በሕይወቴ ውስጥ አብዝቼ ያሰብኳት ሴት ናት። ሴትነት በዛ ልክ ሞገስ ሲላበስ እሷን ነው ያየሁት። በወንዶች ከበባ ውስጥ ያለች ሴት ናት፤ ሁሉም ወንዶች ያዩዋታል እኔ ግን አስባታለሁ።
ብዙ ወንዶች የወንድነታቸውን እድፍ በሴትነቷ ላይ ጥለው ፉት ከሚሉት ትኩስ ቡናዋ እኩል በአምሮት ሲያላምጧት አይቻለሁ። የማይደረስ አጽናፍ ሴትነቷን ለመንካት የሚንጠራሩ አያሌ ወንዶችን አውቃለሁ፣ ስለሀብትና ስለ ውድ መኪና እያወሩ ሴትነቷን ጠልፈው ሊጥሉ ጆሮ ግንዷ ስር ተንኮል የሚዶልቱ ወንዶች አድምጫለሁ።
በእውነትና በእምነት የተለበሰ የጽናት ቀሚሷን ለመግለብ እንደ ሰይጣን ለምድ ለብሰው ስሯ የሚርመጠመጡ ብዙ ወንዶችን አውቃለሁ። ከሰዕታት በፊት መንገድ ላይ እንዳገኟት ተራ ሴት በቀላሉ የሚይዟት መስላቸው የማማለያ ቃላትን ሲጠቀሙ ይሄንንም ታዝቤአለሁ።
እዛ ቦታ ብዙ ነገር አያለሁ፤ ከነፍሷ ጋር ተጋጥሜ አይ ወንድ እላለሁ፤ ራሴን በወንድነቴ እሰድበዋለሁ። አንዲትን ተስፈኛ ነፍስ ለማስነወር ድንጋይ በሚፈነቅሉ ወንዶች ወንድነቴን እጸየፈዋለሁ። በውበቷ ወንድነቱን አጠልሽቶ በሚስቱና በፍቅረኛው ላይ ለመማገጥ በአንዲት ድሃ ነፍስ የማጣት ቀዳዳ ውስጥ ማጮለቁ ትርጉሙ ይጠፋኛል። በሴት ልጅ ላይ ጥቅም አልባ የሆኑ ወንዶችን ሳይ ለምን ወንድ ሆንኩ እላለሁ። ጽናት ትባላለች፤ እንደ እሷ ስም ስጠራው ደስ የሚለኝ የለም።
ከእናቴ ቀጥሎ በሕይወት ዘመኔ አብዝቼ የጠራሁት የሴት ስም የእሷ ይመስለኛል። ጠይም ናት፣ በብዙ ትህትና የተከበበ አይን አላት። ፊቷ ላይ ለሆነ ላልሆነው የሚያዝን ሴትነት በትልቁ ተስሏል። የአንድን ገራጅ አጥር ታኮ በተሰራ ወጋግራ ውስጥ ቡና ትሸጣለች። የሚያሰክር ቡና፤ ወንዶችን ሁሉ አቅል አስቶ የሚያዘላብድ ቡና።
ጽናትን አስባታለሁ፤ አጠገቧ ሆኜ በሴትነቷ ውስጥ ያለውን ህልቆ መሳፍርት ጥንካሬ እታዘበዋለሁ። ከሕይወት ለመላቅ፣ ከወንድነት ለመብለጥ የምታደርገውን ትግል አደንቃለሁ። ሴትነቷን ሽተው የሚያንዣቡባትን፣ የሚያባብሏትን ወንዶች እንዴት ማሸነፍ እንዳለባት ስታስብ አስባለሁ። በሸላቾቿ ፊት እንደ ቆመ ጠቦት በወንዶች ላለመበላት መላ ስትዘይድ አያታለሁ። መሽቶ እስኪነጋ ከነፍሷ ጋር አወጋለሁ።
ጽናትን ብዙ ጊዜ አይቻት አላውቅም፤ ፊቷ ስቆም ከነፍሷ ጋር ስለማወጋ የአካሏ ውበት አይታየኝም። እሷ ፊት ስቆም ነፍሷን ነው የማያት፤ በነፍሴ ነፍሷን አጤናታለሁ። በኔ ዝምታ ውስጥ በዙሪያዬ ያሉ በርካታ ወንዶች ስለጽናት ውበት ሲያወሩ አደምጣለሁ።
ፍቅር የያዘኝ ከነፍሷ ጋር ነው፤ ለየትኛውም ወንድ እጅ ካልሰጠች ነፍሷ ጋር። እንደ እኔ ወንዶች ሁሉ በሴት ልጅ ነፍስ ፍቅር ቢወድቁ እላለሁ። የነፍስ ፍቅር እንደ አካል ፍቅር አይደለም። የነፍስ ፍቅር የማይሞት የማያረጅ ፍቅር ነው። እስከዛሬ አፍቅረን ያጣንው፣ አባረን ያልያዝንው፣ ተመኝተን መና የቀረንው በአካል ፍቅር ላይ ስለቆምን ነው። አሁን እኔ በጽናት ዙሪያ ካሉት ወንዶች ሁሉ ልዩ ነኝ፤ ምክንያቱም ነፍሷን ነው ያፈቀርኩት። ጽናት ለወንዶች ሁሉ አትታይም።
እንዳትታይ ሆና የተፈጠረች ሴት ናት። እሷን የሚያዩዋት ጥቂት አይኖች፣ ጥቂት ልቦች ብቻ ናቸው። አካሏ ላይ የሚያርፍ አይንና ስሜት እንጂ ወደ ልቧ የሚዘልቅ የወንድ ልጅ የሃይል ሞገድ በምድር የለም። ከእኔ በቀር ሁሉም ወንዶች በውበቷ የተሸነፉ ናቸው። እኔ ግን በነፍሷ የተሸነፍኩ ነኝ። እና ደግሞ የሰው ልጅ ሁሉ ለራሱ ሲል የሚወዳት ሴት ናት። በእሷ ነፍስ ውስጥ ለዓለም ሁሉ የሚበቃ ፍሰሀ አለ። ልቧ የመባረኪያ ስፍራ ነው።
ይቺን ሴት ማፍቀር ዋጋው በምን ይለካል? ሁሌ እንዲህ አስባለሁ። የሃሳቦቼ ማብቂያ ግን ሳቋ ነው። ከሳቋ ውስጥ እየወጣ የሚፈስ ጎርፍ አለ። እንደ ጥብሪያዶስ ባህር የሰው ልጅ በታንኳ የማይሻገረው፤ እንደ ጴጥሮስ ያላመነ፣ እንደ ሙሴ ያልተቀባ፣ እንደ አብረሃም ያልተመረጠ፣ እንደ ዳዊት ያልተጠበበ የማይሻገረው ትልቅ፤ በጣም ትልቅ የሴትነት ውቅያኖስ በሳቋና በልቧ በሴትነቷም ላይ አለ፤ ተንጣሎ።
ይቺን ሴት ማሰብ፣ ይቺን ሴት መከተል፣ ይቺን ሴት ሚስት ማድረግ ዋጋው በምን እንደሚለካ ዛሬም ድረስ አልደረስኩበትም። አንዳንዴ እግዜር በምሳሌ መልዕክቱ ላይ ‹ልባም ሴትን ማን ሊያገኛት ይችላል? ዋጋዋ ከቀይ እንቁ እጅግ ይበልጣል› ያለላት ሴት እሷ ትመስለኛለች።
አንዳንዴ ‹ቤትና ባለጠግነት ከአባቶች ዘንድ ይወረሳሉ አስተዋይ ሚስት ግን ከእግዚአብሄር ዘንድ ናት› የተባለላት ትመስለኛለች።
አንዳንዴ ልባም ሴት ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ምን ታደርጋለች ስል በዙሪያዋ እንደ ተኮለኮሉት መሀይም ወንዶች የመሀይም ሃሳብ አስባለሁ። የሃሳቤን ጥጉን ባልደርስበትም የሆነው ሆኖ ግን ጽናት በአንድ ሰዋራ ስፍራ ላይ ወንዶች ሁሉ ፈልገው እንዲያገኙዋት የተደበቀች ሴት ትመስለኛለች።
ብዙ ደስታን፣ ብዙ ፈንጠዝያን፣ ብዙ በረከትን ይዛ የተፈጠረች። ሃሳቤ ማብቂያ የለውም…ስድስት ሰዓት ደርሶ ፊቷ እስክቆም ድረስ በነፍሴ ነፍሷን አስሳታለሁ። ስድስት ሰዓት የሕይወቴ ዜማና ቅኔ ነው፤ ከሥራ ወጥቼ ቡና ለመጠጣት ወዳለችበት የምሄድበት።
እንዳየችኝ ዛሬም ድረስ ማንም ያልፈገልኝን ትሁት ፈገግታ ታሰየኝና ትኩስ ቡና ትቀዳልኛለች። ወንዶቹ እንደወትሯቸው የእሷን ሴትነት የሚመኙ ሆነው አገኛቸዋለሁ።
እኔ በዝምታ አያታለሁ፣ ወንዶቹ በጩኽት ያወሯታል። የሁላችንም ምኞት ማረፊያ የእሷ ነፍስ፣ የእሷ ሴትነት ነው። በዝምታዋ ውስጥ ያለውን ያልተደረሰበትን ከፍታዋን ከእኔ ሌላ የሚያውቀው ያለ አይመስለኝም።
ዝም ቢሉ ብዙ ያውቋት፣ ብዙ ይወዷት ነበር እላለሁ። ዝም ቢሉ ካፈቀሯት በላይ ያፈቅሯት ነበር እላለሁ። ዝም ቢሉ ሊያረክሷት የተመኙትን ያህል በንጽህናዋ ይቀደሱ ነበር እላለሁ። ዝም ቢሉ ወንድነታቸው ያልደረሰበት ከፍታ ላይ ይደርሱ ነበር እላለሁ፤ ግን ዝም አላሉም።
ዝም ማለትም አይችሉም። የሚፈልጉትን በጩኸታቸው የሚያገኙ መስሏቸዋል። እሷን እስካወኩበት ጊዜ ድረስ ለአንድም ቀን ሴት መሆን ተመኝቼ አላውቅም ነበር.፤ እሷን ካወኩ ወዲህ ግን ሴት መሆንን አብዝቼ ተመኘሁ። ከትናንት እስከ ዛሬ በወንድነቴ ውስጥ የእሷን አይነት ልዕልና ፈልጌ አጥቻለሁ።
በወንድነቴ ውስጥ የእሷን አይነት ሴታዊ መባረክ ተመኝቼ አጥቻለሁ። ድጋሚ የመፈጠር እድል ቢገጥመኝ እሷን እሆን ነበር፤ ጽናትን፤ ይሄ በወንድነቴ ውስጥ ያለ የማልቀይረው ሃሳቤ ሆኖ ዛሬም ድረስ አብሮኝ አለ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን የካቲት/2014