ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በቢሾፍቱ ከተማ መኮንኖች ክበብ የመዋኛ ገንዳ ሲካሄድ የቆየው የ2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ ውሃ ዋና ሻምፒዮና ትናንት ተጠናቋል። በዚህም አማራ ክልል በሁለቱም ጾታ አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን የውድድሩ ልዩ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።
በውድድሩ ከተሳተፉ ጥቂት ክልሎች አንዱ በመሆን በርካታ ልዑካንና ተወዳዳሪዎችን ይዞ የቀረበው አማራ ክልል በበርካታ ፉክክሮች በግልና በቡድን የሰበሰባቸው ሜዳሊያዎች አጠቃላይ አሸናፊ አድርገውታል። ክልሉ ቀዳሚ ሆኖ ለማጠናቀቅ የቻለው አስራ ስምንት የወርቅ፣አስራ አንድ የብርና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ነው።
አማራ ክልልን ተከትሎ ኦሮሚያ ፖሊስና ቢሾፍቱ ከተማ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው እንዳጠናቀቁ የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ካወጣው የነጥብ አሰጣጥ ደረጃ ለመረዳት ተችሏል።
አማራ ክልል አጠቃላይ አሸናፊ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ የተለያዩ ተወዳዳሪዎቹ በግልና በቡድን የሰበሰቡት በርካታ የወርቅ ሜዳሊያ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በተለይም በተለያዩ ርቀቶች በግሉ አስር የወርቅ ሜዳሊያዎችን የሰበሰበው አትሌት ጥላሁን አያል በቅብብል ውድድርም ሶስት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ከቡድን አጋሮቹ ማሳካቱ ተጠቃሽ ነው። ለዚህም አስደናቂ ብቃቱ የውድድሩ ኮኮብ ሆኖ እንዲመረጥ አስችሎታል።
በተመሳሳይ በውድድሩ ተካፋይ ከሆኑ ጥቂት ክለቦች አንዱ የሆነው ዳዊት ሕንጻ ተቋራጭ አትሌት የሆነችው ብርሃን ደመቀ በርካታ ውድድሮች ላይ በመሳተፍና አስደናቂ ብቃት አሳይታ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች የውድድሩ ኮኮብ በመሆን ልዩ ተሸላሚ እንድትሆን አድርጓታል።
የአማራ ክልል አጠቃላይ አሸናፊ እንዲሆን ያስቻሉት አሰልጣኝ ማንደፍሮ ተገኝ ከልዩ ተሸላሚዎቹ አንዱ ሆነዋል። የኦሮሚያ ፖሊስ ደግሞ የጸባይ ዋንጫውን አሸናፊ ሆኗል።
ውድድሩ ትናንት ሲጠናቀቅ በተለያዩ ርቀቶች የፍጻሜ ውድድሮች ተከናውነዋል። በተለይም ኢትዮጵያ ኦሊምፒክን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በብዛት የምትሳተፍበት የሃምሳ ሜትር ነጻ ቀዘፋ ውድድር በብዙዎች ዘንድ የሚጠበቅ ነው።
ቀደም ባሉት ውድድሮች በርካታ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አስደናቂ ብቃት ማሳየት የቻሉ ዋናተኞች በዚህ ተጠባቂ ውድድር ድል ሳይቀናቸው ቀርቷል። እንደ ጥላሁንና ብርሃን የመሳሰሉ ኮከብ ተብለው የተመረጡ ዋናተኞች በሃምሳ ሜትር ነጻ ቀዘፋ ያሸንፋሉ ተብሎ ቢጠበቅም አልተሳካላቸውም። በወንዶች ኢትዮጵያን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በመወከል ብዙ ልምድ ያካበተው አቻላ ያኮቤ አሸናፊ ሆኗል። በተመሳሳይ በሴቶች በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን የወከለችው ራሄል ፍሰሐ አሸናፊ መሆን ችላለች።
ሻምፒዮናው በዋና ስፖርት ተወዳዳሪዎች መካከል የልምድ ልውውጥ የተደረገበትና ለ2022 አህጉራዊና ዓለም አቀፍዊ ሻምፒዮናዎች ኢትዮጵያን በመወከል የሚወዳደሩ ምርጥ ስፖርተኞች የተገኙበት መሆኑን የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰረት ደምሱ በተለይ ለአዲስ ዘመን በስልክ በሰጡት ቃለመጠይቅ ገልጸዋል።
በውድድሩ የአማራ፤ የጋምቤላ እና የሲዳማ ክልሎች ተሳታፊ ሲሆኑ የድሬዳዋ ከተማ እና የቢሾፍቱ ከተማ ተወዳዳሪዎችም በተለያዩ ፉክክሮች ተሳታፊ ናቸው።በክለብ ደረጃ ዳዊት እምሩ የሕንፃ ተቋራጭ፤ ሳምሶን ውሃ ዋና ስፖርት ክለብ እና ኦሮሚያ ፖሊስ የተሳተፉ ሲሆን፣ አቻላ ያኮቤ በግል ተወዳዳሪ በመሆን አቅርቧል።
‘’ስፖርት ለሰላም ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት’’ በሚል መሪ ቃል የተካሄደው የ2014 ዓ.ም የክልሎች እና የክለቦች የውሃ ዋና ሻምፒዮና እስከ ትናንት ድረስ በተለያየ የውድድር አይነቶች የተካሄደው ይህ ሻምፒዮና፣ በርካታ ፉክክሮች የተስተናገደበትና አሸናፊዎቹ የተለዩበት ሆኗል።
ሻምፒዮናው በዋና ስፖርት ተወዳዳሪዎች መካከል የልምድ ልውውጥ የተደረገበት ፣ ለ2022 አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሻምፒዮና በመወከል ምርጥ ስፖርተኞች የሚመረጡበት እንደሚሆን ታውቋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 /2014