ፖሊስ መጀመሪያ ሲቋቋም የአራዳ ዘበኛ የሚል ስያሜ ነበረው። በወቅቱ አራዳ የሠለጠነ አካባቢ ስለነበረ እና በደጃች ውቤ ሠፈር በዶሮ ማነቂያ በሠራተኛ ሠፈርና በሰባራ ባቡር አካባቢዎች ውር ውር ስለሚሉ የአራዳ ዘበኛ ተባሉ፡፡ንጉሥ ኃይለሥላሴ በሕግ ዙሪያ ማሻሻያዎችን ወስደው ነበር። የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ እንዲወጣ፤ በእንግሊዞች የሰለጠነ ዘመናዊ ፖሊስ መሠረቱ፡፡እነዚህም አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች ነበሩ፡፡ቀይቶም በከተሞችና በኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር መስመሮች ፖሊሶች እንዲሠማሩ ተደርጎ ነበር፡፡
አገልግሎቱን ለማዘመን የተደረገው ጥረት ቀጥሎ በኮልፌ ልኳንዳ ፈጥኖ ደራሽ የሚባለው የፖሊስ ማሠልጠኛ ካምፕ ተቋቋመ፤ የደቡብ አፍሪካ የነፃነት ታጋይና በኋላም የሀገሪቱ መሪ የነበሩት ኔልሰን ማንዴላ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን የሰለጠኑበት እንደነበር “Long walk to freedom” ማለትም ረጅም ፍኖት ለነፃነት በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፋቸው ጠቅሰዋል፡፡
መንግሥት ኃላፊነት የሚረከበው የዜጎች ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ነው። ዜጎች ሰላምና ደህንነት ሲጠበቅ ሠርተው ይኖራሉ ፣ወልደው ይስማሉ፣ ዘርተው ይቅማሉ ። ይቅማሉ ስል ወልዳችሁ ሳሙ፣ ዘርታችሁ ቃሙ ከሚለው የአዛውንቶች ምርቃት ተነስቼ ነው ፤እንጂ ጫት ቃሙ አለማለቴን አስቡ።
ከጮሌዎችም ከ‹ጨዋዎችም› ወገን ጫት የሚቅሙ መጠጥ የሚቀመቅሙም አሉ። ስለሚቀመቅሙ ካነሳን ዘንዳ ልብስም የሚቀመቅሙ ባለሙያዎች መኖራቸውን አንዘንጋ። ቤታቸውንም ከብታቸውን ውበታቸውን ንጽህናቸውን በየመስካቸው ጠባቂዎች አሉ፡፡ ከላይ ያነሳነውን የዜጎች የሰላምና ደህንነት ጠባቂዎች የሆኑትን ፖሊሶችን ሳንዘነጋ ነው።
የጠቀስናቸው ነገሮች ሁሉ የሚተገበሩት ሰላም እና ደህንነት ሲኖር ነው፡፡ፖሊስም በየአካባቢው የሚሠማራው የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ፣ወንጀለኛን ለመግታት ነው፡፡ማለትም ዜጎችን ከሌቦችና ከቀማኞች እየጠበቀ በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲገቡ ትልቅ አስተዋፅዖ አለው፡፡
የፖሊስ ግርማ ሞገሱ የደንብ ልብሱ ነው። አይደለም መሣሪያ ሳይታጠቅ ዱላውን ሳይጨብጥ ልብሱን አይተው የሚበረግጉ ሌቦችና ወንጀለኞች አሉ፡፡
ነገር ግን በቁንጽሉ አዲስ አበባን ስናያት በተለይ በምሽት ሕዝብ በሚበዛባቸው ዋና ዋና አደባባዮች ፖሊሶች የሉም ማለት ይቻላል፡፡ምግብ ቤቶች በጊዜ ይዘጋሉ። ምግብ በመብላት የሚናፍቀው አርሶአደርም ወዛደርም ላጤም ፀጉሩን እያከከ ይሄዳል ፤አማራጭ አጤ ይሆናል። ለምንድነው በጊዜ 3 ሰዓት ሳይሆን የምትዘጉት ያልኳቸው የምግብ ቤት አስተናጋጆች የሰጡኝ ቀኑን ሙሉ የሠራንበትን ገንዘብ ወጥተን ማለትም ወደ ቤት እየሄድን ሳይሆን እዚህ ሆነን በላተኛ መስለው ገብተው ገንዘቡን ይረከቡናል ። ገንዘብ ከመረከብ በዘለለ ለሕይወታችንም ስንሰጋ በጊዜ እየዘጋን መሄድን መረጥን ብለውኛል፡፡
አንዳንድ ጭፈራ ቤቶችና ቡና ቤቶች መግቢያቸውም ላይ ጥበቃ ስለሚያስቀምጡ ደንበኞቻቸውን የሚተናኮል አይገኝም። ሲመሽ ዶሮ በጊዜ ወደ ቆጥ እንደምትወጣው ሁሉ ሰውም ሌቦችና ቀማኞችን ፈርቶ በጊዜ ወደ ቆጡ (መኝታው) ይወጣል፡፡የዚሁ ነገራችን አንዱ ጣጣም የኪስ ስልኮች የመቀማት ልምድ መስፋፋት ነው፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ ወጣቶች ተኮልኩለው ሰዎች የያዙትን ስልክ በማየት አመቺ አጋጣሚ ሲያገኙ ይቀሙና ይሠወራሉ፡፡በጠቀስኩት ዕኩይ ተግባር የሚታወቁ ሠፈሮች አሉ፡፡በአንፃሩ አንዳንዶች ደግሞ በየጊዜው የሚሠረቅ ገንዘብና የኪስ ስልክ ቀማኞችን ለመግታት ነዋሪዎች ተደራጅተው የአካባቢው ታዳጊ ወጣቶችን አነጋግረው ሰላምና ፀጥታ የፈጠሩ ቀማኞችን ያራቁ አሉ፤እነዚህ ሊመሰገኑ ይገባል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ የደንብ ልብስና አርማውን መለወጡ እንዳለ ሆኖ ቸልተኛ እና ዘገምተኛ አሠራሩንም መለወጥና ማስተካከል አለበት። የደንብ ልብስ ስለተለወጠ ለውጥ አይመጣም። ፖሊስ ምሽት ላይ ስለማይታይ ታክሲዎች የአምስት ብሩን መንገድ 15 ብር ይጭናሉ። ሰው ደግሞ ለደህንነቱ እየሰጋ የማይከፈለውን ከፍሎ ቤቱ ይሄዳል፡፡ጎበዝ በሥፍራው የትራፊክ ፖሊስ አልያም ፖሊስ ቢኖር ይደረግ ነበር? ጥያቄውን ለናንተ ልተወው፡፡
ከሦስት ዓመት በፊት አንድ ታዳጊ ኳስ ዐይቶ ወደ ቤቱ አምስት ሰዓት ሲመለስ ቤቱ ፎቅ ላይ ስለሆነ ክፈቱልኝ ለማለት ስልክ ደወለ፤ የመርካቶ መሳለሚያ ዋናው አስፋልት ዳር በር ሲያንኳኳ የኪስ ስልኩን ያዩ ሰዎች ወግተውት ስልኩን ይዘው ተሠወሩ፡፡ቤተሰብ በር ሲከፍት ልጃቸው ወድቋል፤ደንግጠው ወደ ሆስፒታል ቢወስዱትም ሕይወቱን ማትረፍ አልተቻለም፡፡በአካባቢው ዞር ዞር የሚል ፖሊስ ቢኖር ይህ ድርጊት አይከሰትም ነበር። ቀማኞችም በርትተዋል ፤ይህም ባለቤቱን ካልናቁ አይነት ይመስላል፡፡
በቅርቡም በመሳለሚያ እሳት አደጋ አካባቢ ከንጋቱ 1 ሰዓት መኪኖች ተጋጩ፡፡የመኪኖች ግጭት እንጂ የተጎዳ ሰው አልነበረም። በዚህም በተፈጠረ የትራፊክ መጨናነቅ ሆነ ለ20 ደቂቃ ያህል ወደ መርካቶ፣ አራዳና አካባቢዎች የሚሄዱ ተሽከርካሪዎች ቆመው ቀሩ፡፡ይህ ሁሉ ሲሆን ፖሊስም ትራፊክ ፖሊስም አልነበረም፡፡ዘግይቶ የትራፊክ ፖሊሱ ሲመጣ ግን የትራፊክ መጨናነቁ ተወገደ።
የሚያስቁኝን የፖሊስ እንቅስቃሴዎች ልጥቀስ ፤በየአካባቢው አስፋልት ዳር የሚነግዱ ነጋዴዎችን እኮ ሲያባርሩ ለማየት አንዳፍታ መርካቶ ሜክሲኮ እና መገናኛ አካባቢዎች ማየት ይቻላል፡፡ሰዎቹ የሚሠሩ እንደመሆናቸው መጠን ጥግ ጥግ ይዘው ወደ አስፋልት ሳይወጡ እንዲሠሩ ማድረግ ነው፡፡ገቢዎች ቢሮም የራሱን አማራጭ ፈልጎ ሥርዓት ማስያዝ ይችላል። የፖሊስ ዋነኛ ሥራ ወንጀል መከላከል ተፈጽሞም ከሆነ መርምሮ ለሕግ አካል ማቅረብ ነው። ማምሸትን የሚጠየፉት ፖሊሶቻችን ቀን ቀን ሠራተኛን ሲያባርሩ ይታያሉ ይሄስ ተገቢ ነው? ምሽት ላይ ግን አይታዩም፤ የፌዴራል የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ፖሊሶች ያሉባት ከተማ ምሽት ላይ ፖሊሶች ማምሸትን ተጠየፉ ወይ ያስብለናል። አንዳንዴ ወደ ፒያሳ እና አውቶቡስ ተራ በየመንገዱ ጥግ ተገጥግጠው የሚሳድራቸውን ወንድ የሚጠብቁትን ሴቶች ሲያባርሩ ይታያሉ፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን በየሠፈሩ ኮሚኒቲ ፖሊሲ ተብሎ የተወሰኑ የተደራጁ ቡድኖች አሉ፡፡ቀን ቀን ባለችው ጠባብ ቢሮ ይውላሉ፤ነገር ግን ነዋሪዎችን አደራጅቶ ወንጀል ለመከላከል ተደራጅተው የሚጠብቁበት በየመንደራቸው መብራት ሊያበሩ የሚችሉበትን መንገድ ማሳየት ያስፈልጋል። የኮሚኒቲ ፖሊስ ብቻውን ያመጣው ውጤት ብዙውም ዐይታይም፡፡ግን በየሠፈሩ እየዞሩ መብራት አብሩ ብለው አካባቢውን እየዞሩ ይቆጣጠራሉ፡፡ይህ በራሱ መበረታታት አለበት።
በሸገር ባቡር ከምሽቱ 2 ሰዓት በኋላ ሥራ ያቆማል አንበሳ አውቶቡስም ተመሳሳይ ነው። ሰው በሥራና በተለያየ ምክንያት አምሽቶ ወደ ቤቱ ለመሄድ ትራንስፖርትም አጥቶ በእግር ለመሄድም ፈርቶ የሚታይ ፖሊስ አጥቶ መንከራተት የለበትም። ባቡርም አውቶቡስም የአገልግሎት ሰዓታቸውን ፈቅ በማድረግ ለነዋሪው አለሁልህ ይበሉት።
ከላይ የጠቀስኩት የሸገር የፖሊሶች ዝርክርክ አሠራር ግን እንዲስተካከል እንሻለን፡፡ማምሸትን የሚጠየፉት ፖሊሶቻችን የደንብ ልብሳቸውን ለብሰው በየመሸታ ቤቱ ያምሹ እያልኩ አለመሆኑን ከላይ ያነሳሁላቸው ነጥቦች ይናገራሉ፡፡ፖሊሶች የተቀጠሩት ካምፕ ውስጥ አልያም ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ በምሽት ሊቀመጡ አይደለም። ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ አምሽተው የሚጠበቅባቸውን ሥራ የሚሠሩ አሉ ፡፡እየወጡ የሚሠሩ አሉ። ለሰዎች ሲታዩ ሌባው እራሱ ፍርሃት ፍርሃት ስለሚለው አካባቢውን ጥሎ ይሄዳል።
የሰረቁና ወንጀል የፈጸሙ አካላት ፖሊሶች እንደያዙዋቸው ያውቃሉ፡፡ወንጀል የፈጸሙ ፖሊስ ሲያያቸው ፍርሃት ፊታቸው ላይ የሚነበብባቸው ናቸው፡፡በዕለቱ የት የት ደርሰው እንደነበር ተነጣጥለው ሲጠየቁ አራምባና ቆቦ ምላሽ የሚሰጡ ከሆነ፤ ችግር እንዳለባቸው ፖሊስ ያውቃል። በቀላሉ ይያዛሉ፤ምርመራው ሲጣራ ደግሞ ከዚያ የበለጠ መረጃ ይኖራል፡፡የፖሊሶቹ ትጋት ታክሎበት በተለያዩ ክልሎች የሚሰሙ የፀጥታ ችግሮች ፤በሸገር ሳይደርስ እናስቀር በሚል ነው፡፡ፖሊስ የሰላም ዘብ፣ የህዝቦች ምርኩዝ እና አለኝታ ነው።
ይህን ስል ፖሊሱ በመደበኛ ሥራው የሚጠበቅበትን ግዴታ እየተወጣ ነው አለማቴን ከግምት አስገቡልኝ፡፡የፖሊስ ሥራ ቀኑን ሙሉ እና እረፍት የለሽ ነው፡፡በሰዓታቸው ለተረኛ ፖሊሶች ሥራውን ይቀየራሉ፡፡ቀማኛዎችን ማስወገድ የሚቻለው ፖሊሶች ግን በጎዳናዎች በእግርም ሆነ በመኪና ሲንቀሳቀሱና አካባቢውን ሲቃኙ ነው፡፡ፖሊሶች በምሽት በዋና ዋና ጎዳናዎች በእግር ዞር ዞር እያሉ ከተማውን ይቃኙ። ፖሊሶች በምሽት መጠለያ ጣቢያዎች ብቻ ቢታጨቁ ችግሩን መቅረፍ አይቻልም።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2014