የመንገድ መሰረተ ልማት ‹‹መንገድ ይወስዳል መንገድ ይመልሳል›› ከሚባለውም በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን የሚያስገኝ ልማት ነው። የዜጎችን የዕለተ ዕለት እንቅስቃሴ ከማሳለጥ ባሻገር፤ የአገር ኢኮኖሚን ለማሳደግ፣ አንድን ማህበረሰብ ከሌላው ማህበረሰብ ጋር በባህል፣ በቋንቋ እና በሌሎችም ማህበራዊ እስቶች ለማስተሳሰር፤ የተሻለ አካባቢ ለመፍጠር፣ አገርን ለማበልጸግ የጎላ ሚና አለው። ይህን ታሳቢ በማድረግ የሚከናወን የመንገድ ሥራ ለትውልድ ሽግግርም እንዲሁ ይጠቅማል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ባለፉት አስርት ዓመታት ክልሎችን ከክልሎች፤ ዞኖችን ከዞኖች፣ ከተሞችን ከከተሞች ጋር የሚያገናኙ አለፍ ብሎም ከጎረቤት አገራት ጋር የሚያገናኙ የመንገድ መሠረተ ልማት በማከናወን ግንባታው ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቧ ይታወቃል።
አሁንም የመንገድ ሥራው ተጠናክሮ በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው። ባለፉት ጊዜያቶች ከተገነቡ መንገዶች መካከል አንዳንዶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ የተጠናቀቁ ቢሆኑም ከዚህ ቀደም ተገንብተው ወደ ስራ የገቡ እና አሁን በግንባት ሂደት ላይ የሚገኙ አብዛኞቹ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግን በተባለላቸው ጊዜ የመጠናቀቅ ችግር የሚስተዋልባቸው እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በርካታ ፕሮጀክቶች በግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ። የዛሬው የመሰረተ ልማት አምዳችን በግንባታ ላይ ከሚገኙትና ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው ተስፋ ከሚደረግባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች አንዱ በሆነው የሙከጡሪ- ኮከብ መስክ እና ኮከብ መስክ ዓለም ከተማ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ የሚያተኩር ይሆናል። እነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች የኦሮሚያ ክልልን ከአማራ ክልል ጋር የሚያስተሳስር ናቸው።
ለመንገዶቹ የግንባታ ስራ አመቺነት ሲባል በሁለት ኮንትራት ተከፍሎ እየተሰራ ሲሆን፤ ኮንትራት አንድ የሙከጡሪ-ኮከብ መስክ እና ኮንትራት ሁለት ደግሞ ኮከብ መስክ-ዓለም ከተማን ያካልላል። ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ሙከጡሪ – ኮከብ መስክ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ግንባታ ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ.ም ነው የተጀመረው። የካቲት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ግብ ተቀምጦለት ነበር ወደ ሥራ የተገባው። ይህ ፕሮጀክት 59 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል። የመንገድ ግንባታው በገጠር 10 ሜትር ፣ በቀበሌ 12 ሜትር፣ በወረዳ ደግሞ 21 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ መንገዱን ለመገንባት የሚስፈልገው ገንዘብ ሰባት መቶ ስልሳ ስምንት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሃያ ሁለት ሺ ብር ነው። ወጪው የተሸፈነው በኢትዮጵያ መንግስት ነው።
ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው ዓለም-አቀፉ የስራ ተቋራጭ ቻይና ሪልዌይ ቁጥር ሶስት ኢንጂነሪንግ ግሩፕ፣ የማማከሩን እና የቁጥጥሩን ስራ ደግሞ ኤልዳ ኢንጂነሪንግ ኮንሰልታንት ከዳምራ ኮንሰልቲንግ ጋር በጥምረት እያከናወኑት እንደሚገኝ የአስተዳደሩ መረጃ ያመለክታል።
በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ 40 ኪ.ሜ የሚሆን የአስፓልት ንጣፍ ስራው ተጠናቋል። አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ደግሞ 80 በመቶ ላይ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱን ቀሪ ስራዎችን ጨምሮ የማጠቃለያ ስራዎችን ለመፈጸም በትኩረት እየተሰራ መሆኑንን እንዲሁም ለመንገድ ደህንነት የሚጠቁሙ የተለያዩ የትራፊክ ምልክቶችም በመመረት ላይ እንደሆነ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በቅርቡ በማህበራዊ ድረ ገጹ(ፌስቡክ)ላይ ያሰራጨው ዘገባ አመላክቷል።
በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ የመጠናቀቅ ችግር ካጋጠማቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ ይህ ፕሮጀክት መሆኑን እላይ በዘገባው ውስጥ ከተጠቀሱት መረጃዎች መረዳት ይቻላል። በ2012 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ እቅድ ተይዞለት የነበረ ይህ ፕሮጀክት በ2014 ዓ.ም 80 በመቶ አፈጻጸም ላይ ነው የሚገኘው።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ለስራ ተቋራጩ ተጨማሪ ጊዜ ተሰጥቶታል። ለተቋራጩ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ምክንያት የሆነው ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዙ ችግሮች በማጋጠማቸው ነው። የመንገድ ግንባታ በሚካሄድበት አካባቢ የነበሩ ቤቶች እና ንብረቶች በወቅቱ አልተነሱም ነበር። የካሳ ክፍያ ተከፍሎአቸውም እንኳን በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ሊነሱ አልቻሉም። የወሰን ማስከበር ችግሩ የተፈጠረው የግለሰብ ቤቶች ባለመነሳታቸው ብቻ አይደለም። የመብራት ምሶሶዎች፣ ትራንስፎርመሮች አለመነሳታቸው ጭምር ነው። እነዚህ ችግሮች ሥራ ተቋራጩ ሥራውን በወቅቱ አጠናቅቆ እንዳያስረክብ እንቅፋት ሆነውበታል። በመሆኑም ለተቋራጩ ተጨማሪ ጊዜ መስጠት ግድ ሆኗል ብለዋል ዳይሬክተሩ።
ይህ ብቻም አይደለም። መጀመሪያ ላይ ከታሰበው ተጫማሪ ስራዎችም እንዲሰሩ ተደርጓል። መጀመሪያ ከነበረው ተጨማሪ ስራዎች መስራት ደግሞ ተጨማሪ ጊዜ የሚፈልግ ነው። ይህም ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጥ ሌላው ምክንያት ነው። አሁን በተያዘው በጅት አመት መጨረሻ ድረስ ዋና ዋና ስራዎቹን ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው አቶ ሳምሶን ያብራሩት ።
የሙከጡሪ-ኮከብ መስክ እና ኮከብ መስክ-ዓለም ከተማ ፕሮጀክት አካል የሆነው ኮከብ መስክ-ዓለም ከተማ የመንገድ ፕሮጀክት 47 ኪ.ሜ ርዝማኔ ያለው ሲሆን፣ በአስፓልት ደረጃ እየተገነባ ይገኛል። የግንባታ ወጪውም አንድ ቢሊየን ስድስት መቶ ዘጠና አምስት ሚሊየን ስድስት መቶ ሰማኒያ ስምንት ብር ሲሆን፤ የግንባታው ወጪ በኢትዮጵያ መንግስት ሙሉ ለሙሉ ይሸፈናል።
የመንገዱ መነሻ ኮከብ መስክ ቀበሌ ሲሆን፣ መረሃ-ቤተ ወረዳ ዓለም-ከተማ ላይ ያበቃል።
ፕሮጀክቱ የመንገዱ ትከሻን ጨምሮ በወረዳ 21 ሜትር፣ በከተማ 15 ሜትር በገጠር ደግሞ 10 ሜትር የጎን ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ ነው በመገንባት ላይ የሚገኘው። በ2012 ዓ.ም ነው የተጀመረው። ይህ የመንገድ ፕሮጀክት መስከረም 8 ቀን 2015 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ግብ ተቀምጦለታል።
መንገዱን እየገነባ የሚገኘው ቻይና እስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሊሚትድ ነው። የማማከርና ቁጥጥር ስራውን ደግሞ ቫሊዩ ኢንጂነሪንግ እያከናወነ ይገኛል። በእስካሁኑ የሥራ እንቅስቃሴ የዲዛይን ስራ፤ ቅየሳ ስራ፣ የአፈር ቆረጣ፤ ሙሌት፤ ጠረጋና ድልዳሎ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የአስተዳደሩ ዘገባ ያመላክታል ።
በዚህ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 3.5 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የአፈር ቆረጣ ያለው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የአፈር ቆረጣ ስራው ተጠናቋል። ቀጣዩም እየተከናወነ ነው። 105 ሜትር ርዝማኔ ያለው የጀማ ወንዝ ድልድይ የዚህ ፕሮጀክት የግንባታ አካል ነው። የጀማ ወንዝ ላይ ከሚገነባው ድልድይ በተጨማሪም ፕሮጀክቱ አራት ድልድዮችን፣ 126 የከልቨርቶች ስራንም በማካተት እየተሰራ መሆኑን የአስተዳደሩ መረጃ ያሳያል። የዚህ ፕሮጀክት መጠናቀቂያ ጊዜ ገና ቢሆንም፣ የወሰን ማስከበር ችግሮች አጋጥመዋል። የወሰን ማስከበር ችግሩ ተቋራጩ የኮንትራት ጊዜው እንዲራዘም ከወዲሁ ጥያቄ እንዲያቀርብ መንገድ ከፍቷል። ተቋራጩ ያቀረበው ጥያቄ ተገቢነት እየታየ ነው። ታይቶ ተገቢ መሆኑ ሲታመንበት ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠዋል። ካልሆነ ግን የግንባታ ሥራው በተያዘለት የጊዜ ገደብ አጠናቅቆ እንዲያስረክብ ይደረጋል።
አጠቃላይ ፕሮጀክቶቹ ተገንብተው ሲጠናቀቁ ሙከጡሪን ከእንሳሮ ወረዳና ከመርሃ ቤት ወረዳ ጋራ በቅርበት ያስተሳስራሉ። ፕሮጀክቶቹ የአካባቢ ልማት እና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ምቹ በማድረግ በአካባቢው የሚገኘውን እምቅ አቅም ለመጠቀም ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይታሰባል። ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎችን አሟጦ ለመጠቀም ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። አካባቢዎቹ የጤፍ ምርትን ጨምሮ በርካታ የአዝዕርት እህሎችን በማምረት የሚታወቁ በመሆናቸው አምራችን ከሸማች ጋር በማቀራረብ ግብይት ይበልጥ ያቀላጥፋል ።
ከመንገድ ግንባታው በቅርብ ርቀት ቡርቃ ወንዝ ላይ ከበልበሊት የመስኖ ግድብ ጋር በማስተሳሰር የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቱን ወደ መሃል ገበያ ለማድረስ ሁነኛ አበርክቶም ይኖረዋል። በተጨማሪም በአካባቢው የሚገኙትን በርካታ የቁም እንስሳት እና የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶችን በፍጥነት ወደ ገበያ ለማድረስ ያግዛል።
የሙከጡሪ-ኮከብ መስክ እና ኮከብ መስክ ዓለም ከተማ መንገዶችን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የወሰን ማስከበር ችግሮችን በዘላቂነት መቅረፍ ወሳኝ ነው። በቀጣይም የመንገድ ፕሮጀክቶች በወሰን ማስከበር ችግሮች ምክንያት እንዳይጓተቱ የወሰን ማስከበር ስራዎች የፕሮጀክቱ ግንባታ ከመጀመሩ አስቀድሞ የሚጠናቀቅበትን አካሄድ መከተል ያስፈልጋል። የወሰን ማስከበር ችግሮች ሳይቀረፉ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ማስጀመር መቆም ይኖርበታል።
ከዚህ ጎን ለጎን የመንገድ ፕሮጀክቶች ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገት የሚኖረውን የላቀ አስተዋጽኦ ከግምት በማስገባት ህብረተሰቡ ንብረቱን በወቅቱ በማስነሳት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል። ለራሱ ጥቅም የሚሰጠው የመንገድ ፕሮጀክት እንዲጓተት ምክንያት መሆን የለበትም። የካሳ ክፍያ በተፈጸመበት ማግስት ንብረቱን በማንሳት የመፍትሄ አካል ሊሆን ይገባል።
ወሰን የማስከበር ችግር ከግለሰቦች ባሻገር በመንግስት ድርጅቶች ዘንድም በግልጽ ይታያል። ለአብነት ያህል የውሃ መስመር፣ የቴሌ መስመሮች፣ የኤሌክትሪክ መስመሮች እና ስልክ መስመሮች በሚፈለገው ወቅት አለመነሳት ለመንገድ ግንባታ መጓተት ምክንያት መሆኑን የመንገዶች ባለስልጣን እና ኮንትራክተሮች ሲናገሩ ይደመጣል። እንዲህ ያሉ ችግሮች የቆዩና የቀጠሉ ናቸው። ተቋማቱ ለአንድ ዓላማ የሚንቀሳቀሱ እንደመሆናቸው ተናብበው ሥራውን የጋራ አድርገው መሥራት ይኖርባቸዋል። መልዕክታችን ነው።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29 /2014