አንድ ድሃ ገበሬ ነው አሉ፤ በሬ የለውም:: በገጠሩ አካባቢ በሬ ለሌለው ገበሬ በእርሻ ወቅት በሬ በትውስት መስጠት የተለመደ የትብብር ባህል ነው:: እናም አንድ ገበሬ ለዚህ ድሃ ገበሬ በሬዎች ይሰጠዋል:: ገበሬው ሲያርስ ውሎ ማታ ሁለቱም የተውሶ በሬዎች ገደል ይገቡበታል:: ምን እንደሚያደርግ ጨነቀው:: በአካባቢው እንዲህ አይነት አወዛጋቢ ነገር ሲፈጠር የሚፈታው በሽማግሌ ነው:: በእርሻ ወቅት ጥንድ በሬ ገደል ሲገባ ትልቅ ጉዳት ነው::
ይህ የተውሶ በሬ ገደል የገባበት ሰውዬ ከራሱ በላይ ሽማግሌዎች ምን ብለው እንደሚፈርዱ ጨነቀው:: ሰዎች ተሰባስበው ሲያጽናኑት እሱ በአግራሞት ‹‹የነገን ሽማግሌ ያየው ሰው›› አለ ይባላል:: ሽማግሌዎች ምን ብለው እንደሚፈርዱ ነው ያስጨነቀው::
የፊታችን ሰኞ መስከረም 17 የመስቀል በዓል ይከበራል:: ዋናው መስቀል በ17 ይሁን እንጂ እንደየአካባቢው ባህል ከ12 እና 13 አካባቢ ጀምሮ እስከ 20 ምናምን ሁሉ በዓሉ እየተከበረ ይቆያል::
በዓሉ በብዙ የአገራችን አካባቢዎች በቡድን እየተሆነ ይከበራል:: የመስቀል በዓልን ጎረቤት ተሰባስቦ ማክበሩ የበዓሉ አከባበር ልዩ ባህሪዎችን እየተላበሰ እንዲከበር አድርጎታል::
የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ የመስቀልን ሃይማኖታዊም ሆነ ታሪካዊ ምንነት መተንተን አይደለም:: ይልቁንም በዚህ የመስቀል በዓል ላይ የሚታይ አንድ ድንቅ የባህል እሴትን ማሳወቅና ለሀገራችን ህዝብ ያለውን ፋይዳ ማመላከት ነው:: እንዲህ አይነት እሴቶቻችን ቢከበሩ አልፎ ተርፎም እንዲስፋፉ ቢደረግ ኖሮ ግጭትና አለመተማመን እንዲህ ባልፈነጩብን ነበር ያሰኛል::
እንደሚታወቀው የመስቀል በዓል የቤት ውስጥ በዓል አይደለም፤ ጎረቤት ተሰባስቦ ሜዳ ላይ በጋራ የሚያከብረው ነው:: ይህ በዓል በመጣ ቁጥር አንድ ባህል ይታወሰኛል:: ይሄውም በመስቀል ሰሞን ሽማግሌዎች በእርቅ ሥራ የሚጠመዱበት ሁኔታ ነው:: በአንድ አካባቢ
ጠብ ተፈጥሮም ይሁን በሌላ ምክንያት የተቀያየመ ሰው ካለ ለመስቀል በዓል የግድ መታረቅ አለበት::
የተኮራረፉ ሰዎች እያሉ በዓሉ በፍጹም ሊከበር አይችልም:: እዚህ ላይ በጣም የምታስደስተኝ ሽማግሌዎች የሚጠቀሟት የማግባቢያ ስልት ናት:: በእርቅ የድርድር ሥርዓቱ ውስጥ ከተደራዳሪዎች አንዱ ወይም ሁለቱም ለመታረቅ ፈቃደኛ ካልሆኑ ሽማግሌዎች እንዲህ ይላሉ::
‹‹በሉ እንግዲያውስ በዓሉ ይቅርላችሁ! እኛንም የእንጨት ሽበት አድርጋችሁናል:: የዘንድሮን በዓል እንግዲህ የሰው መሳቂያ አድርጋችሁን እናሳልፈው:: ‹በአካባቢው ሽማግሌ እንኳን የለም እንዴ!› እየተባልን እንሰደብ:: እግዜር ዓመት ዓመቱ አድርሶ ለዚህ ያበቃንን በዓል፤ መብራት ሲወጣ እኛ በእናንተ የተነሳ እንተወው…›› ሲሉ ሽማግሌዎች ያሳስባሉ::
ከተደራዳሪዎች ደግሞ ‹‹እናንተ ለምን ትተውታላችሁ? እናንተ ደምሩ!›› በማለት ሁለቱም የተኳረፉት ሰዎች ‹‹እኔ እቀራለሁ፤ እሱ ይምጣ፤ እኔ እቀራለሁ እሱ አብሯችሁ ይደምር›› ይባባላሉ::
አሁንም ግን ሽማግሌዎች አይበገሩም:: ጭራሽ የምጸት ሳቅ እየሳቁ ‹‹የኛ ባልንጀሮች የደም እርቅ ያስታርቃሉ ‹ጎረቤት ማስታረቅ ያልቻሉ› እየተባልን ደግሞ እዚህ ደመራ ላይ ልንታይ?›› እያሉ ተራ በተራ ‹‹እኔማ የዚያን ዕለት እዚህ አካባቢ አልታይም፤ እኔም አልታይም›› እያሉ ተደራዳሪዎችን ያስፈራሯቸዋል::
የዚህን ጊዜ እንግዲህ የሚታረቁት ሰዎች የግድ መታረቅ እንዳለባቸው ያምናሉ:: እርቁን እምቢ ቢሉ እንደ ጀግና ሳይሆን የሚታዩት እንደ ባለጌ ነው:: በባህሉ ውስጥ ከሽማግሌ ቃል መውጣት ነውር ነው:: በዓሉን ጎረቤትን አስከፍቶ መዋል በአካባቢው ያስተዛዝባል፣ በዕድርም ሆነ በሌሎች ማህበራዊ ግንኙነቶች ላይ ‹‹እሱ ደግሞ ባለጌ ነው›› ያሰኛል:: ምክንያቱም ሽማግሌ ብዙ ነገር ነው:: ነገ በራሱ ላይ የሆነ ነገር ቢደርስ ከሽማግሌ አያልፍምና የሽማግሌን ሀሳብ መቀበል የግድ ነው:: በዚህም ምክንያት ለመስቀል በዓል ክረምቱን ሙሉ ተኮራርፎ የከረመ ሁሉ ይታረቃል::
የእርቅ ሁኔታው እንደየቅሬታቸው ይለያያል:: ቀላል የሚባል መቀያየም ከሆነ ከጎረቤት ሽማግሌዎች አያልፍም፤ ብዙ የተነጋገሩና የመደባደብ ደረጃ ላይ የደረሰ ከሆነ ደግሞ ራቅ ካለ አካባቢ ሽማግሌ ይመረጣል:: የሚመረጡ ሽማግሌዎችም ብዙ የማስታረቅ ልምድ ያላቸውና የሃይማኖት አባቶች ናቸው::
በዚህ በማስታረቅ ሥራ ውስጥ የሚታወቁ ያደኩበት አካባቢ ሽማግሌዎች ዛሬም አሉ:: እነዚህ ሽማግሌዎች እስከ ሩቅ አካባቢ ድረስ ሰዎችን ለማስታረቅ ይሄዳሉ:: የማስታረቅ ጥበባቸው ለብዙ ሽማግሌዎች አርዓያ ሆኗል:: ሽማግሌዎቹ በአዘቦት ቀን እንኳን አብረዋቸው ሲጫወቱ ብዙ ነገር የሚያስተምሩ ናቸው:: ብዙ ጊዜ ነገራቸውን ከሆነ ታሪክ ጋር አያይዘው ነው የሚያወሩት:: በእርቅ ጊዜም እንደዚሁ ናቸው:: ነገራቸውን በሆነ ገጠመኝ ወይም በቆየ ታሪክ እያጣቀሱ የመጋጨትና የመኳረፍን ነውርነት ያስረዳሉ::
የማስታረቅ ጥበባቸው እንደየታራቂዎች ባህሪ ይለያያል፤ ለእዚህም የሚመቻቸውን ስልት ይጠቀማሉ:: በእርቅ ውስጥ ሁሉም የሚጠቀሟቸው ዘዴዎች ቢኖሩም አንዳንዶቹ ደግሞ የራሳቸውን ስልትም ይጠቀማሉ:: አንዳንዶቹም ‹‹ዋሽቶ ማስታረቅ›› ከሚለው ይልቅ አሳምኖ ማስታረቅን ይችሉበታል:: የሚታረቁት ሰዎች ትልቅ ቅሬታ ውስጥ የገቡ ቢሆን እንኳን በሰው ልጅ ውስጥ የሚያጋጥም መሆኑን ያሳምናሉ፤ ከዚያ የከፋ ችግር ያጋጠማቸው ሰዎች እንደነበሩና ታርቀው እንደተጋቡ ወይም በሌላ ወዳጅነት ተሳስረው ትልቅ ነገር ላይ እንደደረሱ የሚያሳይ ታሪክ ይነግሯቸዋል::
እንግዲህ የመስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በላይ እንዲህ አይነት ባህላዊና ማህበራዊ ይዘትም አለው:: በተለይ የተጣሉት ሰዎች ቤተሰቦች በዓሉን በጉጉት ይጠብቁታል፤ ምክንያቱም ቤተሰቦቻቸው ይታረቁላቸዋል:: የተጣሉት የሁለት ጎረቤት አባወራዎች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ሁለቱ አባቶች ሲኮራረፉ ልጆች ከብት ጥበቃ አብረው ነው የሚውሉት፤ ግን አባቶቻቸውን እየፈሩ አንዳቸው ሌላኛው ቤት አይሄዱም፤ በዚህ ውስጥ እንግዲህ የአባቶች መታረቅ ለልጆች የሚፈጥረውን ደስታ አስቡት!
ከዚህ አንድ ነገር እንረዳለን፤ የአዋቂዎች አዋቂ አለመሆን በልጆች ላይ የሚፈጥረውን መጥፎ ጫና! ይሄ ነገር ለጎረቤት ብቻ ሳይሆን እንደ አገር ላለው ሁኔታም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው::
ይሁንና የተማርን ነን ያሉ ሰዎች በፈጠሩት ቡድንና ራስ ወዳድነት ላይ ብቻ ተጠምደው ዘረኝነትን በመስበክ፣ እርስ በርስ በማጨፋጨፍ፣ አልፎም ተርፎ ሀገር በማፍረስ ተግባር ላይ ተጠምደው እናያቸዋለን፤ እነዚህ ተፅዕኖ ፈጣሪ ናቸው የተባሉ ሰዎች ይህን ሲያደርጉ ሌላው ይህን ክፋት እንደ ደግ ይከተላል:: እነዚህ ቡድኖች ያገኙዋትን ትንሽ ክፍተት በመጠቀም፣ አልፎም ተርፎም የሌለ ክፍተት በመፈብረክ እርስ በርስ አጫረሰዋል፤ ጨርሰዋል:: ይህን የሚገታ የሽምግልና ባህል ሳይኖር ቀርቶ ግን አይደለም::
ከዓመት በፊት የፌዴራሉን መንግስት እና በወቅቱ አፈንግጦ የነበረው ህወሓት ወደ ግጭት እንዳይገቡ የሀገር ሽማግሌዎች ወደ መቀሌ ሄደው ነበር:: በወቅቱም ከሽማግሌዎች አንዱ ጋር ቃለ መጠይቅ ባደረግሁ ጊዜ ህወሓቶች ሽማግሌዎቹን አቃለው መልሰዋቸዋል ይባላል ይህ ምን ያህል ትክክል ነው የሚል ጥያቄ ባቀርብም ያጋጠማቸውን መናገር አልፈለገም፤ በእርግጥ ይሄ የሽማግሌ ባህሪ ነው፤ ነገሮችን በምሥጢር ይይዛሉ::
ምንም እንኳን ሽማግሌዎቹ በአሸባሪው ህወሓት የደረሰባቸውን ባይናገሩም፣ ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ግን ህወሓት ቅሌቱን በድርጊት አሳየ! ምን ብሏቸው እንደነበር ግልጽ ሆነ ማለት ነው::
ቡድኑ ሽምግልናን ያህል እሴት በአገር አቀፍ ደረጃ ቢያዋርድም፣ መካር የሌለው ንጉስ ያለ አንድ ዓመት አይነግስ እንዲሉ ፍዳውን ማየት ከጀመረ ዓመት ሊሞላው የወር እድሜ ነው የቀረው:: ሽምግልና ተረግጦ የትም እንደማይደረስ ከዚህም ትምህርት መውሰድ ይቻላል::
ሽምግልና ሰላም ማምጫ ነው፤ ይህ የተከበረ ትውፊት አይሸረሽርምና ለሽምግልና እና ለሽማግሌ ክብር መስጠት ይገባል! ይህ ገንቢ የማህበረሰብ እሴት ተገቢውን እውቅና እንዲያገኝ፣ ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ ላይ በትኩረት መሰራት ይኖርበታል ::
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መስከረም 12/2014