ሰሞኑን ወሬው ሁሉ ስለ ዘይት ሆኗል። ዘይት ይህን ያህል ብር ገባ፤ መንግሥት ይህን ያህል ሚሊዮን ሊትር ዘይት ከውጭ ሊያስገባ ነው፤ ይህን ያህል ሊትር በሸማቾች በኩል ለሕዝብ ተሰራጨ፤ ይህን ያህል ዘይት እና ስኳር በሕገወጥ መልኩ ተከማችቶ ተገኘ ወዘተ.. የሚሉ ዜናዎች በስፋት እየተሰሙ ከርመዋል። ከሁሉም ዜናዎች ግን ጎልቶ እየተሰማ ያለው ይህን ያህል ሊትር ዘይት እና ስኳር በሕገወጥ መልኩ ተከማችቶ ተገኘ የሚለው ነው። ይህን ዜና በተደጋጋሚ እየሰማነው ነው። ዘይቱ እና ስኳሩ በየክፍለ ከተማው፤ በየከተማው፤ ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው ሲጋዝ ወዘተ ነው፤ የሚያዘው። እንኳንም ተያዘ። መልካም ነው።
ነገር ግን ይህ ዜና በተደጋጋሚ ሲነሳ ከማስደሰት ባለፈ ጥያቄን ይቀሰቅሳል። ይሄ ሁሉ ዘይት እና ስኳር በመጀመሪያ ደረጃ እንዴት አንድ ሰው ጋ ሊከማች ቻለ? እስካሁን እንዴት ሳይታወቅ ከረመ? አሁን ከምን በመነሳት ነው እንዲህ በአንድ ጊዜ የተደበቀው ሁሉ መገኘት የጀመረው? ማነው ደባቂው? ማነው ጠቋሚው? እስከዛሬ በዚህ መሰል ጉዳይ የተያዘው ምርት የት ገባ? ደባቂዎቹስ ምን ተፈረደባቸው? ወዘተ …የሚሉ በርካታ ጥያቄዎችን እንድናነሳ እንገደዳለን።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ እንደራሴዎች ፊት ተገኝተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ለኢትዮጵያ ሕዝብ አገልግሎት በውጭ ምንዛሬ የተገዛ ነዳጅ በራሳችን ቦቴ እየተጫነ በጎረቤት አገራት ገበያ ላይ እንደሚቸበቸብ ተናግረዋል። ነዳጅ ከአገር እየተጫነ ሲወጣ መቼም በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ካሉ ሰዎች አንዱ እንኳን አላየውም አይባልም። የደህንነት መዋቅሩ፤ ጉምሩኩ፤ ፖሊሱ፤ ሚሊሻው፤ ሕዝቡ እነዚህ ሁሉ የማየት ግዴታ አለባቸው ፤ አይተዋልም። ነገር ግን ማንም ምንም ስላላለ ቦቴን የሚያህል ግዙፍ መኪና ቀበሌዎችን ፤ ወረዳዎች ፤ ዞኖችን ፤ ከተሞችን ፤ ክልሎችን እንዲሁም ድንበርን አቆራርጦ ጎረቤት አገር ይቸበቸባል።
ይህ አሳፋሪ ውንብድና ነው። በአገር ላይ የሚደረግ ደባ። ነገር ግን ይህ ዘመን አመጣሽ ባህል ነው። በተለይም ባለፈው ክፍለ ዘመን በትውልድ ላይ የተፈጠረው የሞራል መናጋት የፈጠረው ችግር ነው። የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው የሚል በማንኛውም መንገድ ብቻ መክበርን አላማ ያደረገ የውንብድና ባህል በአገር ደረጃ ስር ሰድዷል። መገለጫው ብዙ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነዳጁን ተናግረዋል። የሱ ተቀጥላ የሆነ የዘይት ፤ ስኳር ፤ ዱቄት እና መሰል ውንብድና ደግሞ በመሀል አገር ተጧጡፎ በዓይናችን እያየን ነው።
ያ ሁሉ ጀሪካን ዘይት፤ ያ ሁሉ ኩንታል ዱቄት፤ ያ ሁሉ ኪሎ ስኳር ሚሊዮን ሕዝብ ቀን ከሌሊት በሚተራመስባት እና ጠንካራ የጸጥታ መዋቅር ባለባት ከተማ ውስጥ ጭድ ውስጥ እንዳለ መርፌ ይደበቃል። እንዴት ይህን ድርጊት ወረዳው፤ ክፍለከተማው ፤ ፖሊሱ ፤ ፌዴራል ፖሊሱ ፤ ደህንነቱ እና ሕዝቡ ሳያዩ ተከማቸ? እርግጥ ነው በየዜናው እንደምንሰማው እነዚህ በሕገወጥ መልኩ የተከማቹ ግብአቶች ቀን በቀን ሲገኙ እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው የመንግሥት አካላት ተባብረው እንደሚይዟቸው እንሰማለን። ነገር ግን ዋናው ጥያቄ መጀመሪያውን ተጭነው
ከተማ ሲገቡ እና አለቦታው ሲራገፉ መዋቅሩ እንዴት አላስተዋለም? የሚል ነው። ወይስ መዋቅሩ ራሱ እያገዛቸው ነው ይህ ሁሉ የሚሆነው? በመዋቅሩ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ለግል ጥቅማቸው አልያም ለፖለቲካ አላማቸው መሳካት እንዲህ ዓይነት ተግባር ውስጥ ሊሳተፉበት የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው። ከዚህ ቀደምም እንዲህ ዓይነት ልምድ እንዳለ በተደጋጋሚ ታይቷል። ከለውጡ በፊት፤ በለውጡ ሰሞን እና ከለውጡ በኋላ የንግድ ሳቦታጅ ማድረግ አንድ የትግል ስልት ሆኖ ቆይቷል። አሁንም ይህ ክስተት ያለ የሚመስልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በአገሪቱ ውስጥ በበቂ ሁኔታ ክምችት አለባቸው የተባሉ ነገሮች ሁሉ ከመቅጽበት ከገበያ ጠፍተው የምርት እጥረት የሚከሰተው በሳቦታጅ ነው። አሁንም በየመጋዘኑ ተገኘ የሚባለው ምርት የነጋዴ የስግብግብነት ምልክት ብቻ ሳይሆን የሳቦታጅ መገለጫ ሊሆንም ይችላል።
ልብ ሊባል የሚገባው የዘይቱን መገኛ ብቻ ማወቃችን ችግሩን እንደማይቀርፈው ነው። ከመገኛው ባልተናነሰ እንዲያውም በበለጠ ሁኔታ በመጀመሪያ ደረጃ ዘይቱ እዚያ ጋ ለምን እና እንዴት ደረሰ? የሚለውን ካላወቅን የችግሩን ስሩን ሳይሆን ቅርንጫፉን ብቻ ነው ያገኘነው ማለት ነው። የዘይት ወይም የስኳር ወይም የሌሎች የፍጆታ ዕቃዎች በየመጋዘኑ መደበቃቸው፤ ወይም በፋብሪካዎች ምርት እንዲቆም መደረጉ፤ አልያም ገበያ ላይ መድረስ ከነበረባቸው መጠን በታች እንዲደርሱ መደረጉ ኢኮኖሚያዊ አሻጥር ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ሴራም ሊሆን ይችላል።
እነማን ስኳር እና ዘይትን ለፖለቲካዊ አሻጥር ሊጠቀሙበት ይችላሉ ለሚለው ብዙ መላምት መስጠት ይቻላል። ከአገር ውስጥ ተቃዋሚዎች እስከ የውጭ መንግሥታት በብዙ ምክንያት የአገሪቱን አለመረጋጋት ሊፈልጉት ይችላሉ። ለዚህም ቀላሉ እና ሁነኛው መላ ኢኮኖሚውን ማዳከም እና ድሀው ሕዝብ ኑሮ እንዲከብደው ማድረግ ነው። በዚህ መንገድ ሕዝቡ መንግሥት ላይ ምሬት እንዲሰማው ማድረግ ከዚያም የተራበ ሕዝብ መሪውን ይበላል እንዲሉ ሕዝብ የገዛ መንግሥቱ ላይ እንዲነሳ እና ነውጥ እንዲፈጥር ማድረግ ሊሞክሩ ይችላሉ።
እነዚህ ኃይሎች ለዚህ ሥራቸው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ደጋፊዎች ያሏቸው ሲሆን እነዚህን ባለወንበር ተላላኪዎቻቸውን ከስግብግብ ነጋዴዎች ጋር አንድ ላይ አጣምረው ኢኮኖሚውን ሊያናጉ ይችላሉ። እንደ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያለ ጠንካራ መሠረት የሌለው ኢኮኖሚ ደግሞ እንዲህ ዓይነቱን ጫና ለመቋቋም ስለሚከብደው ቶሎ ችግር ውስጥ የመግባት ዕድሉ የሰፋ ነው። አሁን ያለንበት ሁኔታም እንደዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ የገባን የሚያስመስል ነው።
ስለዚህም አሁን ዘይቱ፤ ስኳሩ እና መሰል ነገር ተገኘ ሲባል ከመገኘቱ ደስታ ባለፈ እንዴት እንዲህ ሊደበቅ ቻለ፤ እነማን ለምን አላማ ደበቁት የሚለውን መለየት እና የሚገባቸውን ዋጋ መስጠት ይገባል። አልያም ነገሩ ሁሉ ውሀ ቅዳ ውሀ መልስ ይሆናል። የዘይት መደበቅ እና መያዙን በስፋት ከአገር ደህንነት አንጻር መመልከት ለነገ የማይባል ሥራ ነው።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2014