«ልማድን ምክንያት አያሸንፈውም» እንዳለው ፈላስፋው ለብዙ ዘመናት በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ሲዘወተሩ የነበሩ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማዶችን በአዲስ ለመተካት መሞከር እጅግ አድካሚ ከመሆኑም በላይ አንዳንዴም አገራዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል። ይህን በምሳሌ ማየት ይቻላል።
የዓለም ንጉሥ የሮማን ኢምፓየሩ ንጉሥ የሚመስላቸው በርካታ ሰዎች በነበሩት በዚያ ዘመን እየሱስ ክርስቶስ ታላቁን መጽሐፍ በማስተማር የዓለም ንጉሥ እርሱ እንደሆነ በነገራቸው ጊዜ የደረሰበትን በደል የምናውቀው ነው። ክፉ ነገር የሰበከ እና ያስተማረ ይመስል ተደብድቦ በወንበዴዎች መካከል እንዲሰቀል ተፈረደበት። ነብዩ መሐመድም ቅዱስ ቁርዓንን ለማስተማር በተንቀሳቀሱበት ጊዜም የደረሰባቸውን እንግልት የምናውቀው ነው። መጀመሪያ ተቃውሞ የተነሳባቸውም ከሰፈራቸው ነው። ምክንያቱም ይዘውት የመጡት ሃሳብ አዋጭ ቢሆንም ከማኅበረሰቡ ልማድ የተለየ ስለነበር በቀላሉ ሊቀበለው አለመቻልም ነበር።
በአገራችንም በተለያዩ ዘመናት ኢትዮጵያን ሲያስተዳድሩ የነበሩ መንግሥታት አዲስ ነገር ይዘው በመጡ ጊዜ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸው እንደነበር ታሪክ ይነግረናል። ለምሳሌ በዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ እና በዳግማዊ ምኒሊክ ዘመን አጋጥመው የነበሩ አንዳንድ ጉዳዮችን በወፍ በረር እንመልከት።
ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ገና ስልጣን ላይ በወጡ ጊዜ ለወታደሮቻቸው ደመወዝ ለመክፈል እንደተዘጋጁ በአዋጅ አስነገሩ። አዋጁ ከመውጣቱ በፊት የኢትዮጵያ ወታደር እየዘረፈ እና የፈለገውን ሴት እየደፈረ ይኖር ነበር። ይሄም ለወታደሩ እንደ ደመወዝ ይቆጠርለት ነበር። በዚህም ብዙ ሕዝብ ለከፋ በደል እና ስቃይ ተዳርጎ ቆይቷል። ይህን ተከትሎ ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ለወታደራቸው ደመወዝ እንደሚከፍሉና ከዚህ በኋላ አንድም ወታደር ሕዝቤን ቢዘርፍ እና ሴቶችን ቢደፍር ከባድ ቅጣት እቀጣለሁ ብለው ጥብቅ መልዕክት ለወታደሮቻቸው አስተላለፉ። ነገር ግን ከመንግሥት ደመወዝ ተከፍሎት የማያውቀው ወታደር ከመንግሥት ደመወዝ መከፈሉን በደል እንደተፈጸመበት ቆጥሮት ነገሩን በክፋት አይን ይመለከተው ነበር። በዚህም ምክንያት ንጉሡን በተደጋጋሚ በመክዳት ወደ ጫካ የገቡ ወታደሮች ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም።
በተመሳሳይ ከአዳዲስ አስተሳሰቦች ጋር ተያይዞ አጼ ምኒልክ ከሕዝብ በተለያዩ ጊዜያት ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር። አንደኛው ተቃውሞ አጼ ቴዎድሮስ በሞቱ ጊዜ የተፈጠረ ነው። አቤቶ ምኒልክ ከመቅደላ አስር ቤት አምልጠው ሸዋን ለማስተዳደር ላይ ታች ይሉ በነበረበት ጊዜ አጼ ቴዎድሮስ ከእንግሊዞች ጋር ጦርነት አድርገው ይሞታሉ። በዚህ ጊዜ አቤቶ ምኒልክ አባቴን፣ አጼ ቴዎድሮስን ስለተጎዳሁ እኔን የሚወድ ሰው በሙሉ ለሐዘን እንዲቀመጥ ሲሉ ለሸዋ ሕዝብ አስነገሩ።
የሸዋ ሕዝብም እንዴት ለአጼ ቴዎድሮስ መሞት እንድናዝን ይነግሩናል? ከዚህ በፊት የሸዋ መኳንንቶችን እና ሕዝብን በጭካኔ የጨፈጨፈ አጼ ቴዎድሮስ ሆኖ ሳለ እንዴት ለአጼ ቴዎድሮስ እንድናዝን ይነገረናል? ማዘን ከፈለጉ ለብቻዎት ራስዎ ይዘኑ በማለት ሕዝቡ ንጉሱን ገሰጸ። ይህን ተከትሎ አቤቶ ምኒልክም ምንም እንኳን አባታቸውን ኃይለ መለኮትን የገደሉባቸው አጼ ቴዎድሮስ ቢሆኑም፤ አጼ ቴዎድሮስ ህጻኑንን ምኒልክን በምርኮ በወሰዱ ጊዜ ያደረጉላቸውን አባታዊ እንክብካቤ በማስታወስ ለብቻቸው ጫካ ገብተው ለአንድ ሳምንት ያህል በሐዘን እንደተቀመጡ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ። ይሄም ይቅር ባይነታቸው በቀረው የኢትዮጵያ ከፍል ክብርን አስገኝቶላቸዋል።
ሁለተኛው አጼ ምኒልክን በሕዝብ በተለይ (በአግራሞት) እንዲታዩ ያደረጋቸው ጉዳይ ደግሞ ከጎበና ዳጬ ጋር ያደረጉት ዝምድና ነበር። አጼ ምኒልክ የጦር ጄኔራላቸው ከነበረው ጎበና ዳጬ ጋር መጀመሪያ ላይ ከፍተኛ ውጊያ አድርገው ነበር። ጎበና ዳጬ የንጉሡን ብዙ የሰው ኃላይቸውን እና ንብረት ቢያወድምባቸውም ጎበና የሚመራውን ሕዝብ በአገረ መንግሥት ግንባታ በማካተት አገረ መንግሥቱን የጸና ለማድረግ ጎበና ዳጬን ጄኔራላቸው አድርገው ሾሙት። ይህም የአገሪቱ ሰላም እና እድገት መሠረት እንዲጸና በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
አጼ ምኒልክ ሕዝብ በአግራሞት እንዲመለከታቸው ያደረገው ሌላውና ሶስተኛው ጉዳይ ደግሞ ከካዎ ጦና ጋር ያደረጉት ስምምነት ነበር። አጼ ምኒልክ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ግንባታ ጊዜ እጅግ ደም አፋሳሽ ውጊያ ያደረጉት ከወላይታው ንጉስ ከካዎ ጦና ጋር ነበር። በጦርነቱ በሁለቱም ወገን ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ደረሰ። ነገር ግን ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ደረሰ ብለው እምየ ካዎ ጦናን አልገደሉትም። እርስቱንም አልነጠቁትም። እየመረራቸውም ቢሆን ለኢትዮጵያ አገረ መንግሥት መጽናት ሲሉ ሁሉን ነገር ይቅር ለእግዚአብሄር ብለው የካዎ ጦናን እርስት ሳይነጥቁ የወላይታ ገዢ አድርገውት ነበር። ወደ አድዋ ጦርነት ሲዘመቱም የመሐሉን አገር እንዲጠብቅ አደራ ሰጥተውት የዘመቱት ለካዎ ጦና ነበር። በዚህም የወላይታን ግዛት ከኢትዮጵያ ግዛት ጋር በሰላም እንዲቀላቀል በማድረግ አገረ መንግሥቱ እንዲጸና አድረጉት። አሁን ላይ የወላይታ ሕዝብ ስለ ኢትዮጵያ ይሞታል። በማንኛውም ረገድ ኢትዮጵያን ከጠላቶቿ ለመጠበቅ ግንባር ቀደም በመሆን ከፊት ሲሰለፍ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተመልክተናል። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ይቅርባይነት እንደሆነ ልብ ይሏል።
ይህ ሲሆን ግን በርካታ ቁጥር ያላቸው የምኒልክ ዘማች ወታደር ቤተሰቦች እና ወታደሮች ልባቸው በፈላ ዘይት ውስጥ እንደተጨመረ ድንች እርር ድብን ማለቱ አልቀረም። እውነቱ ግን የሞቱት ለአገራቸው ህልውና እስከሆነ ድረስ ከካዎ ጦና ጋር ለሰላም እጃቸውን መዘርጋቱን ሲመኙት የነበረው የጸና አገረ መንግሥት በመመስረት በኩል ከፍተኛ ዋጋ ነበረው።
በተመሳሳይ ሰሞኑን መንግሥት ከወሰነው የክስ መቋረጥ ጋር ተያይዞ በመንግሥት የተወሰኑ ውሳኔዎችን ለመቀበል ብዙዎቻችን ተቸግረናል። በአገር መክዳት ወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ እና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ የነበሩ ግለሰቦችን ክስ መቋረጥ የብዙ ሰዎችን ጆሮ ጭው አድርጓል። ይህ የሆነበት ዋና ምክንያት ደግሞ በእኛ አገር እስከዛሬ የነበረው ልምድ እንደሚያሳየው ሰዎች ከአገር ህልውና ጋር ተያይዞ ጥፋት ካጠፉ እንደጥፋታቸው ከቀላል እስራት እስከ ሞት ቅጣት ይቀጡ ስለነበር ነው።
ነገር ግን ለሐገር ሕልውና እና ለወደፊቱ በጋራ ለመኖር ሲባል ማንም ያደርጋቸዋል ተብለው የማይጠበቁ እና የማይገመቱ ውሳኔዎችን መንግሥት ሊያስተላልፍ ይችላል።
በዓለም ታሪክ እንደ አንደኛው እና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት አስከፊ ጦርነት አልተካሄደም። ነገር ግን የቱንም ያህል አስከፊ ቢሆንም አገራት የወደፊቱን በማሰብ «ይቅር ለእግዚአብሄር» ተባብለው በሰላም ሲኖሩ እያየን ነው። አውሮፓውያን አሁን ለደረሱበት እድገት ዋናው መሠረቱ በአንደኛው እና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የደረሱ ጥፋቶችን ይቅር ተባብለው ወደ ሥራ መዞራቸው ነው።
በሕልውና ዘመቻው ወቅት በኢትዮጵያ ላይ ይደርስ የነበረውን ጉዳት ከምንም ባለመቁጠር ከዳር ቆመው እንደፊልም ሲመለከቱ የነበሩ አካላት “ለምን?” የሚል ጥያቄ በማንሳትና ተቆርቋሪ በመምሰል መንግሥት እና ሕዝብ ያላቸውን የጠበቀ ቁርኝት ለማላላት ብቻ አይደለም ለመበጠስ ሁሉ ተግተው እየሠሩ ነው። በተለይ ኢትዮጵያ ጠል የሆኑ የማኅበራዊ ሚዲያ ጦረኞች ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሄዱበት ያለውን ርቀት ማጠናከሪያ እያደረጉት ነው።
ስለሆነም ይህንን፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ጦረኞች እየሄዱበት ያለውን አገርን የማተራመስ ሥራ ከጁንታው የሚበልጥ እንጂ የማያንስ መሆኑን በመረዳት በሕልውና ዘመቻው ሁሉን አቀፍ ዘመቻ ሲያደርግ የነበረው፣ በውስጥም በውጭም የሚኖረው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንደዚህ ቀደሙ አንድነቱን ጠብቆ ሊቆምና ሊቋቋማቸው ይገባል መልዕክቴ ነው።
አሸብር ኃይሉ
አዲሰ ዘመን ጥር 14 ቀን 2014 ዓ.ም