሪክና የአጻጻፍ ቴክኒካቸውንም ጭምር እያጠና ማቅረብ ጀመረ። ያለፈው የጥበብ አሻራ ለመጪው ጥበብ የሚያቀብለውን መረጃ እያዛመደ ትውልድን በጥበብ ማስተሳሰር አንዱ ተግባሩ ነበር።
ደበበ በኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ውስጥ የሚገኙ የታሪክ፣ የሥነግጥም፣ የትያትር፣ የፍልስፍና (በተለይም የእነ ማርክስን ፍልስፍና)፣ የፖለቲካ … ጽንሰ ሃሳቦችን ከጥንታዊ ሰነዶች ውስጥ እየፈተሸ በማውጣት ‹‹እንዲህ ነበር፣ እንዲህም ኖሯል፣ እንዲህም አ(ታ)ስቧል …›› እያለ በትውልድ መካከል የመሸጋገሪያ ድልድይ ሆኖ አገልግሏል።
ደበበ የተዋጣለት ገጣሚ ነበር። በአገጣጠም ችሎታው ውብ እና ማራኪነት የተነሳ ብዙዎች ‹‹ባለቅኔው ደበበ ሰይፉ›› እያሉ ይጠሩታል። ይህ በሥነግጥም ዓለም ውስጥ የተሰጠው ፀጋ ከሌሎች ጉዳዮች ሁሉ ገዝፎ የሚነገርለት፤ የሚታወቅበትም ነው። ደበበ ሲነሳ ገጣሚነቱ አብሮ ብቅ የሚልለት የጥበብ ሰው ነው። እነዚህ የግጥም ትሩፋቶቹ በአንድ ላይ ተሰባስበው ‹‹የብርሃን ፍቅር›› በሚል ርዕስ ታትመዋል። ይቺ የሥነግጥም መጽሐፍ ደበበ ቀደም ሲል በተማሪነት እና በአስተማሪነት ዘመኑ ሲጽፋቸው የነበሩት ግጥሞች ተካትተው የሚገኙባት ድንቅ መጽሐፉ ነች።
ከዚህች መጽሐፉ በተጨማሪ በ1992 ዓ.ም፣ በሜጋ አሳታሚ ድርጅት አማካኝነት ‹‹ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ›› በሚል ርዕስ ሁለተኛዋ የሥነግጥም መጽሐፉ ታትማ ለንባብ በቅታለች። ነገር ግን በዚህ ወቅት ደበበ በሕይወት የለም ነበር። የዚህችን መጽሐፍ አጠቃላይ ገጽታ በተመለከተ አስተያየት የሰጠው ታዋቂው የወግ ጸሐፊና ሃያሲ መስፍን ኃብተማርያም ‹‹ደበበ ሰይፉ በርዕስ አመራረጡና በሚያስተላልፋቸው ልብ የሚነኩ መልዕክቶች ብቻ ሳይሆን በስንኞቹ አወራረድና የቤት አመታቱ በአጠቃላይ በውብ አቀራረቡ ተደራሲያንን የሚመስጥ ገጣሚ ነው። ስለ ተፈጥሮ ሲገጥም ፀሐይና ጨረቃ፣ ቀስተ ደመናና የገደል ማሚቶ ያጅቡታል። ስለ ፍቅር ስንኞች ሲቋጥር የፍቅረኞችን ልብ እንደ ስዕል ቆንጆ አድርጐ በቃላት ቀለማት ያሳያል። ክህደት ላይ እንደ አንዳንድ ገጣሚያን አያላዝንም። ይልቁንም ውበትና ህይወትን አገናዝቦ ‹ያውላችሁ ስሙት፤ እዩት› ማለትን ይመርጣል … እኔ እንደማውቀው ደበበ ሰይፉ በገጣሚነቱ ሁሌም ዝምተኛ ነው። አይጮህም። ጮሆም አያስበረግግም። ይልቁንስ ለዘብ ለስለስ አድርጐ “እስቲ አጢኑት” ይለናል። ደግመን እንድናነብለት የሚያደርገንም ይኸው ችሎታው ነው” በማለት ጽፏል። (በተጨማሪም፣ ለጥልቅ ሙያዊና ጥናታዊ ምልከታ የብርሀኑ ገበየሁን “የአማርኛ ሥነግጥም” መመልከት ይቻላል። የደበበን ስብስብ ስራዎች የያዘውና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ያብራራውን መጽሐፍም መመልከት ጠቃሚ ነው።)
ደበበ ከገጣሚነቱ ባሻገር ሃያሲም ነበር። ሃያሲ ታሪክ አዋቂ ነው። ያለፈውን ከአሁኑ ጋር እያነፃፀረ የሚያስረዳና የሚተነትን ባለሙያ ነው። የሂስ ጥበብን ከታደሉትና በኢትዮጵያ የዘመናዊ ሂስ ጥበብ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት ሃያሲያን መካከል ደበበ ሰይፉ አንዱ ነበር። ደበበ ያለፉ ታሪኮችንም ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነበር። በዚህም ምክንያት የሚሰጣቸው በሳል አስተያየቶች ከልብ የነበሩና ለለውጥ የሚያነሳሱ እንደነበሩ የሚያውቁት ሁሉ ይመሰክሩለታል። ደበበ ሰይፉ በሥነ ግጥም ተሰጥኦውና በሚያነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች በኢትዮጵያ የሥነጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ጐልቶ ከሚነሱ ከያኒያን መካከል አንዱ መሆኑን ቀደም ያሉት ኃያስያን ጽፈውታል።
የደበበ ችሎታ በዚህ ብቻም አያበቃም። ደበበ የትያትር ጥበብ መምህር ከመሆኑም በላይ በዘርፉ ውስጥ ግዙፍ የሚባል አስተዋፅኦ አበርክቶ አልፏል። ደበበ በመድረክ ላይ የሚሠሩ ቴአትሮችንና የቴአትር ጽሑፎች የያዟቸውን ጽንሰ ሐሳቦች (ኮንሴፕትስ) በመተንተንና ሂስ በመስጠት ለዘርፉ ዕድገት የበኩሉን ምሁራዊ ሚና ተጫውቷል።
ደበበ የቃላት ፈጣሪም ነው። ለአብነት ያህል በትያትርና በሥነጽሑፍ ዘርፎች ውስጥ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መጠሪያ የሆኑ ሙያዊ ቃላትን ወደ አማርኛ በማምጣት አቻ የሆነ የአማርኛ ትርጉም በመስጠት ይታወቃል። በኢትዮጵያ የሥነጽሑፍ ክፍለ ትምህርት ውስጥ እስከ አሁን ድረስ መጠሪያ የሆኑትንና ‹‹ገጸ-ባህርይ››፣ ‹‹ሴራ››፣ ‹‹መቼት››፣ ‹‹ቃለ-ተውኔት›› … እና የመሳሰሉትን ጽንሰ ሐሳቦች ያስተዋወቀን (ከመገኛ ቋንቋቸው ወደ አማርኛ ያሻገረው) ደበበ ሰይፉ ነው። ‹‹Character›› ለሚለው መጠሪያ ‹‹ገፀ-ባህርይ›› በማለት አቻ ትርጉም ሰጥቶታል። ‹‹Setting›› የሚለውና በውስጡ “ጊዜ” እና “ቦታን” መያዙን በመረዳት ‹‹መቼት›› ብሎ ተረጐመው። “መቼት” ማለት ‹‹መቼ›› እና ‹‹የት›› ማለት ሲሆን፤ ጊዜንና ቦታ (Time and Space)ን ይገልፃል። ‹‹Dialogue›› የሚለው ቃል ተዋንያን በትወና ወቅት የሚናገሩት ሲሆን፤ ይህን ቃል ‹‹ቃለ-ተውኔት›› በማለት በአማርኛ የተረጐመው ደበበ ሰይፉ ነው። ደበበ እነዚህንና ሌሎች በርካታ ሥነጽሑፋዊ (ኪናዊ) ቃላትን በመፍጠር ቃላቱ በትውልዶች አንደበት፣ አእምሮ እና ብዕር ውስጥ ለዘላለም እንዲኖሩ፤ ሙያው እንዲጎለብት ያደረገ ባለ ተሰጥኦ የጥበብ ሰው ነው።
ደበበ ለትያትር ትምህርት ዘርፍ ካበረከታቸው አስተዋፅኦዎች መካከል ለትምህርቱ መጐልበት ይረዳ ዘንድ በ1973 ዓ.ም. መጽሐፍ ማሳተሙ የሚጠቀስ ነው። መጽሐፏ ‹‹የቴአትር ጥበብ ከጸሐፌተውኔቱ አንፃር›› የሚል ርዕስ ያላት ስትሆን፣ በኢትዮጵያ የትያትር ሙያተኞች እንዲበራከቱና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ሰፊ ድርሻ አበርክታለች፤ እስካሁንም ከ”መድረክ” ላይ አልወረደችም። ደበበ በዚህ ዘርፍ የተጻፉ የንባብ መጻሕፍት ያለመኖራቸውን ክፍተት ተገንዝቦ ክፍተቱት ለመሙላት ሙያዊ አሻራውን ያሳረፈ የዘርፉ ባለውለታ ነው።
ደበበ ጸሐፌ ፀሀፌ ተውኔትም ነበር። በርካታ ተውኔቶችን ጽፎ ለመድረክ አብቅቷል። አንዳንዶቹም ለበርካታ ጊዜያት ያህል በቴሌቪዥን ታይተውለታል። ደበበ ከጻፋቸውና ከተረጐማቸው ተውኔቶች መካከል ‹‹ከባህር የወጣ ዓሳ››፣ ‹‹እናትና ልጆቹ››፣ ‹‹እነሱ እነሷ››፣ ‹‹ሳይቋጠር ሲተረተር››፣ ‹‹የሕፃን ሽማግሌ››፣ ‹‹ክፍተት››፣ ‹‹እድምተኞቹ››፣ ‹‹ጋሊሊዮ ጋሊሊ›› … ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ በነበረባቸው ዓመታት ከሰራቸው የምርምር ስራዎችና ከጻፋቸው መጻሕፍት መካከል፤
- የትያትር ጥበብ ከጸሐፊ ተውኔት አንፃር
- ደራሲው በአብዮት አውድ
- ዋዜማ ጦርነት ግጥሞች
- ሕዝባዊ ሥነግጥም
- Profile of Peasantry in Ethiopian Novels
- A Critical Analogy of Ethiopian Novels
- Foreign Scholars on Amharic Novels
- A Critical Analogy to Amharic Poetry
- The Need for Marxist Approach in the Teaching of Literature
- Post-Revolution Ethiopian Theaters … የሚሉትና ሌሎች ስራዎቹ ይጠቀሳሉ።
በ1973 ዓ.ም ለአንባቢያን የቀረበው ‹‹ማርክሲዝምና የቋንቋ ችግሮቹ›› የሚለው መጽሐፉ ለሕትመት ከበቁ ስራዎቹ መካከል ተጠቃሽ ነው። በ1960 ዓ.ም. (ደበበ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረበት ወቅት) ከታተሙ ሦስት አጫጭር ታሪኮች መድበል ውስጥ አንዱ የደበበ ሥራ ነበር።
ደበበ ሰይፉ ከእነዚህ ረቂቅ ከሆኑ ምሁራዊ አስተዋጽኦዎቹ በተጨማሪ በበርካታ ኪነጥበባዊ ጉዳዮች ላይም አሻራውን ያሳረፈ ምሁር ነበር። በቀድሞው ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ ለኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ መስፋፋት ሰፊ እገዛ አድርጓል። በኢትዮጵያ ሬዲዮ ውስጥም የኪነጥበብ ዘርፍ ፕሮግራሞች አማካሪ ሆኖ ሰርቷል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም የጥናት መጽሔት አሳታሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሆኖ አገልግሏል። የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዝደንት በመሆንም ሙያዊ ኃላፊነቱን ተወጥቷል። እስከ ዛሬ የዘለቀችው ‹‹ብሌን›› የማኅበሩ የሥነጽሑፍ መጽሔት እንድትጀመርም አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪም በወቅቱ በርካታ የሙያው ባለቤቶች እንዲሰባሰቡና ከውጭ አገሮች፤ በተለይም ከሶቪየት ኅብረት ጋር ሙያዊ ድጋፍና ትብብር እንዲደረግም ጥሯል።
አንጋፋው ደራሲና ሃያሲ አቶ አስፋው ዳምጤ በአንድ ወቅት ስለ ደበበ ሲናገሩ ‹‹ደበበ ስራ ይወዳል፤ ስራው ጥንቅቅ ያለ ነው። … ለቴአትር ዲፓርትመንት ከመከፈቱ ጀምሮ መጽሐፍ ጽፎለታል። ጽንሰ ሃሳቡን እንዲረዱት አድርጓል። ስለ ደበበ ካስደነቁኝ አንዱ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታው ነው። የደራሲያን ማኅበር ሊቀመንበር ሆኖ እኔ ስራ አስፈፃሚ ሆነን ሠርተናል። ቀድሞ ከነበረው የማኅበሩ የሥራ ዘመን ያልታየ እንቅስቃሴ አድርጓል።” ብለውለታል።
አቶ አስፋው ‹እነሆ› የተሰኘች የአጫጭር ልብ ወለዶች እና ‹የጽጌረዳ ብዕር› የሚል የግጥም መድብል መድበሎች፤ እንዲሁም ‹ብሌን› የተሰኘች መጽሔት ታትመዋል›› ሲሉም የደበበን ሁለ ገብ ጥንካሬ ገልፀዋል።
ታዋቂው የወግ ጸሐፊና ሃያሲ መስፍን ኃብተማርያም ደግሞ ‹‹… ደበበ በጣም ጠንካራ፣ ትጉህ ሠራተኛ፣ ለተሰለፈበት ዓላማ ወደ ኋላ የማይል፣ በማስተማር [ተግባሩ] ፈጣሪ (Innovator) ዓይነት ነበር። የምናስተምረውን ኮርስ ‹እንዲህ ብናደርገው፣ እንዲህ ብንለው› እያለ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንድናሻሽል በማድረግ በኩል ፈር ቀዳጅ ነበር። … ደበበ ደራሲ ብቻ አይደለም። ጥሩ የማስተማር ችሎታም ነበረው›› በማለት የአይንና የተግባር ምስክርነቱን ሰጥቶለታል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነጽሁፍ መምህር የነበረው ብርሃኑ ገበየሁ በበኩሉ ‹‹… የደበበ አቀራረቡ ቀላልና የማያሻማ ነው። ድምፀቱ ደግሞ ሐዘን ከሰበረው ልብ የሚፈልቅ እንጉርጉሮ። የአቀራረብ ቀላልነት ውበቱ ነው። ይርጋለምና ልጅነቱ በተናጋሪው ህሊና አንድም ሁለትም ናቸው፤ የማይፈቱ›› በማለት ስለ ደበበ ሰይፉ ስራዎችና ብቃቱ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ባሰፈረው ጽሑፉ ገልጿል። ደበበ ወንድሞቹና እህቶቹ ልክ እንደ’ርሱ አንባቢ እንዲሆኑ ይፈልጋል። ለታናናሾቹም መጻሕፍት እየገዛ ይሰጥ ነበር።
ደበበ ከ1985 ዓ.ም. በኋላ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ባሉ ሰዎችና ሁኔታዎች ማዘኑን ቤተሰቦቹ ይናገራሉ። ከግንቦት ወር 1985 ዓ.ም. በኋላ የማስተማር ስራውን አቆመ። ነገሮችን አብራርቶ ከመግለጽ ይልቅ ዝምታን መርጦ ለስድስት ዓመታት ያህል ቤት ውስጥ ዋለ። ከሰው ጋር የሚገናኝበት ዕድልም አልነበረውም። ‹‹ደበበ እንዴት ነህ?›› ሲባልም ‹‹ደህና›› ብሎ አጭር ምላሽ ከመስጠት ባሻገር የተብራራ ንግግር አይናገርም ነበር (በጣም ለሚወዱት ወላጅ እናቱ ግን መልስ ይሰጥ ነበር ተብሏል)።
በመጨረሻም በኢትዮጵያ የኪነጥበብ ዓለም ውስጥ ትልቅ ድርሻውን ያበረከተውና ምሳሌ መሆን የቻለው ገጣሚ፣ ፀሐፊ ተውኔት፣ ደራሲ፣ ሃያሲ፣ ተርጓሚ፣ መምህርና የሥነጽሑፍ ተመራማሪው ደበበ ሰይፉ ሚያዚያ 16 ቀን 1992 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ስርዓተ ቀብሩም ሚያዚያ 17 ቀን 1992 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን ተፈፀመ። በወቅቱም በርካታ የሥነጽሑፍ ባለሙያዎችና የሕትመት መገናኛ ብዙኃን ስለደበበ ታላቅነት ደጋግመው አስነብበዋል፤ አስደምጠዋልም።
በአዲስ አበባ የሥነጽሁፍ መምህር የነበረው ገዛኸኝ ጌታቸው (አሁን ካናዳ ያለና በደበበ ሕይወትና ሥራዎች ላይ ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ)፣ ደበበ ሰይፉ እንዳረፈ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ እንዲህ ብሎ ጽፎ ነበር። ‹‹ዛሬ የኢትዮጵያ ሥነጽሁፍ አንድ ለጋ ብዕር አጣ፤ ነጥፎ አይደለም ታጥፎ ነው። ዛሬ የኢትዮጵያ ሥነጽሁፍ የዋህ ሃሳብ አጣ። ከፍቶ አይደለም በኖ ተኖ እንጂ። ዛሬ ብዙዎቻችን ካወቅነው ብዙ ነገር አጣን። ካላወቅንም እሰየው፤ ከእንጉርጉሮና ከፀፀት ተረፍን።››
በ1995 ዓ.ም በጀርመን የባህል ተቋም ውስጥ በወይዘሮ ተናኘ ታደሰ አስተባባሪነት ዶክተር ፈቃደ አዘዘ፣ ዶክተር ዮናስ አድማሱ እና ገዛኸኝ ጌታቸው ‹‹የደበበ ሰይፉ ምሽት›› የሚል ደማቅ ዝግጅት አሰናድተውለት ነበር። ደራሲያኑ ነቢይ መኮንን፣ አበራ ለማ እና አብርሃም ረታ ቅኔ ዘርፈውለታል።
ደበበ በስራዎቹ ከሚታወቅባቸው አንዱ “ማህበራዊ ሂስ” (ሶሻል ክሪቲሲዝም)ን መሰረት ያደረጉት ስራዎቹ ሲሆኑ፤ በተመራማሪዎች ዘንድ አብዝተው ከሚጠቀሱለትም አንዱ፡-
ጥሬ ጨው
መስለውኝ ነበረ
የበቁ የነቁ
ያወቁ የረቀቁ
የሰው ፍጡሮች
ለካ እነርሱ ናቸው
ጥሬ ጨው ጥሬ ጨው።
ጥሬ ጨዋዎች
መፈጨት፤ መሰለቅ
መደለዝ፤ መወቀጥ
መታሸት፤ መቀየጥ
ገና እሚቀራቸው፣
‹‹እኔ የለሁበትም››
ዘወትር ቋንቋቸው።
የሚለውና ዘመን ተሻጋሪ ስራው ነው።
(ደበበ ሰይፉ፣ የብርሃን ፍቅር፣ 1971 ዓ.ም)
ደበበ ሰይፉ
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 3 /2014