ኑሮውን በአሜሪካ ሲአትል ያደረገው ኢትዮጵያዊው ያዴሳ ቦጂያ የተወለደው ምዕራብ ሸዋ አምቦ አካባቢ ነው።በደርግ ሥርዓት አባቱ በመንግሥት መገደሉን ተከትሎ ቤተሰቡ ወደ አዲስ አበባ ይመጣል፡፡ቆይቶም ጉዞ ወደ አሜሪካ ይሆናል።
ግራፊክ ዲዛይነርና የኪነጥበብ ባለሙያ ነው።ያዴሳ እአአ በ2006 በሚኖርበት አሜሪካ በግዛት ደረጃ ባቀረበው ኤግዚቢሽን ፣ በ2010 ደግሞ የአፍሪካ ኅብረትን ሰንደቅ ዓላማ ዲዛይን በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን ማግኘት ችሏል። ለበርካታ ጊዜያትም የተለያዩ ሥራዎቹን በኤግዚቢሽን አሳይቷል።በሥራዎቹም የሰብዓዊ መብት፣ የአነስተኛ ማኅበረሰቦች መብት፣የአፍሪካን እና የፍትሕን ጭብጦች በማንሳት ሕዝብን ማነጋገር ችሏል።
አንድ ምሽት ቤቱ ቁጭ ብሎ የአንጋፋውን ላሪ ኪንግን የቃለመጠይቅ ፕሮግራም እየተከታተለ ነበር።የእለቱ እንግዳ ደግሞ የቀድሞው የሊቢያ ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊ ናቸው።ጋዳፊ በወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ነበሩ፤ እሱም ኅብረቱ አዲስ ሰንደቅ ዓላማ እንዲያዘጋጅም ተልዕኮ ተሰጥቶት ነበር።በዚህም መሠረት ሁለት ዓመት ገደማ በቆየው የመረጣ ሂደት ሥራቸውን ካስገቡ 127 ተወዳዳሪዎች መካከል ደግሞ አንዱ ነበር።ሥራውን
ካስገባ በኋላ ግን ረዘም ላለ ጊዜ ውጤቱን ሳይሰማ ቆይቷል።ያዴሳ ቦጂያ፡፡
ላሪ እና ጋዳፊ በኒውዮርክ በሚገኘው የሊቢያ ቆንስላ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ታዲያ ያዴሳ የራሱ ሥራ ከጋዳፊ ጀርባ ተሰቅሎ አየው።አይኑ ያየውን ማመን አልቻለም።እንዴ የኔ ዲዛይን አለ ጮክ ብሎ።ስልኩን አንስቶ አዲስ አበባ ወደሚገኘው የኅብረቱ ጽሕፈት ቤት ደወለ።ስልኩን ያነሳችው ሴት ግን ስለሚያወራው ጉዳይ ምንም እንደማታውቅ ነገረችው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጋዳፊ የያዴሳን ዲዛይን ልብሳቸው ላይ አድርገው በማግስቱም ሲ ኤን ኤን ላይ እየታዩ ነበር።ከሶስት ወር በኋላ ግን ያዴሳ ሥራው ማሸነፉን የሚገልጽ ደብዳቤ ከአፍሪካ ኅብረት ደረሰው።ሰንደቁ ይፋ በሚሆንበት መርሐ ግብር ላይ እንዲታደምም ከነመላ ቤተሰቡ ተጋበዘ።በፈረንጆቹ ጥር 31 ቀን 2010 የያዴሳ የአዕምሮ ውጤት የሆነው የአፍሪካ ኅብረት ሰንደቅ ዓላማ በ14ኛው የኅብረቱ መደበኛ ጉባኤ ላይ ይፋ ሆነ፡፡
ከድሉ በኋላ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በጽሕፈት ቤታቸው አስጠርተው አድናቆታቸውን ገልጸውለታል፤ ሌሎች መሪዎችም አመስግነውታል።ከፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ጋርም ለ5 ሰዓታት የዘለቀ ቆይታ አድርጓል።ከሁሉም በላይ ያስደሰተው ግን በየመንገዱ የሚያገኙት ኢትዮጵያውያን ይሰጡት የነበረው አድናቆት እንደነበር በወቅቱ ተናግሯል።
ሰንደቁ የአፍሪካ አህጉር በ55 ኮከቦች እንዲከበብ የተደረገ ሲሆን፣ ይህም እያንዳንዱ ሰንደቅ አንድ የኅብረቱ አባል አገርን እንዲወክል ታስቦ የተደረገ ነው።ከኅብረቱ ካርታ ጀርባ ያለው ብርሃን አፍሪካ ከፊት ለፊቷ የሚጠብቃትን ብሩህ ተስፋ ያመለክታል።
ያዴሳ በ2015 ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር በነበረው ቆይታ ስለ ዲዛይኑ ሲናገር ‹‹የዲዛይኑ ዋነኛ ማዕከል ወደ አፍሪካ የሚያበራው ጸሐይ ነው።ይህም አፍሪካውያን ለረዥም ጊዜ የሚቆዩ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን በመገንባት ለሰላም እና ለብልጽግና መሠረት የሚጥሉበትን እና በራሳቸው ጉዳይ ራሳቸው መወሰን የሚችሉበትን አዲስ ተስፋ ያሳያል።‹‹በወቅቱ ዲዛይኑን ስሠራ የነበረኝ ሀሳብ ይሄ ነበር።የአፍሪካ መሪዎችም ይህን ሀሳቤን ስለተረዱት ደስ ብሎኛል።እርግጥ ነው ውጣ ውረዶች አሉብን፤ በተለያዩ የአህጉሪቱ ማዕዘናትም ችግሮች አሉ ነገር ግን አፍሪካ ጠንካራ አህጉር የመሆን ጉዞ ላይ እንዳለች የሚያሳዩ ብዙ ምልክቶች አሉ፡፡››ሲል አብራርቷል።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ጥር 29/2014