ሕይወት ዳና አላት፤ መሽቶ በነጋ ቁጥር የምንረግጠው፣ በነፍሳችን ላይ የምናትመው የዕጣ ፈንታ ማህተም አላት። የሕይወት ዳና አንድ ቦታ አይቆምም፤ እስካለን ድረስ የሚከተለን የሰውነት ጥላ ነው። በዚህ የሰውነት ጥላ ከአምና ውስጥ ትናንትን ከዘንድሮ ውስጥ ዛሬን ከከርሞ ውስጥ ደግሞ ነገን እንስላለን። በዚህ የጊዜ ሂደት ከአሁን ተነስተን ወደ ዘላለማት እንሄዳለን፤ ሜላት ከእንቅልፏ ስትነሳ ይሄን እያሰበች ነበር።
ወደ መስኮቱ ተጠግታ መጋረጃውን ገለጠችው። ከታች ከመንገዱ ብዙ ሰዎች ወደዚያ ወደዚህ እያሉ ታዩዋት። ለመኖር የሚከፈል ዋጋ ያስገርማታል። ሰው መሆን ትልቅ ጸጋ ነው በዚህ ጸጋ ውስጥ የሚፈልጉትን አግኝቶ መኖር ደግሞ እጅግ ከባዱ ነገር ነው። ከታች ያየችው የሰዎች ትርምስ ይሄን እውነት ነው ያስረዳት።
‹ሕይወት ሦስት ቀን ናት፤ ትናንት ዛሬና ነገ፤ መስኮቱ አጠገብ እንደቆመች እንዲህ አሰበች። የሰው ልጅ በእኚህ የቀናት ፈረቃ ውስጥ ይመላለሳል። ሁሉም ሰው ነገ አዲስ ቀን ይመስለዋል፣ በመኖር ውስጥ ዛሬን አዲስ ቀን አድርገው የተቀበሉ ጥቂቶች ናቸው።
ዛሬ ከዘላለማት እንደምትልቅ መረዳት ብንችል ኖሮ የማናውቀውን ነገ በመጠበቅ ጊዜአችንን አናባክንም ነበር ስትል ተናግራ መጋረጃውን ዘጋችው። ጀርባዋን ለግድግዳው ሰጥታ ሰፊው ሳሎን ውስጥ ብቻዋን ቀረች። ብቻዋን ስትሆን የሀሳብ ባሪያ ናት። ብቻዋን ሆና ትናንትን የረሳችበት ጊዜ የለም። ትናንት ከነግሳንግሱ ፊቷ ድቅን የሚለው እንዲህ እንደ አሁኑ ብቻዋን ስትሆን ነው። ከታች ከመንገዱ ያየችው የሰዎች የመኖር ግብ ግብ ሴትነቷን ነቀነቀው። እሷም ትናንት ዛሬና ነገ አላት፤ በሕይወት ውስጥ ያበበችበት.፤ የጠወለገችበትም አምናና ካቻምና።
‹ሕይወት ሦስት ቀን ናት፤ ትናንት ዛሬና ነገ›› ስትል በዝግታ አወራች። መንፈሷ ወደ ትናንት አዘገመ።
ትናንት
የሴትነቷ አለላ ሰበዝ ነበር፤ ራሷን ውብ አድርጋ የኳለችበት። በእናቷ የጽናት ክንድ አለም ጠባትና አንሳት ኢምንት ሆና ያየችበት። በእናቷ የሴትነት ሻማ በርታ የወገገች ሳዱላ።
በመደዳ ከተሠሩ የቀበሌ ቤቶች በአንዱ ውስጥ እሷ ሁለት ወንድሞቿና እናቷ ይኖራሉ። ጠዋትና ማታ ከአልጋ ላይ አትነሳም። እናቷ ጓዳ ውስጥ ሲንደፋደፉ እሷ የእጆቿን ጣቶች እየሞረደች እሷ አልጋ ላይ ናት። እናቷ እንጀራ ጋግረው ወጥ ሲሰሩ፣ ቤት አጽድተው ውሃ ሲቀዱ እሷ ተመልካች ነበረች። ‹ውዴ፤ አንቺ ውዴ› ጓዳ ሆነው ይጠሯታል። ውዴ ነው የሚሏት አንድም ቀን ሜላት ብለዋት አያውቁም።
”አቤት..
‹ነይ እስኪ፤ ወፍጮ ቤት ደርሼ እስከመለስ ሊጡን አቡክተሸ ጠብቂኝ› ይሏታል።
‹እማ ደሞ! ጥፍሬ ይሰበርብኛል..› በማለት አልጋ ላይ ሆና የእምቢታ ድምጽዋን ታሰማለች።
እናት ዝም ይላሉ። በእናቷ ዝምታ ውስጥ ዛሬም ድረስ ያልደረሰችበት የፍቅር መንደር አለ። ብትሄድ ብትሄድ ያልደረሰችበት የይቅርታ ወደብ። እዚህ ወደብ ላይ መቼም አትደርስም።
እናት ከጓዳ ወጥተው ወፍጮ ቤት ይሄዳሉ። እሷ ከአልጋ ላይ ሳትነሳ ከወፍጮ ቤት ይመለሳሉ። ከዚያ ገበያ፣ ከዚያ የታመመ ጥየቃ፤ ከዚህ ሁሉ በኋላ ደግሞ ለልጆች ራት ለማዘጋጀት ወደ ማዕድ ቤት ይመለሳሉ።
በሌላ ቀን የእጇን ጥፍሮች በየዓይነት ቀለም
እየተቀባች..‹እማ ምሳ አልደረሰም? አለቻቸው።
‹እንጀራውን ጋግሬ ጨርሻለሁ፤ ወጡ ነው የሚቀረኝ፤ ትንሽ ጠብቂኝ› ይሏታል።
‹እየራበኝ ነው›› አለቻቸው።
ወዲያው ትኩስ እንጀራ ከትኩስ ወጥ ጋር ያቀርቡላታል።
‹ነገ ቅዳሜ ነው የቤቱን ልብስ እንድታጥቢ›› ሲሉ ያዟታል።
‹ደክሞኛል እማ›› ስትል መለሰችላቸው።
እናት ዝም ይላሉ፤ በእናቷ ዝምታ ውስጥ የእግዜር ቅያሜ ይታያታል። በነጋታው የእሷም የወንድሞቿንም ልብስ ታጥበው ታያለች።
ዛሬ..
በብዙ የጽድቅ ሥራ የማትመልሰው የእናቷ የመልካምነት እዳ ተጭኗታል። ትናንቷ በአለት ላይ የተሠራው ሁሉንም በሚችል በእናቷ ሴትነት ነበር። በእናቷ ላይ የሠራችውን የእምቢተኝነት በደል በምን ታስተሰርየው ይሆን? ምን ብትሰራስ እግዜር ይቅር ይላታል?
ዛሬ ትልቅ ሰው ናት። በትልቅነቷ ውስጥ ግን ትናንትን የሚያሽር የይቅርታ መላ አላገኘችም። ቀሪ ዘመኗን ሙሉ ለእናቷ ብትለፋ የእናቷን ውለታ የምትመልስ አይመስላትም። ትናንትናዋ የተሠራው በእናቷ ጎንበስ ቀና ነው። ዛሬ ላይ እንደ ሰው የቆመችው የእናቷን የሴትነት ጽናት ተደግፋ ነው።
እናቷ ታስደንቃታለች። ዓለም ብዙ ጀግና ሴቶች ሊኖሯት ይችላሉ፤ እንደ እሷ እናት ጀግና ሴት ግን የትም አታገኝም። እናቷ የነፍሶች ሁሉ ማረፊያ ናት። በእሷ እምቢተኝነትና በእናቷ ዝምታ ውስጥ ቅያሜ አልነበረም። በእናቷ ልፋት ውስጥ የእሷ እረፍት ነበር። በሕይወቷ ሙሉ ለእናቷ አለመልፋቷ ያናድዳታል።
የእናት ልብ ለልጆቿ የነፃነት ዙፋን ነው። ምድር ላይ አንድ የነፃነት ስፍራ ቢኖር የእናት ልብ ነው ትላለች።
ከትናንት ቁጭት የምትድነው ወደ እናቷ በመሄድ ነው.፤ ሩቅ በመጓዝ እናቷ ካሉበት ትሄዳለች። አይኖቿ የእንባ ጭጋግ አጭገው እናቷን እንዲህ ትላለች ‹አንቺ የዘመኔ ፊደል ነሽ፣ አንቺ ጽድቅ የተማርኩብሽ የመምሬ አድባሬ ነሽ። አንቺ በኔና በታሪኬ መካከል የበቀልሽ የሊባኖስ ዝግባ ነሽ፣ አንቺ ለልጆቼ የምነግራቸው ጥኡም ታሪኬ ነሽ፣ አንቺ በጸጸት ጎጆዬ የምትኖሪ የርህራሄ እርግቤ ነሽ። አንቺ የነፃነቴ ምኩራብ፣ የሴትነቴ አልፋና ኦሜጋ ነሽ። በአንቺ ልብ ውስጥ ቅያሜ የለም፣ በአንቺ ልብ ውስጥ እብለት የለም፤ አንቺ የእውነት ገጽ ነሽ› ትላለች እናቷ መቃብር ላይ ቆማ።
ትናንትን መመለስ ብትችል እሷና እናቷ የነበሩበትን ትናንትና መመለስ ትፈልግ ነበር። ከዚያም እናት ቁጭ ብላ ልጅ ስትደክም ያለውን የመንፈስ ልዕልና ትቆጥር ነበር። ከትናንቷ ውስጥ እንድታስተካክለው ብትጠየቅ የምታስተካክለው ብዙ ነገር ነበር። በሕይወቷ ለፍታ ሳትታክት እናቷን ማገልገል የሕይወት ዘመን ምኞቷ ነበር። ግን አሁን እናቷ አጠገቧ የሉም።
በሕይወት ውስጥ አንዴ ካለፉ የማይመለሱ፣ አንዴ ከባከኑ የማይደገሙ ዕድሎች አሉ፤ በእኚህ ዕድሎች ማጌጥ ከጸጸት መዳን እንደሆነ የገባት አሁን ነው።
ነገ…
አዲስ ታሪክ ትጽፋለች። ከትናንትና ከዛሬ የተቀነጨበ አዲስ ሰማይና ምድር ትገነባለች። የእጆቿ ጥፍሮች እስኪነቃቀሉ ድረስ ለልጆቿ ትኖራለች። የእናቷን እውነት በልጆቿ ነፍስ ላይ ታበቅላለች። እንደ እናቷ ለምትወዳቸው ልጆቿ ልትለፋ ሴትነቷን ትገብራለች። ነገ እናትሽ ምን ዓይነት ነበረች ላሏት የምትመልሰው ብዙ መልስ አላት።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 6/2014