አዲስ አበባ፡- የፍትሕ ሚኒስቴርን ጨምሮ ፖሊስ፣ የክልልና የፌዴራል የፍትሕ ተቋማት የሐሰተኛና ጥላቻ ንግግር ወንጀልን የሚፈጽሙ ሰዎችን ወደ ሕግ ማቅረብ እንዳለባቸው ተጠቆመ።
በፍትሕ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አወል ሱልጣን ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ቁጥጥር ተፈጻሚ መሆን በሚገባው ደረጃ እየተፈጸመ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።
ከዚህ በኋላ ሐሰተኛ የመረጃ ስርጭትን የሚያሰራጩ ሰዎች በአዋጁ ላይ የተቀመጡትን የወንጀል ቅድመ ሁኔታዎች እስኪያሟሉ ድረስ ፖሊስ ምርመራ መጀመር እንዳለበት፤ ማኅበረሰቡም መጠቆም እንደሚችል፤ ዓቃቤ ሕግም ወንጀል የመመርመርና የመምራት ኃላፊነት ስላለበት በዚህ ሂደት ውስጥም ፖሊስ የወንጀል ምርመራ እንዲጀምርና የተጣራ ምርመራ ካለ ክስ መስርቶ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶ ክርክር ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል። ይህ በተጨባጭ እንደሚከናወንም ነው ያስታወቁት።
ይህን ማድረግ ባለመቻላችን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ሰዎች ከመስመር ሲወጡና እንዲህ አይነት መረጃዎችን ሲያሰራጩ ቆይተዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በሐሰተኛ መረጃና ጥላቻ ንግግር ዙሪያ ማኅበረሰቡን የማስተማርና የማሳወቅ፣ የሕጉን ይዘት የመግለጽ በርካታ ሥራዎች ሲከናወኑ እንደነበርም ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ሃገር ውስጥ የሌሉ ሚዲያዎች በውጭ ሃገር ሆነው፤ ሃገር ውስጥ ያሉት ደግሞ ሐሰተኛ “አካውንት” እየከፈቱ ብሔርን ከብሔር፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ሊያጋጩ የሚችሉ መልዕክቶች እያስተላለፉ መሆናቸውንና በተገለፀው ልክ እርምጃ እየተወሰደ እንዳልሆነም ጠቁመዋል።
እንደ አቶ አወል ገለጻ፤ አዋጁ ሲወጣ ዋና ዓላማው በሕዝቦች፣ በብሔሮችና ሃይማኖት መካከል ሰዎች ተቻችለው እንዲኖሩና አንደኛው ሌላኛውን በማንነቱ እንዳያጠቃው ለመከላከል ነው። እንዲህ አይነት ድርጊት የሚፈጽሙ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ የወጣ አዋጅ ቢሆንም፤ በተጨባጭነት በፌስ ቡክም ሆነ በሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች በርካታ የሕግ ጥሰት እየተፈጸመ ነው።
ከዚህ በኋላ ፍትሕ ሚኒስቴር፣ ፖሊስ፣ የክልልም ሆነ የፌዴራል ፍትሕ ተቋማት እንዲህ አይነት ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎችን ለሕግ የማቅረብ ሥራ እንደሚሠሩና በሂደት እየተደራጁ ምርመራው ተጠናክሮ ክስ ተመሥርቶ ወደ ፍትሕ አደባባይ የሚመጡ እንደሚኖሩ ገልጸዋል።
የፍትሕ ሚኒስቴር ሕጉ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ሰፊ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ያነሱት አቶ አወል፤ ነገሮችን በሆደ ባሻነት አሊያም ነገሮችን እያሳለፉ በመሄድ ማኅበረሰቡ እስኪያውቅና እስኪረዳ፣ እንዲሁም ወንጀለኞችን አሳልፎ መስጠት የሚችለበት ሁኔታ ላይ እስኪደርስ ድረስ የተግባቦት ሥራ መሥራት ላይ ትኩረት አድርገን እየተንቀሳቀስን ነው ብለዋል።
በዚህም አብዛኛው ሰው በተለይም ወደ ሚዲያው ቀረብ ያሉት ሰዎች የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የሚያስችል አዋጅ መውጣቱን ያውቃል ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ አወል እንዳሉት፤ በጉዳዩ ዘሪያ የተወሰነ ለውጥና መሻሻል አለ። በተለይ በቅርብ ጊዜ ሐሰተኛ አካውንት የሚባሉት ካልሆኑ በቀር እውነተኛ አካውንት ያላቸው ሰዎች በተቻለ መጠን የሚያስተላልፏቸው መረጃዎች ላይ በተወሰነ መልኩ መጠንቀቅ መጀመራቸው ግንዛቤ ከመስጠት አኳያ ሕጉ ላይ በስፋት መሠራቱን የሚያሳይ ነው። አሁን ደግሞ ይህንን ተላልፈው ወንጀል የሚሠሩ ሰዎች ከእውቀት ማነስ የሚመነጭ ሳይሆን ሆነ ብለው ወንጀል ለመፈጸም፤ ባልተገባ መንገድ ማኅበረሰብ ውስጥ ረብሻና ግርግር እንዲነሳ ለማድረግ አስበውበት እንደሆነ ተናግረዋል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18 /2014