ጠረን ጉልበተኛ ነው:: በተለይም የሰውነት ጠረን በስሜትም በአመለካከትም ላይ ያለው ተጽእኖ ቀላል የሚባል አይደለም:: ሁሉም ሰው የሚታይ ብቻ ሳይሆን የሚያውድ ውበት እንዲኖረው ይፈልጋል:: አይነ ግቡ መሆን ብቻ ሳይሆን ከሩቅ የሚጠራ ጠረን መያዝ የሁሉም ሰው ፍላጎት ነው:: ለዚህም ሲባል ሁሉም ሰው መልካም መአዛ ያለውን ነገር በሙሉ ይጠቀማል:: ከነዚህ መልካም ጠረን ከሚፈጥሩ ግብአቶች ዋነኛው ሽቶ ነው::
ሽቶ ረዥም ታሪክ ያለው የውበት ግብአት ነው:: ለመጀመሪያ ጊዜ ሽቶ መጠቀም የጀመሩት ጥንታውያን ግብጻውያን ናቸው:: ሽቶን የሰሩበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ለአማልክት ለሚያቀርቡት መስዋእት እንዲሆን ነበር:: ስለዚህም ሽቶ በቀላሉ የሚገኝ እና ተራው ህዝብ ሁሉ የሚጠቀመው ነገር አልነበረም:: ቅድሚያ ለአማልክቱ ፤ ከዚያ ለመኳንንቱ ፤ ከዚያ ለባለጸጎቹ ነው የተፈቀደው::
ቀደምቶቹ ስልጣኔዎች ከሚገበያዩቸው ነገሮች መካከል ዋነኛውም ሽቶ ነው:: በተለይ ምስራቃውያኑ የህንድ ፤ የቻይና ፤ የአረብ ስልጣኔዎች በሽቶ ምርት ቀዳሚ ናቸው:: ተራውም ህዝብ ቢሆን ግን የራሱን ጠረን የሚያሳምርበት ሽቶ ለማምረት አልሰነፈም::
በየሀገሩ የተለያየ አይነት ህዝባዊ የጠረን ማሳመሪያ ተፈጥሯል:: በእኛም ሀገር ሰዎች የሰውነታቸውን ጠረን ለማሳመር የተለያዩ አይነት ግብአቶችን ይጠቀማሉ:: ነገር ግን ባህላዊ መዋቢዎች እየቀሩ በፋብሪካ የተመረተ ሽቶ በብዛት ጥቅም ላይ መዋል ከጀመረ ቆይቷል:: የሽቶ ገበያውም እየሰፋ እና ተጠቃሚውም እየበረከተ ይገኛል::
በአለም አቀፍ ደረጃ የሽቶ ገበያ ሽቅብ እየተመዝገዘገ ነው:: መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በአለም አቀፍ ደረጃ ባለፈው የፈረንጆች አመት (2021) በአለም ላይ ለሽቶ ወጪ የተደረገው ገንዘብ መጠን 33 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ነው:: ይህ አሀዝ ከ2022 እስክ 2027 እ.ኤ.አ በአመት የ6 ነጥብ
7 በመቶ እድገት እስመዘገበ ሄዶ በፈረንጆቹ 2027 በአለም ላይ በአመት ለሽቶ ግዢ ይውላል ተብሎ የሚጠበቀው ገንዘብ 47 ቢሊየን ዶላር ያደርሰዋል ተብሎ ይገመታል::
ለዚህ እድገት ዋነኛ መነሻው የወጣቶች መበራከት እና የሰዎች የአኗኗር ስልት ወደ ቅንጦት ያዘነበለ መሆን ተጠቃሽ ነው:: የሰዎች ኑሮ መሻሻል ፤ የከተሜነት መስፋፋት እና ለጤና እና ውበት የሚሰጡት ትኩረት መጨመር የሽቶ ገበያውን ተፈላጊ እያደረገው እንደሚቀጥልም ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት::
ከተለያዩ ተፈጥሯዊ ነገሮች የሚሰራው ሽቶ በስሙ አንድ አይነት ይሁን እንጂ በአይነቱ ግን ብዙ ነው:: አንዳኛው ከሌላኛው የሚለዩት በሰውነት ላይ ጠረናቸው በሚቆይበት ሰአት መጠን ሲሆን በአይነትም ዋነኞቹ 5 ናቸው::
እነሱም የመጀመሪያው ፐርፊዩም ወይም ንጹህ ሽቶ የሚባለው ነው:: ይህ የሽቶ አይነት የአልኮል መጠኑ ዝቅተኛ የመልካም ጠረን ፈጣሪ ቅመሞቹ ክምችትም ከ20 እስከ 30 በመቶ የሚደርስ ሲሆን ከተቀቡት በኋላም በሰውነት ላይ ጠረኑ እስከ 10 ሰአት የሚቆይ ነው:: በተለይም ቆዳቸው ስስ ለሆኑ ሰዎች ይህ ሽቶ የአልኮል መጠኑ አነስተኛ በመሆኑ ይስማማቸዋል::
ሁለተኛው የሽቶ አይነት ዩ ደ ፐርፊዩም የሚባል ሲሆን፣ ይህ አይነቱ ሽቶ የመልካም ጠረን ፈጣሪ ጠረን ፈጣሪ ቅመሞቹ ክምችት ከ15 እስከ 20 በመቶ ብቻ ነው:: በተለይ ለልብስ የሚሆን ነው:: ለአዘቦት ቀን በተለይ የሚሆነው ይህ ሽቶ ጠረኑ ሳይጠፋ እስከ 8 ሰአት የመቆየት አቅም አለው::
ሶስተኛ ዩ ደ ቶይለት የሚባል ሲሆን ክምችቱ ከ5 እስከ 15 በመቶ ብቻ ነው:: ለእለት ተእለት እንቅስቃሴ ጥቅም ላይ የሚውል ነው::
አራተኛው የሽቶ አይነት ኮሎኝ ይባላል:: መለያውም ከሌሎቹ ተለቅ ባለ እቃ መመረቱ ነው:: ጥሩ ጠረን ለመፍጠር በርከት አድርጎ መቀባትን ይፈልጋል:: ጠረን ፈጣሪ ቅመሞቹ ክምችት ከ2 እስከ 5 በመቶ ብቻ ነው:: በሰውነት ላይ ቢበዛ ሊቆይ የሚችለው ለ2 ሰአታት ብቻ ነው:: የአልኮል መጠኑ ከፍተኛ መሆን ስስ ቆዳ ባላቸው ሰዎች ዘንድ ተመራጭ እንዳይሆን ያደርገዋል:: አምስተኛው የሽቶ አይነት ዩ ፍራይች ይባላል:: ጠንካራ ጠረን ለማይወዱ ሰዎች ተስማሚ ነው::
ሽቶዎቹ በገበያ ላይ ያላቸው ድርሻ በጠራታቸው ቅደም ተከተል ሲሆን ፣ፐርፊዩም 40 በመቶውን ሽያጭ ይይዛል:: በጾታ አንጻር ሲታይ ሴቶች ዋነኛ የሽቶ ሸመቾች ሲሆኑ፣ እስከ 60 በመቶ የሚሆነውን ግዢ የሚፈጽሙት እነሱው ናቸው::
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ በተለይ በምእራቡ አለም ሴቶች በየወሩ በሚባል ደረጃ አዲስ ሽቶ ይገዛሉ፤ ወንዶች በአንጻሩ በአመት አንዴ ወይም ሁለቴ ሽቶ ሊገዙ ቢችሉ ነው:: በዚህም የተነሳ የሽቶ አምራቾች ለሴት ደንበኞቻቸው አዳዲሰ ምርቶችን በማስተዋወቅ ተጠምደዋል::
አይማርክ ግሩፕ ድረገጽ በኖቬምበር 2019 ባወጣው መረጃ መሰረት ዋነኞቹ የሽቶ አምራቾች በቢሊየን የሚቆጠሩ ዶላሮች የሚያንቀሳቅሱ ሲሆን፣ ዋነኞቹ አምስት ድርጅቶች የሚከተሉት ናቸው:: ኤቮን ፕሮዳክትስ ይባላል:: መቀመጫውን ለንደን ያደረገው ይህ ድርጅት በ1886 እ.ኤ.አ የተቋቋመ ሲሆን፣ ምርቶቹ እስከ 70 በሚደርሱ አለም ሀገራት ተደራሽ ናቸው::
ከሽቶ ንግድ በተጨማሪ በሌሎች የፋሽን ዘርፎች ላይም የተሰማራው ይህ ድርጅት 23 ሺ ሰራተኞች አሉት፤ በ2018 እ.ኤ.አ ያገኘው አመታዊ ገቢም 5 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ገደማ ነው::
መቀመጫውን ፈረንሳይ ያደረገው እና በ1910 እ.ኤ.አ የተቋቋመው ቻኔል ሌላኛው ግዙፍ ሽቶ አምራች ነው:: ሽቶን ጨምሮ በርካታ ምርቶችን የሚነግደው ይህ ድርጅት በ2018 ብቻ አመታዊ 11 ቢሊየን ዶላር ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ በመላው አለም 25ሺ ሰራተኞች አሉት::
በ1904 ኒውዮርክ ውስጥ የተቋቋመው ኮቲ በ46 ሀገራት ይሰራል፤ 20ሺ ሰራተኞች ቀጣሪው ኮቲ አመታዊ ገቢው በ2018 እ.ኤ.አ ብቻ 9 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር በላይ ነበር::
ሎሬአል ሌላኛው ግዙፍ የሽቶ አምራች ድርጅት ነው:: መቀመጫውን ፈረንሳይ ያደረገው ይህ ድርጅት በ2018 ብቻ አመታዊ ገቢው 30 ቢሊየን ዶላር ገደማ ነበር:: በ150 ሀገራት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ምርቶቹን የሚያከፋፍለው ሎሬአል 36ሺ ሰራተኞች አሉት::
በእድሜም አንጋፋ በገቢም ከፍተኛ ባለ ብዙ ሰራተኛው የሽቶ አምራች ኤል ቪ ኤም ኤች ይባላል:: በ2018 ብቻ 156 ሺ ሰራተኞች እና 4590 ሱቆች የነበሩት ይህ ድርጅት ያስገባው ገቢ 51 ቢሊየን ዶላር ነበር::
እንግዲህ እነዚህ ድርጅቶች በ2018 ብቻ ያስገቡት ገቢ ከ115 ቢሊየን ዶላር በላይ ሲሆን፣ የሌሎች የፋሽን ምርቶቻቸው ሽያጭ ተቀንሶ በሽቶ ንግድ ብቻ ያስገቡት ገቢ ከ25 ቢሊየን ዶላር በላይ ነው::
አቤል ገ/ኪዳን