ስነ ቃል የሕዝብ ነው፤ ሲወርድ ሲወራረድ በሕዝብ ቅብብሎሽ እዚህ ዘመን የደረሰ:: የአንድ ደራሲ ብቸኛ ውጤት አይደለም፤ የሕዝብ ስሜት ነው:: የየዘመኑን የሕዝብ ስነ ልቦና ያሳያል፤ ስለዚህ ትክክለኛውን የማህበረሰቡን ስነ ልቦና ይወክላል ማለት ነው::
የባህል ጥናት ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ የቃል ግጥም ከስነ ቃል ዓይነቶች አንዱ ነው:: የተለያዩ ብያኔዎችና ክዋኔዎችም አሉት::
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባህል ጥናት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር አስቴር ሙሉ ከሠሩት ጥናት ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ የቃል ግጥም ማለት፣ አደራረሱ፣ አከዋወኑ፣ ተስተላልፎው እና አቀራረቡ ብዙ ጊዜ በቃልና በመዜም የሆነ፣ በዘፈን በሙሾ፣ በእንጉርጉሮና በሌሎች ተመሳሳይ ዜማዊ ቅርጾች ውስጥ የሚገኝ ሕዝባዊ ግጥም ነው::
የቃል ግጥሞች መልዕክትና ይዘት የሚያምረው በክዋኔ ሲሆን ነው፤ ይህንንም ከዶክተር አስቴር ጥናት ያገኘነው መረጃ፡- ስነቃልን፤ ከክዋኔ ውጪ ማጥናት ኪነታዊ እሴቱን አንስተው ቃሉን ብቻ፣ ቆዳውን ገፍፈው፣ ስጋውን ቦጭቀው፣ ደሙን አፍስሰው፣ አፅሙን ብቻ ያቀረቡት ዓይነት ነው በማለት፤ ህልውናው ክዋኔው መሆኑን ያብራራል:: ከዚሁ ጥናት ላይ ባገኘነው መረጃ ስለክዋኔ አንድ ነገር እንበልና ወደ ዋናው ጉዳይ እንግባ::
ክዋኔ ውበታዊ የሆነ የድርጊት ባህሪ፣ የንግግር ዘዴ፣ በአካል የሚከወን፣ በጊዜና በቦታ የተገደበ፣ በታወቀ መዋቅር በከዋኞች የሚቀርብ ከመሆኑም በተጨማሪ በተደጋጋሚ የሚፈፀም፣ በግልና በቡድን የሚዋቀር የማንነት ማሳያ ነው:: በሌላ በኩል ክዋኔ የፎክሎርን ፅንሰሃሳብ የሚመራ ውበት ያለው ጥበባዊ ድርጊት ነው:: ይኸውም የፎክሎር ጥበባዊ ድርጊት ከዋኝ፣ ቦታ፣ ተመልካች እና የክዋኔውን ሁኔታ የሚይዝ ነው::
እንግዲህ በቃል ግጥም ውስጥ ግጥሙም ሆነ ሥርዓተ ክዋኔው የሚያሳየን የማህበረሰባችንን አኗኗር፣ በኀዘንና በደስታ ጊዜ የሚኖረውን ስሜት ነው::
እነሆ በአገራችን ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀ ጦርነት እየተካሄደ ነው:: በዚህ ጦርነት የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያዩ ግንባሮች ሆ ብሎ ዘምቷል:: ይህ ለምን ሆነ ብለን ከጠየቅን፤ የኢትዮጵያውያን የጀግንነት ወኔ ተፈጥሯዊና ለዘመናት የሰረፀ መሆኑ ነው:: ዓድዋ፣ ማይጨው፣ ካራማራ፣ … እያልን የምንጠቅሳቸው የጦር ግንባሮች ጀግኖች የተዋደቁባቸው ናቸው:: የጀግንነት ድሎች በተመዘገቡባቸው እንደ አድዋና ካራማራ ያሉ ግንባሮች፣ ድሎቹ እንደ የቃል ግጥም ያሉ የሕዝብ የጀግንነት እሳቤዎችም የተገኙ ናቸው:: ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች መመኪያ የነፃነት አርማ የሆነችው በእነዚህ ሕዝቦቿ ነው::
የዚህን ጀግና ሕዝብ፤ የአይደፈሬነት፣ የአትንኩኝ ባይነት ባህሪ የሚያሳዩን ደግሞ የቃል ግጥሞች ናቸውና እስኪ ጥቂቶችን እንመልከት::
ጀግና ይሙት
ፈሪ ይኑር ቢሻው
አተላ መሸከም ይችላል ትክሻው
ይህን የማህበረሰብ ቃል ግጥም በሚገባ የሚገልጽልን የሸዋሮቢቱ ጀግና እሸቴ ሞገስ ታሪክ ነው:: ንግግሩን ብዙዎቻችን ሰምተነዋል:: እንደሚሞት መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆኖ ነው ያንን ነገር የተናገረው:: ከዚያ አሸባሪ ቡድን ሸሽቶ ማምለጥን አልፈለገም:: መሸነፍን አልፈለገም:: መጠቃት ይቆጨዋል ማለት ነው:: ቁጭት የማያድርበት ሰው፣ መደፈሩ ምንም የማይመስለው ግን ይደበቃል፣
ይሸሻል፤ ይዋሻል፤ ክህደት ሁሉ ሊፈጽም ይችላል:: በተሸናፊነቱ ሲሳለቁበትም ምንም አይመስለውም:: ‹‹አተላ መሸከም ይችላል ትክሻው›› የተባለው ለዚህ ነው::
ተንኮለኛ ገደል
በሬ ያሳልፋል
ዝንጀሮ ይጠልፋል
ጅል ያመጣው ነገር
ለሁሉ ይተርፋል
ይህ የሕዝብ ቃል ግጥም የሚገልጸው የሕወሓትን ዓይነት ድርጊት ፈጻሚዎች ነው:: ጀግና የሚባል ሰው ፀብ አይጀምርም፤ ጀግና ከጀመሩበት በኋላ ነው ድባቅ የሚመታ:: የፈሪ እና የጅል ምልክት ጠብ መጀመር ነው::
ሕወሓት የሰሜን ዕዝን አጠቃና ጦርነቱን አስጀመረ:: እነሆ በጀመረው ጦርነት ይህ ሁሉ አሰቃቂ ግፍ ደረሰ፣ ያ ሁሉ መሠረተ ልማት ወደመ:: አንድ ቦታ የተጀመረ ጦርነት ከጫፍ እስከ ጫፍ ብዙ ነገር አቃወሰ:: ‹‹ጅል ያመጣው ነገር ለሁሉ ይተርፋል›› የተባለውም እንዲህ ዓይነቱን ጥቃት ነው:: ይህንኑ የሚገልጽ ተመሳሳይ የቃል ግጥም ልጨምር::
ቆራጥ ጎበዝ እና ነብር አንድ ናቸው
ሰው ደርሰው አይነኩም ካልደረሱባቸው
በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ጀግንነት ማለት ፀብ መምረጥ አይደለም፤ ጀግና ማለት ቀድሞ ፀብ የሚጀምር አይደለም:: ጀግና ካልደረሱበት አይደርስም:: ከደረሱበትና ከነኩት ግን የደፈረውን አካል ሳያጠፋ አይመለስም::
በነብር የተመሰለበት ምክንያት የጀግና ባህሪ ከነብር ተፈጥሯዊ ባህሪ ጋር ስለሚመሳሰል ነው:: ነብር ከሌሎች እንስሳት ለየት የሚያደርገው በጥንቃቄ የሚጓዝ ፍጡር ነው:: ያልደረሰበትን አይደርስም:: ሰዎችን የሚያጠቃው ድንጋይ ከወረወሩበት ወይም ለመተናኮል ሲቃጡበት ካየ ነው:: ከዚያ ውጪ ምንም ካላደረጉት ከእረኞች ጋር አብሮ ይውላል ይባላል::
ያም ወርዶ ያም ወርዶ
ድቡን ተናነቀው
ጀግና ሊዋጋበት
ፈሪን ምን ጨነቀው
ኧረ ፈሪ ፈሪ
ፈሪ በጉድ ወጣ
ከሰማይ ላይ ሆኖ
የሚተኩስ መጣ
ይህ እንጉርጉሮ ብዙ ጊዜ የሚነሳው ሁለት ተጋጣሚዎች እየተጋጠሙ የሚፈራው ሌላ አካል ሲሆን ነው:: ባላንጣዎቹ ያልፈሩትን እኔ ጋ ይመጣብኛል ብሎ የሚፈራው ፀቡ ውስጥ የሌለው ነው:: ‹‹ኧረ እባካችሁ ታረቁ›› ብሎ ሲማጸን ነው ‹‹እኛ ልንዋጋ አንተን ምን አስጨነቀህ›› ለማለት ነው:: እንዲህ የሚሉት ግን ትክክለኛ እርቅ ፈላጊ ሽማግሌዎችን ሳይሆን ግጥሚያውን ላለማየት የሚሸሸውን ነው:: በመሸሽ ነገርን ማብረድ እንደማይቻል ያምናሉ:: ፀብ ጀማሪው ወገን ከሸሹለት የፈሩት ስለሚመስለው ይከተላል እንጂ ንቆ አይተውም::
ረጅም ምንሽር ተኩሱም ረጅም ነው
ከተጣሉ ወዲያ አስታርቁኝ ምንድነው?
ይህም በተመሳሳይ ፀብ ጀማሪውን አካል ሸንቆጥ ለማድረግ ይጠቅማል:: ፈሪ ፀብ ይጀምራል፤ ከተጀመረ በኋላ ይጨንቀዋል:: ሲጨንቀው አስታርቁኝ እያለ ይማፀናል:: አሁንም ደግመን እናስታውስ፤ በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ጀግና የሚባለው ፀብ የሚጀምር ሳይሆን የተጫረበትን ፀብ የሚያሸንፍ ነው::
አልቤን አለቀሰ
እንባ አውጥቶ እንደ ሰው
መውዜር አለቀሰ
እንባ አውጥቶ እንደ ሰው
ክላሽ አለቀሰ
እንባ አውጥቶ እንደ ሰው
አልጋ ላይ ተኝቶ ትኋን እየላሰው
የዚህ ቃል ግጥም መልዕክት እንዲህ እንደ አሁኑ
ዓይነት አገራዊ አደጋ ሲያጋጥም መሣሪያውን የሚደብቅን ሰው ለመሸንቆጥ ነው:: በገጠሩ አካባቢ በተለይም ቀደም ባለው ዘመን ሥጋቸው የሚበላ የዱር እንስሳትን መግደል እንደ ጀግና እና ተኳሽ ያስቆጥራል:: ለዚያም ጭምር ይጠቀሙበታል::
በሌላ በኩል ግጭት ሲፈጠር መሣሪያውን የሚደብቅ ሰው እንደ ፈሪ ስለሚቆጠር ነው:: ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ መሣሪያ ካልያዘ ሰው ይልቅ ቅድሚያ የሚመታ የያዘ ሰው ስለሆነ ነው:: አንድም መሣሪያውን ለመውሰድ፤ አንድም ሳይቀድመን እንቅደመው በሚል::
መልከ ጥቁርቁር ዝንጀሮ መሳይ
ሳቅ ሳቅ ይለዋል አምባጓሮ ሲያይ
‹‹አምባጓሮ›› ማለት ፀብ ነው:: መልዕክቱም አብጓሮ ሲነሳ የሚጨነቅ ወይም የት ልግባ የሚል ፈሪ ስላልሆነ ሳቅ ሳቅ የሚለኝ ጀግና ነኝ ለማለት ነው:: ማሸነፍ ያኮራኛል ለማለት ነው::
ዝንጀሮ መሳይ የተባለበት ምክንያት፤ በተለይም በገበሬዎች ዘንድ፣ ቅባት እየተቀባባ፣ ሰውነቱን ብቻ እየወለወለ የሚውል ወንድ እንደ ጀግና አይቆጠርም:: በግብርና ሥራም ሆነ በጦርነት እንደ ጀግና የሚቆጠረው አፈር ነካኝ፣ ጭቃ ነካኝ እያለ ሲታሽ የሚውል ሳይሆን አፈር ለብሶ ጭቃ ተቀብቶ ያሰበውን ዓላማ ማሳካት የሚችል ነው::
የማህበረሰቡን ቃል ግጥሞች ለማሳያ ከጠቃቀስን ወደ ዶክተር አስቴር ጥናት እንመለስ:: ከላይ የተጠቀሱት የቃል ግጥሞች የሚፎከሩበትና የሚሸለሉበት የራሱ ክዋኔ አለው:: ብዙ ጊዜ እንደ ሰርግ ያለ ጉዳይ ሲኖርና የአካባቢው ሰው ሲሰባሰብ ነው:: ከዚያ ውጪ በየትኛውም የሥራ እንቅስቃሴ ሊያንጎራጉሩት ይችላሉ:: ለቅሶ ላይ ለሟች ጀግና የሚፎከር ካልሆነ በስተቀር ሌሎቹ በሥራ ቦታም ሊነሱ ይችላሉ፤ በብዛት ግን ሰው በሚሰባሰብበት የሰርግና ሌሎች የድግስ ጉዳዮች ላይ ነው::
ጀግና የሚለው ቃል ‹‹hero›› ከሚለው የግሪክ ቃል ትርጉም መሆኑን የሚገልጸው የዶክተር አስቴር ጥናት፤ ትርጉሙም፣ ሰዎች ካላቸው ችሎታ በላይ የሆነን ጉዳይ ያከናወነ፣ እሱ ሟች ሆኖ ተግባሩ ግን በሰዎች አዕምሮ የሚቀርና በተግባሩም የሚደነቅ መሆኑን ያመለክታል::
የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ጥናት ምርምር መዝገበ ቃላት ደግሞ ጀግና የሚለውን ቃል እንደሚከተለው ይተረጉመዋል:: ለአገር ለወገን መስዋዕትነት ከፍሎ ጥሩ ተግባር ያከናወነ፣ ወኔ፣ ድፍረት በሚጠይቅ ሁኔታ ላይ ጀብዱ የሠራ:: ብርታትን በሚጠይቅ ሥራ ላይ ችግርን ተቋቁሞ ለውጤት የበቃ ማለት ነው ሲል ገልጾታል::
‹‹ጀግና ማለት ከሰዎች መካከል የተሻለ አቅም፣ ብርታትና ዕውቀት ያለው ግለሰብ ነው:: ማንኛውም ማህበረሰብ በራሱ መስፈሪያ ሰፍሮ ጀግና ሲል የሚሾማቸው ግለሰቦች አሉት›› የሚለው የዶክተር አስቴር ጥናት፤ እነዚህ ግለሰቦች የሚለኩበት መስፈሪያ ‹‹ባህል ይባላል›› ይላል::
በነገራችን ላይ ሕወሓት የከፈተው ጦርነት ብዙ ነገርም አስተምሮናል:: በተደጋጋሚ የተባሉት የሕዝብ አንድነትና መተባበር እንዳሉ ሆነው እንዲህ ዓይነት ባህሎችንም መለስ ብለን እንድናይ አድርጎናል:: እነዚህ የጀግንነት ቃል ግጥሞች፣ ፉከራዎችና ሽለላዎች የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን አያገኙም ነበር:: እንደ እሸቴ ሞገስ ያሉ ጀግኖች እንዳሉን አይታወቅም ነበር:: እነዚህ ቃል ግጥሞች ዛሬ የተፈጠሩ ስላልሆኑ ኢትዮጵያ ጥንትም ዛሬም ምን ዓይነት ሕዝቦች እንዳሏት አሳይተውናል::
ኢትዮጵያ የጀግና አገር ናትና ጀግና ቢሰዋ ጀግና ይተካል! እነሆ የሕዝብ ስነ ቃሎችም ሕያው ምስክሮች ይሆናሉ::
ዋልልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2014