ድንገት እግር ከጣለኝ አንድ ስፍራ በተገኘሁበት፤ ከልጅነቴ ጀምሮ ስሰማው የኖርኩትንና አድጌም ትዝታው ያለቀቀኝን ዘፋኝ በአካል አገኘሁት።
እጅግ ከመደሰቴ የተነሳ ዝለል ዝለል ነበር ያለኝ (እንደ ልጅነቴ)። ተማር ልጄ፣ አዲስ አበባ ቤቴ፣… የማደንቀው አቀንቃኝ አለማየሁ እሸቴ፤ የምወዳቸው ዘፈኖች ናቸው። ታዲያ የምወደውን ሰው ሳገኝ አጋጣሚውን ተጠቅሜ በትንሿ የእጅ ስልኬ ምስላችንን አስቀረሁ። ለዘመን ምስጋና ይድረሰውና የሚወዱትን፣ የሚያደንቁትን ሰውም ሆነ የትኛውንም ነገር ከስልካችን ማከማቸት አስችሎናል። አለማየሁ እሸቴን ልጅ እያለው አባቴ የሚዘፍንበት ቦታ ድረስ ወስዶኝ አይቸው ነበር። ግን ፎቶ ለመነሳት አልቻኩም፤ ምክንያቱም በጊዜው የፎቶ ካሜራ የሚገኘው ፎቶ ቤት አሊያም አንበሳ ግቢ ነበር። ገጠመኜ ልጅነቴን፤ ልጅነቴም ሌሎች ትውስታዎቼን አከታተለብኝ እኮ(ነገርን ነገር ያነሳዋል አይደል የሚባለው)።
አንበሳ ግቢም ብዙ ትዝታዎች አሉኝ፤ እንዲያውም የሚበዙት የልጅነቴ ፎቶዎች እዚያ የተነሱ ናቸው (ከአንበሳ ጋር አለመሆኑ ግን ይታወቅልኝ)። የዚያኔ አብዛኛዎቹ ፎቶ አንሺዎች እዚያ ስለሚገኙ የመስክ ፎቶ ለመነሳት ወደ ስድስት ኪሎ መሄድ የግድ ነበር (ያውም በሳምንቱ ታጥቦ ለሚደርስ ፎቶ)። መቼም የዛሬ ልጆች ይሄንን ሲሰሙ ይደነቁ ይሆናል፤ ያው ካሜራ በእጃቸው ነዋ። ፎቶ ቤትም ቢሄዱ በደቂቃዎች ውስጥ ፎቷቸውን ከእጃቸው ማስገባት ይቻላል። በእኛ ጊዜ ግን አንድ ፎቶ ሳምንት ይፈጅበታል፤ አንዳንዴም ሲታጠብ ሊበላሽና ሊጠቁር ይችላል።
እንዲያም ሲሆን አማራጭ የለም የሆነውን ከመቀበል በቀር። መቼም በእኔ ዕድሜ ያለ ሰው አንበሳ ግቢ ብዙ ትዝታ አይጠፋውም። ስድስት ኪሎ ከሚለው የአካባቢው መጠሪያ በላይም «አንበሳ ግቢ» ሚለው ስሙ በእኛ ዘንድ(በዘመኑ ልጆች ለማለት ነው) ይበልጥ ይታወቃል። ምክንያቱም ቅዳሜና ዕሁድ ለልደት ወይም ለሽርሽር ቤተሰብ አዘውትሮ የሚጓዘው ወደዚያው ነበር። የሐምሌ 19 እና ብሄረ ፅጌ መናፈሻም የወቅቱ መዝናኛዎች መሆናቸውን አልዘነጋሁም። በአንድ ልደቴን ፎቶ ለመነሳት ከቤተሰቦቼ ጋር ወደ አንበሳ ግቢ አቀናን። ፎቶ እንደ ቀልድ ስለማይገኝም ያሉንንና ፎቶ ብንነሳባቸው የምንላቸውን አዳዲስ ልብሶች በሻንጣ ይዘናል።
አንበሳ ግቢ ስንደርስም ብዙ እንደኛ ከቤተሰቡ ጋር ፎቶ ለመነሳት በመጡ ሰዎች ተጨናንቋል። እኛም ፎቶ ለመነሳት የሚሆነንን ስፍራ ብንፈልግም የሰዉ መብዛት ሊያፈናፍነን ስላልቻለ እስኪጨርሱ መጠባበቅ ያዝን። ከፊት ለፊታችን ያለው ፎቶ አንሺም የሚያነሳቸውን ሰዎች፤አንዴ አበባ እያስያዘ… አንዴ ጥድ ስር እየከተተ… ሲሻው ደግሞ ሳር ላይ እያንከባለለ ሲያነሳቸው ቆይቶ «ብርሃን ስለበዛበት ፊልሙ ተቃጠለ» የሚል ምላሽ ሰጥቶ ድጋሚ ለማንሳት ይዘጋጃል። በሌላ ጥግ ያለው ፎቶ አንሺ ደግሞ ልብሳቸውን እየቀያየሩ «እንዲህ አንሳን…ደግሞ እንደዚህ ሆነን…›› በሚሉ የአንድ ቤተሰብ አባላት ትዕዛዝ ተሰላችቷል።
ተነሺዎቹ በያዙት ልብስ ሁሉ ለመነሳት ቆርጠው የመጡ በመሆናቸው የድካም ስሜትም አይታይባቸውም። የታከተው ፎቶ አንሺም የያዘው ፊልም መሙላቱን ሲነግራቸው የቤተሰቡ ንዴት እስከ መተናነቅ አድርሷቸው ነበር። እኛም በተራችን ፎቶ አንሺያችንን ይዘን ወደ ተለቀቀው ስፍራ አመራን። ፎቶ አንሺውም 30 ፎቶ ብቻ እንደሚያነሳንና በፍጥነት እንድንዘጋጅ ነገረን። ሁላችንም ቀድመን በየትኛው ልብስ እንነሳ በሚል ሃሳብ ውስጥ ገብተን ከሻንጣው አንዱን ስናነሳ ሌላውን ስንጥል ረጅም ጊዜ ፈጀን። እንደምንም ከመራረጥን በኋላ አንዳንዶቻችን ቆመን፤ ሌላኛዎቻችን ከቆሙት ስር በርከክ እያልን ለፎቶው ተዘጋጀን።
ያው የድሮውን ካሜራ ታውቁት የለ፤ አንዴ «ብልጭ» ብሎ ምስሉን እስኪይዝ መንቀሳቀስ አይፈቀድም። አንድ ሁለት ፎቶዎች እንደተነሳን ግን አንድ ሰው «ልጆቹን እግራችሁ ላይ አስደግፋችሁ፣ አበባ አስይዛችው፣ ጥዱ አናት ላይ አስቀምጣች… ለምን አትነሱም» የሚል ሃሳብ ሰነዘረ። ይህንን የሰሙት እናትና አባቴም ምክሩን ተቀብለው ሲያቅፉን፤ እሽኮኮ ሲያደርጉን፣ ደግሞ ሌላ የሚመች ቦታ ፍለጋ በሚል ግቢውን በመዞር የደከምነው አይረሳኝም። ያኔ እኮ ፎቶ ለመነሳ ፕሮግራም ተይዞ፣ ልብስ ተሸክፎ፣ ቤተሰብ ተሰባስቦ፤ አንዳንዴም የቤት እንስሳ ተይዞ ነበር።
አረንጓዴ የሆነ እና አበባ በብዛት የሚገኝነት የአትክልት ስፍራ ማግኘትም የግድ ይላል (እንደ አሁኑ እያቀናበረ በሌለንበት የሚያኖረን ቴክኖሎጂ አልነበረማ)። ከዚያማ በዕድሜ፣ በቁመት አሊያም እንደ ቤተሰቡ ሁኔታ አግድም በሰልፍ አሊያም ፊትና በኋላ ከፍና ዝቅ እያሉ መነሳት ነው። አሁንማ ሁሉም ተለውጧል፤ ወደ ፎቶ ቤት የሚኬደው መታጠብ ላለበት ፎቶ ሲሆን ብቻ ነው (በዚህ ምክንያት አልበም ከየቤቱ አልጠፋ ይሆን?)። ጊዜውም የ«የሰልፊ ስቲክ» ነው፤ ፎቶ ለመነሳት በእጃችን ላይ ያሉትን ስልኮች መጠቀም አሊያም በእንጨት መሳዩ መቀሰሪያ ራሳችንን እያየን ምስላችንን ማስቀረት ነው። በዚህ ወቅት አንበሳ ግቢ የሚኬደውም አንበሳ እና ሌሎች እንስሳቶችን ለመጎብኘት እንጂ በዋናነት ፎቶ ለመነሳት አለመሆኑን ሳስብ «አይ ጊዜ» ያሰኘኛል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 9/2011
መርድ ክፍሉ