መካኒክ ነኝ፤ ሙያዬን እወደዋለሁ። ራሴን ለመቀየር ብዙ እርምጃዎችን ተራምጃለሁ፤ ዛሬ ላይ እኚህ እርምጃዎች ምርጡን እኔን ፈጥረውታል። ውሎዬ ከመኪና ጋር ነው፣ በግሪስና በዘይት ያደፈ የስራ ልብሴን ለብሼ መኪና ጉያ ውስጥ እንደባለላለሁ።
ራሴን ለመለወጥ ባደረግኳቸው በርካታ እርምጃዎች ውስጥ የመልካምነትን ዋጋ ተምሬያለሁ። ሕይወቴን፣ ኑሮዬን ውብ ያደረጉ እንደኔው ከመኪና ጋር የተቆራኙ ጓደኞች አሉኝ። ጓደኞቼ ለእኔ ከምተነፍሰው አየር እኩል ዋጋ አላቸው።
ምድር ላይ የማልችለው አንድ ነገር ቢኖር ከጓደኞቼ መለየት ነው፤ ዓለም ላይ አንድ ምርጥ ስፍራ ባውቅ የጓደኞቼን ወዳጅነት ነው። ሁሉን አጥቼ በእነሱ የመልካምነት እቅፍ ውስጥ የምኖር ይመስለኛል።
በዚህ ሁሉ የሰላም ስፍራ ውስጥ ግን ከአንድ ሴት ጋር ተዋወኩ፤ ዜማ ትባላለች። ዜማ እንደ ስሟ ዜማ ናት፤ በውበቷ ውስጥ ማንም ያላዜመው ዜማ አለ። በሳቋ ውስጥ ማንም ያልተቀኘው ዜማ አለ። በድምጽዋ ውስጥ ማንም ያላዳመጠው ዜማ አለ። ለዘላለም ያልተዜመ ዜማ፤ ይቺን ተዋወኳት።
ዜማ አፍታ ናት፤ የምንም ነገር አፍታ። በእሷ ሴትነት ውስጥ ምንም ነገር ለዘላለም ሲቆይ አላየሁም። ያለምንም ቅደመ ሁኔታ እንዳየኋት የምትወዳት ናት፤ ለምን ካልክ መልስ አይኖርህም። ያለምንም ዝግጅት የምታስባት ናት፤ ለምን ካልክ መልሱን አታውቀውም፤ ይቺን ሰው ነው የተዋወኳት።
የጉንጯ ልስላሴ፣ የገላዋ ማማር ነፍሴ ውስጥ ይላወሳል፣ የእርምጃዋ ሰበር ሰካ፣ የፍቅሯ ቅኔ መወድስ ልቤ ውስጥ ያረግዳል፤ ይቺን ሴት ተዋወኳት። ከእሷ ጋር ስሆን ልብና አእምሮዬ ለምን ግራ እንደሚጋቡ አላውቅም።
ከእሷ ጋር ስሆን ዓለም ለምን እንደሚጠበኝ አላውቅም። ከእሷ ጋር ስሆን ሁሉ ነገሬ ያደረኳቸው ጓደኞቼ ለምን እንደሚረሱኝ አላውቅም። ከእሷ ጋር ስሆን በማላውቀው በሽታ እሰቃያለሁ፤ ደስ በሚል በሽታ። እንዴት እንደተዋወቅን ልንገራችሁ።
የዛሬ ሶስት ወር አካባቢ በእረፍት ቀኔ እሁድ ከጓደኞቼ ጋር የክት ልብሴን ለብሼ ቦሌ መንገድ ላይ እንቀዋለላለሁ። ከፊት ለፊቴ ዘመናዊ መኪናዋ የተበላሸባት አንድ ሴት ውብ መልኳን አመሳቅላ ትታየኛለች። ውብ የሚገልጻቸው ከሆነ ውብ ብያቸዋለሁ፤ ግን አይገልጻቸውም፤ እነዛን የወርቅ ፍንካች የሚመስሉ አይኖቿን ተማጽኖ በሚመስል አኳኋን አይኔ ላይ ስታንከባልላቸው የሆንኩትን አልረሳውም።
ልቤ ድም ድም እያለ ስሯ ደረስኩ፤ በዚያ ሰዓት ብረዳት የማገኘውን ደስታ ቆጠርኩት። ‹ተበላሽታብሽ ነው? ስል ጠየቅኋዋት። እንደዛ ቀን ለሴት ልጅ ያዘንኩበት ጊዜ ትዝ አይለኝም። ‹አዎ› አለችኝ። ባለዜማ ድምጽዋን ለመጀመሪያ ጊዜ ሰማሁት። አዎ በዜማ ሲባል ምን እንደሚመስል ያኔ ነው ያወኩት። በዚያ ክፉ ሰዓት ብረዳት የማገኘውን ደስታ ቆጠርኩት፤ እልፍ ደስታ አገኘሁ። የማጣውን አሰላሁት፤ ልብሴ ቢቆሽሽ ነው፣ እጆቼ በግራሶና በዘይት ቢርሱ ነው እኚህ ደግሞ ከእሷ መከራ ጋር ሲወዳደሩ ትንሽ ናቸው።
አንዳንድ ጊዜ የማይወዳደር እያወዳደርን ከሰውነት እንጎድላለን፣ የማይበላለጥ እያበላለጥን ከሕይወት እናንሳለን። በሕይወት ውስጥ ከምንም ጋር የማይወዳደሩ እግዚአብሔራዊ እውነቶች አሉ፤ እንዲህ እንደአሁኑ አይነት እውነት፣ በጭንቅ የተያዘችን ነፍስ እንደመታደግ አይነት እውነት። በዚህ ሁኔታ ከዜማ ጋር ተዋወቅን፣ ተቀራረብን፣ አብረን ብዙ ራት በላን።
በእርግጠኝነት የምነግራችሁ አንድ ነገር ቢኖር ዜማን እንዳፈቀርኳት ነው። ብዙ ነገር እፈራለሁ፤ ብዙ ነገር እያስፈራኝ መጥቷል። እሷን ማጣት፣ ከእሷ መራቅ እፈራለሁ። ከኔ በላይ እንዳፈቀረችኝ ሳውቅ ደግሞ ልቤ ይረጋጋል። ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ቤቷ ቀጥራኛለች። ቤቷ የመንግስተ ሰማያት ያህል ናፍቆኛል፤ የገሀነምን ያህልም ቀፎኛል። በዘመኔ ሙሉ የሚያስደንቀኝ አንድ ጥበብ አለ.፤ ፈጣሪ ፍቅርን የሰወረበት ጥበብ።
ቤቷ ሄድኩ፤ በር ላይ ውሻዋ እግሬ ላይ ተንደባሎ እጅ ነሳኝ። ውሻዋን እንደታቀፈች እኔን ከፊት እየመራች ወደ ሳሎን ሄድን። ስለ ሳሎኑ ውበት አልነግራችሁም፤ ሳሎን ስደርስ ስለገጠመኝ ላውራችሁ።
እኔን ሳሎን ጥላ ውሻዋን እንደታቀፈች ወደሚቀጥለው ክፍል አመራች። እስክትመለስ ሳሎኑን ቃኘሁት፤ ግድግዳው ላይ አንድ ፎቶ አየሁ፤ የሕይወቴ የመጨረሻ ቀን መሰለኝ። የሰርጓ ፎቶ በትልቅ ፍሬም ውስጥ ተሰቅሏል፤ ብቻዋን አይደለችም፤ የቀለበት ጣቷን የሚስም አንድ ወጣት አብሯት አለ። ልቤ ይመታል። ራሴ ጠፋኝ። አይኖቼን ወደሌላኛው የግድግዳው እርቃን ሰደድኩ ከሁለት ሴት ልጆቿ ጋር የተነሳችውን ሌላ ፎቶ አየሁ። ቀዘቀዝኩ፤ የመከራ ቅዝቃዜ ምን እንደሚመስል ያኔ አየሁ። ‹ምን አይነት ሴት ናት? ከብዙ ክፉ ነገሮች ጋር አመሳሰልኳት። ከአጋንት፣ ከጭራቅ፣ ምድር ላይ ካለ መጥፎ ነገር ጋር ሁሉ አመሳሰልኳት።
ለዘላለም ማንንም በማልጠላበት ክፉ ስሜት ጠላኋት፤ አቄምኩባት። ቆንጆ ናት፤ ጥሩ ሕይወት አላት፤ ይሄን ሁሉ የሆነች ሴት እንዴት እናት መሆን አቃታት? ለምን ሴት መሆን አቃታት? ለልጆቿ ጥሩ እናት፣ ለባሏ ጥሩ ሚስት መሆን እንዴት ተሳናት? እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ።
ባሏ የሌለው እኔ ምን አለኝ? የልጆቿ አባት ከሰጣት ሌላ ምን የምሰጣት ኖሮ ነው ያፈቀረችኝ? መልስ አልነበረኝም። ብዙ የሚያምር ነገር አላት፤ ግን ሴት አይደለችም። ብዙ የሚወደድ ነገር አላት ግን፤ እምነት የላትም። ብዙ የሚስብ ነገር አላት፤ ግን ፍቅርን አታውቅም። ይቺ ሴት ምን ታደርግልኛለች? ወደ ሕይወቴ መጥታ ነፍሴን ከማቆሸሽ ሌላ ምን ትጠቅመኛለች እያልኩ ሳስብ ነፍሴን ከስጋዬ የመነጠቀ አንድ ነገር ተከሰተ።
‹ምነው አቀረቀርክ..› የሚል ድምጽ ሰማሁ። ለካ አቀርቅሬ ነበር፣ እስከዛ ሰዓት ማቀርቀሬን አላሰታውስም ነበር። ቀና አልኩ። ‹ተዋወቃት እህቴ ናት..› በስብራቴ ውስጥ የዜማ ድምጽ ተሰማኝ። ቁርጥ እሷን የምትመስል ሴት ፊቴ ቆማ አየሁ።
ቁርጥ እሷን የምትመስል እህቷን ተዋወኩ። ግድግዳው ላይ ያለችው ሴት ናት፤ እንደዛ ቀን በራሴ አፍሬ አላውቅም። ለካ እንደዛ ሳማት የነበረው የዜማ እህት ነበረች፣ ለካ ግድግዳው ላይ ከአንድ ወንድና ከሁለት ልጆቿ ጋ ፎቶዋን ያየኋት ሴት ታላቅ እህቷ ነበረች። ነፍሴ ስትረጋጋ የማልረባው እኔ እንደሆንኩ ገባኝ። ከእለታት አንድ ቀን ተጋብተን ልጆች ወልደን አሁን የተሰማኝን እንደምነግራት እርግጠኛ ሆንኩ።
ሰው ለምን ለመፍረድ ይቸኩላል? ይቺ ሴት ያሰብኩትን ሁሉ ብትሆን እንኳን ለምን እንደዛ እንደሆነች ምክንያቷን ማወቅ እንጂ ደርሶ መፍረድ ምን የሚሉት ነው? አይ ሰው አልኩ የራሴ ሰውነት አንሶብኝ።
በመጨረሻም ለአምላኬ ይሄን ነገርኩት፤ በዜማ በኩል ለዘላለም እንደማመሰግነው። ከዛም ለራሴ እንዲህ አልኩት፤ ‹ዜማ የመልካምነት ስጦታዬ ናት፤ ልብሴ ይቆሽሻል ብዬ ብተዋት ኖሮ ይሄን ሁሉ መባረክ አላይም ነበር። መልካምነት ይከፍላል፤ ሁሌም ስጦታ አለው። ለዜማ እንዲህ አልኳት፤ ‹አንቺ የነፍሴ ዜማ ነሽ..።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 20/2014