ስለኢሬቻ የተነገሩ እና የተጻፉ የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ኢሬቻ ማለት ምስጋና ማቅረብ ነው። ‹‹ይሄን ስላደረግህልኝ፣ ከክረምት ወደ በጋ (ብራ) ስላሸጋገርከኝ አመሠግናለሁ›› እየተባለ ፈጣሪ ይመሰገንበታል።
የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ባሳተመው አንድ በራሪ ወረቀት ላይ የሰፈረ መረጃ እንደሚጠቁሙው ፤ ኢሬቻ ማለት በወንዝ ዳርቻ በጥንታዊ የኦሮሞ ህዝቦች ዘንድ ፈጣሪ (ዋቃን) ለማመስገን የሚደረግ ሥነ ሥርዓት ነው። በዓሉ የበለጠ የሚታየው በአተገባበር (ክዋኔ) ነው። በዚህ ክዋኔ ውስጥ የዋቄፈና የሃይማኖት ተቋም የእምነቱ መሪዎች (ቃሉዎች) ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ። የኢሬቻ ሥነ ሥርዓት የትና እንዴት መከበር እንዳለበትም የሚወሰነው በቃሉዎች ነው።
ኢሬቻ በሁለት ቦታና ወቅት ይከበራል። አንደኛው በተራራ ላይ የሚከበር ኢሬቻ ሲሆን፣ ሁለተኛው በጅረትና ሐይቆች ዙሪያ የሚከበር ሥርዓት ነው።
በተራራ ላይ የሚከበረው የኢሬቻ (ሬቻ ቱሉ) በአል የሚከበረው የበጋ ወራት አልፈው የበልግ ወቅት ሲገባ ነው። የሚከበረውም በበጋ ወቅት የነበረውን የፀሐይ ሙቀትና የውሃ እጥረት አስመልክቶ ዝናብ እንዲጥል ፈጣሪን ለመለመን ነው። ቦታውም የደመና እርጥበት የሚታይበት ተራራማ ቦታ ላይ ይሆናል። በቦታው ላይ ሆነውም ለዋቃ ምስጋና ያቀርባሉ።
ሁለተኛው በጅረቶችና ሐይቆች የሚደረገው ነው። ይህኛው በክረምት ወር ማብቂያ እና በብራ ወራት መግቢያ መስከረም ወር አጋማሽ አካባቢ ይደረጋል። አተገባበሩም በሐይቅ ዙሪያ ነው። በክረምት ወቅት ተዘግተው የሚቆዩ መደበኛ ችሎቶች የሚከፈቱበትም ስለሆነ ‹‹የችሎት መክፈቻ›› ተብሎም ይጠራል። ወቅቱ የአበባና የብራ ወቅት ስለሆነም ለዋቃ ዝማሬ የሚቀርብበት ነው። በውሃ ዳር የሚሆነውም ውሃ የዋቃ ስጦታ ስለሆነ ነው።
በዚህ ወቅት በደጋ እና ወይና ደጋ አካባቢ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ከብቶቻቸውን ወደ ሆራ ወይም ጨዋማ ውሃ ያሰማራሉ። ኢሬቻ በውስጡ ባህልንና ፍልስፍናን ያቅፋል። ትውልድና የመኖር ምስጢርን ያቀፈ ስለሆነም ተፈጥሮም ይታይበታል። የእፅዋትን፣ የእንስሳትን ተዋልዶና የትውልድ መተካካትን ከዋቃ ጋር የሚያዛምዱበት ነው።
የኢሬቻ በአል ለዘመናት ሲከበር የኖረ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይበልጥ ደማቅ በሆነ መልኩ እየተከበረ ነው። በቢሾፍቱ በስፋትና በድምቀት ሲከበር የኖረው ይህ በአል ከሁለት አመት ወዲህ ደግሞ በአዲስ አበባም በደማቅ ሥነሥርዓት በሆራ ፊንፊኔ ይከበራል።
በእንዲህ አይነቶቹ የኦሮሞን ባህል በሚያሳዩ በዓላት ላይ የበአሉ ታዳሚዎች በአሉን በኦሮሞ አልባሳት ተውበው ያከብሩታል። ወቅቱ የኦሮሞ የባህል አልባሳት ዲዛይን የሚታይበት ነው። አልባሳቱ አሁን ላይ በዘመናዊ መንገድ እየተሰሩና ለአለባበስና ለጉዞ ምቹ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው። ዘመናዊ ሲደረጉ ግን ባህላዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ ነው። የኦሮሞ ህዝብ በሚወደውና በመረጠው የቀለም አይነት እንዲዘጋጁ ይደረጋል።
በእንዲህ አይነት በዓላት ላይ በመደበኛው የተለመዱት የባህል ልብሶች አሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የባህል ልብሶች በዘመናዊ መንገድ ተሰርተውም ይለበሳሉ። ይህ የባህል ማንፀባረቂያ በዓል ቀኑ ሲደርስ አልባሳቱን በአዲስ አበባ ጎዳናዎችና በኦሮሚያ ከተሞችና የገጠር አካባቢዎች በድምቀት እንመለከታለን።
ባለፈው ዓመት በሸራተን ሆቴል በተዘጋጀ አንድ ሁነት ላይ እንደሰማሁት፤ የባህል አልባሳቱ ዘመናዊ ሲደረጉ ባህላዊ ይዘታቸውን በማጥፋት አይደለም። ከጥራት፣ ከውበትና ከቅልጥፍና አንጻር ነው የሚዘምነው።
እዚህ ላይ ግን አንድ አከራካሪ ነገር እናንሳ። አንዳንድ ሰዎች ባህላዊ የሆኑ ነገሮች ምናቸውም ሳይነካ መቆየት አለበትይላሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ የዘመኑን ባህሪ ተከትሎ ይዘቱን ሳይለቅ በዘመናዊ መልኩ መሰራት አለበት ይላሉ።
በየክልሉ የተለያየ ባህላዊ አለባበስ አለ፤ ያንን በነበረበት ብቻ ይለበስ ቢባል በአሁኑ ጊዜ የማይመች ይኖራል። ሌላው ማህበረሰብም እንዲለብሰው ተደርጎ ነው በዘመነ መንገድ የሚሰራው። ለአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለብዙ ጊዜ እንዲለበስም ለእንቅስቃሴና ለሥራ ምቹ በሚሆን መንገድ ማዘጋጀት ችግር አይኖረውም። አንዳንድ የቆዩ ልማዶችም በሂደት ሊቀሩ ይችላሉ።
ለምሳሌ፤ በአንዳንድ የኦሮሞ አካባቢዎች በድሮው ጊዜ ቅቤ እየተነከረ የሚለበስ ቀሚስ እንደነበር ከታሪካዊ ሰነዶች እናያለን። ያ በነበረበት እንዲቀጥል ቢደረግ በዚህ ዘመን አይሆንም። አሁን ቅቤው እንኳን ተገኝቶ ልብሱ ቢነከር የሚለብሰው አይኖርም። እነዚህ ነገሮች ናቸው እየተጠኑ ዘመኑን በሚመጥን መንገድ የሚሰራው።
በነገራችን ላይ በኢሬቻ ሰሞን በኦሮሞ አልባሳት የሚዋቡ ቆነጃጅት የሚፈልጉትን ልብስ በመጀመሪያ ዲዛይነሯ በሥዕል ሰርታ ታሳያቸዋለች። ዲዛይኑንም ሆነ የቀለም አይነቱን በሚፈልጉት መንገድ ከሆነ በኋላ ትሰራላቸዋለች። ይህ ሲሆን የኦሮሞን ባህል ይገልጻል ተብሎ በብዙዎች ዘንድ የታመነበት ይሰራል።
ከአልባሳቱ ጋር የሚሄዱ ጌጣ ጌጦችን መጠቀምም በዚህ በአል ወቅት ተለምዷል። የጆሮ ፣ የጸጉር ፣ የእጅና የመሳሰሉት ጌጣ ጌጦች ሳይቀሩ ይህን አለባበስ ይበልጥ ሊያስውቡ በሚችሉ መልኩ ይዘጋጃሉ።
የባህል አልባሳት ትንሳኤን እያመለከቱ ላሉት እንዲህ አይነት ጥበባዊ ሥራዎች ከመንግስት በኩል የሚደረገው ድጋፍ ደካማ እንደሆነ ግን ተደጋጋሚ ቅሬታዎች ሲነሱ ይሰማል። በፊት ከነበረው የተወሰነ መሻሻል ቢኖርም፤ ባህላችን ነው፣ የራሳችን ነው የሚለው ስሜት ግን አሁንም የተቀዛቀዘ ነው። መንግስት ተገቢውን ድጋፍ ቢያደርግ በእንዲህ አይነት ጥበባዊ ሥራዎች ላይ የሚሰሩ ወጣቶች ይበራከታሉ፤ ባህሉም እየተጠበቀ፣ አልባሳቱም ይበልጥ እየተለበሱ ይመጣሉ፤ በዚህ ዙሪያ የሚንቀሳቀሰው ኢኮኖሚም ይጎለበታል።
ሃሳብ ከማፍለቅ ጀምሮ ብዙ አዳዲስና ዘመናዊ ሥራዎችን የሚሰሩ ዲዛይነሮች አሉ። ህብረተሰቡ የሚፈልገው ደግም ጥራት ያለውና ዘመኑን በሚመጥን መንገድ የተሰራ የባህል ልብስ ነው። ለዲዛይነሮቹ ድጋፍ ማድረግ የህብረተሰቡን ጥያቄ መመለስ ይሆናል።
በአሁኑ ጊዜ በማህበረሰቡ ውስጥ የባህል ልብስ ፍላጎት እየጨመረ ነው፤ ዳሩ ግን በጥራት የባህል ልብሱ በሚፈለገው ጥራት እየተሰራ አይደለም የሚል አስተያየትም አለ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ሰዎች እየገዙ እየለበሱት ነው። በጥራት ቢሰራ ደግሞ ከዚህም በላይ ተፈላጊነቱ ይጨምራል። በተለይም በበዓላትና በአንዳንድ ሁነታዊ ዝግጅቶች የሚለበሰው የባህል ልብስ ነው።
ትውፊታዊው የባህል ልብስ ከፖለቲካ ጋር እንዲቀላቀል ባይደረግም መልካም ነው። በዚህ ሁኔታ (ፖለቲካዊ መልክ ከተሰጠው ማለት ነው) ዲዛይነሮች ገበያ ላይ የሚፈለገውን ታሳቢ በማድረግ ይሰራሉ ማለት ነው፤ ያ ደግሞ ባህሉን ሌሎች ወገኖች እንዲሸሹት ያደርጋል።
ኢሬቻ አዲስ አበባ ውስጥ መከበር ከጀመረ ገና ሦስት ዓመቱ ነው። ባህላዊ ትውፊቱና ሥርዓተ ክዋኔው ለብዙዎች አዲስ ነው። ከስነ ቃሎች እና የወጣቶች ጨዋታዎች ጋር አልተላመደም። እስከ አሁን ባለው ሂደትም የሚታወቀው በመድረክ ዝግጅቶችና በመገናኛ ብዙኃን ነው። በእነዚህ መድረኮችና መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚተላለፈው ደግሞ የባለሥልጣናቱ መልዕክት ስለሆነ ፖለቲካዊ ይዘት ይኖረዋል።
በበአሉ ወቅት ከሚከናወነው ሥነሥርዓት መረዳት እንደሚቻለው እሬቻ የምስጋና ተምሳሌት ነው። የበአል አከባበሩም በዚህ በምስጋና ፋይዳው ላይ ብቻ መመስረት ይኖርበታል። ይህ ሲሆንም ፈጣሪውን ማመስገን የማይወድ የለምና በአሉን ለፈጣሪው ማመስገኛ የሚያውለው ህብረተሰብ እየጨመረ ይመጣል። ይህን ማድረግ ከተቻለ የበአል አከባበሩን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ማስፋፋትም ይቻላል። ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳው እየጨመረ እንዲመጣ ለማድረግም ይህ ትልቅ ፋይዳ አለው። በመሆኑም በእዚህ የምስጋና ተምሳሌት በሆነው የእሬቻ በአል ፋይዳ ላይ በትኩረት ይሰራ እንላለን።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መስከረም 22/2014