ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ከወራሪ ጠላቶች በመ መከት ከራሳቸው ተርፈው ለአፍሪካውያን ኩራት የሆነ ታሪክ አስመዝግበዋል፡፡ በየዘመኑ የሚመጣው ትውልድ ከአባቶቹ የተረከባት አገር ዳር ድንበሯ ሳይደፈር ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ አደራውን ሲወጣ ኖሯል፡፡ ወጣቱ የአገሩን ዳር ድንበር ከማስጠበቅ በተጨማሪ በየዘመኑ የሚነሱ አምባገነን መንግሥታትን በመቃወምና በመታገል ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ፣ እኩልነትና ነፃነት የሰፈነባት አገር እንድትሆን የራሱን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
በዚህም ተጨባጭ ለውጦችን ማምጣት ችሏል፡፡ ይህ ትውልድ ሃያ ሰባት ዓመት በሕወሓት የበላይነት ሲሰዘወር የነበረውን ጨቋኝ ሰርዓት በማስወገድ ኢትዮጵያ ከድቅድቅ ጨለማ ወጥታ የብርሃን ጭላንጭል እንድታይ የድርሻውን ሚና ተጫውቷል፡፡ ሕወሓት ሀገሪቱን በበላይነት ማስተዳደር ከጀመረ አንስቶ አሠራሩን የሚተቹ ወጣቶች እየታደኑ ግፍና መከራ ሲቀበሉ ኖረዋል፡፡ በተለይም በለውጡ ዋዜማ በተደረጉ ፀረ ሕወሓት ተቃውሟችና ንቅናቄዎች በርካታ ወጣቶች የህይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡
ሕወሓት ስልጣን መልቀቁ አስቆጭቶት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሲነሳ እዚህና እዚያ የሚለኩሳቸውን እሳቶች በማጥፋቱ ሂደት ወጣቱ ከለውጡ አመራሮች ጋር በመሆን ሀገርን የማዳን ሥራ ሠርቷል፡፡
በአገሪቱ ከተከሰተው የጸጥታ ችግር ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡ የገጠማትን ጣልቃ ገብነት /የውጭ ተጽዕኖዎችን / ለመመከት ወጣቱ አንድ ላይ ቆሞ የተቃውሞ ድምፁን አሰምቷል፤ አንድነቱን በማጠናከርና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ግድቡን የታሪኩ አካል ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ ሠርቷል። ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የውጭ ኃይሎችና የውስጥ ባንዳዎች የፈጠሩት ጥምረት ወጣቱ ከምንጊዜውም በላይ ሕብረቱን እንዲያጠናክር አድርጎታል፡፡
በተለይም ከአንድ ዓመት ወዲህ የሕወሓት አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ዓላማ እንዳለው በገሃድ አውጆ ከውጭ ኃይሎች ጋር እየተናበበ እኩይ ተግባራትን መሥራት ሲጀምር ወጣቱ ሀገሩን ከባንዳዎችና ከወራሪዎች ለማታደግ አንድነቱን አጠንክሮ ተነስቷል። በዚህ አገርን የማዳን እንቅስቃሴው በርካታ ስኬቶችን አስመዝግቧል፡፡ በየአካባቢው ተደራጅቶ ሰላምና ጸጥታውን ከማስጠበቅ በተጨማሪ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ታቅፎ ከአሸባሪው ሕወሓትና ከተላላኪዎቹ ጋር በመፋለም የህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ይገኛል፡፡
የዚህ ዘመን ትውልድም ልክ አንደ አባቶቹ ሁሉ በአንድ በኩል ሀገሩን ከጠላት እየተከላከለ በሌላ በኩል የኢትዮጵያን መጻኤ ዕድል በሚወስኑ የልማት ሥራዎች ላይ በንቃት እየተሳተፈ ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ዋልታ መከታ ሆኗታል፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልጽግና ተልዕኮ ሊግ ፕሬዚዳንት ወጣት ብርሃኑ በቀለ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ የወጣቶች ተሳትፎና ንቅናቄ ምን መልክ እንዳለው የሰጠው አስተያየት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ወጣት ብርሃኑ በተለይም ባለንበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጦር ግንባር ተገኝተው እያዋጉ መሆናቸው ለወጣቱ የሚያስተላልፈውን መልዕክት፤ ወጣቱ ከደጀን እስከ ግንባር የሀገሩን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ምን ዓይነት አንድምታና አስተዋጽኦ እንዳለው፤ በቀጣይም ሀገርን ከአሸባሪዎችና ከውጭ ጣልቃ ገቦች ለመመከት ምን ማድረግ እንደሚገባውና ተገደውም ይሁን ወደው ከአሸባሪው ጎን የተሰለፉ የትግራይ ወጣቶችን አስመልክቶ የሰጣቸው አስተያየቶች በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ተካተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልጽግና ተልዕኮ ሊግ ፕሬዚዳንት ወጣት ብርሃኑ በቀለ የኢትዮጵያ ወጣቶች በአገራቸው ሉዓላዊነት ጉዳይ ከማንም ጋር የማይደራደሩ መሆናቸው ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ልምድ ከመሆን አልፎ ባህል እንደሆነ ተናግሯል፡፡ አሁንም ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በገባችበት
በዚህ ወቅት የባንዳዎችንና የውጭ ጣልቃ ገቦችን የተቀናጀ ጥቃት በመመከት የኢትዮጵያን ሰላም ከማረጋገጥ አንጻር የዚህ ዘመን ወጣት ከመቼውም በላይ በከፍተኛ መነቃቃት ላይ እንዳለ ተናግሯል፡፡
እስከ አሁንም የተለያዩ ተግባራትን በመፈጸም ሀገር የማዳን ሥራዎችን እየሠራ እንዳለ አስታውሷል፡፡ ወጣቱ ከሦስት ዓመት በፊት አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን ከስልጣን ለማስወገድ ከፍተኛ መስዋዕትነት እንዳደረገና አሁንም ድረስ በተለያዩ አደረጃጀቶች ታቅፎ የእግር እሳት እየሆነበት እንዳለ ተናግሯል፡፡
አካባቢውን በንቃት በመከታተልና የአባቶቹን የአደራ ሀገር ላለማስደፈር ግንባር ድረስ በመሰለፍ ከጠላት ጋር እየተፋለመ ነው ብሏል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ወጣቱ ባንዳዎችና የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያ ላይ እየዶለቱ ያለውን ሴራ በሚገባ ተረድቶ እየታገላቸው ይገኛል። ጠላትን ለመፋለም ወደ ግንባር የሚተመው ወጣት ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡
በተለይም ከሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ግንባር መዝመት በወጣቱ ላይ ከፍተኛ መነቃቃት እንደፈጠረ የተናገረው ፕሬዚዳንቱ መሪው እየተዋጋ ቁጭ ብሎ የሚመለከት ወጣት የለም በሚል እሳቤ ከመሪው ጎን ቆሞ ጠላትን የመፋለም ፍላጎቱ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱን ገልጿል፡፡
እየተካሄደ ያለውን ጦርነትም የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልጽግና ተልዕኮ ሊግ ‹‹ዘመቻ ዐቢይ›› ብሎ እንደሰየመው ተናግሯል፡፡ ኢትዮጵያ ካላት አጠቃላይ የህዝብ ብዛት ከስልሳ እስከ ሰባ በመቶ የሚሆነው ወጣት እንደሆነ ይገመታል ያለው ፕሬዚዳንቱ ይህ ኃይል የሀገሩን ሰላምና ጸጥታ ከማስጠበቅ አንጻር ትልቅ አቅም እንደሆነ ገልጾ በዚህ ዘመቻ ወጣቱ ታሪክ ለመሥራት በመሽቀዳደም ላይ እንዳለ ገልጿል፡፡ እያንዳንዱ ወጣት መሪውን አርአያ አድርጎ ኢትዮጵያን የማዳን ዘመቻው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይኖርበታል ብሏል፡፡
የብልጽግና መንግሥት ለወጣቱ ተስፋ ይዞ መምጣቱን የገለጸው ፕሬዚዳንቱ በሥራ ዕድል ፈጠራ መልካም ጅምሮች መታየታቸውን አስታውሷል፡፡ ወጣቱ የአገሪቱን ሰላም በማረጋገጥ ፊቱን ወደ ተጀመረው የብልጽግና ጉዞ
በማዞር የራሱን ተጠቃሚነትና የሀገሩን እድገት ማረጋገጥ እንዳለበት ተናግሯል፡፡ ለዚህም የመሪውን አርአያ ተከትሎ ጠላትን በፍጥነት በማስወገድ የኢትዮጵያን ሰላም አስተማማኝ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጿል፡፡
እያንዳንዱ ወጣት ሀገሩ የምታደርግለትን ጥሪ ተቀብሎ ከደጀን እስከ ግንባር ባለው አደረጃጀት ተሳታፊ እንዲሆን ፕሬዚዳንቱ ጥሪ አስተላልፏል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልጽግና ሊግ በአሁኑ ጊዜ ከወቅታዊ የሀገሪቱ ችግር ጋር በተያያዘ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንዳለም ተናግሯል፡፡
ወጣቱም ይሁን የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል ኢትዮጵያ አሁን ስለገጠማት ችግር በቂ መረጃ እንዲኖረው የተለያዩ መድረኮችን በመጠቀም ግንዛቤ የማስጨበጥ፣ የማነቃቃትና ሀገርን ከጠላት መከላከል ለነገ የሚባል ጉዳይ እንዳልሆነ ተቋሙ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ለተለያዩ የወጣት አደረጃጀቶች ከሚያስተላልፈው ወቅታዊ መረጃ በተጨማሪ የኪነጥበብ ሙያተኞችን በመያዝ በተለያዩ የማሰልጠኛ ተቋማት እየተንቀሳቀሰ ለምልምል ወታደሮች የሀገር ፍቅርን የሚገልጹ ኪነጥበባዊ ሥራዎችን በማቅረብ ሞራል የመገንባትና የማነቃቃት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ለአገር የሚከፈል መስዋእትነት ከብርን የሚያጎናጽፍ እንደሆነና እንደማንኛውም ተራ ሞት የሚታይ አለመሆኑን፤ ኢትዮጵያውያን ለማንኛውም ኃይል የማይንበረከኩ፤ ሉዓላዊነታቸው ከሚደፈር ሞታቸውን የሚመርጡ ህዝቦች መሆናቸውን፤ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ላይ የተጎናጸፈችው ድል ለአፍሪካውያን ሁሉ ኩራት እንደሆነ፤ አሁንም የውጭና የውጥ ኃይሎች ተመሳጥረው የከፈቱባትን ዘርፈ ብዙ ጦርነት በድል መወጣቷ ክብሯን ከፍ የሚያደርግ መሆኑን የሚያንጸባርቁ የኪነጥበብ ሥራዎች መቅረባቸውን ተናግሯል፡፡
በዚህን ሰዓት የኢትዮጵያ ወጣቶች የብሔር፣ የሃይማኖት የአመለካከት ልዩነታቸውን ወደ ጎን ብለው በኢትዮጵያ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመመከት ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን አጠናክረው ለእናት ሀገራቸው መከታ ሊሆኗት ይገባል ብሏል፡፡ ይህ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ የተባበረ ክንዱን በጠላት ላይ በማሳረፍ ለየትኛውም ኃይል የማይንበረከክ መሆኑን
የሚያሳይበት መልካም አጋጣሚ እንደሆነም ፕሬዚዳንቱ ተናግሯል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልጽግና ተልዕኮ ሊግ ኢትዮጵያ ላይ እየተካሄደ ያለው ጦርነት የእጅ አዙር ጦርነት እንደሆነ ያምናል፡፡
የህዳሴውን ግድብ መገንባት ነገ በኢትዮጵያ ብዙ ነገሮችን የመለወጥ አቅም እንዳለው የተረዱ የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያ እራሷን እንዳትችልና ከተመጽዋችነት እንዳትላቀቅ አሸባሪ ቡድኑን በመደገፍ ከጀመረችው የብልጽግና ጉዞ የማደናቀፍ ዘመቻ እንደሆነ ይረዳል፡፡ ኢትዮጵያ ካደገች በቀጣናው የምንፈልገውን ጥቅም እናጣለን ብለው ያመኑ የውጭ ኃይሎች በቅጥረኞቻቸው አማካኝነት ሊያፈርሷት እየሠሩ መሆኑን ወጣቱ በሚገባ ተረድቷል፡፡
ኢትዮጵያን እንደ ሶሪያና የመን የማፈራረስ ዕድል እንዳያገኙ ሁሉም ወጣት አንድ ሆኖ ጠላቶቹን የመመከት እንቅስቃሴ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡ ዓለምአቀፍ ሚዲያዎች ለአሸባሪ ቡድኑ የሚወግኑ መረጃዎችን ማስተላለፋቸው ወጣቱ የውጭ ኃይሉን ሴራ በሚገባ እንዲረዳ አድርጎታል፡፡ በተለይም አዲስ አበባ በአማጽያኑ ተከባለች፤ ከተማዋ ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት ስላለባት የአሜሪካን ዜጎች እንድትወጡ የሚሉትና ሌሎቹም ያፈጠጡ ያገጠጡ ውሸቶቻቸው ምን ያህል ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ተናበው እየሠሩ መሆኑን የሚሳይ ነው፡፡
የሚዲያዎቹ ጫጫታና የእነ አሜሪካ ጫና ወጣቱን የበለጠ እልህ ውስጥ አስገብቶ አንድነቱን እንዲያጠናክር ረድቶታል፡፡ በተለይም ወጣቱ ከሦስት ዓመት በፊት ከስልጣን ያባረረውን ተላላኪ መንግሥት ምዕራባውያን እንደገና ወደ ስልጣን ለማምጣት መሞከራቸው ከፉኛ ያስቆጣው በመሆኑ ዳግም የሕወሓትን አገዛዝ ላለማየት የበኩሉን ሁሉ እያደረገ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት በርካታ ወጣቶች ሠራዊቱን እንዲቀላቀሉ ያደረጋቸውም የውስጥና የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሚያደርጉት ሴራ ነው፡፡
በግንባር ከተሰለፉት ውጪ በርካታ ወጣቶች በስልጠና ማዕከሎች ውስጥ እንደሚገኙ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያን ሰላም የበለጠ ለማረጋገጥ ሁሉም ወጣት ወታደራዊ ስልጠና ቢወስድ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግሯል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልጽግና ተልዕኮ ሊግ ከስሙ መረዳት እንደሚቻለው ሰላማዊ ወጣቶችን አፍርቶ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚሠራ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ የወጣት አደረጃጀት የሀገርን አንድነት ለማስጠበቅ የሚሠራ ነው፡፡
ማንኛውም ወጣት የሃይማኖት፣ የብሔርና ሌላም ተጽዕኖ ሳይደረግበት በአገሩ ጉዳይ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን ይገባዋል የሚል አስተምህሮ ያለው ነው፡፡ ግላዊ ጥቅማችን ተነካብን ብለው ከውጭ ኃይሎች ጋር በማሴር ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከተነሱ ጥቂት ግለሰቦች ጋር የቆሙ አንዳንድ የትግራይ ወጣቶች ታሪካዊ ስህተት ሠርተዋል፡፡ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወጣት ትልቁን የአገር ምስል አስከብረው መሄድ ሲገባቸው በግለሰቦች ተታለው የጎጠኛ አስተሳሳብ ተገዢ መሆናቸው ያስቆጫል ብሏል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በርካታ የትግራይ ወጣቶች ወደውም ይሁን ተገደው የአሸባሪ ቡድኑ ታጣቂዎች ሆነዋል፡፡ እነዚህ ወጣቶች በምን ምክንያት አገራቸውን እየወጉ እንዳሉ ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል። ነገ በሠሩት ሥራ የሚጸጸቱ እንደሚሆኑ አያጠራጠርም። አላስፈላጊ መስዋዕትነት ከመክፍል ይልቅ በለውጡ ብርሃን ጨለማቸውን ገፈው በትግራይ ምድር አዲስ አስተሳሰብና አሠራርን በማስፈን አካባቢያቸውን መለወጥ፤ ኢትዮጵያንም ማሳደግ ይኖርባቸዋል፡፡ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወጣት ለውጡን በመደገፍ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡
የትግራይ ወጣቶች ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በአሸባሪው ቡድን እየተደለሉ የከፈሉትን አላስፈላጊ ዋጋ ይመልክቱ፤ በዚህ ጦርነት ለትግራይ ወላጆች ያተረፉላቸው ኀዘን ነው፡፡ ወደውም ይሁን ተገደው አገራቸውን የሚወጉ የትግራይ ወጣቶች እጃቸውን በመስጠት እራሳቸውን እንዲያድኑ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰላምና ብልጽግና ተልዕኮ ሊግ ይመክራል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ኀዳር 24 / 2014