በእናት መንገድ የበጎ አድራጎት ማህበር በአዳማ ከተማ 2010 ዓ.ም በወጣት ምህረት አበበና በወጣት ቤዛዊት ግርማ ሃሳብ አቅራቢነት የተመሰረተ ነው። በወቅቱም በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ትምህርት መማር ያልቻሉ ህጻናትን በማሰባሰብ ነበር ስራቸውን የጀመሩት።
በአሁኑ ወቅት ማህበሩ በርካታ ህጻናት በመመገብ በማልበስና በማስተማር ላይ ይገኛል እኛም የማህበሩን አመሰራረትና የአራት አመታት ጉዞ የማህበሩን ፕሬዚዳንት ወጣት በላይ ደመቀን አነጋግረን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ወጣት ምህረት አበበ ኢተያ በምትባል በአርሲ አካባቢ በምትገኝ አንዲት አነስተኛ ከተማ የተወለደች ሲሆን ቤተሰቦቿ ወደ አዳማ ከተማ በመሄዳቸው አብዛኛውን የልጅነት ጊዜዋን ያሳለፈችው በአዳማ ከተማ ነው።
አዳማ ከተማ ጎሮ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመማር ላይ እያለች ደግሞ ጎረቤቷ ለእንግድነት ከመጣች አንዲት ቤዛዊት ግርማ ከምትባል ወጣት ጋር ለመተዋወቅ ትበቃለች። ምህረት የቋንቋ ትምህርት ቤት እያለች በአንድ ወቅት በአዳማ ከተማ የሚገኝን « ሴዴቂያስ » የሚባል የአረጋውያን መርጃ የበጎ አድራጎት ድርጅት ለመጎብኘት እድሉን ታገኛለች።
በወቅቱ ከአረጋውያኑ ጋር ጥሩ ጊዜ አሳልፋ የነበረ ቢሆንም ያየቻቸው ነገር በጣም አሳዝኗትና ወስጧን ነክቷት ስለነበር የሆዷን በሆዷ ይዛ ነበር ወደ ቤቷ የተመለሰችው።
ከዚህ ጊዜ አንስቶ በሰላም ስለሚኖሩት ብቻ ሳይሆን በችግር ውስጥ ስላሉትም ማሰብ ትጀምራለች። የሀሳቧ መዳረሻና እርዳታና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ብላ የለየቻቸው ደግሞ በገባች በወጣች ቁጥር በየጎዳናው ዳር በእንግልትና በስቃይ ውስጥ ሆነው የምታያቸውን ህጻናት ልጆች ነበር።
በአንድ ወገን እሷ ከምግብ እስከ ልብስ ሌሎችም አስፈላጊ ነገሮች በሙሉ እንዴት እየተሟሉላት እንዳደገች እያሰበችም የእነዚህ ህጻናት አሁን ያሉበት ሁኔታ ብሎም የነገ እጣ ፈንታቸው ያሳሰስባት ነበር።
በሌላ በኩል ደግሞ ምንም ልታደርግላቸው ስላልቻለች ራሷን ትወቅስም ልቧም ይነካ ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆና የአስረኛ ክፍል ፈተና ወስዳ ውጤቷን እየተጠባበቀች እያለች አንድ አዲስ ነገር ይፈጠራል። አንድ ቀን ከጓደኛዋ ቤዛዊት ጋር እደጃፍ ላይ ቁጭ ብለው እየተጨዋወቱ ሳለ እልቧ ውስጥ ስላስቀመጠችው የህጻናቱ ጉዳይ ለጓደኛዋ ሹክ ትላታለች።
ቤዛዊትም ቀድሞም እንደዚህ አይነት ሀሳብ እሷም ውስጥ እንደነበር በመግለጽ የሚያስቡትን ያህል እንኳን ባይሆን የአቅማቸውን ያህል ሊሰሩ እንደሚችሉ ሹክ ትላታለች። በቀናት ልዩነትም አንድ በላይ ደመቀ የሚባል ጓደኛቸውን ያናግሩትና እሱም በሀሳባቸው ስለተስማማ አባላት ወደ መሰብሰብ ይገባሉ።
ወዲያውም አስራ አምስት ፈቃደኛ የበጎ ስራ ተሳታፊ ወጣቶችን በማግኘታቸው ራሳቸውን አደራጅተው በበላይ አስተባባሪነት በየቤቱ በመሄድ ድጋፍ ማሰባሰብ ይጀምራሉ።
ችግሩ ለነገ የሚባል አልነበረምና ገና በመጀመሪያው ዙር ባሰባሰቡት ገንዘብና ቁሳቁስ በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን ያቋረጡ አስራ ሶስት ህጻናትን በማህበረሰቡ ጥቆማ በማሰባሰብ ያቋረጡትን ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ያደርጋሉ። ይህቺ አጋጣሚ ደግሞ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ እጅግ ተቀባይነት ስለስገኘላቸው ሁሉም ትኩረቱን ወደእነሱ ላይ ማድረግ ይጀምራል።
እናም ከአካባቢው ነዋሪዎች ያላቸው በገንዘብና በቁሳቁስ የሌላቸው ደግሞ፤ ወጣቶች በሞራል አረጋውያንና በምርቃት ሲደግፏቸው እነ ምህረትም ይህንን ነገር አጠናክሮ ለመቀጠል «ህብረት ለበጎ» በሚል ስያሜ አባላት በማሰባሰብ ስራቸውን ይቀጥላሉ። በዚሁ ወቅት ደግሞ ሌላ ራእያቸውን የሚያጠናክር እነሱን ደግሞ በጽኑ የሚፈትን አጋጣሚ ይፈጠራል።
በሁለት ሺ አስር አመተ ትምህርት መጨረሻ ላይ የሰፈር ሰዎች አንዲት ወላድ እናት ሰፈራቸው ባለጤና ጣቢያ አካባቢ በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደምትገኝና የእነሱን አለሁ ባይነት እንደምትሻ ይነግሯቸዋል። ምህረትና ሌሎች ሁለት የማህበሩ አባላት በመሆን ሴትየዋ ያለችበትን ሁኔታ ለማየትና እግረ መንገዳቸውንም እነሱ ምን ሊያደርጉላት እንደሚችሉ ለመለየት ወደዛች ችግርተኛ እናት ያቀናሉ።
እውነትም የተባሉት ቦታ ሲደርሱ አንዲት አራስ ልጅ የያዘች እናት በሚያሳዝን ሁኔታ ውስጥ ሆና ያገኟታል። እነሱም በጥልቅ ሀዘን ውስጥ ሆነው እንዴት በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ልትገኝ እንደቻለች ይጠይቋታል። ያቺ እናትም የደረሰባትን ነገርና አሁን ያለችበትን ሁኔታ እንደሚከተለው ታጫውታቸዋለች።
«ከቤተሰቦቼ ጋር እያለሁ አንድ የማፈቅረው ጓደኛ ነበረኝ፤ ቤተሰቦቼ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንድሆን አይፈልጉም ነበር፤ ይባስ ብለው ጓደኛዬን እንድረሳው እንድተወው በማሰብ ከሌላ ወንድ ጋር እንድሆን ሲያደርጉኝ ሳይታሰብ አረገዝኩ። ከዚህ በኋላ ቤተሰቦቼም ማርገዜን ሳያውቁ ከቤት ጠፋሁ፤ ከቤት የጠፋሁት ሳላገባ በማርገዜና እንደዚህ አይነት ነገር ከተሰማ የአካባቢው ነዋሪ እኔን ብቻ ሳይሆን ቤተሰቤንም ስለሚያገለን ነው፤ ከእቤት ከጠፋሁ በኋላ የተለያዩ የጉልበት ስራዎችን እየሰራሁ ቆይቼ እርግዝናዬ እየገፋ ሲመጣ ስራ መስራት ስላልቻልኩ በሰዎች ጠቋሚነት ወደ አዳማ ከተማ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ብሄድ ድጋፍ እንደማገኝ ተነግሮኝ ወደዛው አቀናሁ። ነገር ግን አዳማ ከተማ እንደደረስኩ የሴቶች ጉዳይን ከማግኘቴ በፊት ምጤ ቀደመና መንገድ ላይ ወደቅሁ። በዚህ ወቅት አንድ ለነፍሴ ያለ የባጃጅ ሹፌር ወጣት ልጅ አዳማ ቢሾፍቱ ጤና ጣቢያ አደረሰኝ።
እዛም ደርሼ በሆስፒታሉ አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎልኝ ወንድ ልጅ በሰላም ለመገላገል በቃሁ። በፈጣሪ ፈቃድ በሰላም ብገላገልም ከወሊድ በኋላ ያለው ሕይወቴ ግን ተመልሶ ጨለማ ሆነብኝ ጤና ጣቢያውም ሊያደርግልኝ የሚችለውን አድርጐልኝ ነበር። አሁን ግን የሚያርሰኝ ሰው ከጎኔ የለም። የምበላው የምለብሰውም የለኝም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለሁት» ስትል ታጫውቷቸዋለች።
እነ ምህረትም በሀዘን ውስጥ ሆነው የመጀመሪያ ስራቸው ያደረጉት ወደ ቤታቸው በመመለስ ቤተሰብና ጎረቤት በማስተባበር አጥሚትና ሌሎች ምግቦችን እንዲሁም ልብሶች በማዘጋጀት የመጀመሪያ እርዳታቸውን ማድረግ ነበር። ይህንን ካደረጉ በኋላ በሁለተኛው ቀን መስከረም አንድ አውደ ዓመትና ዘመን መለወጫም ስለነበር በዓልን ከእሷ ጋር ለማሳለፍ ወደዛው ያቀናሉ።
በዚህም ቀን እንዳለፈው ሁሉ ሙሉ ምግብ የበዓልንም ጨምሮ እንዲሁም ሌሎች እቃዎችንም ይዘው ሲሄዱ ያቺን እናት በአስደንጋጭ ሁኔታ ውስጥ ሆና ያገኟታል።
ሴትየዋ በጣም ደክማ ልጇንም ማጥባት የማትችለበት ደረጃ ላይ ደርሳ ነበር፤ ህጻኑም ምግብ ባለማግኘቱ ያለማቋረጥ ያለቅስ ነበር። እቤት ተመልሰው ለእናትየውም ለልጁም ገላ ማጠቢያ የሚሆኑ ነገሮችን ይዘው ይመለሳሉ።
እዛ ከደረሱ በኋላ ግን ሲያስቡት ለካስ ሁለቱም የህጻን ልጅ ገላ ማጠብ አይችሉም ነበር። ነገር ግን ሌላ ሰው ፍለጋ ሲንቀሳቀሱ የሚያልፈው ጊዜ መባከን ስለሌለበት እንደምንም በጥንቃቄ ልጁንም እናትየውንም ገላቸውን አጥበው ልብሳቸውን ቀይረው በተወሰነ ደረጃ ወደነበሩበት ለመመለስ ይበቃሉ። እናትም ከነበረችበት ስለነቃች ምግብም መብላት ልጇንም ማጥባት ትጀምራለች።
ከዚህ በኋላ ያደረጉት ግን አሁን ባሉበት ሁኔታ ቢቆዩ ለእናቲቱም ሆነ ለልጇ ጥሩ ሁኔታ ስለማይፈጠርና ሌላ ሁለቱንም ተረክቦ ሊንከባከብ የሚችል ስላልነበር ከቤተሰብ ጋር ማስታረቅ ነበር። ጉዳዩ እንዲህ በቀላሉ የሚከወን ባይሆንም ከብዙ ልፋትና ልመና በኋላ ሁለቱንም በማስማማት እንዲታረቁና እናትም ልጇን ይዛ ቤተሰቦቿን እንድትቀላቀል ለማድረግ ይበቃሉ።
ነገር ግን አንዳንድ ችግሮች ደግመው እንዳይከሰቱ በማሰብም እነምህረት ቤተሰቦቿና እሷ ጋር በየሁለት ቀኑ በመደወል ያለውን ነገር ይከታተሉ ነበር። ያቺ እናት እነምህረት ላደረጉላት የነፍስ አድን በጎ ተግባር ውለታ ባይሆናቸውም ለስማቸው እንዲሆን ብላ ለልጇ ስም እንዲያወጡላት ትጠይቃቸዋለች። እነሱም እግዚአብሔር ረዳቴ ነው ሲሉ አቤኔዜር ብለውት እናትና ልጅ ዛሬም ድረስ በጥሩ ጤንነትና ፍቅር ከቤሰተቦቻቸው ጋር በመኖር ላይ ይገኛሉ።
የማህበሩ አባላት ፈቃድ አውጥተው በህጋዊ መንገድ መንቀሳቀስ ከመጀመራቸው በፊት እርዳታ በሚያሰባስቡበት ወቅት እንዳጭበርባሪ በመታየት በርካታ ችግሮች ገጥመዋቸዋል።
በአንድ ወቅት አስር የማህበሩ አባላት በህግ ቁጥጥር ስር ውለው በቤተሰቦቻቸው ዋስትና ነበር ለመለቀቅ የበቁት። እነዚህ ፈተናዎች ግን ከአላማቸው የሚያዛንፏቸው አልነበሩም። በጥቅምት 2013 ዓ.ም በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ «በእናት መንገድ የበጎ አድራጎት ማህበር» ተመዝግቦ መንቀሳቀስ ይጀምራል።
በዚህ ወቅትም እንደመጀመሪያው ሁሉ ማህበሩ ዋና አላማው ያደረገው በትምህርት ቁሳቁስ እጦት በጤና እጦት ወይንም በሌሎች ምክንያቶች ትምህርታቸውን መማር ያልቻሉ ህጻናትን ችግር መፍታት፤ ብሎም እነዚህን ህጻናት በስነ ምግባር በማረቅ የተማሩና ለአገር የሚጠቅሙ ዜጋ እንዲሆኑ ማብቃት ነውም።
በአሁኑ ወቅት ለሰላሳ ስምንት ህጻናት በቋሚነት የትምህርት ቁሳቁስ፤ የምግብ፤ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ አልባሳትና የጤና ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። በተጨማሪ በተለያዩ ግዜያት ለጎዳና ህጻናት የምገባና የአልባሳት ስጦታዎችን አሰባስቦ በማቅረብ ሲያበረክት ቆይቷል። ለዓለም ስጋት የነበረው የኮሮና ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅትም ማህበሩ በጎ ፈቃደኛ አባላቶቹን በማሰማራት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በመስራት፤ እንዲሁም ለችግረኛ ህጻናትና ቤተሰቦች ለምግብነት የሚውሉ ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ እንዲዳረስ አድርገዋል።
የማህበሩ ቀዳሚ ዓላማ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ማስረከብ ነው። ይህንን ከግብ ለማድረስም የማህበሩ አባላት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችና ሌሎችንም በማስተባበር በክረምት ወቅት ለህጻናት የማጠናከሪያ ትምህርቶችን እየሰጡ ይገኛሉ።
እንደ አገር ትልቅ ፈተና ሆኖ የነበረውንም የወጣቶች የስነ ምግባር ችግር ለመቅረፍ የግብረ ገብና ስነምግባር ትምህርቶች ይሰጣሉ። ይህ የስነ ምግባር ትምህርት በተለይም ለህጻናቶች «ልጆችን በማስተማር የተሻለች ኢትዮጵያን እንገንባ በሚል መሪ ቃል» በሚሰራቸው ስራዎች የሚመጣውን ትውልድ ከዘረኝነትና ነጻ የሆነ አስተሳሰብ ይዞ እንዲያድግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛል። ማህበሩ እንደ አገር የሚጠበቅበትን ሃላፊነት ለመወጣትም በርካታ ስራዎችን ሲያከናወን ቆይቷል።
ከነዚህም መካከል የኮሮና ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ለአካባቢው ነዋሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ከመስጠት ጀምሮ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸውና በችግር ውስጥ ለነበሩ ዜጎችን ለእለት ፍጆታ የሚውሉ የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችቸን በማቅረብ እንዲሁም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ለተፈናቀሉ ዜጎችና ለሰራዊቱ ድጋፍ በማሰባሰብና እንዲዳረስ በማድረግና በተደጋገሚ የማህበሩ አባላት የደም ልገሳ በማከናወን ብሎም ቤተሰቦቻቸውና ጓደኞቻቸውና ሌሎች የሚያውቋቸውም በዚህ በጎ ተግባር እንዲሳተፉ በማድረግ አገራዊ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ቆይተዋል።
በተጨማሪም የማህበሩ አባላት ሁሌም በማይቆመው የአረንጓዴ ልማት አሻራ ከግል መኖሪያቸው ጀምሮ ችግኞችን በመትከል እየተንከባከቡ ይገኛሉ።
ከዚህ በተጓዳኝ በቋሚነት ሕይወታቸውንም ለመቀየር እየሰራ ይገኛል። የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናትን ከቤተሰቦቻቸው ለመቀላቀል ካልተቻለ ባሉበት የሊስትሮ እቃና ሌሎች ለቀላል ንግድ የሚሆኑ ግብአቶችን በማሟላት ለማቋቋም እየሰራ ይገኛል። በረጅም ጊዜም እቅዳቸውም አንድ ትልቅ ማእከል በመገንባት የጎዳና ህጻናትን እያስተማሩ ለማኖር ለወጣቶች ስልጠና በመስጠት የስራ እድል ለመፍጠር በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል።
ማህበሩ በአሁኑ ወቅት ስልሳ በጎ ፈቃደኛ ወጣት መደበኛ አባላትን እንዲሁም ሃያ የክብር አባላትን ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በቋሚነት ሰላሳ ስምንት ህጻናትን እየደገፈ ሲሆን ከዚህ በተጓዳኝ በአንደኛ ዙር ለሁለት መቶ የጎዳና ህጻናት የምገባና የልብስ ማልበስ መርሃ ግብር መፈጸም ችሏል።
ይህንንም ለሶስት ጊዜ ያደረገ ሲሆን ከበጎ አድራጊዎችም የተሰበሰቡትንም ልብሶች ለህጻናቱ የሚያዛውረው አጥቦ በማዘጋጀት ነው። በአራተኛ ዙርም ለሰላሳ የጎዳና ተዳዳሪ ሴቶች ቅድሚያ ለሴቶች በሚል ድጋፍ አድርጓል። ከዚህ በተጓዳኝ ለቀጣይም ይህንን በጎ ተግባር በማስቀጥል የአባላቱን ቁጥር በማስፋት በርካታ ለችግር የተዳረጉ ህጻናትንና አረጋውያንን ለመታደግ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። ለዚህም የተለያዩ የገቢ ማግኛ መንገዶችን የሚጠቀም ሲሆን የማህበሩ አባላት ወርሃዊ መዋጮ ትኬት ሽያጭ ለበአላት የውሃ ሽያጭ ቀዳሚዎቹ ናቸው።
ከማህበረሰቡ ውስጥ ደግሞ ማህበሩ ዛሬ ለደረሰበት እንዲበቃ የእስታር አካዳሚ ትምህርት ቤት ባለቤት አቶ ብርሃኑ የሚባሉ ግለሰብ ትምህርት ቤታቸውን ለህጻናቱ መማሪያ ለማህበሩ አባላት መሰብሰቢያ ሌሎች ድጋፎችንም አድርገውላቸዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን መጋቢት 2 /2014