ከዓመታዊው የአትሌቲክስ ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነውና በአትሌቶች ዘንድ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ዳይመንድ ሊግ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ይጀመራል። በአውሮፓ፣ እስያ እና አፍሪካ ባሉ 14 የዓለም ከተሞች እየተዘዋወረ የሚደረገውና ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ዝነኛ አትሌቶችን የሚያሳትፈው ውድድሩ በኳታሯ ዶሃ ነው የሚጀመረው። አምስት ወራትን በሚሸፍነው በዚህ ውድድር ላይ ለ13 ጊዜያት በማሸነፍ ከፍተኛውን ነጥብ መሰብሰብ የቻለ አትሌት በዙሪኩ የመጨረሻው ውድድር የዳይመንድ አሸናፊ ይሆናል።
በቀናት ልዩነት በተለያዩ ከተሞች የሚደረገው የአንድ ቀን ውድድር ከኳታር ወደ በርሚንግሃም ተሻግሮ የሚደረግ ሲሆን፤ ሦስተኛው ደግሞ በአሜሪካዋ ዩጂን ይካሄዳል። አገሪቷ (አሜሪካ) ከአንድ ወር በኋላ በስፖርቱ ቁጥር አንድ የሆነውን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የምታዘጋጅ መሆኗ ይታወቃል። በመሆኑም በዳይመንድ ሊጉ ተካፋይ የሆኑ አትሌቶች እንዲሁም ስፖርቱን በበላይነት የሚመራው የዓለም አትሌቲክስ የአሜሪካንን ዝግጅት ለመመልከትና ለመፈተሽ የሚችልበትን ሁኔታ እንደሚያመቻችም ከወዲሁ ይጠበቃል።
ከዚያ በኋላም ምርጦቹ አትሌቶች በራባት፣ ሮም፣ ኦስሎ፣ ፓሪስ እና ስቶክሆልም ከተሞች በወጣላቸው መርሃ ግብር መሠረት ውድድራቸውን የሚቀጥሉ ይሆናል። ነገር ግን አገራት ምርጥ አትሌቶቻቸውን የሚያፋልሙበትና ለረጅም ጊዜ በዝግጅት ላይ የቆዩ አትሌቶች የዓለም ቁጥር አንድ አትሌትነት ክብርን ለመቀዳጀት ጥረት የሚያደርጉበት የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የሚካሄድ በመሆኑ ዳመንድ ሊጉ ለአንድ ወር ያህል ተቋርጦ ይቆያል።
ከቻምፒዮናው መጠናቀቅ ስድስት ቀናት በኋላም ዳይመንድ ሊጉ ወደ እስያ አህጉር በማምራት ወደ ውድድር ይመለሳል። ሻንጋይ እአአ ከ2019 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አዘጋጅነቷ በመመለስ ውድድሩን የምታስተናግድ መሆኑን የዓለም አትሌቲክስ በዘገባው አስነብቧል። ከስድስት ቀናት በኋላም ወደ አገሪቷ ሌላኛዋ ከተማ አስተናጋጅነቱን በማሸጋገር በአዲሲቷ የዳይመንድ ሊግ ውድድር አዘጋጅ ሺንዚን ይደረጋል። ውድድሩ በድጋሚ ወደ አውሮፓ ተመልሶም በሞናኮ፣ ሉዛን እና ብራሰልስ ቆይታውን በማድረግም በስዊዘርላንድ ዙሪክ መደምደሚያውን ያደርጋል።
በዚህ ውድድር ላይም ባለፈው ዓመት በተካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ቻምፒዮን የሆኑ እንዲሁም በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮናው ምርጥ ብቃታቸውን ያሳዩ አትሌቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑበት ይጠበቃል። በተለይም ይህ ዓመት የዓለም ቻምፒዮና የሚካሄድበት እንደመሆኑ አትሌቶች አገራቸውን በመድረኩ ለመወከል እንዲያስችላቸው ያሉበትን አቋም በዳይመንድ ሊጉ ለማሳየት ይረዳቸዋል። ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የዓለም ከዋክብት አትሌቶች በዳይመንድ ሊጉ እንደሚካፈሉ ማረጋገጣቸውን አዘጋጆቹ አመላክተዋል።
የዓለም አትሌቲክስ የዘንድሮው ዳይመንድ ሊግ አሸናፊ ይሆናሉ በሚል ተጠባቂ ካላቸው አትሌቶች መካከል ኢትዮጵያውያኑ ወጣት አትሌቶች ለተሰንበት ግደይ እና ሳሙኤል ተፈራ ተካተዋል። የኦሊምፒክ ነሐስ እና የዓለም ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ ባለቤቷ አትሌት ለተሰንበት፤ በምትታወቅበት የ5ሺ እና 10ሺ ሜትር እንዲሁም በግማሽ ማራቶን ርቀቶች የክብረወሰን ባለቤት መሆኗ ይታወቃል። ይሁንና በእነዚህ ርቀቶች ውድድር የማይካሄድ መሆኑን ተከትሎ የመም ውድድር በሆነው የአንድ ሰዓት ውድድር ተሳታፊ እንደምትሆን የውድድሩ አዘጋጆች አረጋግጠዋል።
የ1ሺ500 ሜትር ርቀት አትሌት የሆነው ሳሙኤል ተፈራ በዳይመንድ ሊጉ ስኬታማ ይሆናሉ በሚል ከፍተኛውን ቅድመ ግምት ካገኙት አትሌቶች መካከል አንዱ ሆኗል። አትሌቱ እአአ በ2018ቱ የበርሚንግሃም የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና አሸናፊ በመሆን ወደ ምርጥ አትሌቶች ምድብ የተቀላቀለ ሲሆን፤ በቀጣዩ ዓመትም በርቀቱ የዓለም ክብረወሰን በማስመዝገብ ተስፋ የተጣለበት ወጣት መሆኑን ማስመስከሩ ይታወሳል።
በዚያው ዓመት በዶሃ የዓለም ቻምፒዮና አገሩን ቢወክልም በገጠመው ጉዳት ምክንያት ውድድሩን ለማቋረጥ ተገዷል። በቶኪዮው ኦሊምፒክም በተመሳሳይ ጉዳት የደረሰበት በመሆኑ እንደተጠበቀው ውጤታማ አልነበረም። በቅርቡ በቤልግሬድ በተካሄደው የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ግን አትሌቱ ወደ ቀደመ አቋሙ መመለሱን በሚያረጋግጥ ሁኔታ የወርቅ ሜዳሊያውን ማጥለቅ ችሏል።
አትሌቱ በዚህ ምክንያት የዳይመንድ ሊግ አሸናፊነት ግምቱን ያገኘ ሲሆን፤ ከሌላኛው ስኮትላንዳዊ አትሌት ግን ጠንካራ ፉክር ሊገጥመው እንደሚችል ነው የሚጠበቀው። ጆሽ ኬር የተሰኘው ይህ አትሌት በቶኪዮ ኦሊምፒክ የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት ነበር።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 /2014