ወርሐ የካቲት ለኢትዮጵያውያን ብሎም ለመላው ጥቁር ሕዝብ ትልቅ ድል የተከናወነበት ወቅት ነው። ዓለም ነጭን የበላይ አድርጎ በሚቆጥርበትና ሁሉም የአፍሪካ አገሮች በቅኝ ግዛት በወደቁበት በዚያን ዘመን ኢትዮጵያን ለመውረር የመጣውን የጣሊያን ጦር በጀግናው አፄ ምኒልክ ቆራጥ መሪነትና በእቴጌይቱ ብልሃትና አጋዥነት እንዲሁም በሕዝብ አንድነት አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ በመጣበት እግሩ ተመልሷል። ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛትን ድል ያደረገችበት የዓድዋ ድል በዓለማችን የሚገኙ ጥቁሮችና በቅኝ ግዛት የነበሩ የአፍሪካ አገሮች ለነፃነታቸው እንዲታገሉ ተስፋ የሆናቸው ፋና ወጊ ድል ነው።
ዛሬም ድረስ ዓለም እየተደመመ የሚታዘበው ዝክረ ዓድዋ በወርሐ የካቲት ኢትዮጵያውያን የተጎናጸፉት ታላቅ የድል በዓል ነው። ድሉ ከኢትዮጵያውያን ባለፈ ለመላው አፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት መሆን የቻለና በተግባርም መሆኑ የታየበት ነው። ለዚህም በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። ታሪክና ትውፊትን መጠበቅ ለአንድ አገርና ሕዝብ ህልውና እንደመሆኑ የዓድዋ ድል በዓል በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል። በዛሬው ዕለትም “አድዋ ለኢትዮጵያውያን ኅብረት የአፍሪካ የነፃነት ጮራ’’ በሚል መሪ ሃሳብ ለ126ኛ ጊዜ የዓድዋ ድል በዓል እየተከበረ ይገኛል።
ከኢትዮጵያውያን ባለፈ ለመላው አፍሪካ የድል ነጸብራቅ የሆነው የዓድዋ ድል ታሪክ ሲነሳ የማይዘነጉት እቴጌ ጣይቱ ብጡል ናቸው። ብልህ የሴት ጀግና ኢትዮጵያዊት ተብለው ይነሳሉ። የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ኢትዮጵያ ላይ ዓይናቸውን በጣሉበት በዚያን ዘመን እቴጌ ጣይቱ ብጡል ከባለቤታቸው ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጎን በመቆም በንጉሠ ነገሥቱ ላይ የተጀመሩ ሴራዎችን እና ጦርነቶችን የተቃወሙ ጀግና ሴት ናቸው። በዓድዋ ጦርነት ከነበሩ የጦር አዛዦችም አንዷ ነበሩ።
እቴጌ ጣይቱ ለምኒልክ ወታደራዊ ስልት ምርኩዝ እንደነበሩ የታሪክ ምሁራን ያነሳሉ። በአብዛኞቹ የፖለቲካ ውሳኔዎች ውስጥ ተሳትፎ ከማድረግ ባለፈ ከአጼ ምኒልክ ጋር ወደ ጦር ግንባር ዘምተዋል። በመሆኑም እቴጌ ጣይቱ ብዙውን ጊዜ ከምኒልክ ጎን የነበሩ ጠንካራ ሴት ሆነው ይጠቀሳሉ። በወቅቱ የአፍሪካን አህጉራት በእጃቸው ለማስገባት ሲውተረተሩ በነበሩ አውሮጳውያን ላይ እቴጌ ጣይቱ ከፍተኛ ጥርጣሬ የነበራቸው መሆኑን የሚያነሱት የታሪክ ምሑራኑ ‹‹አውሮፓውያኑ ደስ የሚል ጠረን የላቸውም ፤ይሰነፍጣሉ›› በሚል አገላለጽም ለአውሮፓውያኑ የነበራቸውን ጥርጣሬ መግለጻቸውን ያነሳሉ።
እቴጌ ጣይቱ ብቻ አምስት ሺ እግረኛ እና ስድስት መቶ ፈረሰኞችን በማሰለፍ የተዋጉ ሲሆን የእቴጌይቱ የጦር ስልት በመጨረሻም ጣሊያኖችን ድል ለማድረግ ረድቷል። በዓድዋ ድል ሶስት ውጊያዎች መደረጋቸው የሚታወቅ ሲሆን ጣይቱ ሁለተኛውን ውጊያ ለማሸነፍ ወሳኝ እንደነበሩም ታሪክ ያስረዳናል። በዓድዋ ድል ትልቅ ድርሻ የነበራቸው መሆኑ በስፋት የሚነገርላቸው እቴጌይቱን በዋናነት ዝነኛ ካደረጓቸው ተግባራት መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡
ጣይቱ ከጣሊያን ጋር ከተደረጉ ስምምነቶች መካከል ኢትዮጵያን ቅኝ ተገዢ ሊያደርጋት የሚችለውን የውጫሌውን ስምምነት ውል አንቀፅ 17 ውድቅ በማድረግ፤ መቀሌን ተቆጣጥረው የነበሩትንም የጣሊያን ወታደሮች ለማሸነፍ እንዲቻል ጣይቱ ባቀረቡት ሀሳብ፤ በዚህም መሠረት ጣሊያኖች የሚጠቀሙበትን የውኃ ምንጭ በኃይል በመቆጣጠር ከመቀሌ እንዲወጡ ማስደረግ በመቻላቸው እና ጣይቱ ብጡል ጣሊያኖች በተሸነፉበት እና በድል በተጠናቀቀው የዓድዋ ጦርነት በነበራቸው ሚናም ይታወቃሉ።
ጣይቱ ብጡል በጊዜያቸው ከነበሩ ሴቶች የተለዩ እንደነበሩም ይነገራል። ይሁን እንጂ ምንም እንኳን የጣይቱን ያህል ባይሆንም ኢትዮጵያ ብዙ ጠንካራ ሴቶች የነበሯት ስለመሆኑ የታሪክ ምሑራን ሲናገሩ ይደመጣል። በወቅቱ ብዙዎች መሣሪያ አንስተው ባይዋጉም፤ የጦር መሪና አዛዥ ባይሆኑም የመኳንንት ሚስቶችን ጨምሮ ብዙ ሴቶች በዓድዋ ጦርነት የጎላ ሚና ተጫውተዋል። ምግብ በማብሰል፣ በማፅዳት፣ ቁስለኞችን በማከም፣ መረጃ በማቀበል፣ ለሠራዊቱ ጉልበት በመሆን ጭምር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከት በመቻላቸው ታሪክ ያወሳቸዋል። ዛሬም ኢትዮጵያውያን ሴቶች በአገራቸው ጉዳይ ላይ ጉልህ አበርክቶ አላቸው።
የአገር ዳር ድንበር ሲደፈርና ህልውናዋ አደጋ ሲያንዣብብበት ቆሞ የሚመለከት ኢትዮጵያዊ ዛሬም የለም። ምንም እንኳን የፖለቲካ፣ የብሔር፣ የሃይማኖትና የአመለካከት ልዩነቶች በስፋት የሚንጸባረቅባት አገር ብትሆንም ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ ላይ ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው በአንድነት ይቆማሉ። የሕይወት መስዋዕትነት ከመክፈል ጀምሮ ሀብት ንብረታቸውን ሳይሰስቱ ካላቸው ብቻ ሳይሆን ከሌላቸውም በማዋጣት የአገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር ቅድሚያ ይሰጣሉ።
ኢትዮጵያ በዘመኗ ሁሉ የሚገጥማትን ችግር መፍታት የሚያስችላት እምቅ ችሎታና አቅም ያላት የብዙ ባህልና እሴት ባለቤት ናት። በተለይም በርካታ ተሳትፎ ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶች በተፈጥሮ የተቸራቸውን ብልሃት ደምረው ታሪክ የማይሽረው በርካታ ገድሎችን ፈጽመዋል። ዛሬም ድረስ ታሪክ የሚያወሳቸውን እቴጌ ጣይቱን ጨምሮ በወቅቱ የነበሩት እልፍ አዕላፍ ሴት እህቶችና እናቶች የፈጸሟቸውን ገድሎች አወድሰን አንዘልቀውም። ‹‹ከእያንዳንዱ የጦር ሜዳ ድሎች ጀርባ አንዲት ጠንካራና ጀግና ሴት አለች›› የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡
ታድያ ዛሬም ጥንካሬና ጀግንነት ጥንትም ያባቶቻችን ነው ያሉት የዘመኑ ሴት እህትና እናቶች በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው ትርጉም ያለው ሥራ በመሥራት ለአገር ኩራት ሆነው መመልከታችን አዲስ አይደለም። በተለይም አገር ጭንቋ በበዛበት በዚህ ወቅት በሁሉም መስክ መረባረብ የግድ ይላል። በአገሪቱ አንድ ዓመት በተሻገረው ጦርነትም ጥቂት የማይባሉ ሴት እህቶችና እናቶች የአገር ዳርድንበር ተነካ ሲባል ከጫፍ ጫፍ ተንቀሳቅሰው የጎላ አበርክቶ ሲያደርጉ መታየታቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
በተለያዩ አካባቢዎች እህቶችና እናቶች ለሠራዊቱ ስንቅ ሲያዘጋጁ ማየት የወቅቱ ዕለታዊ ዜና እንደነበርም እናስታውሳለን ። ከተለያዩ ቀበሌዎች የተወጣጡ ሴቶች ለአገር መከላከያ ሠራዊት የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን በተለያየ ተግባር አሳይተዋል። ዛሬም ድረስ ከሠራዊቱ ጎን በመቆም ድጋፍ እያደረጉ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን በጦርነቱ የተጎዱ ሕጻናትና አዛውንቶችንም እያገዙ ይገኛሉ፡፡
ቤት ንብረታቸውን በመሸጥ ለመከላከያ ሠራዊቱ ድጋፍ ያደረጉ እናቶች የወቅቱ መነጋገሪያ ነበሩ። ጦርነቱ ያስከተለውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ለመከላከል ኢትዮጵያውያን በአንድነት መንፈስ ሆነው ተረባርበዋል። ለዚህም ሴቶች ከፍተኛውን ድርሻ ነበራቸው ። በዓድዋ ጦርነት ወቅት እራፊ ጨርቅ በማሰባሰብ በጦርነቱ የተጎዱትን በማከም፣ ለተራበው ምግብና ውሃ በማቀበል ኃላፊነታቸውን የተወጡ በርካታ ሴቶች ናቸው።
የማኅበረሰቡ አካል የሆኑት የሕክምና ባለሙያዎችም እንዲሁ በጦርነቱ የተጎዱና ሰለባ የሆኑትን በከባድ መሳሪያ ጩኸትና በባሩድ ሽታ ተውጠው ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ቁስላቸው እንዲጠግና ከሕመማቸው እንዲያገግሙ ሙያዊ ድጋፋቸውን ሳይሰስቱ አበርክተዋል። በአውደ ውጊያውም ቢሆን በርካታ እህቶቻችን ደረታቸውን ለጥይት ለመስጠት ለነብሳቸው ሳይሳሱ ተሰልፈዋል። አሁን በእኛ ዘመንም አገር በጦርነት ብቻ ሳይሆን በሁሉም ረገድ የሚረዳትን ትፈልጋለችና በጦር ሜዳ ከመሰለፍ ባለፈም እያንዳንዱ ዜጋ በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ሁሉ ቢተጋ ለአገር ትልቅ ውለታ ነው።
አንድነት ኃይል ነው እንደሚባለው ኢትዮጵያውያን በዘመናቸው ሁሉ የገጠሟቸውን ችግሮች ማሸነፍ የቻሉት በአንድነት መቆም በመቻላቸው እንደሆነ ሁሉ አንድ መሆን ባቃታቸው ጊዜም ለጠላት በር በመክፈት ብዙ ዋጋ ተከፍሏል። ይሁን እንጂ አሸናፊነትና ኢትዮጵያዊነት አይነጣጠሉምና ምንጊዜም ኢትዮጵያውያን ከሚከፋ ፍላቸው ልዩነት ይልቅ አንድ የሚያደርጋቸው አገራዊ አንድነት ከሁሉ ይልቃል። ሴት ወንድ፣ ትልቅ ትንሽ ሳይሉ ሁሉም በአንድ ልብ መካሪ፤ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው ለአገር ዳር ድንበር ዘብ ይቆማሉ።
ኢትዮጵያ ከዛሬ 126 ዓመታት አስቀድሞ በወርሐ የካቲት ከተጎናጸፈችው የዓድዋ ድል በተጨማሪ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታም በዚሁ ዕድለኛ በሆነው የካቲት ወር መሰረቱ ተጥሎ ፍሬውን ማየት ተችሏል። ታድያ ቀጣዩ የግድቡ ምዕራፍ ተጠናቅቆ ሙሉ ለሙሉ የታሰበውን አገልግሎት መስጠት ሲጀምርም ልክ እንደ ዓድዋ ሁሉ ታሪክ የሚዘክረው ዳግም የኢትዮጵያውያን ድል እንደሚሆን ይታመናል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና የዓድዋ ድልን የሚያመሳስላቸው አንድና አንድ የላቀ ሕዝባዊ ተሳትፎ የታየበት መሆኑ ነው። በዓድዋ ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው በአንድነት ለአንድ ዓላማ በመቆማቸው የማይቻል የሚመስለውን ችለው፤ በዘመናዊ መሳሪያ የተደገፈንና የተደራጀን ኃይል ዘመናዊ ባልሆነና ባልተደራጀ ጦር መሳሪያ ድል ማድረግ ችለዋል። ‹‹ከልብ ካለቀሱ ዕንባ አይገድም›› ነውና ብሂሉ በጋራ ለአንድ ዓላማ በመቆም የድል ባለቤት መሆን ተችሏል።
ዛሬም ኢትዮጵያውያን ካለፉት ጊዜያት እጅጉን የሰፉ ልዩነቶች ሰቅዘው በያዙን በዚህ ወቅት እንኳ የአገር ጉዳይ አንድ ሲያደርገን ይታያል። ለዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሌላኛው ዓለም የሚዘክረው የኢትዮጵያውያን የድል ነጸብራቅ፤ የይቻላል ስሜት መገለጫ ታሪክ ነው። ከእናቶች መቀነት የተፈታ ቋጠሮን ጨምሮ ከእያንዳንዱ ዜጋ በተዋጣ የላብ ጠብታ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን መገንባት መቻል የኢትዮጵያውያን አንድነትና የመተባበር ምስጢር ነው። ይህ ሚስጥር ታድያ ወደፊት በርካታ ሁነቶችን ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም መሥራት እንደሚችሉ አመላካች ነው።
በሞታቸው እየተወራረዱ ኢትዮጵያን ለዛሬ ላበቁት ወገኖች ምስጋና ይግባቸውና ቀናት በወራት፣ ወራትም በዓመታት እየተሻሩ ዘመን እንደ ጅረት እየነጎደ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ዛሬም እንደ አዲስ ይነገራል፤ ይጻፋል፤ ይደመጣል። ከአድማስ ባሻገር እንደ ፀሐይ ደምቆ በሚታየው ድል ውስጥ ንግሥት ጣይቱ ብርሃን ዘ-ኢትዮጵያ በሕይወት ዘመናቸው የፈጸሙት ታሪክ የኢትዮጵያ የምን ጊዜም ጀግና ንግሥት ሆነው እንዲነሱ አድርጓቸዋል፡፡
እኛም በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ደርሰን እንደ ትውልድ ታሪክ ዘካሪ ብቻ ሳንሆን ዘመኑ በሚጠይቀው ዘርፍ ሁለንተናዊ አበርክቶ በማድረግ የአዲስ ምዕራፍ አብሳሪ ልንሆን የግድ ይላል። በተለይም የዓድዋ ድል ሲነሳ የኢትዮጵያውያን መተባበርና በአንድነት የመቆም ምስጢሩ ጥልቅ ነውና አገር ካለችበት አሁናዊ ችግር መውጣት እንድትችልም ልክ እንደያኔ ሁሉ በአንድነት ሆነን ለአንድ ዓላማ በጋራ ሆነን ኢትዮጵያን እንገንባ መልዕክታችን ነው።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2014