ኢትዮጵያዊያን ከሌላው ዓለም ከሚለየን ባህሪ አንዱ ገበታችን ነው፤ ብቻችንን የመብላት ልምድ ስላላዳበርን ገበታችን ብዙ ሰዎችን ያሳትፋል፤ ‹‹ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል›› እንዲሉ፤ ብቻ መብላት ባህላችን አይደለም። በእንዲህ አይነት አባባሎችና ‹‹ያለህን አካፍል፣ የተቸገረን እርዳ›› በሚሉ ሃይማታዊ አስተምህሮዎች ተገርተን ስላደግን ቤት ያፈራውን ከሰዎች ጋር መቋደስ የምንወድ ነን። ሰብሰብ ብለን እየተጎራረስን የመመገብ ልምዳችን ለስጋችንም ለነፍሳችንም የሚበጅ ነው ብለን የምናምን ነን። በተለይ ዓመት በዓል ሲሆን እየተጠራራን በመገባበዝ በሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻችን እየደመቅን የምንውልበትን ቀን ሁሌም እንናፍቀዋለን።
በሙስሊሙ በዓል ክርስቲያኑ ጋ፣ በክርስቲያኑ በዓል ሙስሊሙ ቤት እየተገኘን እንኳን አደረሳችሁ መባባሉና እንደየሀይማኖታችን ሥርዓት መስተናገዱ አብሮን የኖረ እሴት ነው። ለተቸገሩ ወገኖቻችን ካለን ላይ ማካፈሉም ከጥንት ጀምሮ የተለማመድነው ኢትዮጵያዊ መገለጫችን ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከሰሞኑ የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ በማህበራዊ ሚዲያ ያስተላለፉትን መልእክት መንደርደሪያ እናድርግ።
‹‹ያለንን ማካፈል የባህላችን አንድ አካል ሆኖ የዘለቀ ዕሴት ነው። እጦት ለገጠማቸው ማካፈል ዐሥር እጥፍ መልሶ የሚያሸልም ተግባር ነው። ከበዓል ሰሞን ባሻገር በቀጣይነት የመስጠት ተግባራችንን ማስፋት በእኩልነት ተደራሽ የሆነ ማኅበረሰብን ለመፍጠር ከሚያስችሉ ግብአቶች አንዱ ነው። በተለያየ የኑሮ ደረጃ ላይ የምንገኝ ሁሉ ማዕድ ማጋራትን እንድናስፋፋ አበረታታለሁ።›› ብለዋል።
ማእድ ማጋራት ምን አይነት ሃይማኖታዊ አንድምታ እንዳለው ከፋሲካ በዓል ጋር አያይዘው እንዲያስረዱን አንድ እንግዳ ጋብዘናል። እንግዳችን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ረዘም ላለ ጊዜ በሰባኪ ወንጌልነት አገልግለዋል። አሁንም የቤተክርስቲያኗ የቅርሳቅርስ፣ ቤተመዘክርና ቤተ-መጻህፍት አስጎብኚ ናቸው፤ ሊቀ ኅሩያን ሽመልስ ሀብተ ጊዮርጊስ ይባላሉ።
እንደ ሊቀ ኅሩያን ሽመልስ አባባል ኢትዮጵያዊያን ሃይማኖታችን ከባሕላችን ጋር በእጅጉ ተያያዥነት አለው። አንዳንድ ጊዜ ሃይማኖቱን የሚደግፉ ባህሎች ሲኖሩ፤ አንዳንድ ጊዜም ባህሉን የሚያጠናክሩ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች እንዳሉ ይገልጻሉ። እንደ ሊቀ ኅሩያን ሽመልስ አባባል መረዳዳት፣ መፈቃቀር፣ መከባበር፣ መደጋገፍ … ዛሬ የነበረ ሳይሆን ከጥንት ጀምሮ አባቶቻችን እየኖሩ ያለፉበትና ማህበራዊ መስተጋብራቸውን ያጠናከሩበት ሃይማኖታዊም ባህላዊም እሴት ነው። ኢትዮጵያዊያን በዓመት በዓል ወቅት ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ ቢሆን በመረዳዳትና በመተጋገዝ ችግሮቻቸውን የሚያልፉ ማህበረሰቦች ናቸው ይላሉ። ይህም በምንም ጉዳይ ሊሸረሸር የማይችል ጠንካራ አብሮነትን እንደፈጠረ ይገልጻሉ።
በክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ ክርስቶስን ከሰማየ ሰማያት ስቦ ወደ ምድር ያመጣው ፍቅር ነው። ክርስትናም ይህንን የሚከተል ነው፤ መፈቃቀርን መረዳዳትን መተዛዘንን ይሰብካል። በክርስትና እምነት ላመነም ይሁን ላላመነ በጎ ነገርን ማድረግ እንደ ግዴታ የተቀመጠ መርህ ነው ይላሉ።
እየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ባስተማረ ጊዜ በጎ ነገሮችን እያደረገ እናንተም ለሌሎች በጎ ነገርን አድርጉ ብሏል። በሌላውም ሃይማኖት ቢሆን መልካምነት፣ ፍቅር፣ መረዳዳት እንዲሁ ይበረታታል። ይህ የጋራ ሃይማኖታዊ እሴት ማህበራዊ መስተጋብሩ እንዲጠነክር አደርጓል ማለት እንችላለን ይላሉ ሊቀ ኅሩያን ሽመልስ።
ለምሳሌ የክርስትና እምነት ተከታዮች በየሳምንቱ ወይም በየወሩ የሚጠጡት ጽዋ ሊኖራቸው ይችላል። ይህ ዝግጅት የሚደረገው ለምግብነት ተብሎ ሳይሆን ፍቅርን፣ ማህበራዊ ቅርርብን ለማጎልበትና ምስጋናን ለማቅረብ ነው። አንዳንዶችም ዝም ብለው ደግሰው ያበላሉ። የሚያበሉት ነገ ሌሎች እንዲያበሏቸው ወይም ብድራቸውን እንዲከፍሉ በማሰብ አይደለም። እግዚአብሄርን በማመስገን፣ እርስ በእርስ በመፈቃቀር፣ ምስኪኖችን በመጎብኘት ማእድን በማጋራት በረከት ይገኛል በሚል ጽኑ እምነት ነው። እውነት ነው በመስጠት ወይም በመለገስ በረከት እንደሚገኝ እየሱስ ክርስቶስ እራሱ ’ስራብ አላበላችሁኝም ስጠማ አላጠጣችሁኝም’ ሲል አስፈላጊነቱን ተናግሯል። እየሱስ ክርስቶስ ነገሮችን የሚገልጸው በምሳሌ ነው፤ ለሌሎች ማድረግ የእግዚአብሄርን ትእዛዝ መፈጸም እንደሆነ ሲያስረዳ ነው።
ማእድን ማጋራትም ይሁን መጋራት ፍቅርን መጋራት ነው። ሰዎች ሰንበቴ ላይ በተሰበሰቡ ቁጥር ማህበራዊ ህይወትን የሚያጠናክሩ ጉዳዮችንም ያከናውናሉ። የታመመን ይጠይቃሉ፣ ሀዘንና ለቅሶን ይደራረሳሉ። አቅመ-ደካማ የሆኑ ማህበረተኞቻቸውን ተረዳድተው ያግዛሉ። ጓዳቸው ባዶ ለሆኑ ሰዎች የአቅማቸውን ቋጥረው እየሄዱ ይጠይቃሉ፤ የጋራ ጸሎት ያደርጋሉ፤ ማእድን ማጋራት ፍቅርን በመስጠት ፍቅርን መቀበል፤ ፈጣሪን ማሰብ ነው። ለዚህም ነው በሃይማኖታዊ አስተምህሮው ሰው ከተረፈው ላይ ሳይሆን ካለው ላይ እንዲያካፍል የሚታዘዘው ይላሉ ሊቀ ኅሩያን።
ቤተክርስቲያን መስጠትን በቅጥር ጊቢዋ ውስጥ የምታከናውን ነች። ለዚህም ነው የኔ ብጤዎች፣ ችግረኞች፣ አቅመ ደካሞች፣ ታማሚዎች እርዳታ ሲፈልጉ ቤተክርስቲያን በር ላይ ቁጭ ብለው የሚማጸኑት። የእለት ጉርስ ያጡ ገበታ ይጋሩባታል፤ በልተው ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ፤ የነገ ተስፋቸውን ያለመልማሉ፤ አንዳንዶችም በተደረገላቸው ድጋፍ መንፈሳቸውን አንጸው፣ ጉልበታቸውን አድሰው ለሥራ ይዘጋጃሉ።
ቢታገዙ እራሳቸውን የሚለውጡ ሰዎች አሉ፤ ለእነዚህ ሰዎች ሁል ጊዜ መስጠት ሳይሆን በሚደረግላቸው ድጋፍ እራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ያስፈልጋል። ባህላዊም ይሁን ሃይማኖታዊ እሴታችን እንዲህ አይነቱን ድጋፍ ያበረታታሉ።
ሰው ከቃላት በዘለለ ተግባርን ማየት ስለሚፈልግ መተጋገዝና መተባበር በድርጊት የሚገለጽ መሆን አለበት። ሐዋርያው ያዕቆብ ‹‹ወንድሙ ተርቦ እያየ እሳት ሙቅ፣ አዲስ ልብስ ልበስ፤ ደስ ይበልህ ሊለው እንዴት ይችላል ይላል። ይልቁንም የሚበላው ነገር ቢሰጠው የበለጠ እንዲያመሰግን ያደርገዋል›› ብሏል። ዛሬ ለወገኖቻችን አንድ ነገር ስናደርግላቸው ነገ ደግሞ እነርሱም ለሌሎች እንዲያደርጉላቸው የሚያበረታታ ነገር ማድረግ ያስፈልጋል።
በዓላት ሰዎች ደስ የሚሰኙባቸው ቀናት ናቸው። የክት ልብስ የሚለብሱበት፣ አስተሳሰባቸውን የሚያድሱበት፣ ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑበትና ተስፋቸውን የሚያለመልሙበት ቀን ነው። ለምሳሌ የፋሲካ በዓልን ብንመለከት እየሱስ ክርስቶስ በሞቱ ሞታችንን የደመሰሰልን፣ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ከሞት ወደ ድህነት ያሸጋገረን፣ ከጭለማ ወደ ብርሃን ያመጣን እንደሆነ ስናስብ ከትናንት መጥፎ ሥራችን ወጥተን በጎ ነገር ለማድረግ እንዘጋጃለን። ያገኘነው ብርሃን ደግሞ ለሌሎች የሚያበራና የሚተርፍ መሆን አለበት። የጋን መብራት እንደሚባለው መሆን የለብንም። ሻማ ሲበራ ለሁሉም በሚያሳይ ቦታ ላይ ከፍ ብሎ እንደሚቀመጥ ሁሉ ሰውም በመልካም ምግባሩ ለሁሉም መትረፍ አለበት።
እንደቤተክርስቲያን አስተምህሮ ትናንት የነበረው የመዋደድና የመረዳዳት እሴታችን መቀጠል ያለበት ያመነ ያላመነ፣ ቀይና ጥቁር፣ በብሄር፣ ቋንቋና በሃይማት እየተለየ አይደለም። በጎ ሥራ ለሁሉም የሰው ዘር ያስፈልጋል። ለእኛ እንዲደረግልን የምንፈልገውን ለሌሎችም ማድረግ ይኖርብናል፤ እኛ ላይ እንዲደረግ የማንፈልገውን ክፉ ነገር ሌላው ላይ ማድረግ የለብንም።
ለችግር መደራረስና መረዳዳት ወይም አንድ ላይ ቁጭ ብሎ ማዕድ መጋራት በዓላት በመጡ ጊዜ ብቻ የምናደርገው ሳይሆን በአዘቦቱም ልንከውነው የሚገባና አብሮነታችንን የሚያስቀጥልልን እሴታችን ነው። ቁሳዊ ድጋፍ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ቸር መመኘትና ቸር ማሰብም ማህበራዊ ህይወትን ያጠናክራል።
እየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር ‹‹እኔ እንደወደድኳችሁ እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ፤ አጠገብህ ያለውን/ያየኸውን/ወንድምህን ሳትወድ ያላየኸውን እግዚአብሄርን እወዳለሁ ብትል ሀሰተኛ ነህ ይላል። ክርስትና ማንኛውንም ሰው ሳናበላልጥ እንድንወድ ያስተምረናል።
የስቅለትን በዓል የምናከብረው ክርስቶስ ለሰው ፍቅር ሲል በመስቀል ላይ ተሰቅሎ፤ ሞቶ፤ በሞቱ ሞታችንን ድል ስላደረግልን ነው፤ የሞተው ለተወሰኑ ሳይሆን ለመላው የሰው ዘር ነው። ስለዚህ ሰው ሰውን ሲወድ ደረጃ አውጥቶ ሊሆን አይገባም፤ በፍጹም ፍቅር መዋደድ እንዳለብን ከክርስቶስ ተምረናል። እየሱስ ክርስቶስ በወደደን ልክ እርስ በእርሳችን መዋደድ አለብን። የክርስትናው አስተምህሮ የሚወደንን ብቻ ሳይሆን የማይወደንንም ጭምር መውደድ እንዳለብን ያስገድደናል። ክርስቶስን በመስቀል ላይ እየሰቀሉት ይቅር በላቸው ብሎ የጸለየላቸው በደልን በይቅርታ ማለፍ እንድንችል ሊያስተምረን ነው። ሞትን ሊሞት የፈቀደውም ሰዎችን ከሀጢያት ለመታደግ ነው። ሰው እየገረፈው፣ ሰው እየሰቀለው፣ ሰው እየገደለው ክፉውን በክፉ ሳይሆን በበጎ ማሸነፍ እንዳለብን ሊያስተምረን ‹‹አባት ሆይ ይቅር በላቸው›› ብሏል።
አባቶቻችን አብሮነታችንን ያስቀጠሉት እንዲህ አይነቶቹን ሃይማታዊና ባህላዊ እሴቶች እያከበሩ በመኖራቸው ነው። የሰው ልጅ ሃይማኖቱ ባያስገድደው እንኳ መልካም ነገርን ቢያደረግ የህሊና ሰላም ያገኛል እንጂ አይጎዳም።
በዓላት ሲከበሩ በጋራ ይጸለያል፣ መልካም ነገር ይበሰራል፣ ይበላል፤ ይጠጣል። ካለን ላይ ስናካፍል የምንሰጠው ምግብ ከምግብነቱ በላይ በፍቅር ያስተሳስረናል። ፍቅር ደግሞ ሰዎችን ይገዛል፤ መዋደድንና አብሮነትን ያጠናክራል።
የዘንድሮው የትንሳኤ በዓል በብዙ ችግሮች መሃከል ሆነን የምናከብረው ቢሆንም ኢትዮጵያዊ መገለጫችንን ሳናጓድል እንደ ከዚህ ቀደሙ እርስ በእርሳችን በመረዳዳት፤ አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ በመባባል የምናከብረው ሊሆን ይገባል።
በአቅራቢያችን ያሉ አቅመ ደካሞችን አለንላችሁ፣ ከጎናችሁ ነን በማለት ያለንን ተካፍለን በዓሉን ማክበር ይኖርብናል። የትንሳኤ በዓል እየሱስ ክርስቶ ለፍቅር ሲል ዋጋ ከፍሎ በአሸናፊነት የተወጣው እንደመሆኑ ምእመኑ የእየሱስ ክርስቶስን አርአያነት ተከትሎ በጎነትንና መልካምነትን ገንዘቡ ሊያደርግ ይገባል። ከቤት ንብረታቸው ተሰደው በመጠለያ ውስጥ ያሉ ወገኖቹን መጠየቅ፤ በየጎዳናው የሚኖሩ ወላጅ አልባ ልጆችና ችግረኞችንም ማስታወስ ይኖርበታል።
ኑሮ ቢወደድም ሁሉም ባለው አቅም እየተረዳዳ በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፍ የተለመደውን ትብብር ማድረግ ያስፈልጋል። በግ እና ዶሮ የማረድ ልምድ ያለው አንድ ቤተሰብ በግ ብቻ አርዶ ዶሮውን ለተቸገረ ሰው ቢሰጥ እዚያኛው ቤትም ደስታ እንዲገባ ያደርጋል። የሁዳዴ ጾም ማጠንጠኛ የሚሆነው ጾም ተፈታ ብሎ አርዶ መብላት ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ማስታወስ ሲቻል ነው። እንዲህ አይነቱ ተግባር ጾሙ ከሚያስገኘው በረከት አንዱ ነው።
በዘንድሮው ዓመት የክርስቲያን ጾም ብቻ ሳይሆን የሙስሊም ወንድሞቻችን ጾምም በተመሳሳይ ጊዜ እየተጾመ ነው። ሁሉም የሚጾመው ከፈጣሪው በረከት ለማግኘት ሲል እንደመሆኑ አንዱ ለአንዱ ፈጣሪ የሚወደውን ሥራ መሥራት ይኖርበታል። በዓመት በዓል ጊዜ ሙስሊምና ክርስቲያኖች እየተጠራሩ በዓላትን ማክበር ዛሬ የተጀመረ አይደለም። በፋሲካም ይሁን በሙስሊሞች ጾም ፍቺ እንደ ከዚህ ቀደማችን እየተጠራራን በፍቅር በማሳለፍ አብሮነታችንን ማጠናከር ይገባናል። ወስብሃት ለእግዚአብሄር።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14 ቀን 2014 ዓ.ም