የፈረንጆቹ ሚያዝያ ወር በገባ ሦስተኛው ሰኞ በሚከበረው የአርበኞች ቀን የሚካሄድ ዓመታዊ ውድድር ነው፤ የቦስተን ማራቶን። ከዓለም አንጋፋ የአትሌቲክስ ውድድሮች መካከል የሚጠቀሰው የቦስተን ማራቶን እአአ 1896 በአቴንስ የመጀመሪያውን ኦሊምፒክ ተከትሎ በቀጣዩ ዓመት (1897) ተጀመረ።
በዓለም አትሌቲክስ ቀዳሚ ደረጃ ከተሰጣቸው ስድስቱ ታላላቅ የጎዳና ላይ ሩጫዎች መካከልም አንዱ ነው። እአአ 2020 በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ውድድሩ ከመሰረዙ ባለፈ ለ124 ዓመታት በተከታታይ ተካሂዷል።
በዓለም ላይ አሉ የተባሉ ዝነኛ አትሌቶች የሚሳተፉበት ውድድሩ ፈጣን ሰዓት ከሚመዘገብባቸውና በአትሌቶችም ዘንድ እጅግ ተመራጭ ከሆኑት የጎዳና ላይ ሩጫዎች መካከል ተጠቃሽ ነው። በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት መሰረዙን ተከትሎ ባለፈው ዓመት ደግሞ ከተለመደው ውጪ ወራትን በማራዘም ነበር የተደረገው።
በዚህ ዓመትም ወደመደበኛ መርሃ ግብሩ ተመልሶ ዛሬ የዓለም ምርጥ የማራቶን ሯጮችን ያፎካክራል። በዛሬው ውድድርም እንደተለመደው በጎዳና ላይ ሩጫ ልምድ ያላቸው ዝነኛ አትሌቶች ይሳተፋሉ፤ የምሥራቅ አፍሪካውያኑ አገራት ኢትዮጵያ እና ኬንያ አትሌቶች ፉክክር ደግሞ በጉጉት የሚጠበቅ ሆኗል።
በወንዶች ዘርፍ በውድድሩ እንደሚካፈሉ ካረጋገጡት አትሌቶች መካከል አምስት የሚሆኑት የግል ምርጥ ሰዓታቸው 2ሰዓት ከ3 ደቂቃ ሲሆን፤ የተቀሩት ደግሞ ከ2ሰዓት ከ10 ደቂቃ በታች በመግባት ፈጣን ሰዓት ያስመዘገቡ ናቸው።
ኢትዮጵያዊው አትሌት ብርሃኑ ለገሰ በዝርዝሩ ውስጥ ስማቸው ከተካተተው ፈጣን አትሌቶች ቀዳሚው ሲሆን፤ እአአ በ2019 የበርሊን ማራቶን የገባበት 2:02:48 የሆነ ሰዓት አለው። አትሌቱ በውድድሩ ብቻም ሳይሆን በማራቶን ከተመዘገቡ ፈጣን የዓለም ሰዓቶች መካከል ሦስተኛው ነው። ይኸውም አትሌቱን የውድድሩ አሸናፊ ሊያደርገው ይችላል የሚል ግምት አሰጥቶታል።
የቫሌንሺያ 2020 ማራቶንን 2:03:00 በሆነ ሰዓት በመግባት የራሱን ምርጥ ሰዓት ያስመዘገበው ኬንያዊው አትሌት ኢቫንስ ቺቤት ደግሞ ቀጣዩ ፈጣን አትሌት ነው። አትሌቱ በተያዘው ዓመት የለንደን ማራቶን የሮጠ ሲሆን፤ አራተኛ ደረጃን በመያዝ ነው ያጠናቀቀው፤ ይኸውም የውድድሩ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆን ማሳያ ነው።
የ2019 የቦስተን ማራቶን አሸናፊው ላውረንስ ቼሮኖም በድጋሚ በውድድሩ እንደሚካፈል አረጋግጧል። አትሌቱ በ2020 የቫሌንሺያ ማራቶን የአገሩን ልጅ ተከትሎ ሁለተኛ የሆነበት 2:03:04 የሆነ ሰዓት የውድድሩ ሦስተኛው ፈጣን አትሌት አድርጎታል።
ያለፈው ዓመት የለንደን ማራቶን አሸናፊው ሲሳይ ለማ እና ክንዴ አጣናው በጥቂት ሰከንዶች የሚበላለጥ ፈጣን ሰዓት አላቸው፤ ለአሸናፊነት ከሚገመቱት አትሌቶች መካከል ናቸው። ሌላኛዎቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለሚ ብርሃኑ እና ሌሊሳ ዴሲሳም ከፍተኛውን የአሸናፊነት ቅድመ ግምት ካገኙት መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው። አትሌቶቹ ያላቸው ፈጣን ሰዓት 2ሰዓት ከ4 ደቂቃ ቢሆንም፣ ከፍተኛ ልምድ አላቸው።
ይኸውም ሌሊሳ ዴሲሳ እአአ 2013 እና 2015 እንዲሁም ለሚ ብርሃኑ የ2016 የቦስተን ማራቶን አሸናፊ በመሆናቸው ነው። በአምናው የቦስተን ማራቶን ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ወጣቱ አትሌት ጀማል ይመርም ቀላል ግምት ከማይሰጣቸው አትሌቶች መካከል አንዱ ነው።
በሴቶች በኩልም በተመሳሳይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸናፊ እንደሚሆኑ በእጅጉ ይጠበቃል። በዚህ ውድድር አንጋፋዋ አትሌት ፋጡማ ሮባ እአአ ከ1997 ጀምሮ በተከታታይ ለሦስት ዓመታት አሸናፊ በመሆን አስደናቂ ታሪክ ማጻፍ ችላለች። እአአ 2014 በአትሌት ብዙነሽ ዳባ የተመዘገበው 2:19:59 የሆነ ሰዓትም እስካሁን ተቀናቃኝ ያላገኘ የውድድሩ ክብረወሰን ነው።
በዚህ ውድድር ከሚካፈሉት መካከል አትሌት ደጊቱ አዝመራው ከፍተኛውን የአሸናፊነት ግምት አግኝታለች። ያለፈው ዓመት የለንደን ማራቶንን ሁለተኛ በመሆን የገባችበት 02:17:58 የሆነ ሰዓትም የአትሌቷ ፈጣን ሰዓት ሲሆን፤ ይህ ሦስተኛ ተሳትፎዋ ይሆናል። የ23 ዓመቷ አትሌት በአምስተርዳም ማራቶን አሸናፊነት የጀመረችውን የጎዳና ውድድር በአዲስ ጉልበትና ብቃት ከክብር ወደ ክብር ትሸጋገርበታለች የሚል ተስፋ አስገኝቶላታል።
እታገኝ ወልዱ እና አባበል የሻነህም ባለፈው ዓመት በቫሌንሺያ እና አምስተርዳም ማራቶኖች ያሳዩትን ብቃት በማሳየት የውድድሩ ምርጥ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑ ይጠበቃሉ።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10 /2014