በምዕራባውያኑ ዘንድ ሰብአዊነት ከሞተ ውሎ አድሯል፤ ኧረ ሰንብቷል! ቤተሰባዊነት፣ እምነት፣ ባህል ገለመሌ ብሎ ነገር የለም። ለእነሱ ከምንም ነገር በፊት ጥቅማችው ትልቁ እሴታቸው ነው። ማንም በእነሱ መስፈርት የሚለካው ከሚያስገኝላቸው ጥቅም አንፃር ነው። ይህ የመንግሥታታቸውም ባህሪ ነው።
ለእነሱ ያልተመቻቸውን ከማጣጣል፤ በእነሱ ሥርዓት ተደላድሎ ለመጋለብ የተመቸ ሰጋር ፈረስ ሲገኝ ደግሞ ይበል እያሉ እሱኑ እያወደሱ ጥቅማቸውን የማስጠበቅ ዘመናት የተሻገረ መገለጫቸው ነው። ከዚህ ውጪ ስለ ዴሞክራሲ፣ ሰብአዊመብቶች… ወዘተ የሚተርኳቸው ትርክቶች የጥቅሞቻቸው ማስጠበቂያ ዜማዎቻቸው ናቸው።
በተለይም ሦስተኛው ዓለም ብለው በሰየሟቸው ሕዝቦች ላይ ቀደም ባለው ዘመን ያደረሱት ግፍ በታሪክ በጥቁር ፊደላት ተከትበው የሚገኙ ናቸው ። ዛሬም ቢሆን ያንኑ ፍላጎታቸውን በተለየ መንገድ በማስፈፀም ተመሳሳይ ታሪክ እየሰሩ ነው። አገራቱን የሸቀጥ፣ የዝቃጭ፣ የክፋት እና የሴራ ተግባሮቻቸው መፈጸሚያ እያደረጉ ነው። በእፍኝ ሰጥተው በቁና ሲቀበሉ፤ በማንኪያ ሰጥተው በአካፋ ሲዝቁ መመልከት የተለመደ ነው።
አገራቱ በትንሽ ክፍያ የነሱን ብራንድ ዕቃዎች በርካሽ የሰው ኃይል አመርተው ወደ አገራቸው ልከው መልሰው የሰጡንን ሽርፍራፊ ሳንቲም በእጅ አዙር ይነጥቁናል። የምድር ፍሬያችን፣ ማዕድኖቻችንን መበለጸጊያቸው፤ እኛን የጦር መሣሪያ ገበያቸው ለማድረግ ግጭትን ማልማት ተቀዳሚ ሥራቸው፤ የእኛ ሞት ለቅሶ የእነሱ ሠርግና ምላሻቸው ነው።
የፍልስፍናቸውና የእምነታቸው ማራገፊያ ለማድረግ ትምህርት ቤቶችን በጠማማ ትምህርት፣ ቤተ እምነቶችን በኑፋቄና በዘረኝነት ይበክላሉ፤ መልካም እሴቶቻችንን ከላይችን ላይ አውልቀን እንድንጥል በብዙ ተጽእኖዎች ያስገድዱናል። እነሱ ልጆቻቸው ላይ በመስራት አገር ይገነባሉ፤ የእኛ ትውልድ በፌዝና በድንዛዜ ውስጥ እየተንከላወሰ በነሱ ብልጭልጭ ተታሎ እነሱን ናፋቂ እነሱን፤ተመልካች እንዲሆንባላቸው ሌት ተቀን ባላቸው አቅም ይሰራሉ።
ከቴክኖሎጂ መስፋፋትና ከመገናኛ ብዙኃኖቻቸው ጉልበት የተነሣ ወጣቱ የቀደመውን ትውልድ የተከበረ የአኗኗር ዘዬ እንዲተው በማድረግ ሁሉን ሸቀጥ አድርጎ እንዲያስብ፤ እራሱንም ከሸቀጥ ያልተለየ አድርጎ እንዲገምት እያደረጉት ነው፡፡ የሚያየው፣ የሚያነበው እና የሚሰማው የምዕራባዊውን ዓለም ማንነትን እንዲይዝ እንጂ እውነተኛ ማንነቱን ይዞ እንዳይኖር እያደረጉት ነው፡፡
የማንነት እጦት ከሥርዓተአልበኝነት ባለፉት ጥቂት አሥርት ዓመታት ካሳለፍነው የፖለቲካ ነውጥና የማኅበራዊ ኑሮ ቀውስ ጋር ተያይዞ፤ ከቤተሰብ ተቋም መዛባትና ከኢኮኖሚያዊ ስጋት ጋር ተዳምሮ ወጣት ማንነቱን አጥቶ ‹‹እኔ እንዲህ ነኝ ›› ለማለት አቅም እያነሰው መጥቷል፡፡
ወይ ራሳችንን በቅጡ አላሲያዝናቸው ወይም ከሌላው የሚኮርጁት ጠቃሚ አለመሆኑን አላሳየናቸው የልጆች አስተዳደጋችን የእውር ድንብር ሆኖ ሞራልየለሽ ትውልድ፤ ትላቅን ማክበር ነውር እስኪመስላቸው ድረስ አይደለም ጎረቤትን እናት አባት የማያከብር፤ ባህሉን ወጉን ትቶ የሱ ያልሆኑትን ጥርቅምቃሚ የለቃቀመ ትውልድ በፍቃዳችን እንድናፈራ አድርገውናል።
በሉአላዊነቱ የሚመካ አገር እንዳይኖር መንግሥታትን በብድርና በእርዳታ ጥገኛ በማድረግ የዜጎቻቸው መብት ላይ የፈለጉትን እንዳይወስኑ እግር ከወረች አስረው የፈቃዳቸው ማስፈጸሚያ አደርጓቸዋል። አገራቱን የግጭትና የጦርነት ሜዳ በማድረግ ከሕዝቦች መከራ ስቃይና ሞት አትራፊ ነጋዴዎች ናቸው።
ይህ ሁሉ ይበቃል!!!!! በቃ…… የምንልበት ወቅት ላይ ነን። በተለይም እኛ ኢትዮጵያውያን ዓይናችንን ከፍተን በአግባቡ መመልከት ያለብን ታሪካዊ ወቅት ላይ ነን። እነዚህ ኃይሎች በቀደዱልን ቦይ እየፈሰስን አለመሆናችንን በተጨባጭ ማረጋገጥ ይጠበቅብናል። ሁሉም ነገር መነሻ እና ፍጻሜም እንዳለው ለማወቅ ዓይናችንን በሰፊው ከፍቶ ማየት የግድ የሚልበት ሰዓት ላይ ደርሰናል።
በመላው አገሪቱ እየተሰማ ያለው የሰቆቃ ለቀሶ እውነተኛ ምክንያቱ እኛ ከምንገምተው ባለፈ እነዚህ ኃይሎች በእኛ ላይ እየሰሩት ካለው ሴራ የመነጨ መሆኑን ልናስተውል ይገባል። ይህንን ዘመናት ያስቆጠረ የሴራ ትብታብ ለመፍታትና ከሴራው እራሳችንን እንደ ሀገርና ሕዝብ ለመታደግ ለአዲስ አስተሳሰብ እራሳችንን ማስገዛት ይኖርብናል።
በአንድም ይሁን በሌላ አለመታደለ ሆኖ ከአገራችን ታሪክ የበዛውን ክፍል የያዘው ጦርነት ነው። ከያንዳንዱ ጦርነት በስተጀርባም የከፈልነው ዋጋ ከፍ ያለ ነው። ጦርነቶቹ፣ በተለይም እርስበርሳችን ስናካሂዳቸው የነበሩ ጦርነቶች ሁላችንንም እንደ አገር እና ሕዝብ ተሸናፊ ያደረጉ ናቸው።
ዛሬ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ነን። ይህንን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ በአዲስ የቃል እውነት በይቅርባይነት፤ አንድ በመሆን በመደመር ጀምረን ወደ ከፍታችን እጅለእጅ ተያይዘን እንጓዝ፤ ለዚህ የሚሆን ዝቅ ማለትንም እንልመድ ።
ነገሩ ካለፈ በኋላ ከምንቆጭ ለወዳጅም ለጠላትም እውነተኛ የኢትዮጵያዊነት መልካችንን እናሳይ፤ የነብር ቆዳ ያህል የተዥጎረጎረውን እኛነታችንን ውበታችን ድምቀታችን እንዲሆን ዕድል እንስጠው።
ከሁሉም በላይ የጦር መሣሪያ ራሳቸው እየሸጡለን ስለ ሰላም ስለ ድርድር ቀድመው የሚያወሩት፤ የልብ ትርታዎቻችንን እየተከተሉ በመገናኛ ብዙኃኖቻቸው ፀባችንን የሚያራግቡት ለምን ይመስላችኋለ፤ እውነት አዝነውልን? ተሳስታችኋል! ….ኢትዮጵያን ሊቀራመቱ ያሰፈሰፉ አካላትን ልብ ብላችሁ ተመልከቱ። ታሪክ ያላቸውን ሕዝቦች የማጥፋት ስውር ሴራ ይዘው ስለሚንቀሳቀሱ እንደሆነ ለማየት አይከብዳችሁም።
ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ሊቢያን ማየት ተገቢ ነው። እነዚህ አገራት በቀደመው ዘመን ሥልጣኔቸው የሚታወቁ፤ አሁን ላለው ዓለም ከፍ ያለ ባለውለታዎች ናቸው። ያለ ኃጢያታቸው ብዙ ዋጋ እንዲከፍሉ ሆነዋል። አሁንም እየከፈሉ ነው።
ከዚህ ተጨባጭ ታሪክ ተምረን ልንነቃ ይገባል። በሚቻለን ሁሉ ፀብን በፍቅር እየቀየርን፣ መልካም አስተሳሰብን እየተጋራን ከተበጀልን የሴራ ትብታብ እንጠበቅ። ዜጎቻችንንም እናንቃ። እየተላለቅን ዳግም እንደ ግመል ሽንት ወደኋላ አንጎተት። በትናንሽ አጀንዳ ተከፋፍለን የአሻንጉሊቶቻቸው መሣሪያ እንዳንሆን አንድነታችንን እናጠንክር። ለዚህም እንንቃ! መንቃት ያተርፈናል።
ምዕራቡም፤ ምሥራቁም፤ ሰሜኑም፤ ደቡቡም፤ እገሌ ከእገሌ ሳይል በስውር ካራ ቅርጫ ሳያደርጉን እንንቃ። የእምነት፣ የሃይማኖት አገራችንን፤ አብሮነት መገለጫ ምድር፤ የሰው ዘር መገኛ ጣሪያ አልባ ሙዚየም የሆነችውን አገራችንን አንዳናጣ አንንቃ….. በበረከት የተሞላችውን አገራችን ኃላፊነት በጎደለው መንገድ እንዳናጣ እንንቃ። ሁከት ይሰዳል በረከት እንዲሉ አበው የተሰጠንን በረከት ሰደን ለልመና እጃችንን ወደ አጥፊዎቻችን ሳንዘረጋ ይብቃን ወደ ቀልባችን እንመለስ !።
ብስለት
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2014