ኢትዮጵያ ጡቷን እየጠቡ ሳይሆን እየመጠመጡ ባደጉት በልቶ ካጅ ልጆቿ ክህደት ተፈጽሞባት ህልውናዋ አደጋ ላይ በወደቀ ጊዜ እንደዓይናቸው ብሌን የሚመለከቷት ታማኝ ልጆቿ ዝም ብለው አልተመለከቷትም።
ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ አገር ያሉ የቁርጥ ቀን ልጆቿ አንድነታቸውን አጠንክረው ጠላቶቿን ለመመከት ሲሰለፉ ጊዜ አልፈጀባቸውም። በተለይም ወጣቶች ከአባቶቻቸው የተረከቧትን አገር ክብሯ እንደተጠበቀ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉንም ነገር አድርገዋል።
ከደጀን እስከ ግንባር ባሉ አደረጃጀቶች ውስጥ ታቅፈው ለእናት አገራቸው ጥሪ መልስ ሰጥተዋል። የገንዘብ፣ የጉልበት ፣ የሀሳብ ፣ የሕይወት ዋጋ ከፍለዋል፤ እየከፈሉም ነው። በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ከሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ የአሜሪካንና የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት በማውገዝ ድምጻቸውን በዓለም አደባባይ እያሰሙ ይገኛል። በዚህም ተጽዕኖ ፈጥረዋል።
በዛሬው የወጣቶች አምድ ዝግጅት ይዘን የቀረብነው እንግዳ ኑሮውን በአውሮፓ ያደረገ ወጣት ሲሆን አገሩን ከገባችበት ችግር ለማውጣት የኢትዮጵያ ኮሚኒቲን በማስተባበር የሚንቀሳቀስ ነው። በተለይም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው የፖለቲካ ውጥረት የአገሩን ጉዳይ በንቃት እየተከታተለ ከእርሱ የሚጠበቀውን ለማድረግ እንዳነሳሳው ይናገራል። በአውሮፓ አገር በኖረባቸው ጥቂት ዓመታትም የዲያስፖራውን አንድነት የሚያጠናክሩ ሥራዎችን ሠርቷል።
አዲስ ዘመን ከወጣቱ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርቧል። ሊቀ ትጉኋን ደረጀ ነጋሽ ይባላል። ወጣት ነው ፤ ወጣት በመሆኑ ለጊዜው በማዕረጉ ያገኘውን አንቱታ ትቼ አንተ እንድለው ተስማምተናል። የትውልድ ቦታውንና አካባቢውን ከመጥቀስ ይልቅ ኢትዮጵያዊ ማለትን መርጧል።
አሁን የሚኖረው በኢጣሊያ አገር ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የኢጣሊያንና አካባቢው አገረ ስብከት ማለትም የቤልጄም፣ የማልታ፣ የቱርከ፣ የስፔንና የፈረንሳይ የሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ኃላፊ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ጣሊያን ከመሄዱ በፊት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጠቅላይ ቤተክህነት በስብከተ ወንጌልና በዜና ቤተክርስቲያን ከፍተኛ ሪፖርተርነት አገልግሏል። ያኔ የታዘበውን እንዲህ ይገልጻል።
ሕወሓት በስልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታት ከቤተክርስቲያን ቀኖና እና ዶግማ ውጭ እስከ ትላልቅ ማዕረግ ድረስ በመንግሥት ትዕዛዝ የማሾምና ኦርቶዶክስን እናፈርሳለን እስከማለት የደረሰ አጀንዳ ቀርጾ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ሊቀ ትጉኋን ደረጀ ይናገራል። ሊቀ ትጉኋን ደረጀ አሁን የሚኖረው በጣሊያን ሮም ከተማ ነው።
ወደ ጣሊያን አገር በሄደበት ወቅት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ሰዎች ቤታቸውን ዘግተው ተቀምጠው ስለነበር ተንቀሳቅሶ ሥራውን መሥራት እንዳልቻለ ይናገራል። ይሁንና ቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ ሃያ ሁለት ሺ ሰው የሚከታተለው የዙም ጉባኤ በመፍጠር ሥራውን ያከናውን ነበር። ይህም ከበርካታ ኢትዮጵያውያን ጋር የመተዋወቅ ዕድል ፈጥሮለታል።
ሊቀ ትጉኋን ደረጀ ከኢትዮጵያ ከወጣ ገና ሁለት ዓመቱ በመሆኑ ከለውጡ በፊትም ይሁን ከለውጡ በኋላ አገሪቱ ላይ ላይ ሲፈጸሙ የነበሩ ሴራዎችን በሚገባ ያውቃቸዋል። እናም እንደ አንድ ወጣት በምን መንገድ አገሩን የመታደግ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ያስብ ነበር። ሊቀ ትጉኋን ደረጀ በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ለሃይማኖታዊ ተልዕኮው ሲዘዋወር ከሚያገኛቸው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲዎች ጋር ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ በጥልቀት ይነጋገር ነበር።
በተለይም የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ጉባኤ ቅርንጫፍ ቢሮውን በአውሮፓ ሲከፍት አስተባባሪ ሆኖ በመሾሙ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲዎችን የማግኘት እድሉ የበለጠ መስፋቱን ይናገራል። ይሁንና አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በየኤምባሲዎቹ ባስቀመጣቸው ካድሬዎቹ አማካኝነት ኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲዎች በዘርና በሃይማኖት ተከፋፍለው እንደነበር ያስታውሳል።
በኤምባሲዎቹ የሚሰሩ ካድሬዎች በኢትዮጵያ በጀት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እየተንቀሳቀሱ ኮሚኒቲውን ሲከፋፍሉ እንደኖሩ ይናገራል። በዚህ የተነሳ በአንድ ከተማ ላይ ብቻ ከአስራ ስምንት በላይ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲዎች ተፈጥረዋል። እነዚህን ሁሉ በአንድ ኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ማሰባሰቡ ፈታኝ እንደነበር ይገልጻል። የኢትዮጵያ መንግሥት ባስተላለፈው ውሳኔ አንዳንድ ኤምባሲዎች ሲዘጉና ሠራተኞቹም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ሲያደርግ ይሠራ የነበረው የመከፋፈል ሴራም መሪ ያጣል።
ሊቀ ትጉኋን ደረጀና ባልደረቦቹ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ተከፋፍሎ የነበረውን ኮሚኒቲ አንድ የማድረግ ሥራ መሥራት ይጀምራሉ። በተገኘው አጋጣሚ ስለወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታ በማስረዳትና በማስተባበር ለታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ ለተፈናቃዮችና ለመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ብር በማዋጣት ድጋፍ ማድረግ እንደተቻለ ይናገራል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ሰልፎችን በማድረግ ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫና እንዲያቆሙና በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ ድምጽ ማሰማት ይጀምራሉ። ከኢጣሊያ ቴሌቪዢን ጀምሮ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ትክክለኛ መረጃ እንዲዘግቡ በኢትዮጵያ ላይ የሚሰራጩት ሐሰተኛ መረጃዎች እንዲቆሙ ብርቱ የተቃውሞ ሰልፎችን ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያን እንደ ሶሪያና የመን ማፍረስ የማይቻል መሆኑን በጎዳና ሰልፎች ሲገልጹ እንደከረሙና አሁንም በአውሮፓ አገራት የኢትዮጵያን ጥቃት የመመከቱ ጉዳይ ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን ሊቀ ትጉኋን ደረጀ ይገልጻል ።
በአውሮፓ የሚኖሩ የአሸባሪው ቡድን ደጋፊዎችም በትግራይ ሕዝብ ስም በየጎዳናው እየተንከባለሉ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ሀሳባቸውን ሲገልጹ ፤ ያደጉበትንና የለመዱትን ውንብድና ሲፈጽሙ እንደነበር የታዘበው ሊቀ ትጉኋን ደረጀ በዚህም ላይ ከምዕራባውያኑ ድጋፍ ይደረግላቸው እንደነበር ይገልጻል።
በኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት ተምረው የኢትዮጵያን ባህል ፣እሴት ማስተዋወቅ ሲገባቸው እናታቸውን የሚወጉ ልጆችን ማየት ያናድድ የነበረ ክስተት ነው ይላል። እነዚህ አካላት የሚከተሉት የተሳሳተ መንገድ እንደሆነ በመንገር የመምከርና የመገሰጽ ሥራ እንደተሠራና በርካቶችን ከጥፋት መንገድ መመለስ እንደተቻለም ገልጿል።
ምዕራባውያን ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያን በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ሲገዟት እንደነበር የተናገረው ወጣቱ አሁን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት መምጣቱ ምቾት ስላልሰጣቸው አሸባሪውን ቡድን በመደገፍ ወደ ነበረበት ሥልጣን የማምጣት ፍላጎት እንዳላቸው በግልጽ እየታየ ነው ብሏል።
ኢትዮጵያ ከአውሮፓም ይሁን ከአሜሪካ ጋር የረዥም ዘመን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላት አገር እንደመሆኗ የኖረውን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር የምትፈልግ እንጂ የምታበላሽ አለመሆኗን በዲያስፖራዎቿም አማካኝነት ለማስረዳት ተሞክሯል። ዲያስፖራው ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለ አገሩ እውነተኛ ገጽታ ሲያስረዳ እንደነበር ሊቀ ትጉኋን ደረጀ ይገልጻል።
ነገር ግን በእርዳታና በሌሎች ድጎማዎች አሳበው ሉዓላዊነቷን ለሚዳፈሩ የውጭ ኃይሎች ቦታ እንደማትሰጥ፤ የመንበርከክ ታሪክ እንደሌላት፤ ሕዝብ የመረጠው መንግሥት እንዲከበር፤ የአሸባሪው ሕወሓት ድርጊት እንዲወገዝ ዲያስፖራው ትግል እያደረገ መሆኑን ተናግሯል። በዚህ ትግል ላይ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የአውሮፓና የሌላ አፍሪካ አገር ዜጎችን ማሳተፍ እንደተቻለም ገልጿል።
የ‹‹NO MORE›› ንቅናቄው ከኢትዮጵያውያን አልፎ ወደ አፍሪካውያንም እየተጋባ መምጣቱን፤ አፍሪካውያን የኢትዮጵያን አቋም ደግፈው የውጭ ኃይሎችን ማውገዝ መጀመራቸውን ገልጿል። ከሃያላን አገራት እንደ ቻይናና ሩሲያን የመሳሰሉት ከኢትዮጵያ ጎን መቆማቸውም የምዕራባውያኑ ጫና እንዳይበረታ ያደረጉ ሁነቶች እንደሆኑ አስረድቷል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ዘርፈ ብዙ ጦርነት ተከፍቶባታል ያለው ሊቀ ትጉኋን ደረጀ ከጠላት ጋር ፊት ለፊት ከሚደረገው ውጊያ በተጨማሪ በህዳሴው ግድብ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ፣ በሚዲያ ጦርነት እንደተከፈተባት ገልጿል።
በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ከምንግዜውም በላይ ድምጻቸውን እያሰሙ ያሉት እነዚህን ሁሉ ተጽዕኖዎች ለመቋቋምእንደሆነና እየመከቱ መሆናቸውንም ተናግሯል። ሶሪያና የመን በአጭር ጊዜ ውስጥ የፈራረሱት ጥቂት ተሰርቶባቸው እንደሆነ የገለጸው ሊቀ ትጉኋን ደረጀ ምዕራባውያን አለ የተባለ ኃይላቸውን በሙሉ አስተባብረው እንኳ ኢትዮጵያን ማፈራረስ እንደማይችሉ ተረድተዋል ብሏል።
ለዚህም ዋናው ምስጢር ኢትዮጵያውያን ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች ያስተሳሰሯቸው ጠንካራ ሕዝቦች በመሆናቸው ነው። እስከ አሁን ኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበው አደጋ ገብቶት እንቅስቃሴ እያደረገ ያለው ዜጋ ጥቂቱ ነው። ሁሉም በሙሉ አቅሙ ሆ ብሎ ሲነሳ ደግሞ ከዚህም በላይ ነገሮችን የመለወጥ አቅም እንዳለን መረዳት ያስፈልጋል ብሏል።
ሊቀ ትጉኋን ደረጀ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በሰው ልጅ ላይ እየሠራ ያለውን ግፍ በቃላት መግለጽ እንደሚከብድ ይገልጻል። የተፈጸሙ ግፎች በዓለም ላይ ከተፈጸሙት ግፎች ሁሉ የሚዘገንኑ ናቸው ይላል። ግፉ ከሰው አልፎ ለእንሰሳ የተረፈ፤ የክፋት ጥግ የታየበት እንደሆነ ይናገራል። ኢትዮጵያ ታሪኳ፣ ክብሯ፣ ኢኮኖሚዋ እንደገና ከዜሮ እንዲጀምር ለማድረግ የተሞከረ እንቅስቃሴ ጭምር ነው ይላል።
ለዘመናት እንዲህ አይነት ጨካኝ ትውልድ እንዲፈጠር ሲሠራ ነበር፤ ትውልዱ ኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዳይኖረው ሆን ተብሎ በጫት፣ በሀሽሽ ፣ በመጠጥ የናወዘ እንዲሆን ተደርጓል ብሏል። አሁን ወጣቱ ከተሰጠው መሪ ጎን በመቆም ላለፉት ዓመታት ሕወሓት ያበላሸውን የአገር ገጽታ ማስተካከል ፤ ነባር ታሪኳን ያቆሸሸውን ጉድፍ ማጽዳት፤ በተጀመረው የለውጥ ጉዞ ኢትዮጵያን ወደፊት ማራመድ ይኖርበታል ይላል።
ዘንበል ያለችውን ኢትዮጵያን ቀና ለማድረግ የሚጥረውን መሪ ሁሉም ሊደግፈውና ሊያግዘው እንደሚገባ የተናገረው ሊቀ ትጉኋን ደረጀ በተለይም ወጣቱ ከየትኛውም የኅብረተሰብ ክፍል በላይ በግንባርም በደጀንም ተሰልፎ የኢትዮጵያን ሰላም በማረጋገጥ የአባቶቹን አደራ መጠበቅ እንዳለበት ተናግሯል። ዲያስፖራውን በማስተባበር ኢትዮጵያን የማዳን ትጋት የሕወሓት አሸባሪ ቡድን ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ያለየውን ሕዝብ በመጨረሻው ሰዓት አንድ እንዳደረገው የጠቀሰው ወጣቱ ከድሉ በኋላም ይህንን አንድነት አጠናክሮ በመቀጠል ኢትዮጵያን ማበልጸግ አንደሚገባ ገልጿል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እስከ አሁን እንደሚያደርጉት ሁሉ በቀጣይም የውጭ ተጽዕኖን በማስቆም አገራቸውን በኢኮኖሚ መደገፍ ይኖርባቸዋል። ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የኢኮኖሚ ጦርነት በአሸናፊነት ለመወጣት እያንዳንዱ ዲያስፖራ ወደ አገር ቤት የሚልከውን ዶላር ሕጋዊ በሆነ መንገድ በመላክ አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርበታል። በአሁኑ ሰዓት መንግሥት ከውጭ የገንዘብ መላኪያ ክፍያውን መቀነሱም የዲያስፖራውን ድጋፍ የሚያግዝ ጥሩ ርምጃ መሆኑን ሊቀ ትጉኋን ደረጀ ይገልጻል።
ከዚህ አንጻር አምባሳደር ደሚቱ ሀንቢሳ በአውሮፓ አስር አገራት የሚሰሩት የማስተባበር ሥራ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ መሆኑን በመጥቀስ በሁሉም አገራት ያሉ ኤምባሲዎች ለዲያስፖራው ግንዛቤ በማስጨበጥ ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የኦኮኖሚ ጦርነት መመከት የሚያስችል ንቅናቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።
ሊቀ ትጉኋን ደረጀ ኢትዮጵያ አሁን በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ላይ ድል እየተቀዳጀች መሆኗ በተለይም የውጭ ኃይሎችን የሐሰተኛ ሚዲያ ዘመቻና ጫና ለመቀልበስ ትልቅ አቅም ይፈጥርላታል ይላል። በርካታ ቦታዎች ከአሸባሪው ነጻ መሆናቸውም በርካታ ዲያስፖራዎች ኢትዮጵያውያን ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ እንዲመጡ ያደርጋቸዋል።
እንደ ሊቀ ትጉኋን ደረጀ ከሰሞኑ የተገኘው ድል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለገና በዓል አንድ ሚሊዮን ዲያስፖራ ወደ አገሩ እንዲገባ ላስተላለፉት ጥሪ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው። በውጭም በውስጥም ያለው ኢትዮጵያዊ በድሉ ሳይዘናጋ አሁንም ትግሉን እንዲያጠናክርም ጥሪ አቅርቧል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 1/2014