
የኢትዮጵያን ስፖርት በበላይነት የሚመራውና የሚቆጣጠረው የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር በአዲስ መልክ ተደራጅቶ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል። ሚኒስትሩ ባለፉት ሁለት ወራትም የተለያዩ መዋቅራዊ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። ሚኒስቴሩ በአሁኑ ሰአትም በዓመቱ የያዛቸውን ዕቅዶች ወደ ተግባር ለመቀየር ቅድመ ሁኔታዎችን አጠናቋል።
ከአዲስ ዘመን ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት በኢ.ፌ.ዴ. ሪ. ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንዳረጋገጡት፤ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የቀድሞውን የስፖርት ኮሚሽን ዕቅድ መሰረት በማድረግ በዓመቱ የሚያከናውናቸውን ስራዎች አቅዷል። እቅዱን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች አጠናቋል። ቀድሞው የነበሩ አስራሮችን መሠረት በማድረግ ለእቅዱ ስኬት የሚያግዙ የህግ ማዕቀፎችንና ማሻሻያዎች እየተደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ በ1990 ዓ. ም የተዘጋጀውን የስፖርት ፖሊሲ በማሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየትና ግብዓት በመውሰድ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ እንዲጸድቅ ይደረጋል። ስፖርት የራሱ የሆነ አዋጅ ያልነበረው አካል እንደመሆኑ፤ በዚህ ላይ የማሻሻያ ሀሳቦች ቀርበው ባለድርሻ አካላትን እንዲሳተፉበት በማድረግ ወደ ስራ እንዲገባ ጥረት እየተደረገ ነው። በተጨማሪ ብሄራዊ የስፖርት ማህበራትን (ፌዴሬሽኖች) መልሶ ማቋቋምና ማደራጀት ላይም ሚኒስትሩ አተኩሮ በመስራት ላይ ይገኛል።
” የዚህ ዕቅድ ዓላማም በአገሪቷ 31 የሚሆኑ የስፖርት ማህበራት፣ ኮሚቴዎችና አሶሴሽኖች እንደመኖራቸው በአግባቡና በህጋዊ መንገድ ከመደራጀት አንጻር ችግሮች ይስተዋላሉ ” የሚሉት አምባሳደር መስፍን፤ የጥራት እና ሰፊውን ህዝብ የማሳተፍ ችግርም በተመሳሳይ የሚንጸባረቅ እንደመሆኑ ዓለም አቀፍና ሃገር አቀፍ መስፈርት አሟልተው እንዲደራጁና እንዲመዘገቡ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል። ይሕን ለማድረግ የሚያስችል የስፖርት ማህበራት ማቋቋሚያ ወደ ተግባር ለማስገባት እየተሰራም ሲሆን፤ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ በስራ ላይ እንዲውል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገር እና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በሚመለከትም ከመንግስት የሚጠበቀውን ድጋፍ መስጠት የዕቅዱ ሌላኛው አካል ነው። ሀገር የምትወከልበት ዓለም አቀፍ ውድድሮች መርሃ ግብራቸውን ተከትለው ሲመጡ መንግስት ድጋፍ ያደርጋል ። በሀገር ውስጥ በሚካሄዱ ውድድሮችም ላይ ድጋፍ በመስጠት ሆነ አብሮ በመስራት ተሳታፊ ይሆናል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በማሳያነት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ለአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊነት ወደ ካሜሩን ሲጓዙ እንደ መንግስት ምን መደገፍ አለበት የሚለውን ማቀዱትን አምባሳደር መስፍን አስታውሰዋል ።
” ጊዜው ሲደርስም ዝግጅቱን በፋይናንስ፣ በምክረሃሳብ እንዲሁም በቅርብ ክትትል በማድረግ ረገድ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ። የተተኪ ወጣቶች የስፖርት ልማትን በሚመለከትም በሃገር አቀፍ ደረጃ እስከ ዞኖችና ወረዳዎች ወርዶ ከመስራት ባለፈ በመንግስት የትምህርት ተቋማትም ጭምር ታዳጊ ስፖርተኞችን ለማፍራት በጥረት ላይ ነው ። ይህንንም ስራ በመገምገም፣ ስታንዳርድ በማውጣት ማኑዋል በማዘጋጀት እንዲሁም ሂደቱን በማስቀጠል እየተሰራ ይገኛል። ከታዳጊዎች ጋር ተያይዞ የስፖርት ማጎልመሻ ትምህርት በአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምርት ቤቶች የሚሰጥ ቢሆንም በመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ላይ ግን የካሪኩለሙ አካል አይደለም። በመሆኑም በካሪኩለለሙ እንዲካተት ከኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ጋር እየተሰራ ነው ” ብለዋል።
ከሌሎች የስፖርት ተቋማት ጋር እንደየኃላፊነታቸው በቅርበት ግንኙነት መስራት ከእቅዶቹ መካከል ይገኛል። በበፊቱ የስፖርት ፖሊሲም ይሁን በአዲሱ የስፖርት ፍኖተ ካርታ ስፖርት ህብረተሰቡ በሚኖርበት፣ በሚሰራበትና በሚማርበት ስፍራ ተሳታፊ በመሆን ጤናማ፣ አምራችና ብቁ ዜጋ መፍጠርን ማዕከል ያደርጋሉ። በመሆኑም ሚኒስትሩ ስፖርት ለሁሉም በሚለው ላይ በስፋት መስራት የሚለውን ከትኩረት አቅጣጫዎቹ መካከል አካቷል። አዲሱን አደረጃጀት ወደ መሬት በማውረድ ተግባራዊ እንዲሆን በመንግስት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ዕቅድና ሃብትን በማዋሃድ እንዲሁም አዲስ መዋቅር በማዘጋጀት ወደ ስራ ከመግባት ባለፈም በወቅታዊ ሁኔታዎች ተቋሙ ተሳታፊ መሆኑንም ሚኒስትር ዲኤታው አመልክተዋል ።
አምባሳደሩ በመጨረሻ፤ በአገራዊው የህልውና ዘመቻ ሀብት በማሰባሰብ እንዲሁም በደጀንነት ስራዎች ላይ ሚኒስትሩ ተሳታፊ ነበር። በውጪ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሃገር እንዲገቡ ከተደረገው ሃገራዊ ጥሪ ጋር በተያያዘም እንደዘርፍ ምን ማድረግ አለበት በሚለው ላይ የራሱን ዝግጅት አድርጓል። በዚህም መሰረት የስፖርት ተቋማትን እንዲጎበኙና በስፖርታዊ ውድድሮች ተሳታፊ እንዲሆኑ፣ የእግር ጉዞዎች፣ የ5ኪሎ ሜትር ሩጫ እና የመሳሰሉት ላይ ለመስራት ትኩረት ተሰጥቶ ወደ ተግባር እየተገባ መሆኑን አስረድተዋል ።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታኅሳስ 21/2014