በየምክንያቱና በሰበብ አስባቡ መደገስ የሚወድ ህዝብ ቢፈለግ፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን ከፊት ሳንሰለፍ አንቀርም። ኧረ እንዲያውም ድግስ የሚባለው ነገር ከእኛ ጋር የተለየ ቁርኝት ያለው ይመስለኛል። እርግጥ ነው፤ ባጣጣሙት ልክ ደስታን ከሌሎች ጋር መጋራት ባህላችን ነውና በአንድ በኩል መልካምነቱ ይጎላል።
ደጋሽ ካጠራቀመው፣ ከተበደረው አሊያም ያለውን ሽጦ በሚያዘጋጀው ድግስ ተካፋይ የሚሆኑለትን ሰዎችም እንደ ወጉ «ብሉልኝ፤ ጠጡልኝ» እያለ ቁጭ ብድግ ይላል። ይሄ መስመር ሲስት ግን ብክነት የሚባል ስም ያሰጠዋል። እኛ የምናውቀው የለመድነውም፤ ደግሶ ማብላት እንጂ፤ ደግሶ ለራስ መብላት አይደለማ።
እስኪ አስቡት ከአንድ ቤት በተዘጋጀው ድግስ ላይ ደጋሽ የሆኑት የቤቱ ባለቤቶች ራሳቸው የክብር ዕንግዳ ተሰኝተው፣ እርስ በእርሳቸው «ብሉልኝ፤ ጠጡልኝ» ሲባባሉ። ይህን አይነት የደጋሽነት ስሜት ደግሞ በእነዚሁ ኢትዮጵያውያን የስራ ቦታዎች ወይም ተቋማት መዘውተር ከጀመረ ደግሞ ዋል አደር ማለቱ ብቻ ሳይሆን፤ ደግሶ እንግዳን በመጥራት ብሉልኝ፣ ጠጡልኝ የሚለውን ህዝባዊ ባህል ወደ “በራስ ለራስ” ወይም ደጋሹም፣ ተጋባዡም አንድ አካል የሚሆንበት እውነታ ተቀይሯል፡፡
አሁን አሁን እየሆነ ያለውም እንዲያ ነው(ብክነት)። ለምሳሌ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በርካታ ድግስ በየመስሪያ ቤቱ እና ተቋማቱ ሲከናወን ቆይቷል(የሴቶች ቀንን አስመልክቶ)። እኔ ግን ምን ታዘብኩ መሰላችሁ ራሳችን ደግሰን ራሳችን ስንበላ እንደነበር።
የሴቶች ቀን ወይም «ማርች 8» የሚሉትን በዓል ካለፈው አርብ ጀምሮ ስናከብር፤ እንዴት እንደነበር አላስተዋላችሁም? ላስታውሳችሁ፤ በርካታ ሴቶች በአንድ አዳራሽ ተሰብስበው «ስለ ጾታዊ ጥቃት፣ ስለ ሴት ልጅ ችሎታ፣ ሴት ልጅ፤ ሃገር፣ እናት፣ ሚስት ልጅ፣… ስለመሆኗ» እንዲሁም ይህንን የመሳሰሉ ግንዛቤ ማስጨበጫዎችና ውይይቶች ሲካሄዱ ነበር።
ይህንን ማድረጋቸው መልካም ሆኖ ሳለ፤ በየአዳራሹ የውይይቱ ተካፋይ ለመሆን የታደሙት «እነማን ናቸው?» ብለን ብንጠይቅ(አንጠይቅም እንጂ)፤ የምናገኘው መልስ፤ ጾታዊ ጥቃት ያልደረሰባቸው አሊያም ከጥቃቱ ያገገሙ፣ ችሎታቸውን በስራ እና በእውቀታቸው በማረጋገጥና በተወዳደሩበት ስፍራ መቻላቸውን ያሳዩ፣ እናት፣ ሚስትና እህት የሆኑ «ስኬታማ ሴቶች» ናቸው።
የተጨቆነችውና «አትችልም» የምትባለው ሴት ግን ይህንን በዓል የማክበር እድሉን አላገኘችም። በደረሰባት ጥቃት ከቤት የተደበቀች፣ ከሆስፒታል እና ከማገገሚያ ማዕከል የምትገኝ፣ እየቻለች «አትችዪም» በመባሏ ህልሟን ሳታሳካ ከጓዳ የቀረች፣ ልጆቿን ለማሳደግ ሰውነቷ እስኪዝል ከአቅሟ በላይ የምትሰራው፣ በጥጋበኛ ባለቤቷ የምትደበደበው፣ ጉልበቱን በተማመነው የምትደፈረው፣ … ሴት፤ የታለች?
ዕለቱ እንዲህ ዓይነቷ ሴት እንድትታሰብና ክብርንም እንድታገኝ ነበር መታወሱ። መንገዱን ስቶ በየቢሮው የምንሰራው፣ ነግደው ያተረፉት፣ ተምረው ብዙዎችን ከሚመሩት፣ የሚኒስትርነት ደረጃን ካገኙት፣ በስራቸው ክብርን ከተጎናጸፉት፣… ሆነ እንጂ። ሃሳቤ እነዚህ ሴቶች አይከበሩ አይደለም፤ ነገር ግን ሴትን ልጅ እናብቃት ከተባለ ዕድሉን ያላገኘችውን መርዳት ነው የሚገባው።
እነዚያ ሴቶች እኮ እኛ ከወንዶች እንወዳደር ዘንድ ድልዳል ሆነው አረማምደውናል። እናም ስለ ሴት ልጅ ክብር፣ እኩልነትና ችሎታ እያስተማሩ ማንቃት ተገቢ ነው። ታዲያ «የሴቶች ቀን» እያልን በከተማ የምንገኘው ራሳችንን ማክበራችን ተወት አድርገን እኛ ያገኘነውን እድል ስላላገኙት ማሰብ እንደሚገባን ከግምት ይግባልኝ።
ሌላው ደግሞ ራሳችን ደጋሽ ራሳችን በዪ የምንሆነው፤ ዕለቱን ለማክበር በምናዘጋጀው መድረክ የሚልቁት ተሳታፊዎች ሴቶች በመሆናቸው ነው። «እንዴት?» ለምትሉ መልሴ፤ «ስለ ጾታዊ ጥቃት፣ ስለ ሴት ልጅ ችሎታ፣ ሴት ልጅ፤ ሃገር፣ እናት፣ ሚስት ልጅ፣… ስለመሆኗ» እንዲሁም ይህን መሰል ጉዳይ ለራሷ ሊነገራት ይገባል?
ምክንያቱም የሴቷን ስነ ልቦና የሚጎዱት፣ እድል የማይሰጧት፣ የሚጨቁኗት፣ ጥቃት የሚያደርሱባት እና በራሷ መቆም እንዳትችል ከሚያደርጓት ምክንያቶች የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት ወንዶች ናቸው። ለሴቷ ወንድ ስለሚያደርስባት ጥቃት መንገር ለውጥ ሊያመጣ አይችልምና ዕለቱን ወንዶች በመማር የሚያሳልፉበት ቢሆን መልካም ነው።
ይህንን ስል ግን ወንዶች እንደኛው ዕለቱን ብቻ እንዲያከብሩት ሳይሆን ሴትን ልጅም ማክበር እንደሚገባ እንዲያውቁ ነው። እንጂማ ሴቶች፤ እኛው በየተቋማችን አክብረን ጥቃት ሰንዛሪውንና የጥቃት ሰለባዋን ከዘነጋን ድግሳችንን ራሳችን አዘጋጅተን ራሳችን በላን ማለት ነው። ስለዚህም ከዛሬዋ ዕለት ጀምሮ አከባበራችን አቅጣጫ ሊይዝ ይገባል መልዕክቴ ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2011
ብርሃን ፈይሳ