ጠዋት ነው… ጤዛዎች ከነጠላቸው.. አእዋፍት ከነዜማቸው.. ጋሻው ዘወትር ከሚቀመጥባት ከመስኮቱ አንጻር ካለችው ወንበር ላይ ተቀምጦ ጋዜጣ ያነባል።አጠገቡ ለንባብ በተዘጋጀችው ጠረጴዛ ላይ ትኩስ ቡናና ርዕሱ የተሸፈነ መጽሐፍ ተቀምጧል።ማንበብ ይወዳል፤ ከንባብና ትኩስ ቡና ፉት ሳይል የቀረበት ጊዜ የለም።አብዛኛው ጎደሎነቱ በማንበብ የተሸፈኑ ናቸው።አብዛኛው ማለዳዎቹ በንባብና በትኩስ ቡና የተጀመሩ ናቸው።
ማንበብ ባይኖር ኖሮ ምን ይሆን እንደነበር ሲያስብ ይፈራል፤ ዘላለማዊ ፍርሀት። ዓይኑን ከጋዜጣው ላይ ነቅሎ በመስኮቱ በኩል ወረወረ።በዝምታው ውስጥ ኤልሳ ብቅ አለች፤ ኤልሳ ማነች? እሱ የሕይወቴ ትዕንግርት ይላታል፤ እውነት ነው ትዕንግርት ከመሆን ውጪ ምንም ልትሆን አትችልም። ከውጪ የሚያጓራ ንፋስ ተሰማው።
ጋዜጣውን አጣጥፎ ቡናውን ፉት አለ።ዓይኑን ርዕሱ የተሸፈነው መጽሐፍ ላይ ተከለ፤ መጽሐፉ ውስጥ የሕይወቴ ትዕንግርት የሚላት ኤልሳ የምትባል ገጸ ባህሪ አለች። ኤልሳ ሴት ብቻ አይደለችም፤ በሴትነቷ ውስጥ ሌላ ሴትነት፣ ሌላ ተፈጥሮ፣ ሌላ ሰውነት ያላት ናት።በብዙ ነገሯ ሙሉ ናት።
እውነት ለመናገር ከገጸ ባህሪዋ ኤልሳ ጋር ፍቅር ከያዘው ቆይቷል።ከኤልሳ ጋር ላለመለያየት ሲል መጽሐፉን ቀስ እያለ ነው የሚያነበው።በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ነበር አንድ ሱቅ ውስጥ ቁርጥ ኤልሳን የምትመስል ሴት ያየው። የሕይወቱ አስደናቂ ገጠመኝ ከዚህ ይጀምራል።ነገሮች
ሁሉ የማይታመኑ ሆነውበታል፤ በገሀዱ ዓለም የሌለችን የአንድን ደራሲ የምናብ ሴት መውደዱ ሳያንሰው ይባስ ብሎ እሷን የምትመስል ሴት በአካል ማየቱ ሌላ ግርምትን ፈጥሮበታል። የሰው ልጅ በምኞቱ ብዙ ተአምራትን መፍጠር የሚችል እንስሳ እንደሆነ ያነበባቸው በርካታ መጽሐፍት ነግረውታል።
ምኞት ምንምነትን ወደ ሙልአት የሚቀይር ኃይል እንደሆነ ቢያምንም የኤልሳ በአካል መገለጥ ግን ከሚያምነው እውነት በላይ ሆኖበታል። ከሆነው ሁሉ በላይ ግን የኤልሳ ሰው መሆን አስደንቆታል።
መጀመሪያ ሲያያት ህልም ነበር የመሰለው።እንደ ኤልሳ የሆነች፣ እንደ እሷ የምትስቅ፣ እንደ እሷ የለበሰች ሴት አጠገቡ ቆማ ሲያይ ምን ማለት እንዳለበት ግራ ተጋብቶ ነበር። በሕይወት ውስጥ ያሉ ሁሉም ነገሮች በማሰብ የሚሳቡ እንደሆነ ደረሰበት።እስከ መጨረሻው አስቦ ኤልሳን የምትመስለውን ሴት ወደ ሕይወቱ ሊስባት ተመኘ።
የማለዳው ስስ ንፋስ የግቢውን አረንጓዴ እጽዋት እያስለቀሰ ወደ ቤት ሲገባ ከተቀመጠበት ተነሳ።ኤልሳን ወዳየበት ቦታ አቀና። ‹ሁሉም ሰው ለዚህ ዓለም ታሪክ› ነው።እስከ ዛሬ ድረስ ያነበበው ታሪክ በሆነ ሰው የተጻፈ የሆኑ ሰዎች ታሪክ እንደሆነ ልብ አለ።ከዕለታት አንድ ቀን በማናውቀው ቦታና በማናውቀው ደራሲ ታሪካችን ተጽፎ ትውልድ ያነበናል፣ እሱም ራሱ በሆነ ሰው የሆነ ቦታ ላይ እየተነበበ እንደሆነ አሰበ፤ በትናንትና በዛሬው ውስጥ የተረዳው እውነት ይሄ ነው።
ርዕሱ የተሸፈነውን መጽሐፍ በእጁ እንደያዘ ነው።ወደ ሥራ ሲሄድና ከሥራ ሲወጣ ዓይኑን ወደ ሱቋ ጣል አድርጎ አይቷት ያውቃል፤ መመሳሰላቸው ይገርመዋል።ለወራት ያህል በዛ መንገድ ተመላልሷል።አንድም ቀን አዋርቷት ግን አያውቅም።አውቆ ይሆን ሳያውቅ የመጽሐፉ ታሪክ የእሷ ታሪክ ይመስለዋል።
መጽሐፉ ላይ ያለችው ኤልሳ የማይመጣ የልጅነት ፍቅረኛዋን የምትጠብቅ ሴት ናት።ለጠየቃት ሁሉ እጮኛ እንዳላት የምትናገር።እምነቷ፣ ጽናቷ፣ አፍቃሪነቷ ይገርመዋል።ይቺኛዋም ሴት መጽሐፉ ላይ እንዳለችው ሴት የማይመጣ ፍቅረኛዋን እየጠበቀች ቢሆንስ ሲል ይፈራል።
ቀርቦ ወደድኩሽ ካላት በኋላ መጽሐፉ ላይ እንዳለችው ሴት ፍቅረኛ አለኝ ብትለው ምን ይውጠዋል? ሊያወራት ይልና ይሄን ሲያስብ ወደ ኋላ ይላል። ካለችበት ደረሰ፤ ዓይኑን ወዳለችበት ወረወረ።ዓይኑ ብረት መዝጊያ ከሚያህል ትከሻ ጋር ተላተመ።ኤልሳ ውፍረታቸው ሱቋን በሞላው ሦስት ወንዶች ተሸፍናለች።እያሳቋት ነው፤ ሳቋ..ሱቁን አልፎ፣ ሦስቱን ጎረምሶች አልፎ ጆሮው ደረሰ።መጽሐፉ ላይ ካለችው ኤልሳ የምትለይበትን አንድ ነገር አወቀ። የመጽሐፏ ኤልሳ ብዙ አትስቅም፤ ብትስቅም ሳቋ መንደር አልፎ ሩቅ አይሰማም።ተለያዩበት።
ለወራት በዚያ መንገድ ሲያገድም፣ ለወራት በዛ ቦታ ቆሞ ሲያያት እንደዛ ስትስቅ፣ እንደዛ በጎረምሳ ተከባ አላያትም ነበር።ዛሬ ምን ሆና ይሆን? ርዕሱ የተሸፈነውን መጽሐፍ ጭኑ ላይ እየጠበጠበ በሀሳብ ባዘነ።የጎረምሶቹ አርበ ሰፊ ትከሻ የሚናፍቃትን ሴት ከልለው ነፍሱን አራቆቱበት።
ገለል ባሉበት ቅጽበት ያየው ነገር ግን ሌላ ነበር።ሱቁ ውስጥ ያለችው ሌላ ሴት ናት።ከጎረምሶቹ ጋር ስትስቅ የነበረችው፣ ሳቋ ከአገር አገር የሚሰማው የሚያውቃት ሴት አልነበረችም። ልቡ ድም ድም እያለ ወደ ሱቁ ተጠጋ።ጎረምሶቹ ሲወጡ ዓይኑን ወደ ውስጥ ማተረ ከሳቂታዋ ሴት በቀር ሌላ ማንም አልነበረም።
እንደዛ ቀን መንፈሰ ደካማ ሆኖ አያውቅም።እንደዛ ቀን ጥበብ ርቆት አያውቅም።እንደዛ ቀን ባዶነት ተሰምቶት አያውቅም። ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ የጠፋችውን ኤልሳን በመጽሐፉ ገጽ ውስጥ ሊፈልጋት ሌሊቱን ሙሉ ቁጭ ብሎ መጽሐፉን ሲያነብ አደረ።ኤልሳ የምትጠብቀው የልጅነት ፍቅረኛዋ መጥቶላት ከእሱ ጋር አብራ ስትኖር መጽሐፉ ያበቃል።
ጠዋት ሲሆን ከእንቅልፉ ነቃ፤ ከመስኮቱ አንጻር ካለው ወንበር ጋ ተቀምጦ ከትኩስ ቡና ጋር ጋዜጣ ሲያነብ አረፈደ።ርዕሱ የተሸፈነው መጽሐፍ የገጸ ባህሪዋን መጨረሻ ቢነግረውም እውነተኛዋ ኤልሳ ትቀረዋለችና የእሷን መጨረሻ ለማወቅ ከወንበሩ ተነሳ። እንዲሆንለት የሚመኘውን እውነት በሀሳቡ እየመላለሰ ወደ ኤልሳ መንደር አቀና።እንደ ትናንቱ በጎረምሳ ቀልድ ከጣሪያ በላይ የምትስቅ ሴት ሳይሆን በዝምታዋ ቅጥር የምትደረምስ ጨዋ እንስት ናፍቆ፣ በወንዶች አጀብ ጎጆዋን የቀለሰች ነፍስ ሳትሆን በእርጋታዋ የጠለለ ውቅያኖስ የምትናውጥ አንዲት ነፍስ ሽቶ ወደ ፊቱ አለ።
ግን እንደ ሀሳቡ የሆነ ምንም አልነበረም።በዛው ሰዓት፣ በዛው ቦታ ከነዛ ጎረምሶች ጋር ያቺኑ ሴት ከጣሪያ በላይ እየሳቀች አገኛት። በዛ መንገድ ለዘመናት አለፈ፤ ኤልሳን የምትመስለውን ሴት ግን ዳግም አላያትም። አንዳንድ እድሎች አንድ ጊዜ ናቸው፤ በሕይወት ዘመን ዳግመኛ አይመጡም።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 27/2014