በአንድ አገር ብቻ ሳይሆን በዓለም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ብሎም አካባቢያዊ ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ የህዝብን ንቃተ ሕሊና ለመቅረጽና ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር አክቲቪዝም ትልቅ ድርሻ ስለማበርከቱ በርካታ ዓለምአቀፍ ማሳያዎች ይነሳሉ። በኢትዮጵያም በተለይም የማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋትን ተከትሎ ይሄው ተግባር እየተበራከተ እንደመሆኑ በአዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ገጽታው የሚነሱ ነገሮች አሉ። ታዲያ የአክቲቪዝም እንቅስቃሴ በእትዮጵያ እንዴት ይገለጻል፤ ያሉት መልካም ገጽታዎችና ችግሮችስ ምን ይመስላሉ፤ በቀጣይስ ምን ሊሠራ ይገባል፤ በሚሉ ጉዳዮች ላይ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ምሑራን የሚሉት አላቸው።
አክቲቪዝምና አክቲቪስት አቶ በረከት ሐሰን፣ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ አክቲቪዝም በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ተሃድሶን ለማምጣት፣ ማህበረሰቡንም ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ ደረጃ የሚያሸጋግር ለውጥ ለማምጣት በግለሰቦች ወይም በቡድኖች የሚከናወን ተግባር ነው። እነዚህ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ደግሞ በአንድ አገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን ዓለምአቀፋዊ ጉዳዮችን ጉዳያቸው አድርገው የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሰብዓዊ መብት፣ ጾታና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ለውጥ እንዲመጣ በሰፊው የሚሞግቱበት እንቅስቃሴ ነው።
የአክቲቪዝም ሚና በዋናነት አንድን ማህበረሰብ ማሻገር ነው ሲባል፤ አንድን ጉዳይ በማንሳት የመጣለትን ሃሳብ፣ አቅጣጫና ጉዳይ ዝም ብሎ ወደማህበረሰቡ በማድረስ ማህበረሰቡን ይቀይራል ማለት አይደለም። ትልቁ የአክቲቪዝም ሚና የሚሆነው አንድን ጉዳይ አንስቶ (ለምሳሌ ስለ ሰብዓዊ መብት ጥሰት) እና አንድን አቅጣጫ ብቻ ወስዶ በመመልከት ማህበረሰቡ በዚያ ጉዳይ ላይ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን እንዲቃወም መሥራት ነው። ይህ ሲሆን ግን ብዙ ማጥናትንና ስለጉዳዩ ማወቅን፤ ማህበረሰቡን ማሻገር የሚችል የሃሳብ ልዕልናን መታጠቅን ይጠይቃል።
በእነዚህና መሰል ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ በርካታ የአክቲቪዝም እንቅስቃሴዎች በዓለም ዙሪያ ያሉ ሲሆን፤ የማህበራዊ ሚዲያው እንዳሁኑ በስፋት ከመጀመራቸው በፊትም በሚዲያዎች ጭምር ከፍተኛ እንቅስቃሴዎች ተካሂደዋል። በእስከአሁን ሂደት የአክቲቪዝም እንቅስቃሴዎች በርካታ ለውጥን ሲያመጡ መመልከት ተችሏል። በተለይ የማህበራዊ ሚዲያው (እንደ ፌስ ቡክ፣ ቲዊተርና ሌሎችም) የአክቲቪዝም እንቅስቃሴን በከፍተኛ ደረጃ አግዘዋል።
በኢትዮጵያም ይሄው እንቅስቃሴ የመንግሥት ለውጥ እስከማድረግ አድርሷል። በሌሎች የዓለም አገራትም የአክቲቪዝም እንቅስቃሴው በጣም እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በተለይም የማህበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ተችሏል። ለዚህ ደግሞ የ2012ቱ የዐረብ አብዮት አንድ ማሳያ ሲሆን፤ የአሜሪካው ዎል ስትሪት እንዲሁም ኡጋንዳና ቬንዙዌላ የነበሩ የአክቲቪስት ተጽዕኖዎችም ተጠቃሽ ናቸው። በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ፅጋቡ ሞትባይኖር በበኩላቸው እንደሚሉት፤ አክቲቪስትነት ከጋዜጠኝነት ይለያል።
ምክንያቱም፣ ጋዜጠኝነት ተጨባጭ የሆነ ሐቅን ወደ ህብረተሰቡ በማስተላለፍ ዳኝነቱን ለህብረተሰብ ይሰጣል፤ በአንጻሩ አክቲቪዝም፣ አንድን ሃሳብ ተከታዮቹ እንዲቀበሉት የማድረጊያ ሂደት ነው። ሆኖም በአንድ አገር ሁለንተናዊ ሂደት ውስጥ ሁለቱም አስፈላጊ ናቸው። በበርካታ አገራትም እንደ ጋዜጠኝነቱ ሁሉ ዓላማን መሰረት ያደረጉ የአክቲቪዝም እንቅስቃሴዎች ለውጥን ሲያመጡ ታይቷል። ለአክቲቪዝም ሥራው ደግሞ የማህበራዊ ሚዲያው ሰፊ አማራጭ ሰጥቷል። በጋዜጠኝነት ውስጥ ያሉት ሳይቀር ሙያው የሰጣቸውን አቅም ተጠቅመው ወደ አክቲቪስትነት የሚሄዱበትን ዕድል ፈጥሯል።
ሚዲያውም በዚያው ልክ እያደገ ይገኛል። ሆኖም አክቲቪስትነቱን ጋዜጠኝነቱ በሰጣቸው ዕውቀትና ልምድ ተጠቅመው መሥራት ቢችሉ መልካም ይሆናል። አክቲቪዝም በኢትዮጵያ እንደ አቶ ፅጋቡ ገለጻ፤ በተለያዩ የዓለም አገራት አክቲቪስቶች እያደጉ ነው ያሉት። ይህ ደግሞ የማህበራዊ ሚዲያው ምህዳር መስፋት ውጤት ነው። ሆኖም አጠቃቀሙ በሌላው ዓለምም ሆነ በኢትዮጵያ የራሱን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል። ከዚህ አኳያ ሲታይ አክቲቪዝም በኢትዮጵያ የተወሰኑ ሰዎች በትክክል የሚጠቀሙበትና የተሻለ ሃሳብ እንዲንሸራሸርበት እያደረጉበት ሲሆን፤ በአንጻሩ በአብዛኛውና በብዙ ቁጥር የሚገለጹት አክቲቪስቶች ግን ለህዝቡ የትኛው ቢሆን ይጠቅማል በሚል ሳይሆን እነርሱ በሚፈልጉት መልኩ እንዲጓዝ የሚያደርጉበት መስክ ሆኗል።
አክቲቪስትነትን በአግባቡ ባለመረዳት ያለው የአጠቃቀም ሂደት እነርሱ የሚፈልጉት የተወሰነ ቡድን ወይም የህብረተሰብ ክፍል ወይም የፖለቲካ ፓርቲ ሊሆን ይችላል የዚያ ሃሳብና ፍላጎት ብቻ እንዲደመጥ የሚያደርጉበት ሂደትም እንደ አገር ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል። ይህ ደግሞ ሚዛናዊ በሆነና አንዱን ሲጠቅም ሌላውን በማይጎዳ መልኩ እንዲጓዝ የሚያደርጉ ሃሳቦች እየራቋቸው የመምጣቱ፤ የእኔን ተቀበሉ እንጂ ለህዝብ ሃሳብ መሥራትና እውነትን አድርሶ ዳኝነትን ለህዝብ የመስጠት አካሄድ የመጥፋቱ ማሳያ ነው። በሁሉም አካባቢ የሚታየውም የራስን ጎራ ለይቶ ፍጭት ማድረግ ነው።
እውነተኛና ሚዛናዊ አክቲቪስት ግን መሥራት ያለበትን የህብረተሰብ ለውጥ አምጪ ሃሳቦች የማመንጨትና የህዝቡን ንቃት ማሳደግ ነበር። እናም የፈለገው ሰው ተነስቶ የፈለገውን የሚጽፈበትና አክቲቪስት የሚሆንበት አግባብ እየታየ፤ በተከታይ ብዛትም የጻፈውን ሰው እንዲያምነው እየሆነ ነው። በዚህም ግላዊ አስተሳሰቦች እየገነኑና ህብረተሰባዊ ጉዳዮች እየተዘነጉ ወደከፋ ችግሮች እየወሰዱ ይገኛል። እንደ አቶ በረከት ገለጻ ደግሞ፤ አክቲቪዝም በኢትዮጵያ ለምልሞ ወጥቷል የሚባለው ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ነው። በተለይ በኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ መሄድና 16 ሚሊዬን የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች መኖር አክቲቪስቶች በቀላሉ በርከት ያሉ ተከታይ እንዲያፈሩና ሃሳቦቻቸውን የሚጋሯቸው እንዲያገኙ አድርጓቸዋል።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ የአክቲቪዝም እንቅስቃሴ ትልቁና መሰረታዊው ችግር የሙያ ድንበር/መስመር ማጣትና መጣረሶች ናቸው። ጋዜጠኛውም ሆነ ፖለቲከኛው አክቲቪስት፤ አክቲቪስቱ ጋዜጠኛም ፖለቲከኛም ሲሆን ይታያል። እነዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ መሰረታዊ ስህተቶች ናቸው። አንድ ጋዜጠኛ አክቲቪስት የሚሆን ከሆነ የጋዜጠኝነቱን ሙያ ያበላሻል፤ በተመሳሳይ አክቲቪስቱ ጋዜጠኛ፣ ፖለቲከኛውም አክቲቪስት ሲሆን በዚያው ደረጃ የሚታይ ነው። አቶ በረከት እንደሚሉት፤ ይህ አካሄድ የኢትዮጵያ የአክቲቪዝም እንቅስቃሴ በተለይም የማህበራዊ ሚዲያው ባህሪ በአብዛኛው መነሻና መሰረት የሌላቸው ሃሳቦችን ሲያንሸራሽሩ፤ የውሸት ዜናዎችንና መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ፤ አንዳንዴም ከግላዊ ቅሬታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ሲያነሱ ይታያል።
ይህ የሃሰትና መሰረት የሌለው ወሬ ጉዳይ ደግሞ በዓለምአቀፍ ደረጃ ትልቅ ችግር ተብሎ የሚታሰብ ነው። በዚህ መልኩ የውሸት ዜናም ሆነ የግል ቅሬታን ይዞ በመውጣት፣ ብዙ ላይክና ሼር በማግኘት ሂደት ውስጥ ሳይታሰብ ወደ አክቲቪስትነት የሚገባበት አካሄድ ደግሞ አክቲቪዝም ለምን ዓላማ እየተካሄደ እንደሆነ በመዘንጋት ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለሚያመሩ ሃሳቦች መበራከት በር ከፍቷል። ይህ የአክቲቪስቶች ችግር ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ያለው የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ህብረተሰብ የአጠቃቀም ዘይቤም ችግር ሲሆን፤ ህብረተሰቡ ከማህበራዊ ሚዲያዎች የሚወስዳቸው መረጃዎች የትኞቹ ናቸው ብሎ ለይቶ ያለመረዳት ክፍተትም ነው። ሆኖም በአገሪቱ ከፍተኛ ለውጥ እንዲመጣ ያደረጉ አክቲቪስቶች መኖራቸው አይዘነጋም።
እነዚህ አክቲቪስቶች ትክክለኛ መረጃ በመስጠትና ተገቢ የሆነ መረጃን በተገቢው መንገድ በማድረስ ህዝቡን በከፍተኛ ሁኔታ በማነሳሳት በአገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁነት ላይ ለውጥ እንዲመጣ አድርገዋል። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ የአክቲቪዝም እንቅስቃሴ ሲታይ በአብዛኛው በውሸት ዜናና በግል ቅሬታ ላይ ተመስርተው የሚቀነቀኑ ናቸው። አንድ መረጃም ከአንድ አካል ስለመጣ ብቻ ሰበር ዜና ተብሎ የሚወጣ አይደለም። የተሰጠውን መረጃ ትክክል ስለመሆን አለመሆኑ ማረጋገጥና አክቲቪስቱ ከቆመበት ዓላማ (ለምሳሌ፣ ከሰብዓዊ መብት፣ ከሴቶች መብት፣ ከአከባቢ ጥበቃ፣ ወዘተ.) አኳያ በማገናዘብ ለህብረተሰቡ የሚጠቅምና ወደሚፈለገው ደረጃ የሚያሸጋግር ስለመሆን አለመሆኑ ማረጋገጥ መቻል አለበት።
ለምሳሌ፣ አሜሪካ ውስጥ የጥቁሮች መብት እንዲከበር ተግተው የሚሠሩ አክቲቪስቶች አሉ፤ በመላው ዓለምም ለአየር ንብረት ለውጥ ችግር መቀረፍ የሚሟገቱ አክቲቪስቶች አሉ፤ ለሴቶች እኩልነትና ተጠቃሚነትም የሚሞግቱ አሉ። ዋናው ጉዳይ ዓላማቸውን ለማሳካትና ህዝባዊ ሽግግርን ለመፍጠር የትኛው መረጃ ነው ትክክልና የሚጠቅመው ብለው መመርመርና በግንዛቤ ላይ ተመስርተው ሃሳባቸውን ማራመድን የሚጠይቅ መሆኑን መገንዘብ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይሄን የማድረግ ጉድለት ይታያል። አሉታዊ ገጽታው አቶ በረከት እንደሚናገሩት፤ በኢትዮጵያ ያለው የአክቲቪዝም እንቅስቃሴ በዚህ መልኩ መገለጽ፣ አክቲቪስቶች የቆሙለትን ዓላማ አውቀው እንዳይሠሩ አድርጓቸዋል።
በዚህ መልኩ ዓላማን አውቆ ያለመሥራት ሂደትም በሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ጥላቻን፣ ጸብና ቂመኝነትን ጭምር ሲዘሩ ይስተዋላል። ሲፈልጉ የፖለቲካ፣ ሲያሻቸው የአካባቢ ጥበቃ፤ ሲላቸውም የጾታ ጉዳይ፤ ካልሆነም የብሔርና ሌላም ጉዳይ ይዘው እዚያም እዚህም ሲረግጡ መታየታቸውም ለዚሁ ነው። እናም ለአገርና ህዝብ መለወጥ ጉልህ ድርሻ ያደረጉ ጥቂት አክቲቪስቶች ተግባር በተቃራኒው ይሄን መሰል የሙያ፣ የዓላማና ተልዕኮ መጣረስ የሚታይባቸው አክቲቪስቶች በሚፈጥሩት ስህተት አገርና ህዝብ ወዳልተፈለገ ችግር እንዲያመሩ እያደረጋቸው ይገኛል። ይህ አካሄድ ደግሞ የእንደዚህ ዓይነት አክቲቪስቶች የአክቲቪስትነት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል።
ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች አንድም፣ በሚያነሷቸው የውሸትና ስሜት ቀስቃሽ ጉዳዮችም ሆነ ግለሰባዊ ቅሬታዎች ምክንያት በሚያገኟቸው የተከታይና ተጋሪ ብዛት ሳያስቡት ወደአክቲቪስትነት የገቡ፤ አንድም ዓላማና ተልዕኳቸውን ለይተው የሚታገሉበትን ምክንያትን አውቀው የገቡ ሊሆኑ ስለሚችሉ ነው። የውሸት ዜና በወጣ ቁጥር ደግሞ ሰዎችን ወደተሳሳተ አቅጣጫ እየመራ፤ የጥላቻ መልዕክቶችም ሲበዙ ለግጭት ምንስኤ እየሆነ፤ ሌላው ቀርቶ አክቲቪስቱ ባስተላለፈው መልዕክት ስር የሚሰጡ አስተያየቶች ለጥላቻ በር እየከፈቱ መሆናቸውን በኢትዮጵያ መመልከት ተችሏል።
በማህበረሰብ ሚዲያው እንቅስቃሴና አጠቃቀም ባለው ሰፊ ጉድለትም ሃይማኖትን፣ ብሔርን፣ ግለሰባዊ ማንነትን፣ ወዘተ መሰረት ያደረጉ ስድቦች፣ የጥላቻ መልዕክቶችና ጥቃቶች መደበኛ በሚመስል ገጽታ በሰፊው የሚንሸራሸሩበት አሳፋሪ፤ ብሎም ኢትዮጵያዊ የሚታወቅበትን ሁሉን አክባሪነት ገጽታና ኢትዮጵያዊነትን የማይመጥን ከመሆኑም በላይ፤ ወደፊት ችግር ይፈጥራል ተብሎ የሚነገርለት ሳይሆን አሁን ላይም ችግር ፈጥሮ በህዝቦች መካከል መጠራጠርና መቃቃር እንዲፈጠርና ግጭት እንዲከሰትም አድርጓል። ይህ ደግሞ የማህበራዊ ሚዲያው ጥቅም እንዳለው ሁሉ የአጠቃቀም ግድፈት ሲኖርም ጉዳት እንዳለው ማየት የተቻለበት ነው። አሁን ባለው የችግር ደረጃ ሊታረም የማይቻል ከሆነና በዚሁ ከቀጠለ ጉዳቱ ከዚህም የከፋ ስለሚሆን ማስተካከያ ሊደረግበት ይገባል።
አቶ ፅጋቡ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ምንም እንኳን አሁን ላይ ሚዲያዎች እየተበ ራከቱ የመጡና የተወሰኑ አማራጮችን ማየት ቢጀምርም ቀደም ሲል ይህ አማራጭ ባለመኖሩ ህብረተሰቡ መረጃን ቶሎ ቶሎ ባለበት ቦታ ለማግኘት የመገናኛ ብዙሃኑ ይሄን ማድረግ ባለመቻላቸው የማህበራዊ ሚዲያዎችን በአማራ ጭነት መያዙ የአክቲቪዝም እንቅስቃሴዎች እንዲያድጉ እንደ አንድ ሰበብ ሆኗል። ሆኖም አንድ አክቲቪስት ለገጹ ጓደኛም ሆነ ተከታይ ሲያፈራ የሚያራምደው ሃሳብ ለህዝብ ለውጥና አንድነት፤ ለተሻለ ተጠቃሚነትና የጋራ ዕድገት መሆን እንጂ ራስን ጠቅሞ ሌሎችን ለመጉዳት መዋል አይገባውም።
ነገር ግን አሁን የሚታየው ማንም ሰው ተነስቶ አክቲቪስት ስለሚሆን የፈለገውን ሃሳብ ፈጥሮ እያራመደና ወደሌሎችም በማ ጋባት ችግር እያስከተለ ይገኛል። ሆኖም ኢትዮጵያውያን ነጋቸውን የተሻለ ማድረግ ስለሚችሉበት ጉዳይ የሚመክሩበትና ለዚሁ በጋራ መሥራት የሚገባቸው እንጂ፤ በአክቲቪስትነት ስም ጎራ ከፍለው በሚሻኮቱ ግለሰቦች አጀንዳ የሚናቆሩና የሚጣሉ መሆን፤ አክቲቪስቶችም ቢሆኑ ህዝቡን ወደተሻለ ለውጥና አብሮነት ስለማሻገር እንጂ በራስ ስሜትና ፍላጎት እየገፉ ወዳልተፈለገ መገፋፋትና ግጭት እንዲያመራ ማድረግ አልነበረባቸውም። እናም አክቲቪዝሙ አሁን ላይ እየፈጠረው ያለው ችግር ከቀጠለ የባሰ አደጋ ማስከተሉ ታውቆ ሊሠራ ይገባል።
መፍትሔና መልዕክት እንደ አቶ ፅጋቡ ገለጻ፤ አሁን ቴክሎጂ እያደገና ተጠቃሚውም እየበዛ ከመሆኑ አንጻር አክቲቪዝምን ማጥፋት አይቻልም። እናም አማራጭ ሊሆን የሚችለው አንድም ህብረተሰቡ አማራጭ እንዲኖረውና የሚጠቅመውን ሃሳብ ለይቶ እንዲይዝ ማድረግ፤ ሁለተኛም አክቲቪዝሙ የጋዜጠኝነት ጽንሰ ሃሳብን ተገንዝቦ በዛ አግባብ ህብረተሰባዊ ተጠቃሚነት ላይ አተኩሮ እንዲሠራ ማስቻል ነው። በተመሳሳይ ውጤታማ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን የሚመለከት ጠንካራ ሕግ አውጥቶ መተግበር ይገባል። ምክንያቱም አሁን ባለው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሁኔታ ህዝቡ በሚፈለገው ልክ ንቃተ ህሊናው አድጓል ማለት ስለማይቻል፤ ለምን እንጠቀማለን የሚለው ባለመታወቁም፣ አገሪቱንም ሆነ ህዝቡን ዋጋ እያስከፈለ ስለሆነ አጠቃቀሙ መታረቅ ስላለበት ይሄንን መቆጣጠር የሚቻልበት አካሄድ ሊኖር ያስፈልጋል።
በዚህም አክቲቪስቶች ከቁርሾ ወጥተው ለህዝብ ጠቃሚ መረጃን ማጋራት፤ መንግሥትም ለጊዜውም ቢሆን ይሄን የጥፋት ዘር የማሰራጨትና የግጭት መንስኤ መልዕክቶች የማጋራት አካሄድ የሚቆጣጠርበትን ዕድል መፍጠር አለባቸው። ከዚህ በተጓዳይ አብዛኛው ህብረተሰብ ገጠር የሚኖርና የሚዲያም ተደራሽነት የሌለው እንደመሆኑ ከማህበረሰብ ራዲዮኖች ጀምሮ ሚዲያውንና ጋዜጠኝነትን ማሳደግ፤ መንግሥትም ይሄንን በመደገፍ የህብረተሰቡን አማራጭ ማብዛት ይገባል። በተመሳሳይ ጥሩ ስነምግባር ያላቸውና ለመልካም የህዝብ ለውጥ የሚሠሩ አክቲቪስቶችን መንግሥት እየደገፈ በምን መልኩ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ መጥቀም ይችላሉ በሚለው ላይ ሃሳብ እንዲያንሸራሽሩ ማድረግ ያስፈልጋል።
አቶ በረከት በበኩላቸው እንደሚሉት፤ እንደ አገር 16 ሚሊዬን ሰው የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ሆነ ማለት፤ በዚያው ልክ የዚህ ማህበራዊ ሚዲያ ተደራሽ ያልሆነውን ሰፊ የገጠሩ ህብረተሰብ ክፍል በተመሳሳይ የውሸትና የግል ቅሬታ ስሜት መልዕክቶች ለመመረዝ የሚኖረው ዕድል የሰፋ ነው። ይሄን መሰል የተዛባ መረጃ ስርጭት ደግሞ በህብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጥረው አደጋ አሁን እየታየ ባለው መልኩ የሚገለጽ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ የመንግሥትም ሆነ የሚዲያ ተቋማት አጀንዳዎች የሚቀረጹትም ሰፊውን የህብረተሰብ ጉዳይ ሳይሆን የ16 ሚሊዬን የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚን ማዕከል የማድረግቸው ሂደት መታረም አለበት።
ምክንያቱም ሰፊው የገጠርና የአርሶአደሩ ማህበረሰብ ስሜትና ፍላጎትም ከግምት ሊገባ ይገባዋል እንጂ፤ እንደ አንድ ግብዓት ከመጠቀም ባለፈ የማህበራዊ ሚዲያውን ተከትሎ መሾምና መሻር ተገቢ አይደለም። አብዛኛው ህብረተሰብ ከማህበራዊ ሚዲያው ውጪ እንደመሆኑም ፖሊሲና እቅዶችም በዚሁ አግባብ ሊቃኙ ይገባል። በተመሳሳይ አንዱን በማኮሰስ፣ ኢትዮጵያ ዊነትን ወደኋላ የሚስብ፣ ሃይማኖትን ወይም ብሔርን ከፍና ዝቅ በሚያደርግ የሚሰነዘሩ የጥላቻ መልዕክቶችን ማርገብ የሚቻልበት አካሄድ መታየት አለበት። ባለው ተጨባጭ ሁኔታም ትልልቅ የሚባሉ መገናኛ ብዙሃን ባሉበት አገር ላይ መረጃዎችን ቀድመው ለህዝብ ተደራሽ የሚያደርጉት የማህበራዊ ሚዲያዎች ናቸው።
ይህ ደግሞ የሚዲያ ተቋማት ምን ያክል ወደኋላ እንደቀሩ አመላካች ነው። ከዚህ አኳያም የመን ግሥት የሥራ ሐላፊዎች/ባለስልጣናት በያንዳንዱ ሁነትና ጊዜ ለመገናኛ ብዙሃን ክፍት መሆን አለባቸው። ይህ ሲሆን ተገቢውን መረጃ በሰዓቱ ለማህበረሰቡ ማድረስ ስለሚቻል ማህበራዊ ሚዲያው በሐሰት መረጃ በህብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ መቀነስ ይቻላል። ሚዲያዎችም በተቻለ መጠን አቅማቸውን ገንብተው፣ የሰው ሐይላቸውንም አደራጅተውና ተደራሽነታቸውን አስፍተው መረጃን በተገቢው ወቅት ለማህበረሰቡ ማድረስ የሚችሉበትን አግባብ ለመፍጠር መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
ከመደበኛው የመረጃ ማሰራጫ አውታራቸው ባለፈም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮችን ተጠቅመው ትኩስና ወቅታዊ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ማድረስ ይኖርባቸዋል። ከዚህ ባለፈ በአክቲቪዝም ጉዞ ውስጥ የሚታይን የሙያ መጣረስና የዓላማ መሳት አካሄድን የሚያርም ዕርምጃ መውሰድ ይገባል። ለዚህም ተቋማት በተለይም ሚዲያዎች እንደ ቢቢሲና ሌሎችም ካሉ ዓለምአቀፍ ተቋማት ተሞክሮዎችን በመውሰድ ለአባሎቻቸው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም መመሪያ ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ፣ ጋዜጠኞች ተቋማቸውን ወክለው ለዘገባ ሲሰማሩ ለተቋማቸው መረጃ እንዲያመጡ እንጂ በስማቸው በከፈቱት የግል የማህበራዊ ሚዲያ መረጃውን እንዲለቅቁት አይደለም።
ሆኖም እነዚህ ጋዜጠኞችም ሆኑ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ አመራሮች በማህበራዊ ገጻቸው ስድብና ጥላቻን ሲያስተላልፉ ይታያል። ይህ ደግሞ ግለሰቦቹ ባሉበት ተቋምም ያን መሰል አስተሳሰብ አለ ተብሎ እንዲገመት ስለሚያደርግ የሚዲያ፣ የከፍተኛ ትምህርት፣ የፖለቲካና ሌሎችም ተቋማት የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም መመሪያ ሊያዘጋጁ የግድ ይላል። አክቲቪስቶችም በጥቂቶች እንደሚታየው ሁሉ አክቲቪስትነት ቀላል ሙያ እንዳልሆነ ተገንዝበው ከዚህ መሰል አካሄድ በመውጣት ህዝብና አገርን መሰረት አድርገው ወደመሥራት ቢገቡ መልካም ነው።
በትክክለኛ መረጃ ታግዘውና ዓላማቸውንም ለይተው በሁሉም መስክ አገርና ህዝብን ለማሸጋገር መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ይሄን መሰል አካሄድ ሲለመድም አሁን ያለውን ችግር መሻገር ይቻላል። ይህ የማይሆንና ባለው ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ ግን አገርም ሆነ ህዝብ ከእነዚህ አካላት ከሚያገኙት ጥቅም ይልቅ ጉዳታቸው ያመዝናል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 9/2011
በወንድወሰን ሽመልስ