‹‹በምግብ እጥረትና በጅምላ ጭፍጨፋ የትግራይ ህዝብ እየተፈጀ ነው። ግፍ እየተፈፀመበት ይገኛል።›› በማለት መንግስት እንዲወገዝ፣ ቢቻል በውጪ ሃይሎች ጫና እያስፈጠሩ ለማስጨነቅ ጥረት ማድረግ የተጀመረው የሕወሓት የሽብር ቡድን የሰሜን ዕዝን የመከላከያ ሰራዊት ካጠቃ በኋላ፤ መንግስት ህግ የማስከበር ዘመቻው እየተሳካለት የቡድኑን የተወሰኑ መሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ተከትሎ ነበር። በውጪ ያሉ የሽብር ቡድኑ ጀሌዎች መሬት ላይ እየተንከባለሉ ድራማ እየሰሩ ‹‹ የትግራይ ህዝብ በምግብ እጥረት ሊያልቅ ነው፤ ግፍ እየተፈፀመበት ይገኛል›› በማለት በተደጋጋሚ የማስመሰል ድራማ መስራታቸውን በማስተጋባት የዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃንም አጅበዋቸዋል።
‹‹በምግብ እጥረት ህዝቡ ሊያልቅ ነው። ›› በሚል ለሚቀርበው አቤቱታ 70 ዓለም አቀፍ እና 33 የአገር ውስጥ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የሰብዓዊ እርዳታ እንዲያደርጉ መንግስት ፈቀደ። የመንግስትን ስም በጅምላ ጭፍጨፋ እና ግፍ በመፈፀም ስም ሲወቅሱ፤ መንግስት በበኩሉ ዓላማው ጦርነት ሳይሆን ሰላም መሆኑን በማሳወቅ የተናጠል የተኩስ አቁም አወጀ።
የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ የትግራይ ህዝብ የጥሞና ጊዜ እንዲያገኝና አርሶ አደሩም የጥይት ድምጽ ሳይሰማ ወደ እርሻ ተግባሩ እንዲሰማራ በማሰብ የተላለፈ ነበር። ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ የአሸባሪው ቡድን ተመሳሳይ የተኩስ ማቆም እርምጃ መውሰድን አልመረጠም። መከላከያ ከትግራይ ክልል ቢወጣም፤ አሸባሪው ከሰላም ይልቅ ግጭቱን በማስፋት ላይ ትኩረት አድርጓል።
ቡድኑ ዓላማው በውጪ የኢትዮጵያ ጠላቶች ተቀርፆ የተሰጠው ኢትዮጵያን የማፈራረስ አጀንዳ ማስፈፀም በመሆኑ፤ የትግራይ ህዝብን አታሎና አባብሎ አንዳንዱን አስገድዶ ለጦርነት በማሰለፍ የአፋር እና የአማራ ክልልን በመውረር አጥቅቷል። ሲቪል ሰዎች ሰብአዊ ክብራቸው፣ በህይወት የመኖር እና ከበቀል እርምጃ የመጠበቅ መብታቸውን ገፎ ኢሰብአዊ ተግባራትን እየፈጸመ ይገኛል። በዚህም ሴቶችና ህጻናት በግፍ ተጨፍጭፈዋል፣ ተደፍረዋል። አረጋውያን ያለጧሪ፣ ልጆች ያላሳዳጊ ቀርተዋል። በጥቅሉ አሸባሪው ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች የከፋ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት አድርሳል፣ ዘረፋዎችንም ፈጽማል።
የሽብር ቡድኑ አሁንም ድረስ በጦርነት ተሳትፎ የሌላቸውን ሰላማዊ ሰዎችን መግደል፣ ከመኖሪያቸው በሃይል እያፈናቀለ ነው። ግጭቱን ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች በማስፋቱ ከ300 ሺህ ህዝብ በላይ ህዝብ ከቀዬው እንዲፈናቀልና በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ህይወታቸውን እንዲያጡ አድርገዋል።
ይህ ሁሉ ግፍና በደል እየተፈጸመ ባለበት በዚህ ወቅት እንኳን አለም አቀፉ ህብረተሰብ በሽብር ቡድኑ የተካሄዱ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚያስጠይቁ ወንጀሎችን ጭምር ለማውገዝ ፈቃደኛ አልሆነም። ይልቁኑም የቡድኑን ተግባር የሚያበረታቱ ለቡድኑ የልብ ልብ የሚሰጡ ተግባራትን ሲያከናውን ይስተዋላል።
የቡድኑ ታጣቂዎች ዛሬም ሲቪሎችን በከባድ መሣሪያ በመደብደብም ጭምር ዘግናኝ ድርጊት እየፈፀሙ ነው። በአማራ ክልል ቆቦ ውስጥ፣ አጋምሳ በሚባል አካባቢ፣ በርካታ ቤቶችን በማቃጠል የጅምላ ግድያ ፈጽመዋል። የቡድኑ ታጣቂዎች በገቡባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ሁሉ የዕርዳታ መጋዘኖችን ዘርፈዋል። ይህም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሊወገዝ አልተፈለገም። የዚህ ዝምታ ትርጉሙ ምን ይሆን?
የሽብር ቡድኑ በአፋር ክልል ብቻ ሳይሆን በአፋር ክልል የሀይል ጥቃቶችን በማድረስ በክልሉ በኡዋ፣ ጎሊና እና አውራ ወረዳ በከባድ መሳሪያ ባደረሰው ጥቃት ትምህርት ቤቶች ፈርሰዋል፤ የእርዳታ መጋዘኖች ወድመዋል። በአፋር ክልል ብቻ በአጠቃላይ 455 ትምህርት ቤቶች ላይ በቡድኑ ጥቃት ደርሷል።
በጋሊኮማ ከ240 በላይ ህጻናት፣ ሴቶችና አረጋውያን የጅምላ ጭፍጨፋ ፈጸሟል። ሌሎችም በጦር ወንጀለኝነት የሚያስጠይቁ ድርጊቶችን ቢፈጽምም የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ አሜሪካን እና ሌሎች ሀገራትና የሰብአዊ መብት ተቋማት ቡድኑ የሚፈፅመውን ዘግናኝ ድርጊት ለማውገዝ ፈቃደኛ አልሆኑም ።
በተቃራኒው መንግስት በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ተኩስ ከማቆም ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደርግም፤ አለም አቀፉ ህብረተሰብ ለጥረቶቹ እውቅና ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም። ከዛ ይልቅ ለችግሩ መንግስትን ተጠያቂ ለማድረግ ሲተጉ ይስተዋላል።
የሽብር ቡድኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናትን በጦርነቱ በማሰለፍ የጥይት ማብረጃ በማድረግ ለፈጸመው የጦር ወንጀለኝነት፤ የሰብዓዊ እርዳታ ማዕከላትን በመዝረፍ ለፈጸመው ወራዳ ተግባር ሆነ ‹‹የምዋጋው ለትግራይ ህዝብ ነው›› እያለ እነርሱን ተገን አድርጎ ግጭቱን ሲያስፋፋ ድርጊቱን በተገቢው መንገድ ማውገዝና እርምጃ መውሰድ አልወደደም።
የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች በበኩላቸው በአሸባሪው ሕወሓት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተረጂዎች የእርዳታ አቅርቦቶች ለማድረስ ያሳየው ቸልተኝነት ሌላው አሳዛኝ ክስተት ሆኗል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ የሰብዓዊ ድጋፍ ቁሳቁሶችን ጭነው ወደ መቀሌ ከተላኩት 466 የጭነት ተሽከርካሪዎች እስካሁን ድረስ የተመለሱት 38 ብቻ ናቸው በማለት ሰሞኑን ማሳወቁት ተከትሎ የቡድኑን ተግባር አለመኮነኑም ሌላው ወቅታዊ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል።
እዚህ ላይ ማረጋገጥ የሚቻለው የዓለም አቀፉ ማህብረሰብ የአሸባሪው ቡድን የሚያደርሰውን ግፍና በደል ጆሮ ዳባ ልበስ ከማለት ማለፉ ቡድኑ ተጨማሪ ጥቃት እንዲፈጸምና የህዝቦችን ኑሮ እንዲያመሰቃቅል የልብ ልብ እየሰጠው ይገኛል።
በዓለም ምግብ ፕሮግራም በኩል የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርሱ የተላኩት የጭነት ተሽከርካሪዎች አለመመለስ የሰብዓዊ ድጋፍ ለተጎጂዎች የማድረስ ስራውን አስቸጋሪ ከማድረግ በተጨማሪ፤ ተጎጂዎች ቀጣይ ዕርዳታን እንዳያገኙ የሚያደርግ ተግባር ነው። ይህንን ተግባሮች አለማውገዝ ምን ማለት ሊሆን ይችላል!
በሌላ በኩል ደግሞ አሸባሪው ሕወሓት ተሽከርካሪዎችን በመውሰድ ለጥፋት ተግባሩ መፈፀሚያ እያዋላቸው እንደሆነ በስፋት እየተነገረ ከመሆኑ አንጻር ጉዳዩን በዝምታ ማለፍ ምን አንድምታ ይኖረው ይሆን ? መኪናዎቹ አሸባሪው የሽብር ተግባራት በተሻለ አቅም ለመተግበር እየተጠቀመበት ከሆነ ጉዳዩ ምን ትርጉም ሊይዝ ይችላል ?
በአሸባሪው ቡድን ሀገር የማፍረስ ሴራ ውስጥ የምዕራባዊያኑ እጅ እንዳለ በስፋት ለሚናገሩና ለሚሞግቱ ሀይሎች ይህ እውነታ ምን ማለት እንደሚሆን ብዙ መናገር የሚጠይቅ አይደለም። በተለይም የምእራቡ አለም በሀገራት ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የውስጥ ጉዳዮችን መሳሪያ የማድረጉ ጉዳይ ሲነሳ እውነታው የበለጠ ትርጉም ይኖረዋል።
እነዚህ ሀይሎች ቡድኑ እየተሸነፈ መሆኑን ሲረዱ ደግሞ ለቡድኑ ህይወት ለመስጠትና ለመታደግ ባላቸው አቅም ሁሉ ሲንቀሳቀሱ በመንግስት ላይ ማዕቀብ፣ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ሲያዘንቡ መመልከቱ ደግሞ እየተለመደ መምጣቱ የነገሩን ፈርጀ ብዙነት ማሳያ እየሆነ ነው።
ከዚህ አንጻር የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በቅርቡ በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት እና በአማራ ክልል ባለስልጣናት ላይ እንዲሁም በኤርትራ መንግስት አመራሮች ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ መጣል የሚያስችል በቅድመ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ማስተላለፋቸው የዚሁ አንዱ ማሳያ ነው። ከሁሉም በላይ ለውሳኔው ተፈጻሚነት ቅድመ ሁኔታ ተደርጎ የተቀመጠው ያለ ቅድመ ሁኔታ መንግስት ከአሸባሪው ቡድን ጋር ውይይት ይጀምር የሚለው ሀሳብ አሳፋሪ ነው።
አሸባሪ ተደርጎ ከተፈረጀ ቡድን ጋር ያለ ቅድመ ሁኔታ ወደ ድርድር እንዲክድ የሚጠይቀው የባይደን አስተዳደር ጥያቄ የህግም ሆነ የሞራል በመሰረት የሌለው፤ ለኢትዮጵያ መንግስት ብቻ ሳይሆን መንግስቱ የሚወክለውን የኢትዮጵያ ህዝብ አሳንሶ ያየ ውሳኔ ነው።
በእርግጥም አሜሪካም ሆነ የተባበሩት መንግስታት የምግብ ፕሮግራም ቡድኑ በጫካ በነበረበት ጊዜ አንስቶ ለቡድኑ በግልጽም በስውርም ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበር ይታወሳል። በ1977 ዓ.ም በሀገሪቱ ድርቅ በተከሰተበት ወቅት ለተጎጂዎች በእርዳታ የመጣን የእርዳታ አቅርቦት ቡድኑ በአደባባይ ሸጦ እራሱን ሲያጠናክር ማንም ምንም አላለውም። በእርዳታ ስም የፖለቲካ አጀንዳቸውን አስፈጽመዋል፤ ዛሪመ፣ ቢሆንቸቨ እየሆነ ያለው ከዚህ የተለየ አይደለም፤ የሽብር ቡድኑ እነሱም በዜጎች ነፍስ ቁማር እየተጫወቱ ነው።
የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም እያደረገ ያለው እርዳታ በእርግጥ የታለመለት ዓላማ ምን ያህል እያሳካ ነው የሚለው በጥያቄ የሚያዝ ነው። የላካቸው መኪኖቹ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ አለመመለሳቸው ምን ማለት እንደሆነ ከሱ በላይ ሊያሳስበው የሚገባ አይኖርም።
ለእርዳታ እህል አቅርቦት የሎጀስቲክ አገልግሎት ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው። ለነዚህ መኪኖች የሚወጣው ወጪም የቱን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነም ለድርጅቱ የተሰው አደለም። ይህ ገንዘብ ደግሞ በተረጂዎች ስም የመጣ መሆኑ ደግሞ ከሁሉም በላይ አነጋጋሪ ይሆናል።
የሽብር ቡድኑ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር እየፈፀመ ነው ሲባል በግልፅ ማንም አይቶ አረጋግጦ ሊታዘብ በሚችል መልኩ፤ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዳይሆን መኪናዎችን አግዷል፤ የእርዳታ ቁሳቁስ መቀመጫ መጋዘኖችን ዘርፏል፤ አቃጥሏል። ከዚህ አልፎ በሽብር ተግባሩ ላይ ተጠምዶ የዘር ማትፋት ወንጀሎችን በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች እያካሄደ ነው።
አለም አቀፉ ህብረተሰብ ቡድኑ በእየፈጸመ ላለው ተግባር ተገቢው ፍርድ እንዲያገኝ ከመጠየቅ ይልቅ አሁንም ጉዳዩን በተቃራኒው እያበረታታ ይገኛል። አሁንም በተለይ የምእራቡ አለም ሀገራት ትኩረታቸው በመንግስት ላይ ማዕቀብ በመጣል ጫና መፍጠር ነው።
የሀገራቱ ፍላጎት የሽብር ቡድኑን ድርጊት በመደገፍ እርሱን እንዲጠናከር በማድረግ ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ እና ጠንካራ መንግስት ተፈጥሮ አገሪቷ እንዳታድግ ያለመ ይመስላል። ይህ አላማቸው እስኪሳካላቸው ምንም ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይሉም አሁነኛ ተግባራቸው በተጨባጭ ያሳያል።
በስልጣን ላይ ያለውና በምርጫም የህዝብ ይሁንታ ያገኘው የሀገሪቱ መንግስት የእነርሱን ዓላማ ለማስፈፀም የተመቸ እንዳልሆነ ቀድመው የተረዱት ይመስላል፤ ከዚህ የተነሳም ከጥንት ጀምሮ ሲረዱት የነበረው አሸባሪ ሕወሓት ዛሬም የመንግስት አካል እንዲሆን የመፈለጋቸው እውነታ ከብሄራዊ ጥቅም አንጻር እያሰሉት ይገኛሉ።
ይህ ሁኔታ ግን በየትኛውም አይነት ጫና ማእቀብ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። መንግስት የህዝቡን ይሁንታ ያገኘው ለሀገርና ለህዝብ ካለው ውግንና አንጻር መሆኑን እነዚህ ሀይሎች በአግባቡ ሊገነዘቡት ይገባል። ከኢትዮጵያዊ የሞራል እሴት አኳያም ይህን የሚያደርግበት የሞራል ሆነ የህግ መሰረት የለውም። ይህንንም በግልጽ በአደባባይ አሳውቋል።
አሜሪካን ጨምሮ በእርዳታ እና በማዕቀብ ስም በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ዓላማቸውን ለማስፈፀም የሚጥሩ አገራት ከአሁን በኋላ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ወታደራዊና ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ እንደፈለጉ ገብቶ መፈትፈት የሚችሉበት እውነታ አይኖርም።
ሀገራቱ እንደሚሉት ሰብአዊነት የሚያሳስባቸው አይደሉም። ለዚህም ከሁሉም በላይ ሰብአዊነትን ከብሄራዊ ጥቅም ጋር ለማስተሳሰር መሞከራቸው በራሱ ትልቅ ስህተት ነው። ይህንን ስህተት ቀድሞ ከማረም የበለጠ የትልቅነት መለኪያ ሊኖራቸው አይችልም። ይህንን ከፍተኛ ስህተት ተሸክሞ ስለ ሰብአዊነት ማውራት ሆነ መስበክ ትርጉም የሌለው ቀልድ ነው!
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም