እንደ መንደርደርያ…
መምህሩና ድምፃዊው ጌቴ አንለይ ክንዴ በቀድሞው ጎጃም ክፍለ አገር በደብረማርቆስ ከተማ አብማ የሚባል አካባቢ ነው የተወለደው። ከአባቱ አቶ አንለይ ክንዴ እንዲሁም ከእናቱ ወ/ሮ የንጉሴ ከቤ የተገኘው ጌቴ ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ ነው።
የተማሪነት ዘመኑን ከጨረሰ በኋላ በሥራ ሕይወቱ ከደብረማርቆስ ከተማ ሰባት ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ የገጠር ከተማ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት ውስጥ ፕሮዳክሽን ቴክኖሎጂ የሚባል የትምህርት ዓይነት በማስተማር ለሁለት ዓመታት ያህል ትውልድን በሥነምግባርም በእውቀትም ቀርጿል።
ጌቴና ሙዚቃ
ገና በልጅነቱ ነበር ጌቴና ሙዚቃ ትውውቅ የጀመሩት። ከሙዚቃ ጋር አብረን ነው የተፈጠርነው የሚለው ጌቴ የስድስት አመት ልጅ እያለ ማንጎራጎር እንደ ጀመረ ይናገራል።
ምስኪን የልጅነት ነፍሱ ለሙዚቃ እጇን የሰጠችው በጥላሁን ገሰሰ ዘፈኖች ነበር። ሙዚቃን ከማወቁ አስቀድሞ የጥላሁን ገሰሰን ሙዚቃዎችን አደመጠ። በጥላሁን ገሰሰ ውስጥ ሙዚቃን ተማረ። በትንሹ የጌቴ ልብ ውስጥ የሙዚቃ መስፈርትም ሙዚቃ ራሱም ጥላሁን ገሰሰ ሆነ።
ከጥላሁን ገሰሰ ቀጥሎ ጌቴን የተቀበሉት የትምህርት ቤት ክበባትም ችሎታውን እንዲያወጣ ዕድል ፈጠሩለት። የስድስተኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ ሕዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ ላይ የመዝፈን ዕድል ገጠመው። ከዚያ ወዲያ በወረዳ አውራጃና ኪነቶች እየዘፈነ ሽቀብ መምዘግዘግ ያዘ። የመጀመሪያ አልበሙንም በ1981 አ.ም አወጣ።
ከመጀመሪያ አልበሙ በኋላ ጌቴ በሙዚቃው ማደግ ስለፈለገ ወደ አዲስ አበባ መጣ። ማረፊያ ቦታውም አንጋፋዎቹ ችሮታው ከልካይ እና ማሪቱ ለገሰ በሚዘፍኑበት ጊዮን ሆቴል አደረገ። ቦታው ለጌቴ ያልተለመደ ዓይነት ነበር። ሙሉ ባንድ ቢጠብቅም ዘፈኑ በማሲንቆ እና በታዳሚዎች ጭብጨባ ብቻ ታጅቦ የሚደረግ ነበር፤ ዘፈነ። 25 ብር ክፍያውንም ተቀበለ። ከዚያ በኋላ አዲስ አበባ ላይ ጥሩ ሙዚቃዎች ይሰሙበታል በሚባልበት ቦታ ሁሉ ጌቴ አለ።
ጌቴ ከዚያ በኋላ በርከት ያሉ አልበሞችን ቢሠራም አንድ ነጠላ ዜማ እና አንድ አልበም ግን ጎልተው ይጠቀሳሉ። መጀመሪያ ነጠላ ዜማውን እንመልከት። ወቅቱ 2000 አ.ም የኢትዮጵያ ሚሊኒየም የሚከበርበት አመት ነበር።
ሁሉም ድምጻዊ አለኝ የሚለውን ሥራ ለመሥራት እየተሯሯጠ ነው። ጌቴም እንደ ሙያ አጋሮቹ አንድ ለወቅቱ የሚስማማ ሙዚቃ ለመሥራት ፈለገ። ኤልያስ መልካን ፈለገ። ፈላጊ የበዛበት ኤልያስ ግን ስልኩን አጥፍቶ ጠፋ። ጌቴ አማራጭ መፈለግ ሲጀምር ሌላኛው አቀናባሪ ሁንአንተ ሙሉ ለሌላ ሥራ ጌቴ ጋር ደወለ። አጋጣሚ አገናኛቸውና ሙዚቃው ሁንአንተ ስቱዲዮ ተቀረጸ።
ሙዚቃው አንዴ ብቻ ነበር የተቀረጸው። ከዚያ በጣም ጥቂት ማስተካከያ ተደርጎበት እጅ ሳይበዛበት ለሕዝብ ተለቀቀ፤ በጣም ተወደደ። ጌቴ ይህን ሙዚቃ የብዙ አልበም ዋጋ ያለው ሙዚቃ ነው ይለዋል። የጌቴን ስም በሕዝብ ዘንድ በአግባቡ እንዲታወቅ ያደረገ ሙዚቃ ነበር።
ወደ አልበሙ እንሻገር። ‹‹መልክሽ አይበልጥሽም›› የሚለው ይህ በ2008 አ.ም የወጣ ሙዚቃ ጌቴ እና ኤልያስ አዲስ የሙዚቃ መንገድ ያበጁበት ሥራ ነው። ነገሩን ለብቻው እንመልከተው።
የጌቴና የኤልያስ መልካ ትስስር
ኢትዮጵያ ውስጥ ለተሠሩና በብዙዎች ዘንድ አድናቆት ለተቸራቸው በተለይም በዘጠናዎቹ የተሠሩትን ምርጥ ሙዚቃዎች የጥበብ እጁ ያልዳሰሰቻቸው የሉም ማለት ነገር አጋናኝ አያስብልም። ምክንያቱም ሰውዬው ከጥበብ ተፈጥሮ ለጥበብ ኖሮ በጥበብ ተማርኮ ጥበብን አፍቅሮ ጥበብን ተድሮ በጥበብ ያለፈው ኤልያስ መልካ ነውና።
ምናልባትም ባንድ ጊዜ ድንቅ ገጣሚ፣ ምርጥ የዜማ ደራሲና ተአምረኛ አቀናባሪ ሆኖ ለመፈጠር ኤልያስ መልካን ሆኖ መፈጠር ሳያስፈልግ አይቀርም።
ዓለምን እርግፍ አድርገው ወደ ሙዚቃ ገዳም የመነኑ፣ ወደ መንፈሳዊነት የሚያደሉት የኤልያስ ግጥሞች በጌቴ አንለይ አልበም ላይም ተስተውለዋል። ጌቴ አንለይ ኤልያስ መልካን ሰውን እንዳዲስ መፍጠር ይችልበታል- ሲል ያንቆለጻጽሰዋል። ለጌቴ አንለይ ኤልያስ መልካ ሙዚቃን በቅጡ የተረዳ፣ ሙዚቃም እንደ ቅርብ ወዳጇ የምታደላለት፣ ላመነው ካልሆነ አድር ባይነት የማያውቅ ለሙዚቃ የተፈጠረ ጠቢብ ነው።
ድምፃዊና መምህሩ ጌቴ በ2008 የለቀቀው «መልክሽ አይበልጥሽም!!» አልበሙ የሙዚቃ አፍቃርያንን ተንከራታች ልብ ያሳረፈ፣ ዘፈንን አፍቅሮ በመሀል ከተማ ውስጥ ለመነነ ጆሮ ገዳሙ ለመሆን የሚመጥን ሥራ ነው።
ኤልያስና ጌቴ በመልክሽ አይበልጥሽም አልበም ላይ ተጠበውበታል፤ በተለይም የአልበሙ መጠሪያ በሆነው መልክሽ አይበልጥሽም ሙዚቃ ውበትን አሎሎው ዓይኗ፣ ስንደዶ አፍንጫዋ፣ ዞማ ጠጉሯ፣ የተኳለ ቅንድቧ፣ ባቷ፣ ተረከዟ መቃ አንገቷና ሳንቃ ደረቷ ከመሳሰሉና ጆሮን ካሰለቹ ግጥሞች ከፍ ባለ መልኩ ፍልስፍናን የዘሩበት ሙዚቃ ነበር።
በዚህም የተነሳ «መልክሽ አይበልጥሸም!» የተሰኘው ዘፈን በብዙዎች ዘንድ እስካሁን በልዩ ሁኔታ የሚደነቅ ሀሳብን የያዘ ሙዚቃ ነው። ትክክለኛው የሴት ልጅ ውበት ያለው ከውስጧ መሆኑንና አፍቃሪው ገፀባህሪይ ስብዕናዋን የውጪው መልኳ በምንም መስፈርት እንደማይበልጠው አነፃፅሮ ያቀርባል።
በቅንብር ደረጃም ቢሆን ይህ ሙዚቃም ሆነ ጠቅላላ አልበሙ በብዙዎች ዘንድ እንደ ባህል ድምጻዊ የሚታየው ጌቴ አንለይ በዘመናዊ መልኩ ራሱን የገለጠበት ሥራ ሲሆን፣ ኤልያስም ሙዚቃን በተለየ እና ረቂቅ በሆነ መልኩ መሥራት እንደሚችል ያስመሰከረበት ነው።
የምስጋና መባ
በጌቴ ሕይወት ላይ አሻራቸውን ያኖሩ፤ በመኖራቸው መኖሩን የኳሉ ብዙ ሰዎች አሉ። በችሎታው አምነው የታመኑለት በፈለገ ባስፈለጋቸው ወቅት አለንልህ ከጎንህ ነን በርታ ግፋ ቀጥል ያሉት ያለምንም ምላሽ ውለታ የዋሉለትን እልፎች ጌቴ አመስግኗል።
ያጠፋ ሲመስላቸው በቤተሰብነት ቁጣ በያገባኛል መቆርቆር የገሰፁትን፣ የሕይወትን ብርቱ ሰልፍ ሲሰለፍ እንዳይንገዳገድ ድጋፍ የሆኑለትን ሰዎቹንም በምስጋና ችሮታው ላይ አልዘነጋቸውም።
የሦስት ልጆች አባት የሆነው ጌቴ በቀጣይ የሙዚቃ ሥራዎቹን አጠናክሮ የመቀጠል ፍላጎት እንዳለው የገለጸ ሲሆን፤ ሥራውን እንደ ትልቅ ሰው አማክረው መርጠው በሥራውና በሕይወቱ ለሚደግፉት ለልጆቹ ዋለልኝ ጌቴ፣ ሚካኤል ጌቴና፣ ዳዊት ጌቴ እንዲሁም ለባለቤቱ ኤልሳ ሸዋታጠቅ ምስጋናውን አቅርቧል።
የጌቴ መልዕክት!
ማንኛውም በሕይወት ትግል ላይ ያለ ሰው ጠንክሮ በመታገልና ተስፋ ባለ መቁረጥ መንፈስ ሊመላለስ እንደሚገባው መልዕክቱን አስተላልፏል። የሙዚቃ ሕይወትም ላይ እንደ ስሜት በመሰማራት እንዲሁም የያዙትን አጥብቆ በመያዝ ለውጥ እንደሚመጣ በመግለጽ ሁሉም ሰው ተስፋን ስንቁ ሊያደርግ እንደሚገባውም ተናግሯል።
የእረፍት ቀን ውሎ
ሁልጊዜም በፀሎት ተጀምረው በጸሎት የሚያልቁ ቀናትን እንደሚያሳልፍ ጌቴ ይናገራል። አብዛኛውን ጊዜውን ሙዚቃውን በመሥራት እንዲሁም ለሙዚቃ ሥራው የሚደግፉትን ነገሮች በማሰናዳት ያሳልፋል። የእረፍት ቀን ውሎውም ልክ እንደ ሥራ ቀኑ ሁሉ ውጥረት የበዛበት ነው። በእረፍት ቀኑም ግጥምና ዜማ መፈለግ፣ የድምፅ ልምምዶች ማድረግ ትንሽ መንቀሳቀስ ለልጆቹና ባለቤቱ ጊዜ መስጠትና ሌሎችንም ተግባራት ይከውንበታል።
በጌቴ ህይወት ዙሪያ ያደረግነውን ቆይታ የምንጠቀልለው ጌቴ ከፍ ያለ ዝናን ባተረፈበት መልክሽ አይበልጥሽም አልበም ላይ የአልበሙ መጠሪያ ከሆነው መልክሽ አይበልጥሽም ሙዚቃ ግጥም ዘፈኑ መግቢያ ላይ ያሉ ስንኞችን በመጋበዝ ነው። መልካም የእረፍት ቀን!
መልክሽ አይበልጥሽም
ለኔ አዲስ ነሽ ውዴ ነሽ ውዴ ነሽ ውዴ
ሁሌም ነሽ ለኔ አዲስ ሁሌ አዲስ ነሽ ውዴ
በእጄ እስክትገቢልኝ እስከሚያቅፍሽ ክንዴ
አይደለም መውደዴ
ቢሳሳ ነው እንጂ ያልጠገበሽ ሆዴ
አይጠግብሽም ሆዴ
የብርቅ የህይወት ቅመም ደማም ነሽ መውደዴ
እናና ዘመዴ (2)
አንቺኑ ነው ያልኩት ወድጄሽ ከሆዴ
ወድጄሽ ከሆዴ
መች አይኔስ ሆነና ከላይ አይቶሽ ብቻ
ከላይ አይቶሽ ብቻ
መች ድሮስ ሆነና ካንገት በላይ ምርጫ
ካንገት በላይ ምርጫ
ልቤ አንቺን እንጂ መች መልክሽን ብቻ
መች አየ እሱን ብቻ
መች ይተውሽ ነበር ሆ አይኔሽ ቢያሽ ድሮ
ባይኖር እንኳን መልክሽ ውብ ባትሆኚም ኖሮ
ቢደምቅም ባይደምቅም ሆ ቢበርደው ቢሞቀው
ላይሽ ብቻ አይደለም ሆ ድንኬ የደመቀው
ከላይ እይኝ ባለች ባደባባይቷ
አንቺ አትመዘኚም በብልጭልጪቷ
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2014