አዲስ ዘመን ጋዜጣ ባለፉት 81 ዓ መታት በርካታ ሁነቶችን ዘግቧል። በእነዚህ ሁነቶች የየዘመኑን ባህሪ ያሳየናል። በወቅቱ ምን ይባል እንደነበር፣ የዘመኑን የገበያ ሁኔታ፣ የማስታወቂያ ባህሪ፣ ምን ይፈቀድ ምን ይከለከል እንደነበር ስለሚነግረን ያንን ዘመን እንድንኖረው ያደርገናል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በየዘመኑ የነበሩ መንግስታትን ታሪክ ብቻ አይደለም ሰንዶ የሚያስቀምጥ። የማህበረሰቡን ወግ፣ ባህልና ልዩ ገጠመኞችን ጭምር ነው። በየመዘኑ የነበረው የቋንቋ አጠቃቀም ምን ይመስል እንደነበር ሳይቀር ያሳየናል። በዚህ አጋጣሚ የምናሳስባችሁ ነገር እኛ ድሮ አዲስ ዘመን ላይ የወጡ ጽሑፎችን ዛሬ ላይ ስናስነብባችሁ እንደወረደ ነው። ለምሳሌ አረፍተ ነገሩ ረጅም ከነበረ አንቆርጠውም፤ የሚጠቀሙት ቃላትም እንዳለ ነው። ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ ‹‹ገለጸ›› የሚል ነው የምንጠቀም፤ ያኔ የነበረው ‹‹ገለጠ›› ከሆነ እንዳለ ነው የምናስቀምጠው።
በዛሬ የአዲስ ዘመን ዱሮ አምዳችንም ጋዜጣው በመስከረም ወር በተለያዩ ዓመታት ምን ይዞ እንደወጣ በጥቂቱ እናቃምሳችሁ!
የፓርላማ አባሎች ከባንክ የወሰዱት ብድር ሁለት ሚሊዮን 800 ሺ ብር መሆኑ ተገለጠ የህግ መምሪያ ምክር ቤት አባሎች ለንብረት መቋቋሚያ ብለው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰዱት ብድር ምክር ቤቱ በመዘጋቱ ምክንያት የብድር አከፋፈል ችግር ሳያስከትል እንደማይቀር አንድ የባንኩ ባለሥልጣን ገለጡ።
ጊዚያዊው የወታደር አስተዳደር ባወጣው አዋጅ፤ ‹‹በአሁኑ ጊዜ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ምክር ቤት አባሎች አመራረጥ የዴሞክራሲን መንፈስ ያልተከተለ ከመሆኑም በላይ ምክር ቤቱ እስከ አሁን ያገለገለው ለህዝብ ሳይሆን ለባለሥልጣኖች፣ ለመሳፍንት እና ለራሳቸው በመሆኑ የአገሪቱ መሰረታዊ ችግር የሆነውን የመሬት ይዞታን የሚያሻሽል ህግ ከማውጣት ተቆጥበው የራሳቸውን የኑሮ ደረጃ የሚያዳብር ህግ በየጊዜው በማውጣት ከህዝብ የተሰጣቸውን ከፍተኛ ሥልጣን ለግላቸው መጠቀሚያ እያደረጉ በህዝብ ላይ ተጨማሪ ችግር ስላደረሱ የምክር ቤቱ መኖር ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› ለተባለው ዓላማ እንቅፋት መሆኑን በመገንዘብ የህግ መምሪያ እና የህግ መወሰኛ ምክር ቤቶች እንዲዘጉ መወሰኑ ይታወሳል።
በአምስተኛው የህዝብ እንደራሴዎች ምርጫ ለህግ መምሪያ ምክር ቤት አባልነት ከተመረጡት 250 መማክርት መካከል ለንብረት መቋቋሚያ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራት ኪሎ ቅርንጫፍ ብድር የወሰዱት መማክርት 211 መሆናቸው ታውቋል።
ከህዳር ወር 1966 ዓ.ም ጀምሮ ለተከበሩ መማክርት ከባንኩ የተሰጠው ጠቅላላ ብድር አንድ ሚሊዮን ስምንት መቶ ሺ ብር ያህል መሆኑን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራት ኪሎ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቀጀላ ዋጮ ገልጠዋል። ከዚህም ውስጥ አሁን በመማክርቱ ላይ የቀረበው ዕዳ አንድ ሚሊዮን ሦስት መቶ ዘጠና ሺ ብር ያህል መሆኑ ተገልጧል።
የህግ መምሪያ ምክር ቤት አባሎች ከባንኩ ብድር የወሰዱት ከወር ደሞዛቸው ተቆራጭ እያደረጉ ዕዳውን በሦስት ዓመት ውስጥ ከፍለው ለመጨረስ ውል በመፈራረም ነበር። ተበዳሪዎቹ ገንዘቡን የወሰዱት እርስ በርስ ዋስትና በመጠራራት እንደነበር ተረጋግጧል።
መስከረም 21 ቀን 1967 ዓ.ም
አዲሱን የለቅሶ ዜማ የመንደር አልቃሾች ተቃወሙ
የቤተሰብን ጤንነትና አካል እንዲጠብቅ ተብሎ በጸሎት መልክ የቀረበውን አዲሱን የሀዘን ዜማ አንዳንድ አልቃሾች መቃወማቸው ተገለጸ።
አዲሱን የለቅሶ ዜማ የመንደር አልቃሾች ኮርስ ወስደው እንዲያጠኑ ተጠይቀው ፈቃደኛ ሆነው አልተገኙም።
አዲሱ ዜማ አንድ ሰው ሲሞት በህብረ ዝማሬ እየተዜመ ሙታንን ለመሸኘትየሚያስችል ነው። በተለይም አንድ ሰው በሞተ ጊዜ የሟቹ ቤተሰቦች ደረት በመደለቅ መሬት በመፈጥፈጥና ፊት በመንጨት የሚደርስባቸውን ከባድ ጉዳት የሚያስወግድና ሥርዓትና መልክ ያለው ነው። ዜማውን የደረሱት አቶ አብርሃም መኮንን የመንደር አልቃሾች እንዲያጠኑት ቢጠይቋቸው ‹‹ብላችሁ ብላችሁ በእንጀራችን መጣችሁ? ቄሶቹ በአንድ በኩል ያወግዛሉ እናንተ ደግሞ ይህን ትላላችሁ ለእኛ ሥራችን ነው›› ብለው እንደወቀሷቸው ተናግረዋል።
የአሁኑ የአልቃሾች ዜማ ወንዱና ሴቱ ተለይቶ አይነገርበትም። የሞተችው ሴት የሆነች እንደሆነ ለወንድ ያለቅሱበታል። ሟቹ አርበኛ የሆነ እንደሆነም አቶ እገሌ እህል ሲያመርት፣ እርፍ ሲይዝ እንዲህ አልነበረም ተብሎ ሙሾ ይቆምበታል። በጠቅላላ ዜማው ሥርዓት የሌለው ነው። ነገር ግን በህብረት እየተዘመረ የሚዜመው የለቅሶ ዜማ በአልቃሾች ቢጠና ጥቅሙ እንደሚያመዝን አንዳንድ አልቃሾች ተናግረዋል።
መስከረም 7 ቀን 1963 ዓ.ም
ማስታወቂያ
ፊልም በሚታይበት ጊዜና ፊልም ለመለወጥ ብርሃን በሚደረግበት ጊዜ የብልግና ድምጽ ምልክት የሚሆን ድምጽ ሰሚዎችን እስከማደንቆር ይሰማል። ይህ ከጠላት የተወረሰ የብልግና ድምጽ እንዳይሰማ እያስጠነቀቅን የፉጨት ድምጽ የሚያሰሙትን የሚያስገድዱ ፖሊሶች መታዘዛቸውን እናሳውቃለን።
አዲስ ዘመን በየዘመኑ የነበሩ መንግስታት የፖለቲካ ባህሪንም ይነግረናል። ባለሥልጣናቱ ምን ያደርጉ እንደነበር፣ ምን አይነት አሰራር፣ ህግና ደንብ እንደነበር ይነግረናል።
ከዛሬ 47 ዓመታት በፊት በዘመነ ደርግ መስከረም 21 ቀን 1967 ዓ.ም ጋዜጣውን የሚከተለው ዜና ይዞ ወጥቷል።
መስከረም 8 ቀን 1941 ዓ.ም
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2014