ቤተ-እምነቶች ሰዎች ከፈጣሪያቸው ጋር በጸሎት የሚገናኙባቸው፣ ምህረትና ይቅርታ የሚጠየቅባቸው፣ ፍቅርና ሰላም የሚሰበክባቸው፣ ቅዱስ ሥፍራዎች ስለሆኑ በምእመናን ዘንድ ልዩ ክብርና ሞገስ አላቸው። ምእመናን ወደ ቤተ እምነት ቅጥር ግቢ ውስጥ ሲገቡ ጸሎታቸው ወደ ፈጣሪያቸው እንዲያደርሱ ልባቸውን ከሀጽያት ከበደልና ከክፋት አንጽተው ነው። አንዳንዶችም የእግራቸውን ጫማ ሳይቀር አውልቀው፤ እንደየ ሃይማኖታቸው አስተምህሮ ለብሰው ለጸሎት ይሰየሙባቸዋል። በየትኛውም ሃይማኖት ስር ያሉ ምእመናን ግባቸው ጽድቅን ማግኘት ስለሆነ ፈጣሪ የሚወደውን መልካም ሥራ ይሠራሉ።
በአገራችን ብሂል ‹‹ሳል ይዞ ስርቆት፤ ቂም ይዞ ጸሎት›› ይባላልና ሰዎች ወደ ቤተ-አምልኮ ሲሄዱ ተጣልተው ከሆነ ይታረቃሉ፣ በድለው ከሆነ ሀጥያታቸውን ተናዘው ንስሃ በመግባት ልባቸውን አንጽተው “አዲስ” ሰው ይሆናሉ።
ቤተ-እምነቶች መለኮታዊ ሀሳብ ብቻ የሚከናወንባቸው ቦታዎች በመሆናቸው ጸብና ግርግር፤ ዋዛና ፈዛዛ አይስተናጋድባቸውም። በጸሎት ሰዓት አማኞች ለፈጣሪያቸው ምስጋናና ክብር ያቀርቡባቸዋል፤ በመከራ ጊዜ ይሸሸጉባቸዋል። በርካታ ሰዎች በመስጊዶችና በቤተክርስቲያን ሥር እየተጠለሉ የገጠሟቸውን ክፉ ጊዜዎች አሳልፈዋል።
ቤተ-እምነቶች የምህረትና ይቅርታ የሚጠየቅባቸው ቦታዎች እንደመሆናቸው ሰዎች በደል ፈጽመው እንኳ ቢሆን ሸሽተው ወደ ቅጥር ገቢው ውስጥ ከገቡ በፈጣሪ እቅፍ ውስጥ እንዳሉ ስለሚቆጠር ደፍሮ ጥቃት የሚሰነዝርባቸው አካል አይኖርም። ይህ ከጥንት ጀምሮ የነበረና ዛሬም ያለ ሃይማኖታዊ እሴት ነው።
ከሰሞኑ ታዲያ ከሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻችን ያፈነገጡ ጸያፍ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ተመልክተናል። መስኪዶችና ቤተክርስቲያኖች ብዙዎችን በጉያቸው ይዘው እንዳልታደጉ ዛሬ እንደቀላል ነገር ድፍረት በተሞላበት መንገድ ሲቃጠሉ እያየን ነው። ያም ብቻ አይደለም፣ አትግደል የሚለውን የፈጣሪ ቃል ሲማር የኖረ ሃይማኖተኛ በውይይት መፈታት የሚችለውን እዚህ ግባ የማይባል ጉዳይ እያራገበ የገዛ ወንድሙን ሲገድል እየተመለከትን ነው።
ለመሆኑ ሃይማኖተኛ ሆኖ በሌላ ሃይማኖት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን መፈጸም ምን ያህል ከሃይማኖቶች አስተምህሮ ጋር አብሮ ይሄዳል? እንዲህ አይነቱ አድራጎት በአገር ሰላምና አንድነት ላይ ምን ተጽዕኖ ይፈጥራል? አገርን ለማፍረስ የተዶለተውን ሴራ ለማክሽፍ ከሃይማኖት አባቶችና ከምእመናን ምን ይጠበቃል? የሚሉትንና ሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ ከኦርቶዶክስ ክርስትና እና ከእስልምና አባቶች ጋር ያደረግነውን ቆይታ በዛሬው የ‹‹አገርኛ›› አምድ ዝግጅታችን ይዘን ቀርበናል። መልካም ንባብ ይሁንላችሁ።
መጋቤ ካህናት አባ ሃብተጊዮርጊስ አሥራት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የገዳማት መምሪያ ዋና ሃላፊ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት ቤተክርስቲያንና መስኪድ ከተቋቋሙበት ዓላማ አንጻር አንድ ናቸው። ሁለቱም እንደየ ሃይማኖታቸው አስተምህሮ ተከታዮቻቸው ሰማያዊውን ጸጋ ለማግኘት ቃልን የሚሰሙባቸው፣ የሚጸልዩባቸው፣ የሚሰግዱባቸው ሥፋራዎች ናቸው። ሁለቱም ሃይማኖቶች “ወንድም ወንድሙን አይበድል” ብለው ያስተምራሉ ይላሉ። መዋደድ፣ መተዛዘን፣ መደጋገፍ ሁለቱም ሃይማናቶች ከሚጋሯቸው እሴቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
ሰሞኑን በጎንደርና በወራቤ አካባቢ ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ግጭት መፈጠሩ የሚያሳዝን ነው፤ በሰው ህይወትና በሃይማኖት ተቋማት ላይ ጉዳት አስከትሏል። እንደርሳቸው አባባል የሃይማኖት ሰዎች በዚህ ልክ ግጭት ይፈጥራሉ የሚል እምነት የላቸውም። ከግጭቱ ጀርባ የፖለቲከኞች እጅ አለበት ባይ ናቸው።
የሃይማኖት ተቋማትና ምእመናንን ኢላማ ያደረጉ የፖለቲካ ነጋዴዎች በሚፈጥሩት ሴራ፤ አንዳንዶቹ ተልእኮ ይዘው ሌሎችም ሁኔታው ሳይገባቸው ግጭት እየፈጠሩ ለዘመናት ተከባብሮ የኖረው ምእመን እንዳይተማመን የማድረግ ሥራ እየሠሩ ናቸው።
የፖለቲካው ጉዳይ የሚቀጣጠለው የሃይማኖት ጦርነት ስናስነሳ ነው በሚል አስልተው፣ አቅደውና ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ስላሉ ነው። እነዚህ ጥቂት ሰዎች የብዙኋኑን የልብ ትርታ እያዳመጡ ለስሜቱ ስስ የሆኑ ጉዳዮችን በመነካካት ትርምስ እንዲፈጠር እየጣሩ ናቸው። ያ ባይሆን ኖሮ ጎንደር ላይ የተቀሰቀሰው ግጭት በቀላሉ በተፈታ ነበር፡፡
ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት ጉዳይ የጎላ ልዩነት አይፈጥርብንም፤ ሙስሊምና ክርስቲያን በማህበራዊ ህይወታችን ተለያይተን አናውቅም። ሀዘንና ደስታን እየተጋራን ብዙ ዓመታትን አብረን ኖረናል፤ ይህ ወደ ፊትም የሚቀጥል ነው።
ቤተክርስቲያኖች ሲሰሩ ሙስሊሙ በገንዘብም በጉልበትም ይረዳል፤ መስኪዶችም ሲሰሩ ክርስቲያኑ እንደዚያው ይረዳል፤ ዛሬ እሚቃጠሉ ቤተ-እምነቶች የአንድ እምነት ተከታዮች ብቻ የሠሯቸው አይደሉም፤ ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች በመስጊዶች መቃጠል ይቆጫሉ እንጂ አይደሰቱም፤ እውነተኛ ሙስሊሞችም በቤተክርስቲያኖች መቃጠል ያዝናሉ እንጂ አይደሰቱም።
ተቃቅፎና ተደጋግፎ እዚህ የደረሰ ማህበረሰብ ዛሬ የፖለቲካ ሴረኞች በሰሩት ደባ ሊለያይ አይችልም። ምእመኑ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያን የማፈራረስ ሴራ አንግበው የሁለቱን ታላላቅ ሃይማኖት ተከታዮች ለማባላት ተግተው እየሠሩ መሆኑን መረዳት ይኖርበታል።
አለመግባባትና ግጭት በተፈጠረ ቁጥር ሃይማኖታዊ መልክ እያስያዙ ቤተክርስቲያንና መስጊድን መቃጠል ኢትዮጵያን ወደ ከፋ ትርምስ ለማስገባት የታሰበ የፖለቲከኞች አሻጥር መሆኑን ምእመኑ በሚገባ መረዳት ይኖርበታል።
ጎንደር የተፈጸመው ድርጊት እንደ ሰብዓዊ ፍጥረትም እንደ ባለሃይማኖትም ያሳዝናል፤ ያሳፍራልም። ችግሩን እዚያው መፍታት ሲቻል ሌላ ቦታ ሄዶ አጸፋ መስጠት ግን ጉዳዩን ለማባባስ እና ለማስፋፋት ካልሆነ በስተቀር መፍትሄ አይሆንም።
ስህተቱን ማረም እንጂ ስህተቱን በስህተት መድገም ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ አይደለም። ፈጣሪ የሚወደው ቂምና በቀልን ሳይሆን ሰላምና ፍቅርን ነው። ሁላችንም የአዳምና የሄዋን ልጆች ነን። እርስ በእርሳችን የምንጋጭ ይመስለናል እንጂ ግብ ግብ የያዝነው ከፈጣሪችን ጋር ነው። ምክንያቱም የሚቃጠሉት ቤተ-እምነቶች ፈጣሪ የሚመሰገንባቸው ናቸው። ሰው ፈጣሪውን የሚያመሰግን እንጂ የሚያሳድድ መሆን የለበትም።
የሚቃጠሉትን ቤተ-እምነቶች ነገ የሁለቱም እምነት ተከታዮች ተባብረው ይሠሯቸዋል እንጂ መስኪድ በተቃጠለበት ቦታ ላይ ቤተክርስቲያን አይሠራበትም፤ ቤተክርስቲያን በተቃጠለበት ቦታ ላይም መስጊድ አይሠራበትም።
መተኪያ የማይገኝለት ክቡር የሆነው የሰውልጅ ነፍስን ግን መመለስ አይቻልም። “አትግደል” የሚል ሃይማኖት እየተከተሉ ነፍስ ማጥፋት ፍጹም ሀጥያት ነው። እውነተኛ የሀይማኖት ሰው ወንድሙን አይጠላም፤ አይገድልም፤ ቤተ እምነትን አያቃጥልም፡፡
ቤተክርስቲያንና መስጊድ የጸሎት ቦታ ብቻ ሳይሆኑ ችግረኞች የሚረዱባቸውና የሚሸሸጉባቸውም ጭምር ናቸው። መጋቤ ካህናት አባ ሃብተጊዮርጊስ ቀደም ሲል ስለተከሰተ አንድ ጉዳይ የሰሙትን እንዲህ ይናገራሉ ‹‹መርካቶ የሚገኘው ራጉኤል ቤተክርስቲያን መጀመሪያ የነበረው እንጦጦ አካባቢ ነበር፤ ታቦቱ ከእንጦጦ ተነስቶ መርካቶ ሲገባ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ አለመግባባት ይፈጠራል። ጉዳዩ አንድ፣ ሁለት እያለ ወደ ጸብ ያድግና እዚያው መርካቶ በርካታ ሰዎች ሆነው የተወሰኑ ሰዎችን ማጥቃት ይጀምራሉ። በዚህን ጊዜ ጥቃቱ የበረታባቸው ሰዎች ወደ አንዋር መስጊድ ዘለው ይገባሉ። በወቅቱ መስጊዱ ውስጥ የነበሩ ኢማሞች ሸሽቶ መስጊድ የገባ ሰው አይነካም›› ብለው እንደታደጓቸው መስማታቸውን ነግረውናል። ቤተክርስቲያንም ይሁን መስጊድ ሰዎች ከሚያሳድዷቸው ጠላቶቻቸው ሸሽተው የሚሸሸጉባቸው ናቸው። ለሰዎች ጥላ ከለላ ናቸው። እንደ ሃይማኖታዊ እሴታችን ሸሽቶ በሃይማኖት ተቋማት ቅጥር ግቢ የገባ ሰው ማንም አንቆ አያወጣውም። ዛሬ ቤተ-እምነቶች ለሌሎች ጠባቂ መሆናቸው ተረስቶ ሲቃጠሉ መመልከት ያሳፍራል። አባቶቻችንን ያቆዩልንን እሴቶች ብናከብር አለመግባባትና ግጭቶችን መቆጣጠር እንችላለን።
ወጣቶች ሌላ ሀገር የላችሁምና ለአባቶቻችን እሴቶች ዋጋ ስጡ፤ በስሜት ተነሳስታችሁ ነገ የሚጸጽታችሁን መጥፎ ሥራ አትስሩ፤ በተለይም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰራጩ ግጭት አባባሽ ምስሎችና መልእክቶችን እያያችሁ አገርን ለማፈራረስ ቀን ከሌት ለሚተጉ አካላት መሳሪያ አትሁኑ። እኛ ኢትዮጵያውያን ተዋልደን፣ ተዛምደን፣ ተጋምደን ያለን ህዝቦች ነን፤ ንቁ፤ ብልህ ሁኑ፤ በጥበብ ተጓዙ›› ብለዋል መጋቤ ካህናት አባ ሃብተጊዮርጊስ፡፡
ሌላው የግል አስተየታቸውን የሰጡን ሼህ ሙሃመድ አሊ ሙሳ ናቸው። ነዋሪነታቸው አዲስ አበባ፣ አራዳ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ ሁለት ነው። እንደ እርሳቸው አባባል ሁሉም ሰው መነሻው አደምና ሃዋን ናቸው። ሰው በጊዜ ሂደት በገባውና በተረዳው መንገድ እንደየራሱ ሃይማኖት ፈጣሪውን ያመልካል። ሙስሊምም ክርስቲያንም በሃይማኖት ይለያዩ እንጂ የሚገዙት ለአንድ ፈጣሪ ነው። ሁሉም ጀነት ለመግባት ፈጣሪ የሚወደውን በጎ ሥራ ይሠራል። ፈጣሪ ክፋትን አይወድም፤ ክፋትን እየሠሩ ሃይማኖተኛ መሆን አይቻልም። ፈጣሪ የሚወደው መረዳዳትን፣ መተጋጋዝን፣ መዋደድን ነው፡፡
አባቶቻችን የሃይማኖት ልዩነታቸውን ጠብቀው በመከባበር በመተዛዘንና በመደጋገፍ ዘመናትን አሳልፈው አገር አስረክበውናል። ሼህ ሙሃመድ አሊ ሙሳ የጥንቶቹ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች ፍቅራቸውን ለመግለጽ አደረጉ ስለተባለው አንድ ጉዳይ የሰሙትን እንዲህ ይናገራሉ።
‹‹ሙስሊምና ክርስቲያን በዋና ሃይማታዊ ጉዳዮቻቸው ቢለያዩም በብዙ ነገሮች ይመሳሰላሉ። ልዩነታቸውንና አንድነታቸውን የገለጹበት መንገድ እንዲህ ነው። ሁለቱም የየራሳቸውን ከብት ባርከው ካረዱ በኋላ በተለያየ ክር እያሠሩ በአንድ እቃ ይቀቅሉታል። ከዚያም ሲበስል አውጥተው የየራሳቸውን ይመገባሉ። እንግዲህ ስጋው አንድ ላይ ሲቀቀል በመረቁ መነካካቱ አይቀርም፤ በማህበራዊ ህይወታቸው ብዙ የሚጋሯቸው ነገሮች እንዳሉ ጥሩ ማሳያ ነው። ልዩነትንም አንድነትም አክብሮ መኖር እንደሚቻል በምሳሌ ያረጋገጡበት ነው። አሁን የሚመጣው ትውልድ የቀደሙት አባቶቹ እንዴት ተስማምተውና ተከባብረው እንደሚኖሩ መረዳት አለበት።
እኔ የምኖረው አዲስ አበባ ቢሆንም ተወልጄ ያደግሁት በድሮው ወሎ ክፍለ ሀገር ነው። ወሎ ሙስሊምና ክርስቲያን በአንድ ቤት ውስጥ ይኖራሉ። የአንድ ቤተሰብ አባላት ግማሹ ሙስሊም ግማሹ ክርስቲያን የሚሆንበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ለምሳሌ ስለ እኔ ልንገርህ፤ የመጀመሪያው ልጄ ክርስቲያን ነው። በሃይማኖት ብንለያይም የእርሱ ልጅነት የእኔ አባትነት የሚካድ አይደለም። ታዲያ ማ ማንን ነው የሚያጠቃው፤ እንዲህ ወደ ኋላ እየሄድን ብንመለከት የዓለም ህዝብ በሙሉ የዘር ግንዱ አንድ ነው። ሰው ከሃይማኖት በፊት የነበረ ታላቅ ፍጥረት ነው፤ ሃይማኖት አንዱ ዓላማው ሰው በሰላምና በፍቅር እንዲኖር መጠበቅ ነው።
የሃይማኖት አባቶች ወጣቱን በመምከርና በመገሰጽ በስሜት እየተገፋፉ የሚፈጽማቸውን ድርጊቶች ማስቆም ይኖርባቸዋል። እንዲህ አይነቱ መጥፎ ድርጊት ለአገር አንድነትም ይሁን ለእድገት ጥሩ ስለማይሆን ወጣቶቻችን አገራቸው እንዳትበታተን አስተውለው መጓዝ ይኖርባቸዋል። ጎንደር የተፈጸመውን ድርጊት ሁላችንም አውግዘናል። ነገር ግን ያንን ምክንያት በማድረግ ወራቤ ላይ ቤተክርስቲያኖችን ማቃጠል ችግሩን ከማባባስ ውጭ መፍትሄ አይሆንም። መፍሄው በፍቅር፣ በመከባበርና በመቻቻል መኖር ብቻ ነው፡፡
የሃይማኖት አባቶች ወጣቶችን እየሰበሰቡ ማስተማርና መምከር እንደ ድሯችን ተከባብረንና ተመካክረን እንድናድር ማድረግ ይኖርባቸዋል። መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላትም ችግር ከመድረሱ በፊት ፈጥኖ በመድረስ አጥፊዎችን እየተከታተሉ ርምጃ መውሰድ (ለህግ ማቅረብ) ይኖርባቸዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 /2014