
ዲቪ ደርሷቸው ወደ አሜሪካ የሚያደርጉት የጉዞ ሂደት የዘገየባቸው የኢትዮጵያ እና የሱዳን ዜጎች የአሜሪካ መንግሥትን ከሰሱ።
12ቱ ሱዳናውያን እና ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች እአአ 2022 ‘የአሜሪካን ዳይቨርሲቲ ቪዛ ሎተሪ’ አሸናፊ ቢሆኑም አሜሪካ ሊያስገባቸው የሚችል የጉዞ እና መኖሪያ ፍቃድ እስካሁን ማግኘት አልቻሉም።
በከሳሽ ‘ተስፋዬ’ እና ተከሳሽ ‘ብሊንከን’ በሚል በተከፈተው የክስ መዝገብ ላይ፤ ከሳሽ ቤተሰቦች በካርቱም እና አዲስ አበባ የሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ያቋረጡትን መደበኛ የቪዛ አገልግሎት ሥራቸውን አለመጀመራቸውን በክስ መዝገቡ ተመልክቷል።
ከሳሽ ቤተሰቦች በክስ መዝገባቸው ላይ የአሜሪካ መንግሥት የቪዛ ሂደታቸውን በሌላ የአሜሪካ ኤምባሲ እንዲታይልን አልፈቀደም ሲሉ በአሜሪካ መንግሥት ላይ ቅሬታ አቅርበዋል።
በአሜሪካ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት ሕግ መሠረት፤ የፍርድ ቤት ጣልቃ ገብነት እስከ ሌለ ድረስ የዳይቨርሲቲ ቪዛ ሎተሪ አሸናፊዎች የሥራ ዘመኑ ከመጠናቀቁ በፊት የቪዛ ቃለ መጠይቅ ማድረግ አለባቸው።
በዚህ መሠረት እአአ የ2022 ዲቪ የደረሳቸው ሰዎች የቪዛ ቃለ መጠይቃቸውን ከሴፕቴምበር 30 2022 (መስከረም 10 2015 ዓ.ም.) በፊት ማከናወን አለባቸው። «እነዚህ ከሳሾች የአሜሪካ ቋሚ ነዋሪ የመሆን በሕይወት አንድ ጊዜ የሚገኝ ዕድል ነው ያላቸው።
ዩናይትድ ስቴትስ አጋጣሚውን በመጠቀም ተቀብላቸው ብዝሃነታችንን ማስፋት አለበት። የባይደን አስተዳደር ግን የዲቪ ሎተሪ ቪዛ ጉዳዮች ቅድሚያ እየነፈገ ነው።
ቪዛቸው ከመስከረም 10 /2015 በፊት የማይሰጣቸው ከሆነ ይህ ወርቃማ ዕድል ያመልጣቸዋል» ሲሉ የከሳሾች ጠበቃ ከርቲስ ሊ ሞሪሰን ተናግረዋል።
የአሜሪካው ዳይቨርሲቲ ኢሚግራንት ቪዛ ፕሮግራም በየዓመቱ ከተለያዩ አገራት 50 ሺህ ሰዎችን በዕጣ አማካይነት ወደ አሜሪካ እንዲፈልሱ ዕድል ይሰጣል።
የዲቪ ሎተሪ ዕጣ አሸናፊዎች ከቪዛ ሂደት መዘግየት ጋር በተያያዘ በአሜሪካ መንግሥት አስተዳደር ላይ ክስ ሲመሰርቱ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።
ከጥቂት ወራት በፊት የዲቪ ሎተሪ አሸናፊ የኢራቅ ዜጋ፤ በባይደን አስተዳደር ላይ ክስ በመመስረት፤ የቪዛ ቃለ መጠይቅ የሚካሄድበት ቦታ እንዲቀየር ሆኗል በማለት ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን የካቲት 12 /2014