በአገራችን ዋና ዋና ከተሞች በወር መጨረሻ አካባቢ ደመወዝ ወጣ አልወጣ እያሉ ሰራተኞች የሚጠያየቁትን ያህል ምን አልባትም ከዚያም በላይ በሌላ አንድ ትእይንት የወሩ መጨረሻ ሲታሰብ ይስተዋላል። ይህን ወቅት አንዳንዶች በጉጉት ሲጠብቁት ሌሎች ደግሞ በስጋት ይርዱበታል። መኪኖች በብዛት ተሰልፈው ተራ ሲጠብቁ የሚታዩበት ነው። ነዳጅ ለመቅዳት ወረፋ መያዝ።
ይህን ትእይንት በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የተንቀሳቀሰ ሁሉ ይመለከተዋል፤ በአገር አማንም ይህ እየሆነ ነው። የወሩ መጨረሻ የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ የሚከለስበት መሆኑን ተከትሎ ነው ይህ የሚሆነው። ብቻ ምን አለፋችሁ ነዳጅ ለመቅዳት በየወሩ ተራ መያዝ ተለምዷል።
የነዳጅ ዋጋ ሊጨምር ይችላል ከሚል ስጋት ነዳጅ ሽሚያው ይጦፋል። ሁሉም በመኪናው ሊያቁር፣ ህገ ወጦች በአንጻሩ ነዳጅ የለም፣ ዋጋ ይጨምራል ተብሏል፣ ወዘተ. እያሉ ከነዳጅ ማደያዎች ጋር እየተሻረኩ ነዳጅ በበርሜል፣ በጀርካን፣ በሌላም በሌላም መንገድ ሲያሸሹ ይታያሉ። እናም ይህ ወቅት በውድ ዋጋ የሚቸበችቡበት ህገወጥ ንግድ የሚያጦፉበት ነዳጅ የሚይዙበትና የሚሸጡበት አርገውታል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን መንግስት ከሁለት ወራት በኋላ በሚተገብረው የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ አሰራር ላይ ከትናንት በስቲያ በአዳማ ከተማ ለጋዜጠኞች ባዘጋጁት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ እንደተጠቆመው፤ አገሪቱ በውጭ ምንዛሬ ከውጭ የምታስገባውና ለዜጎች ከዓለም ዋጋ በእጅጉ ባነሰ ዋጋ እያደረሰች ያለችው ይህ ነዳጅ ለከፍተኛ ህገወጥ ንግድ ተዳርጓል።
የነዳጅ ማደያ በሌለባቸው አካባቢዎች ነዳጅ በተለያዩ መንገዶች ቢደርስ እኔ ብዙም ችግር አለው ብዬ አላስብም፤ ባለሀብቶች ወይም መንግስት እነዚህ አካባቢዎች ነዳጅ እንዲያገኙ ለማድረግ ማደያ ባልገነቡበት ሁኔታ እዚህ አካባቢ ያለውን ህገወጥነት መከላከልም ሊያስቸግርም ይችላል። ነዳጁ ለተጠቃሚው የሚሸጥበት ዋጋ ተጠቃሚውን በእጅጉ የሚጎዳ መሆኑ ላይ ነው የበለጠው ክፋቱ። ነዳጁ የሚጓጓዝበት፣ የሚከማችበትና የሚሸጥበት መንገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት አለመሆኑ ሌላው ችግር ቢሆንም የዛሬው ጉዳዬ አይደለምና አቆይቼዋለሁ።
ህገወጥ ግብይቱ እየተስፋፋ ያለበት ሁኔታ በእጅጉ አሳሳቢ እየሆነ ነው። ጥቂት በማይባሉ የአገሪቱ አካባቢዎች በቅርበት የነዳጅ ማደያዎች እያሉም ጭምር ነዳጅ ከማደያ ውጭ በየመንደሩ በውሃ መያዣ ፕላስቲክ ኮዳዎች ሳይቀር በአደባባይ በውድ ዋጋ መቸብቸቡ ግብይቱ ምን ያህል ህገወጥ እየሆነ መምጣቱን ያመለክታል።
አንድ ጓደኛዬ በቅርቡ ከአዲስ አበባ በስተምስራቅ አቅጣጫ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነዳጅ በሚገባበት መስመር ከዋናው መስመር ጥቂት ኪሎ ሜትሮችን ገባ ብሎ ለስራ ጉዳይ ተገኝቶ ነበር። በአንድ የጥቃቅን ንግድ ስፍራ በሚመስል ቦታ የታሸገ ውሃ እንዳለ አይቶ ለመግዛት ይጠይቃል፤ ውሃ እንደሌለ ይነገረዋል፤ ያ ታዲያ ምንድነው ሲል ቤኒዝን ይባላል፤ ሌላ ሰው እንዲሁ፣ እነዚህ መረጃዎች የነዳጅ ህገወጥ ግብይቱ ሄዶ ሄዶ የት እንደደረሰ ጥሩ ማሳያዎች ይሆናሉ።
በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ነዳጅ በጀርካን፣ በበርሜል ወዘተ እየተጓጓዘ መቸብቸብ ከጀመረ ቆይቷል፤ ይሄ ብዙም አዲስ አይደለም፤ አዲስ የሚሆነው እዚህም እዚያም በፕላስቲክ የውሃ ኮዳ ጭምር እየተፈጸመ መሆኑ ላይ ነው።
የነዳጅ ህገወጥ ግብይቱ በእዚህ ላይ ብቻ አላቆመም። በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ዋጋ ከጎረቤት አገሮች አንጻር ሲታይ በጣም ርካሽ መሆኑም ህገወጥነቱ ይበልጥ እንዲስፋፋና ወደ ኮንትሮባንድ ንግድ እንዲሸጋገር እያረገው ነው። ነዳጃችን ለኮንትሮባንዲስቶችም ተዳርጓል። ኮንትሮባንዲስቶች ይህን ነዳጅ፣ ነዳጅ በውድ ዋጋ ወደሚሸጥባቸው ጎረቤት አገሮች እያስወጡ ናቸው።
ሁኔታው ከመሀል አገር ወይም ነዳጅ ማደያዎች በስፋት ከሚገኙባቸው ከተሞች በበርሜል፣ በጀርኪን እየተገዛ ወደ ውጭ የሚላክበት ብቻ እንዳልሆነ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት። መቼም የነዳጅ ቦቴ እየተጠለፈ ነው ማለት ያስቸግራል። ተጠለፈም ሲባል ተሰምቶ አይታወቅም። ነዳጅ ለየማደያው የሚልከው የመንግስት አካል እንደመሆኑ በምንም መልኩ ማደያዎችም ካልተላከላቸው ቦቴ ነዳጅ አያወርዱም። ባለቦቴውም ያልተባለበት ቦታ ወስዶ ያራግፋል ተብሎ አይታሰብም። የሰነድ ርክክብም አለና።
የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ከትናንት በስቲያ ከሁለት ወራት በኋላ በሚጀመረው የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ ስርአት ላይ የሚመከር መድረክ ባካሄደበት ወቅት እንደተጠቆመው፤ በአገሪቱ የነዳጅ ማደያ ተደራሺነት ችግር በስፋት ይስተዋላል፣ በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢ የነዳጅ ማደያ የለም። በአሁኑ ወቅት ደግሞ እንደ ባጃጅ ያሉ ተሽከርካሪዎች በአገሪቱ በስፋት እየተንቀሳቀሱ እንደመሆናቸው ለእነዚህ ተሽከርካሪዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ ያስፈልጋል። በእዚህ ላይ እጥረት ሳይኖር እጥረት እንዳለ አድርገው የሚያናፍሱ፣ የነዳጅ ማጓጓዝ ሂደቱ መጠነኛ መጓተት ሲታይበት ትልቅ ችግር እንደተፈጠረ አድርገው የሚያናፍሱት ወሬ እና የመሳሰሉት በነዳጅ ግብይቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳረፉ ሲሆን፣ የነዳጅ ህገወጥ ግብይት እንዲጦፍ ምክንያት እየሆኑ ናቸው።
የነዳጅ ህገወጥ ግብይቱ የበለጠ እየጦፈ ይገኛል። የዚህ አንዱ ምክንያት ደግሞ ነዳጅ ወደ ውጭ አገር በኮንትሮባንድ እንዲወጣ እየተደረገ ያለበት ሁኔታ ነው። በውጭ ምንዛሬ ከውጭ እንዲገባ እየተደረገ፣ ህዝቡን ከኑሮ ውድነት ለመታደግ በሚል ከዓለም ገበያ ዋጋ በታች ለተጠቃሚ እንዲተላለፍ እየተደረገ ያለን ነዳጅ በህገወጥ መንገድ ወደ ውጭ አገር መላክ እየተለመደ መጥቷል።
ከፍ ብዬ እንደጠቀስኩት በአገሪቱ የነዳጅ ማደያ ተደራሽነት ችግር በስፋት ይስተዋላል። ከፍተኛ የትራፊክ እንቅስቃሴ ያላቸው እጅግ በርካታ ወረዳዎች የነዳጅ ማደያ እንደሌላቸው ይነገራል። በአንጻሩ ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት የሌላቸው አንዳንድ የጠረፍ አካባቢዎች ላይ ደግሞ ነዳጅ ማደያ በስፋት እየተገነባ መሆኑ ይገለጻል።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን በነዳጅ ግብይት የትርፍ ህዳግ በየጊዜው በማይስተካከልባትና ይህን ተከትሎ ባለነዳጅ ማደያዎች ሁሌም ቅሬታ እያነሱ፣ ይህም ለነዳጅ ማደያ መሰረተ ልማት አለመስፋፋት ዋና ችግር መሆኑ እየተገለጸ ባለበት ሁኔታ በእነዚህ አካባቢዎች የነዳጅ ማደያ በስፋት እየተገነባ ነው። የክልል መንግስታት በነዳጅ ማደያ ግንባታ ለሚሳተፉ ባለሀብቶች የመሬትና የመሳሰሉትን ማበረታቻዎች በማድረግ በነዳጅ ማደያ ተደራሽነት ላይ በትኩረት እንዲሰሩ ጥሪ እየቀረበ በአንጻሩ ብዙም የትራፊክ እንቅስቃሴ በሌላባቸው በተወሰኑ የአገሪቱ ጠርፍ አካባቢዎች የነዳጅ ማደያዎችን በስፋት እየተገነቡ ናቸው።
ይህ ለምን ሆነ ተብሎ ሲጠየቅ ነገሩ ወዲህ ነው እየተባለ ነው። ነገሩ “ይሄ ሙጃ አጨዳ ዱባ ለመስረቅ ነው” የሚለውን አባባል ያስታውሳል። ይህን ያህል ኢንቨስትመንት በእነዚህ ጠርፍ አካባቢዎች ስራ ላይ ማዋል በእርግጥም የሙጃ አጨዳው አይነት ነው። ማደያዎቹ እየተገነቡ ያሉት ነዳጅ በኮንትሮባንድ ወደ ጎረቤት አገሮች ለማሻገር ነው እየተባለ ነው። የሚገርም አፍራሽ ሂሳብ ነው።
ደግነቱ መንግስትም በዚህ ላይ ነቅቷል፤ ነብር አያኝ በሉ ብሏል። ለአካባቢው የሚያስፈልገው የነዳጅ መጠን ታውቆ ያ መጠን እንጂ በተከፈተው ማደያ ሁሉ ነዳጅ እንደማያስገባ አስታውቆ እየሰራ ነው። የህገወጦቹ ተግባር ግን አሁንም በጥንቃቄ መታየት ይኖርበታል።
መንግስት በቅርቡ የሚያደርገው የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ አሰራር በነዳጅ ዋጋ ላይ ተጥሎ የነበረውን ድጎማ ቀስ በቀስ በማንሳት የነዳጅ ዋጋው በዓለም ገበያ ዋጋ መሰረት እንዲከናወን ሲያደርግ በነዳጅ ላይ የሚታዩት እነዚህ ህገወጥ ተግባሮች ሊቆሙ እንደሚችሉ ይጠበቃል። እዚያው ድረስ ግን ችግሩ ግዙፍ አገራዊ ችግር እንደመሆኑ ቁጥጥርና ክትትሉ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29 /2014