ብዙዎች ስለ “አንድነት” ሃይል ይናገራሉ። የመተባበር ጥቅምን፣ ፍቅርን እንዲሁም በጋራ የመኖር ውበትን ይሰብካሉ። የሚሰማ የሚያዳምጥ ግን ጥቂት ነው። አንዳንዶች ደግሞ ስለ ፀብ ይዘምራሉ፣ የመለያየት አታሞን ይደልቃሉ። ይሄ እኩይ አላማቸው በፍጥነት እደጃፋችን ላይ ይደርሳል። ይገርማል። ዓለማችን ግን ተባብሮ እንጂ ተለያይቶ፤ ተዋድዶ እንጂ በጥላቻ ሰክሮ በተድላና በደስታ መኖር እንደማይቻል በተለያዩ ግዜያት አሳይታናለች።
ሰው ከራሱ ግንድ ብቻ ሳይሆን አያሌ ግዜ ከተፈጥሮ ጋር ተጣልቷል። የመኖር ህግን ባለማክሩ “ተፈጥሮ” በእራሷ ፍርድ ቤት ቅጣቷን አስተላልፋበት ታውቃለች። ከመልክዓ ምድሩ፣ ከደኑንና ከእንስሳቱን ጋር አብሮ መኖር ስለተሳነው “የተዛባው” ሚዛን መልሶ መጥፊያው ሲሆን ተመልክተናል። አሁንም ድረስ በተለያየ ግዜ የሚደርሱ አደጋዎች የሚያሳዩን ሰው “እኖር እሻሻል” ብሎ በሚሰራቸው ስህተቶች ወደ ዓለመኖር ጥልቅ ውስጥ በቅፅበት ተንሸራቶ እንደሚከተው ነው።
በምድራችን ላይ የተከሰቱ መለያየቶች አያሌ ጥፋቶችን ሲያስከትሉ ተመልክተናል። አብሮ እንጂ ተነጥሎ ድሎት እንደማይገኝ ተምረንበታል። በፍቅር የሚገኝ ሃይል፣ በስግብግብነት ከሚገኝ ንዋይና ሃብት በእጅጉ እንደሚሻል እራሷ ተፈጥሮ በአስደናቂ ሁኔታ ሳትታክት ታስተምረናለች። እኛ ግን ይሄን እንዴት ማየት አቃተን?
የእኛ ተነጥሎ ሁሉንም የማግበስበስ ፍላጎት እራሳችንን ብቻ ሳይሆን ከጎናችን ያለውንም እንደሚጎዳ ማወቅ ይኖርብናል። እንኳን በአንድ አገር ውስጥ ይቅርና ዓለማችን ላይ ድንበርና ወሰን ማበጀታችን የሰው ልጅ ሰብአዊነትን እየሸረሸረው መጣ እንጂ የፈየደልን ምንም ነገር የለም። በመንደር እና ክልል ተወስነን ጠርዝና ጠርዝ ይዘን መናቆራችን ሁላችንንም ይዞ ይጠፋ ይሆን እንጂ አማናችንንም አይጠቅምም። እንኳን በአንድ አገርና ጥላ ስር እየኖርን ይቅርና ከቤተሰባችን ጋር ህይወታችንን ስንመራ “የአንድነት፣ የፍቅርና አብሮ የመኖር” ትርጉሙ የማይገባን ከሆነ ተያይዘን እንወድቅ ይሆናል እንጂ በመለያየትና በጥላቻ ውስጥ አንዳች እንኳ አንጠቀምም። ይሄን ጉዳይ በሚከተለው ታሪክ ውስጥ በተሻለ መረዳት እንችላለን እንደምንችል ተስፋ አደርጋለሁ።
ሁለት ጭንቅላት ያለው እንግዳ ወፍ
በአንድ ወቅት ሁለት ጭንቅላት ያለው እንግዳ ወፍ ይኖር ነበር። አንዱ ወደ ግራ ሌላኛው ደግሞ ወደ ቀኝ ያዘነበሉ ናቸው። ይሁን እንጂ አንድ አካል ተጋርተው ቢኖሩም ሁለቱም የየራሳቸው ሃሳብና አመለካከት ነበራቸው። ሁለቱ ራሶች በጣም ቀላል በሆኑ ምክንያቶች እንኳን እርስ በእርሳቸው ይጣሉ እና ይከራከሩ ነበር። አንድ አካል ቢጋሩም ሁለቱ ራሶች እንደ ተቀናቃኝ ባህርይ ስላላቸው ሁል ግዜም አይስማሙም።
እነዚህ አንድ አካል ሁለት ጭንቅላት ያላቸው እንግዳው ወፎች በወንዝ ዳርቻ አጠገብ በአንድ ትልቅ “የባያን ዛፍ” ውስጥ ይኖሩ ነበር። በአንድ እለት በወንዙ ላይ ሲበርሩ የወፉ የግራው ራስ ቀይ ፍሬ ያላት ውብ ዛፍ ተመለከተ። ወዲያው ባየው ነገር ተደስቶ ፍሬውን ለመብላት ፈለገና ምኞቱን ለማድረስና ጣፋጭ ፍሬውን ለመብላት ወደ ታች በረረ።
ምኞቱ ተሳክቶለት የሚጣፍጥ ፍሬውን ነቅሎ በወንዙ ዳር ተቀምጦ መብላት ጀመረ። ፍሬው በግራ ጭንቅላቱ ተበላ። ምግቡን እያጣጣመ ባለበት ቅፅበት ግን ሌላኛው የቀኝ ጭንቅላቱ “ልቀምስ አንድ ቁራጭ ልትሰጠኝ ትችላለህ?” ሲል ይጠይቀዋል። የግራ ጭንቅላቱ “ተመልከት እኛ አንድ ሆድ ብቻ አለን። ስለዚህ በአፌ ውስጥ ብበላ እንኳ ወደ ሆዳችን ብቻ ይገባል” በማለት ሊያሳምነው ይሞክራል። ይሁን እንጂ የቀኝ ጭንቅላቱ “እኔ ግን ፍሬውን መቅመስ እፈልጋለሁ። ስለዚህ ለእኔ መስጠት አለብህ” በማለት ይለማመጠው ይጀምራል። አሁንም ግን ሊያዳምጠውና ልመናውን ሊሰማው አልፈቀደም ነበር።
ይልቁኑ የግራ ጭንቅላቱ በቁጣ እንዲህ ሲል መለሰለት “ፍሬውን ቀድሜ ያየሁት እኔ ነኝ ስለሆነም ከማንም ጋር ሳላጋራ መብላት መብቴ ነው” ሲል ቁርጡን ነገረው። ይህን በሚናገርበት ወቅት ራስ ወዳድና የበዛ ስግብግብነት ይታይበት ነበር። የቀኝ ጭንቅላቱ በሁኔታው አዝኖ ዝምታን መረጠ።
ከጥቂት ቀናት በኋላም እንደገና በወንዙ ላይ ምግባቸውን ፍለጋ ይበሩ ነበር። በቅኝታቸው ውስጥም የቀኝ ጭንቅላቱ በዛፍ ውስጥ የሚያምር ፍሬ አየ። ወዲያውኑ ከዛፉ አጠገብ ወረደና ፍሬውን ወስዶ ለመብላት ሞከረ። በዛፉ ውስጥ የሚኖሩት ሌሎች ወፎች ግን “እንዳትበሉት። መርዛማ ፍሬ ነው። ይገድላችኋል” በማለት አስጠነቀቋቸው። በዚህ ግዜ ማስጠንቀቂያውን የሰማው የግራ ጭንቅላቱ ጩኸቱን አቀለጠው። “አትብላው። አትብሉት ተብለናል” በማለት መልክቱን እየደጋገመ ይነግረው ጀመረ። ሆኖም የቀኝ ጭንቅላቱ መልዕክቱንም ሆነ የወንድሙን ተማፅኖ የመስማት ፍላጎት አላሳየም ነበር።
ሁሉንም ችላ ብሎ “ስላየሁት እበላዋለሁ። እኔን ለማስቆም መብት የለህም” በማለት የግራ ጭንቅላቱ በወንድሙ ላይ ክፉኛ ጮህበት “እባክህን ፍሬው ገዳይ ነው አትብላው። ሁላችንም እንሞታለን” እያለ ደጋግሞ ቢለምነውም “እኔ ስላየሁት እሱን የመብላት መብት አለኝ” ከሚል ምላሽ ውጪ ሊያዳምጠው አልቻለም ነበር። በግልጽ ለማወቅ እንደሚቻለው ከዚህ ቀደም “ቀዩን ፍሬ” ወንድሙ ባለማካፈሉ በግራ ጭንቅላቱ ላይ ለመበቀል መፈለጉን ነው። በመጨረሻ፣ ሮዝ ፍሬ የቀኝ ጭንቅላቱ በላው። በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥም ባለሁለት ጭንቅላት ያለው እንግዳ ወፍ እጣ ፈንታ ሞት ሆነ።
እኛ ከዚህ ታሪክ
ከባለ ሁለት እራሱ ወፍ ብዙ ነገር መማር ይቻላል። መተባበር፣ መደማመጥ እንዲሁም “አንተ ተብስ አንቺ ትብሽ” ካልተባባልን መጨረሻችን ተያይዞ ውድቀት መሆኑን ያስገነዝበናል። እኛም እንደ ባለ ሁለት እራሱ ወፍ ህልውናችን የተገመደና የማይነጣጠል ነው። ታዲያ ይሄን መረዳት የምንችለው ወደ ጥፋት የሰደድነውን እጅና እግራችንን መለስ ስናደርገውና በጥሞና ማሰላሰል ስንችል ነው። አይደለም ያለንን ብቸኛ አገር ለመበተን መፍጨርጨር በቤተሰብ ውስጥ በግለሰቦች የሚደረግ ጠብ መላውን ቤተሰቡን ክፉኛ እንደሚጎዳ ማወቅ ይኖርብናል። ይህን ስንረዳ ከገባንበት የቁልቁለት መንገድ ተደጋግፈን መውጣት እንችላለን። ሰላም!
የዮቶር ክንድ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5/2013